Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

እውቀት

እውቀት

“ዘመኑ የኢንፎርሜሽን ዘመን ነው” ይላሉ ሲናገሩ። ነገር ሁሉ በእውቀትና በማስረጃ የተደገፈ ሆኗል። የመጨረሻው ዘመን ነውና እውቀት በዝቷል። “አላውቅም” የሚባል ነገር ቀርቷል። ሁሉም ሰው ያውቃል። እውቀት ትምህርት ቤት ብቻ መሆኑ ቀርቶ፥ ዛሬ ዛሬ ከያዝነው ሞባይል ስልክ ጋር እጃችን ውስጥ ገብቷል። አለም በእጃችን ናት፥ የፈለግነውን መረጃ በፈለግነው ደቂቃ ውስጥ እናገኛለን። እድሜ ለጎግል! ደስ ያለንን ኢንፎርሜሽን ለማግኘት ምንም አይነት ጊዜ አይፈጅብንም፥ በደቂቃ ውስጥ እናገኘዋለን። 

ድሮ ድሮ ሲያመን ቶሎ ብለን ለመሄድ የምናስበው ዶክተር ጋር ነበር፥ አሁን አሁን ግን ጎግልዬ ምልክቱን ንገሯት እንጂ፥ በሽታችሁን ለቤተሰብ ሳይሆን ለራሳችሁ በግልጽ ታበስራቹሀለች። ትንሽ ቆይቶ መድሀኒቱንም ከፋርማሲ የማዘዝ መብት ሳይሰጣት ይቀራል ብላችሁ ነው? 

“እውቀት ሀይል ነው” እያሉ ይናገራሉ። ለነገሩ አባባሉ እውነት ነው። እውቀት ብዙ ነገሮችን በተሻለ መንገድ ለማከናወን የሚጠቅመን አስፈላጊ ነገር ነው። ህይወታችንን በተለያየ አቅጣጫ እያቀለለ፥ የቀን ለቀን ተግባሮቻችንን በተሻለ መንገድ እንድናከናውን የሚረዳን ነገር ነው። እኛ እንኳን በየቀን ኑሮአችን ውስጥ በምንፈልጋቸው የተለያዩ እርዳታዎች ዙሪያ የምንፈልገው፥ እውቀት ያለውን ሰው ነው። ለምሳሌ ትንሽ ቢያመን፥ እኛን የሚረዳበት እውቀት ያለው የህክምና ባለሙያ ስለሆነ፥ ቶሎ የምናስበው ወደ ዶክተራችን ጋር ለመሄድ ነው። ቤት ለመስራት ብናስብ፥ ቤት በመስራት ዙሪያ እውቀት ያላቸውን ሰዎች መሀንዲሶችን ለማናገር እንሄዳለን። መኪናችን ቢበላሽ፥ መካኒካችን ጋር በመሄድ በመኪና ዙሪያ ባለው እውቀት ችግሩን እንዲነግረንና እንዲረዳን እንጠይቃለን። 

ሁላችንም በሆነ ነገር ዙሪያ ከሌሎች ነገሮች ከፍ ያለ እውቀት አለን። ለምሳሌ፣ በየቀኑ በምንሰራው ነገር ዙሪያ ከሌሎች በሌላ የስራ ዘርፍ ውስጥ ከሚሰሩ ሰዎች የተሻለ እውቀት አለን። የወር ደሞዛችንንም ልዩ ልዩ ያረገው፥ የእውቀት ደረጃችን ነው። የዚህች ምድር አሰራር እንዲህ ነው።  እውቀታችን በጨመረ መጠን፥ ሰዎችን የምንረዳበት ወይንም የምንጠቅምበት አቅም ስለሚያድግ፥ ደሞዛችንና ተፈላጊነታችን ይጨምራል። መጽሀፍ ቅዱሳችንም እንዲሁ በተለያዩ ቦታዎች እውቀት በጣም አስፈላጊ ነገር መሆኑን፥ ነፍሳችን እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አለመሆኑንና መልካም የሆነው ነፍሳችን በእውቀት መሞላትዋ እንደሆነ ጽፎልናል። ታዲያ ነፍሳችን መሞላት አለባት እያለ መጽሀፍ ቅዱስ የሚነግረን የእውቀት አይነት ከላይ እንደዘረዘርነው ስለ ጤናችን፣ ስለ መኪናችን፣ ስለ ኮምፒውተር ሲስተሞቻችን ያሉን የእውቀት አይነቶች አይደሉም። እነዚህ እውቀቶች ጊዜያዊና በዚህች ምድር እስከኖርን ድረስ ብቻ የሚጠቅሙ፥ አይምሮአችንን ብቻ እንጂ ነፍሳችንን ሊሞሏት የማይችሉ የእውቀት አይነቶች ናቸው። ነፍሳችንን የሚሞላ ግን አንድ ዘላለማዊ የሆነ እውቀት አለ። ይሄ ዘላለማዊ የሆነና ነፍሳችንን የሚሞላ እንዲሁም መጽሀፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ይኑራችኑ የሚለን እውቀት፥ ስለ እግዚአብሄር ሊኖረን የሚገባ እውቀት ነው። እግዚአብሄርን ማወቅ ነው:: እረፉ እኔም አምላክ እንደሆንኩ እወቁ እንደሚለው፥ ነፍሳችንን የሚሞላ ብቻ ሳይሆን ነፍሳችንን ማሳረፍ የሚችል ብቸኛ እውቀት ነው። የትኛውም ምድር ላይ ያለ የእውቀት አይነት፥ ነፍሳችንን የማሳረፍ አቅም የለውም። ነፍሳችንን የሚያሳርፋት፥ እግዚአብሄርን በማወቅ ውስጥ የምናገኘው እውቀት ብቻ ነው። መጽሀፍ ቅዱስ እውነት አርነት ያወጣችኋል ሳይሆን፥ እውነትን ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል እንደሚለው፥ እውነት አርነት የሚያወጣን ስናውቀው ብቻ ነው። ስለ እውነት የምናገኘው እውቀት ነው አርነት የሚያወጣንና የሚያሳርፈን። እውነት ደግሞ እራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እውነት እግዚአብሄር ነው። ስለዚህ ብዙ ጨለማዎቻችን እየተገፈፉ፥ ወደ ሙሉ አርነት የምንወጣው፥ እግዚአብሄርን እያወቅን በመጣን መጠን ነው። አንድ ሰው በጣም ተምሮና ብዙ እውቀት አግኝቶ ትልቅ የስልጣን ደረጃ ላይ ቢደርስ እንኳን፥ እግዚአብሄርን ካላወቀ ግን ነፍሱ ባዶ ናት። እውቀት ያለው አይምሮው ውስጥ ብቻ ነው። ነፍሱ ውስጥ ምንም አይነት እውቀት የለም። አይምሮው ደግሞ እዚህ ምድር ላይ ቀሪ ነገር ነው። ስለዚህ ብዙ አመታቶች ለፍቶ የተማረው እውቀት ሊጠቅመው የሚችለው፥ እግዚአብሄር በወሰነለት በዚህች ምድር ቆይታው ብቻ ይሆናል። 

“ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም” (ምሳሌ 19:2) 

ስለ እግዚአብሄር የምናገኘው እውቀት፥ ነፍሳችንን ከማሳረፉም በላይ ከብዙ የጥፋት መንገዶች እኛን ማዳን መቻሉ ደግሞ በጣም አስደናቂ ነው። መጽሀፍ ቅዱስ በሆሴእ ምእራፍ 4 ቁጥር 6 ላይ ሲናገር፥ “ህዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቷል” እንደሚለው፥ ስለ እግዚአብሄር ከጎደለው እውቀት የተነሳ፥ አንድ ሰው ወይንም ጥቂት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፥ ህዝብ ወደ ጥፋት እንደሄደ የእግዚአብሄር ቃል ይናገራል። ዛሬም የብዙ ጥፋቶቻችን ዋና መሰረት፥ ስለ እግዚአብሄር ያለን እውቀት ማነስ ሆኖ እናገኘዋለን። መጽሀፍ ቅዱሳችን በሮሜ መጽሀፍ ምእራፍ አንድ ላይ እንደሚናገረው፥ “እግዚአብሄርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን፥ እግዚአብሄር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አይምሮ አሳልፎ ሰጣቸው” ይልና ይሄንንም ተከትሎ፥ እነዚህ ለማይረባ አይምሮ ተላልፈው የተሰጡት ሰዎች፥ ወደ ብዙ ጥፋትና ሀጢያት ውስጥ መግባታቸውን እየዘረዘረ በመናገር ቃሉ ይቀጥላል። ሰው እግዚአብሄርን ለማወቅ ባልወደደ መጠን፥ ተላልፎ የሚሰጠው ለማይረባ አይምሮ ነው። ተላልፎ የሚሰጠው፥ ከንቱ ለሆነ አይምሮ ነው። እግዚአብሄርን ማወቃችን ግን ከማይረባ አይምሮ እየጠበቀ ከንቱነትን ከእኛ ያርቃል። 

እግዚአብሄርን ስላለማወቅ ስናነሳ ከህይወታቸው ብዙ ልንማርባቸው የምንችላቸው ሁለት ሰዎች በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተጽፈው እናገኛለን። ሁለቱ የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ። የኤሊ ልጆች፥ የአባታቸውን የክህነት አገልግሎት እያዩ ያደጉ፥ እነርሱም ልክ እንደ አባታቸው የክህነትን አገልግሎት ተቀብለው፥ ካህናቶች በመሆን በቤተ መቅደስ ውስጥ ለማገልገል የተሾሙ የእግዚአብሄር አገልጋዮች ነበሩ። መቼም ስለ ክህነት አገልግሎት ስናስብ፥ አንድ ሰው ካህን ከሆነ ከሌሎች እግዚአብሄርን ከሚከተሉ ሰዎች ስለ እግዚአብሄር የተሻለ እውቀት ሊኖረው እንደሚገባ እናስባለን። በተለይ ደግሞ በብሉይ ኪዳን ይሄ አገልግሎት በጣም ከባድና ብዙ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው አገልግሎት መሆኑን እናውቃለን። በክህነት አገልግሎት የሚያገለግሉት የኤሊ ልጆች፥ በቤተ መቅደስ ውስጥ ብዙ እግዚአብሄርን ደስ የማያሰኙ ነገሮችን የሚያደርጉ፣ የክህነቱን ስርአት ትክክል ባልሆነ መንገድ የሚያደርጉ፣ የእግዚአብሄርን ቁርባን የሚንቁ፣ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር የሚተኙና እግዚአብሄርን የሚያስቆጡ፥ ሀጢያታቸውም በእግዚአብሄር ፊት ታላቅ የሆነችባቸው ልጆች ነበሩ። ታዲያ ስለ ኤሊ ልጆች ሀጢያት የሚናገረው የእግዚአብሄር ቃል ወደዚህ ድርጊት የወሰዳቸውን ዋና ምክኒያት እንዲህ በማለት ሳይናገር አላለፈም። “የኤሊ ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፥ እግዚአብሄርንም አያውቁም ነበር” በማለት እዚያው በ1ኛ ሳሙኤል ምእራፍ 2፡12 ላይ ይነግረናል። የኤሊ ልጆች እግዚአብሄርን አለማወቃቸው ወደ ከንቱነት ወደ ምናምንቴነት ህይወታቸውን ከመውሰዱም በላይ፥ ከላይ በሮሜ መጽሀፍ ላይ ለማይረባ አይምሮ የተሰጡ ሰዎች ብሎ ካላቸው ሰዎች ጋር ተመሳሳይ የሆነ የህይወት አካሄድ ሲኖራቸው እንመለከታለን። 

ሰው እግዚአብሄርን ባላወቀው መጠን፥ ህይወቱ የሚሄደው ወደ ከንቱነት ነው። እነዚህ በክህነት ያገለግሉ የነበሩት የኤሊ ልጆች፥ አገልግሎታቸው እግዚአብሄርን ከማወቅ ውጪ ነበር። እግዚአብሄርን በማወቅ አልነበረም ያገለግሉ የነበሩት። እግዚአብሄር ደግሞ ልናገለግለው ከመነሳታችን በፊት፥ መጀመሪያ የሚፈልገው እርሱን እንድናውቀው ነው። ለዚያ ነው በሆሴዕ መጽሀፍ ላይ “እግዚአብሄርን ማወቅ ጠልተሀልና እኔም ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሀለሁ” በማለት፥ እግዚአብሄር እርሱን ከማወቅ ውጪ የሆነውን ክህነት ወይንም አገልግሎት እንደሚጠላ የተናገረው። ሰውን እንኳን እኮ እናገልግለው ብለን ስንነሳ፥ ያ ሰው ማን መሆኑን ባህሪውን፣ የሚወደውን፣ የሚጠላውን፥ የሚፈልገውን፣ የማይፈልገውን ነገር ጠንቅቀን ካላወቅን፥ ያንን ሰው እናገልግለው ብለን ልናበሳጨውም እንችላለን። ለእኛ በጣም ጥሩና የሚያስደስተን አገልጋይ ማለት፥ እኛ ማን መሆናችንን ባህሪያችንንና ፍላጎታችንን ጠንቅቆ ያወቀና የተረዳ ሰው ነው። ትልቅ የሆነውን አምላክ ልናገለግል ስንነሳ፥ መጀመሪያ የሚፈልገው እንድናውቀው ነው። ማንነቱን እንድናውቅ፣ የሚወዳቸውን፣ የሚጠላቸውን ነገሮች እንድናውቅ፣ የሚያስደስተውን ነገሮች ደግሞም የሚያሳዝነውን ነገሮች ባህሪያቶቹን ሁሉ እንድናውቅ ነው። በዚህ እውቀት ውስጥ የሆነ አገልግሎት፥ እርሱ እንደሚፈልገው ስለሚሆን ደስ ያሰኘዋል። በተለይ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለማገልገል እድል የተሰጠን ሁላችንም እንደመሆናችን፥ አገልግሎቶቻችን መጀመር ያለባቸው እግዚአብሄርን ከማወቅ ነው። 

የእግዚአብሄር መሻት፥ የሰው ልጆች በሙሉ እሱን እንዲያውቁት፥ ምድር ሁሉ እሱን በማወቅ እንድትሞላ ነው። መቼም እግዚአብሄር የሚባል ሁሉን የፈጠረ አምላክ እንዳለ ብዙዎቻችን ብናውቅም፥ እግዚአብሄርን በቅርበት ማወቅ፣ ከእርሱ ጋር ቅርበት ያለው ወዳጅነት መኖር፣ በህይወት መንገዶቻችን ውስጥ እሱን ማወቅ ደግሞ ሌላ ራሱን የቻለ ነገር ነው። ለምሳሌ እናንተን ሰዎች ሁሉ በተመሳሳይ ደረጃና መጠን አይደለም የሚያውቋችሁ። ሰዎች ከእናንተ ጋር ባሳለፉት ጊዜ መጠን፥ ስለ እናንተ ያላቸው የእውቀት ደረጃ የተለያየ ነው። ከሰዎች ጋር ያሉን ግንኙነቶች እያደጉ የሚሄዱት፥ በሰጠናቸው ጊዜ መጠን ነው። ጊዜ በሰጠነው መጠን መተዋወቃችን ይጨምራል። አብረንማ መኖር ከጀመርን፥ ህይወትን አብረን መጓዝ ከጀመርን፥ አብሮን የሚኖረው ሰው በሆነ ጉዳይ ላይ ሊሰጥ የሚችለውን ምላሽ ሁሉ ሳይቀር ነው ማወቅ የምንጀምረው። ሊል የሚችለውን፣ ሊያስብ የሚችለውን ነገር ሁሉ ቀድመን ማወቅ እንጀምራለን። እከሌማ ይሄንን አያደርግም። እሱማ እንደዚህ ሊል አይችልም ብለን፥ ሊልና ላይል የሚችላቸውን ነገሮች፥ ሊያስብና ላያስብ የሚችላቸውን ነገሮች እርግጠኞች እስከምንሆን ድረስ፥ አብረን ያሳለፍነው ጊዜ በዚያ ሰው ላይ የሚኖረንን እምነት ጠንካራ ያደርገዋል። ይሄንን እምነት የሚፈጥረው ከዚያ ሰው ጋር ባሳለፍናቸው ጊዜያቶች ውስጥ ስለዚያ ሰው የምናገኘው እውቀት ነው። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እግዚአብሄር ሊሰጥ የሚችለውን ምላሽ ፈቃዱንና ሀሳቡን እያወቅን የምንሄደው፥ እግዚአብሄር እራሱን እያወቅነው በመጣነው መጠን ነው። እግዚአብሄርን ስለማወቅ አስፈላጊነት ይሄንን ያህል ካልን፥ እግዚአብሄርን ለማወቅ የሚረዱንን ሁለት ዋና ዋና መንገዶች እስኪ እንመልከት፥

  1. መጽሀፍ ቅዱስን ጊዜ እየሰጠን ማጥናት— እግዚአብሄርን በስፋት ልናውቅ ከምንችልባቸው ዋና ዋና መንገዶች ውስጥ አንዱ፥ የእግዚአብሄር ቃል ነው። መጽሀፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሄር ማንነቶች፣ ስለ ባህሪያቶቹ፣ ስለሚወዳቸውና ስለሚጠላቸው ነገሮች፣ ስለሚደሰትባቸውና ስለሚያዝንባቸው ነገሮች፣ ዋጋ ስለሚሰጣቸውና ስለማይሰጣቸው ነገሮች፥ በቀጥታም ሆነ በተለያዩ ምሳሌዎችና ታሪኮች እየዘረዘረ ይናገራል። በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጻፉልን የተለያዩ ሰዎች ታሪኮች እንኳን ሳይቀሩ፥ ዋና አላማቸው፥ በታሪኮቻቸው ውስጥ እግዚአብሄርን፣ ማንነቶቹንና ባህሪያቶቹን ለእኛ ማስተዋወቅ ነው። ለምሳሌ የአስቴር መጽሀፍ፥ በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ እግዚአብሄር የሚለው ስም በፍጹም ያልተጠቀሰበት መጽሀፍ ይሁን እንጂ፥ ታሪኩን በማስተዋል ስናነበው ግን እግዚአብሄር ሞገስና ውበት ሰጪ አምላክ መሆኑን፣ እግዚአብሄር ትክክለኛ ፍርድ ፈራጅ አምላክ መሆኑን፣ እግዚአብሄር ህዝቡን የማይጥል እንዲሁም ያከበሩትን የሚያከብር፥ በጥላቻና በክፋት የሚሄዱትን ሰዎች ደግሞ እንደ ስራቸው የሚሰጥ አምላክ መሆኑን እንዲሁም ብዙ የእግዚአብሄርን ባህሪያቶች እንማርበታለን። የብሉይ ኪዳንን ታሪኮች ስናነብ፣ ለአባቶቻችን እግዚአብሄር ይመልስላቸው ከነበሩት መልሶች፣ ይመራቸው ከነበሩት መንገዶች፣ ያደርግላቸው ከነበሩት ነገሮች ሁሉ፥ ስለ እግዚአብሄር ማንነት ብዙ የምንማራቸው ነገሮች አሉ። 

    እንግዲህ ከላይ ስንመለከት፥ እግዚአብሄርን ሳያውቁ ማገልገል ስላለው ትልቅ አደጋ ከኤሊ ልጆች ህይወት ተመልክተናል። የአንደኛ ሳሙኤልን መጽሀፍን ስታነቡ፥ የኤሊ ልጆች በነበሩበት ዘመን የተወለደና በቤተ መቅደስ ያደገ አንድ ልዩ ሳሙኤል የሚባል ልጅ ደግሞ ነበረ። ሳሙኤል አካባቢው እያየ ያደገው የኤሊ ልጆች ትክክል ያልሆነ የህይወትና የአገልግሎት አካሄድ ህይወቱ ላይ ተጽእኖ ሳይፈጥርበት፥ እግዚአብሄርን በማወቅ አድጓል። ሳሙኤል የተበላሸ የአገልግሎት አካሄድ ካላቸው ከኤሊ ልጆች ጋር ቢያድግም፥ የተለየ መንፈስ ይዞ እንዲያድግ ስለረዳው አንድ ሚስጥር የእግዚአብሄር ቃል በአንደኛ ሳሙኤል ምእራፍ 3፥21 ላይ እንዲህ በማለት ይነግረናል። “..እግዚአብሄርም በእግዚአብሄር ቃል ለሳሙኤል በሴሎ ይገለጥ ነበር” ይላል። እግዚአብሄር ለሳሙኤል በሴሎ ይገለጥለት የነበረው፥ በቃሉ ውስጥ ነበር። ሳሙኤል እግዚአብሄርን ለማወቅ እድል ያገኘው፥ በቃሉ ውስጥ ነበር። ታዲያ ይሄ በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ እግዚአብሄርን ለማወቅ እድል ያገኘው ልጅ ሳሙኤል፥ በዘመኑ ሁሉ ታማኝ የእግዚአብሄር አገልጋይ ሆኖ አልፏል። በተሰጠው ዘመንና እድል፥ እግዚአብሄርን ደስ በሚያሰኝ ህይወትና አገልግሎት ሄዷል። 

  2. እግዚአብሄርን መከተል  እግዚአብሄርን ቃል ከማንበብ ቀጥሎ እግዚአብሄርን የምናውቅበት ሌላው ዋነኛ ነገር እግዚአብሄርን መከተል ነው። መጽሀፍ ቅዱስ በሆሴዕ መጽሀፍ ላይ ሲናገር “እንወቅ” ይልና ወዲያ ቀጠል አርጎ “እናውቅም ዘንድ እግዚአብሄርን እንከተል” በማለት እግዚአብሄርን ማወቅ የሚገኝበትን መንገድ በግልጽ ይናገራል። እግዚአብሄርን ማወቅ የሚገኘው፥ እግዚአብሄርን ከመከተል ነው። 

    ኢየሱስ በምድር አገልግሎቱ ሲመላለስ፥ ሊጠቀምባቸውና ሊሰራባቸው የወዳደቸውን ሰዎች ከሰዎች ሁሉ መካከል እየጠራ “ተከተለኝ” ይል ነበር። “ተከተለኝ” በምትለዋ ቃል ውስጥ አንድ ሚስጥራዊ ትርጉም አለ። “እመራሀለሁ” የሚል ትርጉም። “ተከተለኝ” የምትሉት፥ ወደ ሆነ ቦታ ልትመሩ ወይንም ልታደርሱ የምትሹትን ሰው ነው። እግዚአብሄርን ስንከተል፥ የእርሱን ምሪት አምነን ነው። ወደ ወደደው ቦታ ህይወታችንን እንደሚወስደው፥ ህይወታችንን በሚወስዳቸው መንገዶች ሁሉ ውስጥ እርሱ አዋቂ እንደሆነ አምነን ነው። 

    መኖርና እግዚአብሄርን በመከተል መኖር በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። አንድ ሰው የራሱን የህይወት ምርጫዎች እየተከተለ ሊኖር ይችላል። እግዚአብሄርን መከተል ማለት፥ እኛ መሄድ የምንፈልግባቸውን መንገዶች እየተውን፥ እርሱ ኑ ወደሚለን መንገዶች መሄድ ማለት ነው። እግዚአብሄርን መከተል ማለት፥ በእግዚአብሄር ቃል ላይ የተጻፉልንን ትእዛዞች እንዲሁም እግዚአብሄር ለግል ህይወታችን የሰጠንን ምሪቶች እየተከተልን ወይንም እየታዘዝን መሄድ ማለት ነው። 

    የእስራኤል ህዝቦች ተከተሉኝ ብሎ እግዚአብሄር ሊመራቸው በወሰዳቸው የምድረበዳ አመታቶች ውስጥ፥ በስፋት እግዚአብሄርን ለማወቅ እድል አግኝተው ነበር። እግዚአብሄር በደመናና በእሳት አምድ ሲመራቸው ያዩት፥ እግዚአብሄርን በተከተሉባቸው የምድረበዳ መንገዶች ውስጥ ነበር። መና የወረደላቸው፣ ውሀ ከደረቀ አለት ውስጥ ሲፈልቅ ያዩት፣ የኤርትራ ባህር ሲከፈል አይተው እግዚአብሄር ተዋጊ ስሙም እግዚአብሄር መሆኑን ያወቁት፣ ጸሀይን በገባኦን እያቆመ ሲዋጋላቸው ያዩት፣ ህግና ስርአቶቹን ተምረው የበለጠ እግዚአብሄርን ወደ ማወቅ ያደጉት፥ እግዚአብሄርን በተከተሉባቸው የምድረበዳ መንገዶች ውስጥ ነው። እግዚአብሄር ምንጊዜም ህይወታችንን የሚመራው፥ እርሱን የበለጠ ወደምናውቅባቸው የህይወት መንገዶች ነው። 

    ብዙ ሰዎች ሲናገሩ፥ “እኔ እግዚአብሄርን የበለጠ ያወኩት በመከራ ወይንም በችግር ወይንም በህመም ውስጥ ያለፍኩ ጊዜ ነው” እያሉ ሲናገሩ እንሰማቸዋለን። እግዚአብሄር እንድንማር የወደዳቸውን ነገሮች፥ በምን ውስጥ ህይወታችንን ቢያሳልፈው እንደምንማረው ያውቃል። ስለ እርሱ እንድናውቅ የወደዳቸውን ነገሮች፥ በምን ውስጥ ብናልፍ እንደምናውቃቸው ያውቃል። ሰው በሆነ እርዳታ በሚፈልግበት ችግር ውስጥ ካላለፈ “የእግዚአብሄር እርዳታ” የሚባለው ነገር እንዴት ነው ሊገባው የሚችለው? ሰው በመከራ ውስጥ ካላለፈ፥ የእግዚአብሄር አብሮነት የሚለውን ነገር እንዴት ይማረዋል? “ልባቸው ለተሰበረ እግዚአብሄር እንዴት ቅርብ ነው” የሚለውን ቃል፥ ሰው በሆነ አጋጣሚ ልቡ ተሰብሮ እግዚአብሄር ሲቀርበው ካላየ፥ የእግዚአብሄር ቅርበት የሚሰጠውን ደስታና ሰላም እንዲሁም መጽናናት፥ የእግዚአብሄር ቅርበት የሚሰጠውን ፈውስና ሰላም እንዴት ይለማመደዋል? 

    እኔ በግል ህይወቴ፥ የመንፈስ ቅዱስ ማጽናናት የሚባለው አስደናቂ ነገር በልቤ ውስጥ ገብቶ፥ እየደገፈ ሲያቆመኝ ያየሁት፥ በጣም የምወደውን ወላጅ አባቴን ባጣሁበት የህይወቴ ወቅት ነበር። “እግዚአብሄር አጠገቤ ካለ ምንም አልሆንም። እርሱ ከእኔ ጋር ይሁን እንጂ፥ የትኛውንም ሀዘን አልፈዋለሁ” የሚለው እምነት የገባብኝ ከዚያ በኋላ ነው። የሀዘን ጉልበት ከመንፈስ ቅዱስ የማጽናናት ጉልበት እንደማይበልጥ የተማርኩበት፥ ሰው አይዞሽ ብሎ ሊያጽናና ያልቻለው ልቤ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ እየገባ ሲፈውሰውና ደህና ሲያረገው ያየሁት፥ በጣም የምወደውንና ያለ እርሱ መኖር የማልችል ይመስለኝ የነበረውን አባቴን ሳጣው ነው። አሁን ላይ አባቴ በአካል አጠገቤ አለመኖሩን እራሴን ማስታወስ እስከሚያስፈልገኝ ድረስ፥ ምንም አይነት ክፍተት እንዳይሰማኝ የሆነ መጽናናትና ፈውስ ህይወቴን ሞልቶታል። የእግዚአብሄር አባትነት ጥልቀቱ የገባኝ ደግሞ እግዚአብሄር ወላጅ አባቴን ወስዶ እርሱ ብቻውን አባት ሊሆነኝ ከፈለገበት ጊዜ ጀምሮ ነው። 

    ሌላ ምሳሌ ደግሞ ወስደን ብናይ፥ ሰዎች የእግዚአብሄርን መልካምነት በተለያየ አይነት ሁኔታ ውስጥ ይማሩታል። ጸሎታቸውን ሲሰማ ሲያዩ፥ የልባቸውን መሻት ሲሰጣቸው፥ መልካም መልካም ነገሮችን በማድረጉ ውስጥ የእግዚአብሄርን መልካምነት ይማሩታል። እኔ የእግዚአብሄርን መልካምነት ተምሬው ልቤ ውስጥ ተጽፎ የቀረው፥ በህመም ውስጥ ባለፍኩበት በአንድ የህይወቴ ወቅት ነበር። እያመመኝ ነው እግዚአብሄር እንዴት መልካም አምላክ እንደሆነ ነፍሴ ተረድታው የቀረችው። እግዚአብሄር እኔ የእርሱን መልካምነት ልረዳ የምችለው፥ በጊዜው ባመመኝ ነገር ውስጥ ቢያሳልፈኝ እንደሆነ ገብቶታል። በብዙ ህመምና እምባ ውስጥ ሆኜ፥ “እኔ ቢያመኝም ባያመኝም አንተ መልካም ነህ። የእኔ የህይወት መውጣትና መውረድ ቋሚ በሆነው ማንነትህ ውስጥ ያለውን መልካምነትህን አይለዋውጠውም” የሚለውን መረዳት ያገኘሁት፥ እግዚአብሄር ባሳለፈኝ በዚያ መንገድ ውስጥ ነው። ልክ እዛ መረዳት ጋር ስደርስ፥ ነፍሴም ስጋዬም ተፈወሱ። ከዚያም በጊዜው ያለፍኩበት ህመም አላማ፥ ይሄንን ነገር ማስተማርና ልቤን በዚህ አቅጣጫ መለወጥ እንደነበር ተረዳሁ። አንዳንዱን በከፍታ፣ አንዳንዱን በዝቅታ ውስጥ ያስተምረናል። አላማው ግን አንድ ነው። ማንነቶቹን ለእኛ ማስተማር። ነፍሳችንን ከራሱ በሆነ እውቀት እየሞላ እኛን ከከንቱ እና ከማይረባ አይምሮ መጠበቅ ነው። 

    ሰው እግዚአብሄር አብሮት ሲሆን ካላየ ነገ ይገጥመኛል ብሎ ለሚያስበው ችግር እንዴት እምነትን ያገኛል? መዝሙረ ዳዊት ላይ ሲናገር፥ “ምድር ብትነዋወጥ፣ ተራሮችም ወደ ባህር ልብ ቢወሰዱ እኛ አንፈራም” ከማለቱ በፊት፥ “አምላካችን መጠጊያችን ነው። ሀይላችን ነው። ባገኘን በታላቅ መከራ ደግሞ ረዳታችን ነው” ይልና፥ ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባህር ልብ ቢወሰዱ እኛ አንፈራም ይላል። የእነዚህ ሰዎች ያለመፍራታቸው ምክኒያት የሁሉ ነገር ሰላም መሆን አይደለም። በሚያስፈራሩ ነገሮች ውስጥ የእግዚአብሄርን መጠጊያ መሆን፣ የእግዚአብሄርን ረዳትና ሀይል መሆን ማወቃቸው ነው። ይሄ እምነት የሚመጣው ደግሞ፥ በህይወት መንገዶቻችን ውስጥ ስለ እግዚአብሄር ከምናገኛቸው እውቀቶች ነው። እግዚአብሄርን የምናውቀው፥ ትእዛዞቹንና ምሪቶቹን በመከተል በምንሄድባቸው የህይወት ጎዳናዎች ውስጥ ነው ምክኒያቱም እግዚአብሄርን ህይወታችንን የሚመራው፥ እርሱን የበለጠ እንድናውቀው ወደሚያደርጉን የህይወት መንገዶች ነው።

“እንወቅ እናውቅም ዘንድ እግዚአብሄርን እንከተል” (ሆሴእ 3፡6) 

 ዝግጅት

 ዝግጅት

	አንዲቷ  ልመና

አንዲቷ  ልመና