Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

	አንዲቷ  ልመና

አንዲቷ  ልመና

ከሌሊቶች ውስጥ በአንዱ ሌሊት ነው እግዚአብሄር ለንጉስ ሰለሞን በራእይ ተገልጦ ምን እንድሰጥህ ለምነኝ ያለው። ለእኛ ለሰዎች መለመን ብዙም የሚያስደስተን ነገር አይደለም። ምክኒያቱ ደግሞ የበዛውን ጊዜ ለመስጠት ስንነሳ፥ ከራሳችን የሚጎልብን ነገር ስላለ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ስንሰጥ፥ ከሙላታችን ሳይሆን ከጉድለታችን ነው። እሱንም ደግሞ የምንጠየቀውን ነገር የመስጠት አቅሙ ካለን ነው። ይሄ ሁሉን የሚችለው አምላክ ግን፥ ምንም ነገር ቢለመን መስጠት የሚችለው ሁሉንቻይ ማንነቱን ተማምኖ ነው የወደድከውን ለምነኝ እያለ ወደ ሰለሞን የመጣው። ለማንም ሰው የትኛውንም ያህል ብዙ ነገር ቢሰጥ፥ ከእርሱ ላይ አንዳች የሚጎልበት ነገር የለም። ምንም ነገር ብንጠይቀውም ከአቅሙ በላይ ስለማይሆን አይደነግጥም። የማልችለውን ነገር ይጠይቁኝ ይሆን ብሎም አይፈራም። ማድረግ ባልችልስ ብሎ ደግሞ አይጨነቅም። ታዲያ፥ ሰለሞን በተሰጠው በዚህ እድል የጠየቀው ጥያቄ እግዚአብሄርን እጅግ በጣም ደስ ከማሰኘቱ የተነሳ፥ ከለመነውና ካሰበው በላይ ብቻ ሳይሆን፥ ያለመናቸውንም ብዙ ነገሮች አብሮ ሰጥቶታል። “እግዚአብሄርም አለው፥ ፍርድን ትለይ ዘንድ ለራስህ ማስተዋልን ለመንህ እንጂ፥ ለራስህ ብዙ ዘመናትን ባለጠግነትንም የጠላቶችህንም ነፍስ ሳትለምን ይህን ነገር ለምነሀልና፥ እነሆ እኔ አንደ ቃል አድጌልሀለሁ። እነሆ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ፥ ከአንተም በኋላ እንዳይነሳ አድርጌ፥ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሀለሁ።  ደግሞም ከነገስታት የሚመስልህ ማንም እንዳይኖር፥ ያለመንከውን ባለጠግነትና ክብር ሰጥቼሀለሁ። አባትህም ዳዊት እንደ ሄደ ስርአቴንና ትእዛዜን ትጠብቅ ዘንድ በመንገዴ የሄድህ እንደሆነ፥ እድሜህን አረዝመዋለሁ።” (1ኛ ነገስት 3፥11-14) የሰለሞን ልመና እግዚአብሄርን እጅግ በጣም ደስ አሰኝቶት ነበር። ለካ እግዚአብሄር ከመመለሱ በፊት፥ ጸሎቶቻችንንና ልመናዎቻችንን ይመዝናቸዋል። ከልመናዎቻችን መካከል እንደ ፈቃዱ የሆኑና እርሱን በጣም የሚያስደስቱት፥ እንዲያውም ያለመናቸውን ሌሎችም ነገሮች ጨምሮ እንዲሰጠን የሚያስገድዱት የልመናና የጸሎት አይነቶች አሉ። እግዚአብሄር መልስ ከመስጠቱ በፊት፥ የጠየቅነውን ጥያቄ ከፈቃዱ ጋር ይመዝነዋል። ባይመዝነውማ ኖሮ፥ ሁሉን መስጠት ስለሚችል የለመነውን በሙሉ ሰጥቶን ቢሆንማ ኖሮ፥ እርግጠኛ ነኝ ማናችንም እዚህ አሁን ያለንበት ቦታ ጋር አንሆንም። ምናልባትም በህይወት የማንቆይ ብዙዎች እንኖራለን። የለመነውን ሁሉ ያልሰጠን እግዚአብሄር ይባረክ። ጥያቄዎቻችንን ሁሉ ከዘላለም ሀሳቡ አንጻር እያመዛዘነ፥ ለእኛ ቢገባንም ባይገባንም ከብዙ ፍቅሩ የተነሳ፥ በማስተዋል የሚመልስልን አምላክ ይባረክ። ዳዊትም አለ “እግዚአብሄርን አንዲት ነገር ለመንኩት፥ እርሷንም እሻለሁ። በህይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሄር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሄርን፥ ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።” (መዝሙር ዳዊት 27:4) ይሄ፥ ዳዊት ከዚህ በፊት እግዚአብሄርን የለመነው የመጀመሪያ ልመናው አይደለም። በህይወቱ የለመነው የመጨረሻ ልመናውም አይደለም።  እንደማንኛችንም ሰዎች፥ ብዙ ጊዜ ጸልዮ፥ ከእግዚአብሄርም ሌሎች ልመናዎችን ለምኖ ያውቃል። ነገር ግን ይህቺ ከብዙ ልመናዎቹ የበለጠችበት ብርቱ ልመናው ነች። ብዙ ነገሮችን አስቦ አውጥቶና አውርዶ፣ ስለ እግዚአብሄር ባገኘው እውቀትና መገለጥ ውስጥ ሆኖ፣ በህይወቱ እግዚአብሄር ማን እንደሆነ፥ እግዚአብሄር ለእርሱ ምን ማለት እንደሆነ አስቦ፣ ከነፍሱ ጋር ተማክሮ፥ ከልቡ ጋር ተጨዋውቶ፥ ብዙ ነገሮችን አይቶና ገምግሞ እግዚአብሄርን የለመነው ልመና ነው። ይሄንን የምለምነውን አንዲት ልመና ደግሞ እሻዋለሁ አለ። “ለዘላለም በእግዚአብሄር ቤት ውስጥ መኖር፣ ደስ የሚያሰኘውን እግዚአብሄርን ማየት፣ መቅደሱንም መመልከት እፈልጋለሁ አለ።” ዳዊት እግዚአብሄርን ልክ እንደለመነው፥ እግዚአብሄር ልመናውን ሰምቶለታል። በህይወቱ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሄር ቤት ኖሯል። ደስ የሚያሰኘውን እግዚአብሄርን ተመልክቷል። በእግዚአብሄር ቤት መኖር ብቻ ሳይሆን፥ በህይወቱ ዘመን ሁሉ የእግዚአብሄርን ሀሳብና ፈቃድ አገልግሎ እንዲያልፍ፥ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ይሄ ነው የማይባል አሻራ እንዲያሳርፍ፥ የራሱን ዘመን ፈጥሮ፥ እኛ እንኳን እስከዛሬ የዳዊት አምላክ እያልን፥ ዳዊት ከእግዚአብሄር ጋር የነበረው ግንኙነት ህይወታችንን እየለወጠው ይቀጥላል። 

ለዘላለም በእግዚአብሄር ቤት መኖር፣ ደስ የሚያሰኘውን እግዚአብሄርን ማየት፣ መቅደሱንም መመልከት ለዳዊት፥ ከልመናዎቹ ሁሉ የበለጠችበት ብርቱ ልመናው ነበረች። ትልቁ ልመናችሁ ምንድነው? ልባችሁ ውስጥ ያለው መሻት፥ የነፍሳችሁ ልመና ምንድነው? የውስጣችሁ ጩኸት፥ የዘውትር መሻታችሁና የአንድ ነፍሳችሁ ጸሎት ምንድነው? ደጋግማችሁ እግዚአብሄርን የምትጠይቁት አንዲቷና ከሁሉ የምትበልጠው ልማናችሁ ምንድናት? መልሱን ለእናንተ እየተውኩ፥ እኔም በተራዬ ልክ እንደ ዳዊት ብዙ ነገሮችን አውጥቼ ካወረድኩ፥ ብዙ ካሰላሰልኩ በኋላ እግዚአብሄር ባስተማረኝ ነገሮችና እስከዛሬ ድረስ በተገለጡልኝ መገለጦች ውስጥ ሆኜ፥ እግዚአብሄርን አንዲት ነገር ለመንኩት። እርስዋንም እጅግ በጣም እሻለሁ። “በዘመኔ ሁሉ የእግዚአብሄርን ፈቃድ እኖርና አገለግል ዘንድ፥ በዚህ መንገድ ውስጥ የሚያስከፍለውን ዋጋ ሁሉ መክፈል እችል ዘንድ” ብዬ ለመንኩ። እናንተስ? የእግዚአብሄርን ፈቃድ መኖር ቀላል ህይወት ነው። አልጋ በአልጋ ነው ብንል ራሳችንን ውሸታሞች እናረጋለን። እንዲያውም ኢየሱስ፥ “እኔን መከተል የሚፈልግ ቢኖር፥ መስቀሌን ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት እርሱን መከተል፥ ከመስቀል ወይንም ዋጋ ከመክፈል ውጪ እንዳልሆነ ግልጹን ተናግሯል። የእርሱን ፈቃድ እኖራለሁ ብለን ከመነሳታችን በፊት፥ በዚህ መንገድ ውስጥ የሚያስከፍለውን ዋጋ ለመክፈል ካልወሰንን፥ መንገዱ መሀል ላይ ግራ መጋባታችን የማይቀር ነው። የነገሩ አስደሳችነት ግን ይሄ ነው። በዚህ ህይወት ውስጥ የምንከፍለው ዋጋ በሙሉ፥ በመቶ እጥፍ በሚመጣው ህይወት ውስጥ የምንቀበለው ትልቁ ሽልማታችን ነው። የእግዚአብሄር ቃል ሲናገር፥ “አለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፥ የእግዚአብሄር ፈቃድ ግን ለዘላለም ይኖራል” እንደሚለው፥ ሁሉ ነገር ሲያልፍ፥ ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው የእግዚአብሄር ፈቃድ ብቻ ነው። እኛ እራሳችን፥ ጊዜያችንን ስንጨርስ፥ ከዚህች ምድር አላፊዎች ነን። ዛሬ ላይ በዚህ ህይወት የምንኖረው የእግዚአብሄር ፈቃድ ግን፥ ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር ነው። ዛሬ ላይ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመኖር የምንከፍላቸው ዋጋዎች በሙሉ፥ ለዘላለም የሚኖሩ ናቸው። መጽሀፍ ቅዱሳችን ላይ የተጻፉልን አባቶቻችን፥ ከዚህች ምድር ካለፉ ስንትና ስንት ሺህ አመታቶች ቢቆጠሩም፥ በተሰጣቸው ዘመን፥ ዋጋ በመክፈል የኖሩት የእግዚአብሄር ፈቃድ ግን፥ ለዘላለም ጸንቶ ሲወራና ሲነገር ይኖራል። ልክ አባቶቻችን የኖሩት የእግዚአብሄር ፈቃድ ተጽፎ ዛሬ እንደምናነበው፥ እኛም ዛሬ የምንኖረው ህይወት፥ እኛም ዛሬ ላይ የምንኖረው የእግዚአብሄር ፈቃድ የሚጻፍና ለዘላለም የሚኖር ነው። እያንዳንዱ ዋጋ የሚጻፍ ነው። እያንዳንዱ እንደ እግዚአብሄር ሀሳብ የምንከፍለው ዋጋ በሙሉ መንፈሳዊ አለም ላይ የሚጻፍ ነው። ይሄ የምንነጋገረውን ነገር በደምብ የሚያስረግጥልንን አንድ ምሳሌ እስኪ ወስደን እንመልከት። የዘፍጥረትን መጽሀፍ የጻፈው ሙሴ ነው። የፍጥረትን መጀመሪያ፥ እንዲሁም በዘፍጥረት መጽሀፍ ላይ የተጻፉትን ሰዎች ታሪክ በሙሉ የጻፈው ሙሴ ነው። እነዚህ ለእኛ ምሳሌ ይሆናሉ ተብለው፥ በዘፍጥረት መጽሀፍ ላይ የተጻፉልን ሰዎች በነበሩበት ዘመን፥ ሙሴ ገና አልተወለደም ነበር። ሙሴ የተወለደው፥ እነርሱ ካለፉ ከብዙ መቶ አመታቶች በኋላ ነው። በዘፍጥረት መጽሀፍ ላይ እንደምናነበው፥ እነ አቤል በእግዚአብሄር ፊት የተወደደ መስዋእት ሲያቀርቡ፣ እነ ሄኖክና እነ ኖህ አካሄዳቸውን ከእግዚአብሄር ጋር ሲያደርጉ፣ እነ አብርሀም እግዚአብሄርን በመታዘዝ 75 አመታቶች ሙሉ የኖሩበትን ሀገር በእምነት ታዘው ጥለው ሲወጡ፣ እነ ዮሴፍ “በእግዚአብሄር ፊት ይሄንን ሀጢያት አላደርግም” ብለው ሲሸሹ፥ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመኖር ዋጋ ሲከፍሉ፥ ሙሴ በቦታው አልነበረም። ሙሴ አልተወለደም ነበር። የእነዚህን ሁሉ ሰዎች ታሪክና የኖሩትን ህይወት እንዲጽፍ፥ ያልነበረበትን ህይወት መገለጥ ለሙሴ የሰጠው እግዚአብሄር ነው። እነዚህ ሰዎች ኖረው ካለፉ በኋላ፥ በህይወታቸው ውስጥ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመኖር የከፈሉትን ዋጋ፥ ከተጻፈበት መንፈሳዊ አለም ውስጥ አውጥቶ ለትውልድ ጽፎ ያስቀምጥ ዘንድ፥ ለሙሴ የሰጠው እግዚአብሄር ነው። እነዚህን ትውልድ ሲታነጽ የሚኖርባቸውን ትልልክ የታሪክ መገለጦች ለሙሴ የሰጠው እግዚአብሄር እራሱ ነው። ሙሴ እራሱ እየጻፈ ይደነቃል። wow ይላል። ለካ አባቶቼ ለእግዚአብሄር ኖረዋል። ለካ ከእኔም በፊት ይሄ ሁሉ ታሪክ አለ በማለት፥  ለራሱ ህይወት እየተማረ፥ የተሰጠውን መገለጥ በወረቀትና በብእር ለእኛ እንዲገባን አድርጎ ጽፎልን እንዲያልፍ ያደረገው እግዚአብሄር ይባረክ።  እነ ኖህ፣ እነ ሄኖክ፣ እነ አብርሀም ይስሀቅ ያቆብና እነ ዮሴፍ እነዚህ ትልልቅ ታሪክ ያላቸውና ከእግዚአብሄር ጋር ለመጓዝ ዋጋ የከፈሉት የእግዚአብሄር ሰዎች፣ ልክ እንደ እኔና እንደ እናንተ ሰዎች ነበሩ። መላእክቶች ወይንም ልዩ ፍጥረታት አልነበሩም፥ ሰዎች ነበሩ። መጽሀፍ ቅዱስ የእነዚህን ሰዎች ህይወት በስፋት የጻፈው፥ የህይወታቸው አሻራ መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲያርፍ ያረገው፥ ዋጋ በመክፈል ለመኖር የወሰኑት የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው። የእግዚአብሄርን ፈቃድ መኖር። ዘላለም የማይጠፋ ህይወት መኖር። ለዘላለም የሚኖር ታሪክ መኖር። እነዚህ ታሪካቸው በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈልን ሰዎች ታዲያ፥ እኛ ከዚህች ምድር ካለፍን በኋላ፥ ታሪካችን ተጽፎ ለትውልድ መማሪያ ይሆናል። ታሪካችን፥ ዛሬ ላይ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመኖር የምንከፍላቸው ዋጋዎች በሙሉ፥ በመንፈሳዊ አለም ላይ ተጽፈው፥ ለዘላለም ይኖራሉ ብለው በፍጹም አላሰቡም። እነርሱ በጊዜው ሰምተው የተከተሉትን የእግዚአብሄርን ድምጽ ብቻ ነው የሚያውቁት። ዛሬ የምንኖረው ህይወት፣ ዛሬ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ የምንከፍለው ዋጋ፥ መንፈሳዊ አለም ላይ የሚጻፍ ነው። መንፈሳዊ አለም ላይ የሚቀመጥ ነው። ይሄንን ለማወቅ መጽሀፍ ቅዱሳችንን ማንበብ በቂ ነው። ዛሬ ላይ ታሪካቸው በዝርዝር ተጽፎ የምናነባቸው አባቶቻችን ከዚህ ምድር ካለፉ ብዙ ሺህ አመታቶች ቢቆጠሩም፥ የኖሩት የእግዚአብሄር ፈቃድ ግን አላለፈም። በህይወታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉበት የእግዚአብሄር ፈቃድ ግን አላለፈም። አለሙም ምኞቱም ሲያልፉ የእግዚአብሄር ፈቃድ ግን ለዘላለም ጸንቶ ስለሚኖር፥ ከኖሩት የእግዚአብሄር ፈቃድ ጋር ስማቸው አብሮ ይነሳል። 

በነ አብርሀም፣ በነ ኖህ፣ በነ ይስሀቅ፣ ያእቆብና ዮሴፍ ዘመን እኮ ምድር ላይ ይኖሩ የነበሩት እነዚህ ስማቸውን የጠቀስናቸው የእግዚአብሄር ሰዎች ብቻ አልነበሩም። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ምድር ላይ ነበሩ። እግዚአብሄር በስፋትና በዝርዝር ሁኔታ ለሙሴ የሰጠው ግን፥ ፈቃዱን የኖሩትን ሰዎች ታሪክ ብቻ ነው። ይሄ አያስደንቅም? ለምሳሌ በመጽሀፍ ቅዱሳችን ላይ ስለተጻፉልን ስለ ሁለቱ ሴቶች ታሪክ፥ ስለ ሩትና ስለ ኦርፋ ብንመለከት፥ በአንድ ወቅት፥ በተመሳሳይ የህይወት አካሄድ ውስጥ ህይወታቸው ያለፈና፥ ሁለቱም ባሎቻቸውን በማጣት በተመሳሳይ ዋጋ መክፈል ውስጥ ያለፉ ሴቶች ነበሩ። መጽሀፍ ቅዱስን ስታነቡ ግን፥ የኦርፋን ህይወት የሆነ ቦታ ላይ ያቆመውና፥ መጽሀፍ ቅዱስ፥ የሩትን ህይወት እየተከተለ መጻፍ ይጀምራል። ሙሉ መጽሀፉ በራሷ በሩት ስም እስኪጠራ ድረስ፥ ህይወቷን በስፋትና በዝርዝር ጽፎታል። ይሄ የሆነው ሩት ከኦርፋ የተለየ ምንም ነገር ስለነበራት አይደለም። ልዩ ያደረጋት አንድ ነገር ብቻ ነው። ልክ እንደ ጓደኛዋ እንደ ኦርፋ፥ የራሷን ህይወት በማስቀደም፥ የለመደችው ሀገር ውስጥ የመቆየት ምርጫ የነበራት ቢሆንም፥ ኑሀሚንን በእውነተኛ ፍቅር በመውደድና የእግዚአብሄር ፈቃድ ስለሆነው ፍቅር የሚያስከፍለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል እስከ ሞት ድረስ ጨክና ስለነበረ ነው። ከዚህች አንድ ተራ የነበረች ሞአባዊት ሴት ህይወት፥ ምንድነው የእግዚአብሄርን ቀልብ የሳበው? ምንድነው የእግዚአብሄርን ትኩረት ወደ ህይወቷ የወሰደው? ምንድነው በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ቦታ የሰጣት፣ ምኗ ነው የመጽሀፍ ቅዱስን ትኩረት የሳበው? ብላችሁ ስትጠይቁ፥ ሩት ታደርግ የነበረው ነገር በሙሉ የእግዚአብሄርን ሀሳብና ፈቃድ ነበር። ከህይወቷ የምትማሩት ነገር በሙሉ፥ ትጋቷ፣ መስዋእትነት የተሞላበት ፍቅሯ፣ ሰውን ከራሷ በላይ መውደዷ፣ መሰጠቷ፣ አክብሮቷ፣ የውሳኔ ሰው መሆኗና ባህሪዎቿን በሙሉ በመጽሀፉ ላይ ስታጠኑ፥ የእግዚአብሄርን ትኩረት የሚስቡ የእግዚአብሄር ፈቃዶች ነበሩ። በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ስንኖር፥ ታሪካችን አይጣልም። የሚጣል ታሪክ አይኖረንም። ዛሬ ላይ አይምሰለን እንጂ፣ ነገ ላይ ለዘላለም የሚኖር ታሪክ ነው እየኖርን ያለነው። ዳዊትም በመጽሀፉ ላይ “ስለ አፍህ ቃል ጭንቅ የሆኑ መንገዶችን ጠበኩ” እንዳለ፣ ዛሬ ላይ የእግዚአብሄርን ሀሳብ ለመኖር የምንጠብቃቸው ጭንቅ መንገዶች፣ የአንደበቱን ቃል ለመኖርና ለማድረግ የምናልፍባቸው ከባባድ መንገዶች፥ ነገ ላይ የክብር ሽልማቶቻችን ናቸው። ነገ ላይ የዘላለም አክሊሎቻችን ናቸው። ነገ ላይ ተጽፈው የሚቀመጡ ትልልቅ ታሪኮቻችን ናቸው። ጳውሎስ እንዳለው በዚህች ህይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ የምናደርገው ከሆንን፥ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን፣ የእኛ ተስፋ ይህቺ ምድር አይደለችም። ሌላ አለ፥ ለዘላለም የሚጠብቀን ክብር አለ። ያ ክብር ደግሞ፥ ዛሬ ላይ በምንኖረው ህይወት ላይ የተመሰረተ ነው። ስለዚህ ዛሬ ቆም ብለን ህይወቶቻችንን ብንፈትሽ፣ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ነው ወይ እየኖርኩ ያለሁት? ነገ ላይ አክሊልና ሽልማት ከእግዚአብሄር እጅ የምቀበልበትን ህይወት ነው ወይ እየኖርኩ ያለሁት? ነው ወይስ ዝም ብሎ ከንቱ ህይወት ነው እየኖርኩ ያለሁት? የእግዚአብሄርን ፈቃድ ነው እያደረኩ ያለሁት? የእግዚአብሄርን ፈቃድ ነው እያገለገልኩ ያለሁት?  ሰው መቼም የእግዚአብሄርን ፈቃድ አያገልግል እንጂ የሆነ ነገር እኮ አገልጋይ ነው። ወይ የሰዎችን ሀሳብ አገልጋይ ነው። ወይ የራሱን ምኞትና ፈቃድ አገልጋይ ነው። ወይንም ደግሞ የሰይጣንን ሀሳብ አገልጋይ ነው። ሰው የሚያገለግለውን ይመርጣል እንጂ፥ ሳያገለግል ግን መኖር አይችልም። ዳዊት ግን በገዛ ዘመኑ የእግዚአብሄርን ፈቃድ አገልግሎ አንቀላፋ እንደተባለው፥ በዘመናችን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ብናገለግል፥ ኪሳራ የሌለበትና ዘላለም የምናተርፍበትን ህይወት እንኖራለን። ምድር ላይ የነበሩ ሰዎች በሙሉ፥ የራሳቸው ሀሳብ አገልጋይ ሆነው እንደፈለጉ በሚኖሩበት ሰአት፥ ሰው ሁሉ በአይኑ ፊት ደስ የሚያሰኘውን በሚያረግ ሰአት፥ ኖህ አካሄዱን ከእግዚአብሄር ጋር እንዳደረገ፥ አካባቢያችን ላይ ያሉ ሰዎች የእግዚአብሄርን ሀሳብ አለማገልገል፥ እኛን ሊያዳክመን አይገባም። ሳሙኤል ያደገው እዛው ቤተመቅደስ ውስጥ ትክክል ያልሆነ የህይወትና የአገልግሎት አካሄድ የነበራቸውን የኤሊን ልጆች እያየ ነበር። ይሁን እንጂ ከልጅነት እስከ መሞቱ ድረስ፥ በትክክል የእግዚአብሄርን ሀሳብ ያገለገለ ትልቅ የእግዚአብሄር ሰው ሆኖ አልፏል። የእግዚአብሄርን ሀሳብ ለመኖር፥ የማንም ሰው እርዳታና ድጋፍ አያስፈልገንም። የሚያስፈልገን የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ብቻ ነው። እዩ የተባልነው ከፊታችን የተሳለውን ክርስቶስን እንጂ፥ ግራና ቀኛችን ያሉ ሰዎችን አይደለም። የእብራውያን መጽሀፍ ጸሀፊ በምእራፍ 11 ላይ፥ የእምነት አባቶችን ከዘረዘረ በኋላ፥ ምንም በእምነት የተመሰከረላቸው ሰዎች ቢሆኑም እንኳን፥ እነሱን እያያችሁ ሩጡ አላለም። ይልቁንም እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች ካሉልን አለ። እነርሱ የእግዚአብሄር ጸጋ ምስክሮች ብቻ ናቸው። እኛ ደግሞ የእምነታችንን ጀማሪና ፈጻሚ የሆነውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትእግስት እንሩጥ በማለት፥ ይሄንን ሩጫ በትክክለኛ መንገድ ለመጨረስ የምንመለከተው ነገር በጣም አስፈላጊ መሆኑን ይነግረናል። በትክክል የአብን ፈቃድ ጨርሶ ያለፈውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ ነውርን የናቀውን፣ በፊቱ ስላለው ደስታ በመስቀል የታገሰውን፣ በዚህ ምድር ሲኖር የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመኖር የሚከፈለውን ሁሉ ዋጋ የከፈለውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ ከፊታችን ያለውን ሩጫ በትእግስት እንሩጥ። ሲደክመን ኢየሱስን እንየው፣ ተስፋ ስንቆርጥ ኢየሱስን እንየው፣ ስናዝንና በተለያዩ ነገሮች ልባችን ሲጎዳ ኢየሱስን እንየው፣ ስንፈተንም ኢየሱስ እያየን በቀረልን ዘመን የእግዚአብሄርን ሀሳብና ፈቃድ እየኖርንና እያገለገልን ከዚህች ምድር እንለፍ።  

እውቀት

እውቀት

ጠቢብ

ጠቢብ