Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ጠቢብ

ጠቢብ

መጽሀፍ ቅዱሳችንን ስናጠና፥ በስፋትና በተደጋጋሚ እየተጠቀሰ የምናገኘው ነገር ነው ጥበብ። በተለይም የምሳሌ መጽሀፍ እየደጋገመ አየደጋገመ ያነሳዋል። የርእሱ መደጋገም፥ የነገሩን አስፈላጊነት እያመለከተን፥ እዚሁ የምሳሌ መጽሀፍ ላይ፥ ጥበብ ከቀይ እንቁ እንደምትበልጥ፥ የከበረ ነገር ሁሉ እንደማይስተካከላት፥ እንዲሁም እኛ በዚህች ምድር ላይ፥ ውድ ብለን ካስቀመጥናቸው ነገሮች ሁሉ በላይ ውድ እንደሆነች ይነግረናል። ይህቺ ምድር ላይ ካሉ ነገሮች ሁሉ በላይ ውድ የሆነችው አይነተኛ ነገር፥ በራሷ አንደበት ውድነቷን ትናገራለች። ነገስታት የሚነግሱት በእኔ ነው ትላለች። እግዚአብሄር ሰማያትን ሊሰራ ሲነሳ አብሬው ነበርኩ፥ እግዚአብሄር የመንገዱ መጀመሪያ አርጎኛል በማለት ከጥንት ጀምሮ ይጠቀምባት እንደነበር በራሷ አንደበት ትመሰክራለች። አንዳንዴ ደግሞ፥ በጎዳና ላይ በመውጣት እየተጣራች፥ ድምጽዋን ከፍ አድርጋ ለሚሰሟት ሁሉ እንዲህ እያለች ትጮሀለች “እናንተ አላዋቂዎች እስከ መቼ አላዋቂነትን ትወዳላችሁ፥ ወደ ዘላፋዬ ተመለሱ፥ እነሆ መንፈሴን አፈስላችኋለሁ። ቃሌንም አስተምራችኋለሁ። ነገር ግን እኔን ሊሰማኝ የሚፈልግ ስለሌለ፥ ምክሬንም የሚሰማ ስለሌለ፥ ድንጋጤ እንደ ጎርፍ ሲመጣ አልመልስም፥ ተግቶ የሚፈልገኝም አያገኘኝም። የሚሰማኝ ግን ትላለች ጥበብ፥ የሚሰማኝ በእርጋታ ይቀመጣል፥ ከመከራ ስጋትም ያርፋል” በማለት በሰው ልጆች ህይወት ውስጥ፥ እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኗንና የሚሰሟትን ሁሉ ከብዙ ጥፋት እንደምታድን ትናገራለች። ከእድሜያችን ቁጥር ብዛት ልምድን ልናገኝ እንችላለን። ጥበብ ግን በእድሜ ዘመን ብዛት አትገኝም። ባሳለፍናቸው የህይወት ልምምዶች ውስጥ፥ ልምድን ወይንም ደግሞ “ይሄ ሰው በሳል ነው” እንደሚባለው ብስለትን እናገኝ ይሆናል። ጥበብ ግን፥ ባሳለፍናቸው የህይወት ልምምዶች ውስጥ የለችም። እድሜያችን በጨመረ ቁጥር፥ በህይወቶቻችን የምናልፍባቸው ውጣ ውረዶች ብዙ ትምህርቶችን አስተምረውናል፥ ጥበብ ግን በዚህች ምድር ላይ ከኖርናቸው ዘመናቶች ቁጥር ጋር ምንም አይነት ተያያዥነት የላትም። ካለፍንባቸው የህይወት መንገዶችም የምናገኛት ነገር አይደለችም። ጥበብ ከእግዚአብሄር ቃል ወይንም ከእግዚአብሄር መንፈስ የምትሰጥ የእግዚአብሄር ውድ ስጦታ ናት። ለዚህ ትልቁ ማስረጃችን በኢዮብ መጸሀፍ መጨረሻ ላይ ኤሊሁ ስለተባለው በእድሜ አካባቢው ከነበሩ ሰዎች በጣም ያነሰ፥ ነገር ግን የእግዚአብሄር መንፈስ ጥበብን ስለሞላበት ልጅ ስናነብ የምናገኘው ነው። ወቅቱ፥ እግዚአብሄር ኢዮብን ለመፈተን በተለያዩ የህይወት ፈተናዎች ውስጥ የሚያሳልፈው ወቅት ነበር። ኢዮብ እያለፈ የነበረባቸውን ከባባድ የህይወት ፈተናዎች ስለሰሙ፥ ጓደኞቹ ከሩቅ ሀገር እርሱን ለማጽናናትና ከጎኑ ለመሆን መጥተው ነበር። እነዚህ ኢዮብን ለማጽናናት የመጡ የኢዮብ ወዳጆች ታዲያ፥ አጠገቡ በመሆን የሚያልፍበትን ሁሉ በአይናቸው ካዩና ከተመለከቱ በኋላ፥ ትክክል ነው ብለው ያመኑትን አስተያየቶች ከመስጠት ወደኋላ አላሉም። የሚገርም ነው፥ በተለይ ስለ እግዚአብሄር የሚናገሩት አስደናቂ አስደናቂ ነገሮች እኮ፥ ዛሬ ላይ እኛ የስብከት መልእክቶቻችንና የዝማሬ ግጥሞቻችን የምናረጋቸው ናቸው። እነዚህ የኢዮብ ወዳጆች ታዲያ፥ እግዚአብሄር በኢዮብ ላይ የነበረውን ሀሳብ በማወቅ አልነበረም ይናገሩ የነበሩት። ንግግራቸው ሁሉ እግዚአብሄር በኢዮብ ላይ የነበረውን ሀሳብ ከማወቅ ውጪ፥ ከእውቀት ውጪ ነበር። ታዲያ ኢዮብና የኢዮብ ወዳጆች ያደርጉ የነበሩትን ረጅም ንግግሮች በትእግስት ቁጭ ብሎ ለረጅም ሰአታት ያዳምጥ የነበረ፥ አንድ ኤሊሁ የተባለ በእድሜ ከኢዮብም ሆነ ከኢዮብ ወዳጆች ያነሰ አንድ ወጣት ልጅ ነበረ። ኤሊሁ፥ በኢዮብ መጽሀፍ ምእራፍ ሰላሳ ሁለት ጀምሮ የምታገኙት ልጅ ነው። ትእግስተኛ ነው። አዳማጭ ነው። ለረጅም ሰአታቶች ዝም ብሎ የማዳመጥ አቅም አለው። ያውም ደግሞ፥ አካባቢው ከነበሩ ሰዎች የተሻለ መናገር የሚችልበትን እውቀት ይዞ በትእግስት ዝም ብሎ መስማት ከባድ ነገር ነው። እኔ በዚህ ሁኔታ ስንት ጊዜ ራሴን ታዝቤው አውቃለሁ መሰላችሁ። ሁሌ ከምመኘውና እግዚአብሄርን ከምለምነው ነገር አንዱ፥ ለረጅም ጊዜ ማዳመጥ የምችልበትን አቅም እንዲሰጠኝ ነው። ታዲያ ይሄ ኤሊሁ የተባለው ወጣት፥ አካባቢው ላይ የነበሩትን የኢዮብንና የወዳጆቹን ንግግር አዳምጦ ከጨረሰ በኋላ፥ በሶስቱም በኢዮብ ወዳጆች አፍ ምንም አይነት መልስ እንደሌለ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ ሲል በቁጣ መንፈስ ተናገሮ ነበር። “እኔ በእድሜ ታናሽ ነኝ። እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ። ስለዚህም ሰጋሁ፥ እውቀቴን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈራሁ። እንደዚህም አልሁ “አመታት በተናገሩ ነበር። የአመታትም ብዛት ጥበብን ባስተማረች ነበር። ነገር ግን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ። ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ፥ ማስተዋልን ይሰጣል። በእድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም። ሽማግሌዎችም ፍርድን አያስተውሉም። ስለዚህ ስሙኝ፥ እኔ ደግሞ እውቀቴን እገልጥላችኋለሁ አልሁ። እነሆ ቃላችሁን በትእግስት ጠበቅሁ። የምትናገሩትን ነገር እስክትመረምሩ ድረስ ብልሀታችሁን አዳመጥሁ።” በማለት ጥበብ ከእድሜያችን ብዛት እንደማትገኝ ይልቁንም ሁሉን የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ለሰው ልጆች ማስተዋልን እንደሚሰጥ ይናገራል። ጥበብ፣ ማስተዋልና እውቀት ከመንፈስ ቅዱስ ወደ ልባችን የሚፈሱ የእግዚአብሄር ስጦታዎች ናቸው እንጂ እዚህ ምድር ላይ የምናገኛቸው ነገሮች አይደሉም። እንዲያውም የኢሳይያስ መጽሀፍ ምእራፍ 11 ላይ ስናነብ የእግዚአብሄር መንፈስ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የሀይል፣ የእውቀትና እግዚአብሄርን የመፍራት መንፈስ እንደሆነ ይነግረናል። 

መጽሀፍ ቅዱሳችን ስለ ጥበብ በተለያዩ ቦታዎች በስፋትና በብዛት የጻፈልን ሲሆን፥ ሁለት አይነት የጥበብ አይነቶች እንዳሉ ሳይነግረን አላለፈም። አንደኛውና የመጀመሪያው፥ ሰማያዊ ወይንም ላይኛይቱ ጥበብ ብሎ የሚነግረን ከላይ የሚወርድና በመንፈስ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ለእኛ የሚሰጥ ፍጹም የሆነ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው። ሁለተኛው የጥበብ አይነት ደግሞ፥ ምድራዊ ጥበብ ነው። ያእቆብ በመጽሀፉ በቀጥታ ስለዚህ የጥበብ አይነት ሲናገር፥ ከላይ የሚወርድ ጥበብ እንዳልሆነ ከምድር፣ ከስጋ እንዲሁም ከአጋንንት እንደሆነ ይናገራል። ይሄ ምድራዊ የሆነ ጥበብ፥ ቅንአትና አድመኛነት፣ ሁከትና ክፉ ስራን የተሞላ እንደሆነ እንዲሁ በመጽሀፉ ሶስተኛ ምእራፍ ላይ ይገልጻል። ይህቺ አለም፥ የራሷ የሆኑትን ተጠቃሚ የምታደርግበት የራሷ የሆነ ጥበብ አላት። ይሄ የአለም ጥበብ ታዲያ፥ ከእግዚአብሄር ጥበብ የሚለይበት ዋና ነገሩ፥ ትኩረቱ ስጋዊነት ላይ ብቻ መሆኑ፥ ራስ ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑ ነው። የአለም ጥበብ ሁልጊዜ የሚያተኩረው፥ ራስ ላይ ብቻ ነው። ራስን መጥቀም፣ ራስን መውደድ ላይ ብቻ ነው። በየትም ብዬ በየት፥ የፈለኩትን ነገር እጄ ላስገባ ይላል የአለም ጥበብ። የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው እንደተባለው ተረት፥ የአለም ጥበብ እጁ ስለሚያስገባው ነገር እንጂ፥ ነገሩ እጁ ስለሚገባበት መንገድ ብዙም ግድ አይለውም። በአንደኛ ቆሮንቶስ ላይ ሲናገር፥ አለም በጥበቧ እግዚአብሄርን ስላላወቀች እንደሚል፥ የአለም ጥበብ ፈጽሞ እግዚአብሄርን አያውቅም። መነሻውም መድረሻውም ራስ ተኮር ነው። ከእግዚአብሄር ወደ ሆነው ጥበብ ደግሞ ስንመጣ፥ ሲጀምር እራሱ፥ የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሄርን መፍራት ነው። ይሄ እግዚአብሄር ጥበብ ብሎ በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ እየደጋገመ የሚነግረን ከቀይ እንቁ የሚበልጠው ውድ ነገር የሚጀምረው እራሱ፥ እግዚአብሄርን ከመፍራት ነው። በሌላ አማርኛ፥ እግዚአብሄርን ከመፍራት ያልጀመረ ነገር፥ በእግዚአብሄር ፊት፣ በእግዚአብሄር እይታ ጥበብ ተብሎ አይጠራም። በእግዚአብሄር አለም ውስጥ ጥበብ የሚል እውቅና የለውም። ከእግዚአብሄር የሆነ ጥበብ ዋና መለያው፥ ትኩረቱ እግዚአብሄርን መፍራት ላይ መሆኑ ነው። እግዚአብሄር ጠቢብ ብሎ የሚጠራው፣ “ይሄ ሰው ጠቢብ ነው” የሚለው እርሱን እየፈራ የሚመላለሰውን ሰው ነው። በአንጻሩ ደግሞ አንድ ሰው በሰዎች አይን በጣም ጠቢብ የመሰለ፣ የተመኘውን ነገር ሁሉ በየትም በየትም ብሎ የሚያገኝ፣ እግዚአብሄርን ለመፍራት ብዙም ቦታ የሌለው፥ ዋና ትኩረቱ የተመኘውን ነገር እጁ ማስገባት የሆነ፥ ከዚህም የተነሳ፥ የሚያገኛቸውን አማራጮች ሁሉ የሚጠቀም ሰው ሊሆን ይችላል። ይሄ ሰው ምናልባት እኛ ከውጪ ስናየው፥ ሰው የሚፈልገው ነገር ሁሉ ያለውና የተሟላለት ሰው ነው፣ እግዚአብሄር ግን ከላይ የሚያየው ሞኝ እንደሆነ ነው። መጽሀፍ ቅዱስ ስለ አለም ጥበብ ሲናገር እንዲህ ይላል። የአለም ጥበብ በእግዚአብሄር ፊት ሞኝነት ነው። ታዲያ ይሄ የእግዚአብሄርን ጥበብ የምናገኝባቸውን ሶስት ዋና ዋና መንገዶች እንይና የዛሬው ጽሁፋችንን እናጠቃልል። 

  1. የእግዚአብሄርን ቃል ማሰላሰል— የእግዚአብሄርን ቃል ሆነ ብሎ ማሰላሰል፥ ከእግዚአብሄር የሚሰጠውን ጥበብ ከምናገኝባቸው ዋና ዋና መንገዶች ውስጥ አንዱ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ቃሉን ስለማንበብ እንጂ ስለ ማሰላሰል ትኩረት ስንሰጠው አይታይም። አይምሮአችን በጥበብ የሚሞላው፥ ያነበብነውን ቃል በማሰላሰል፥ ቃሉ ውስጥ ያለውን መንፈስ ስናገኘው ነው። ኢየሱስ ሲናገር፥ እኔ የምነግራችሁ ቃል መንፈስ ነው ህይወትም ነው እንዳለው፥ ቃሉ ሰምተነው አሜን ብለን ብቻ የምንሄደው ነገር አይደለም። ውስጡ መንፈስ አለ። ይሄንን መንፈስ የምናገኘው ደግሞ፥ ጊዜ ሰጥተን በማሰላሰል ውስጥ ነው። ዳዊት በመጽሀፉ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሄርን ህጎች፥ የእግዚአብሄርን ትእዛዛት ጊዜ ሰጥቶ አንደሚያሰላስል ይናገራል። አንድ ቦታ ላይ እንዲያውም “አለቆች ተቀምጠው አሙኝ፥ ባሪያህ ግን ህግህን ያሰላስል ነበር” በማለት የእግዚአብሄርን ህግና ትእዛዛት ለማሰላሰል ጊዜ የሚሰጥ ሰው እንደሆነ ይናገራል። አለቆቹ ያሉት ሀሜት ላይ ነው። ሌላ ቦታ ላይ ናቸው። የዳዊት አይምሮ ግን፥ በእግዚአብሄር ቃል ቢዚ ነው፥ ሌሎች ለመንፈሱ የማይመቹትን ሀሳቦች የሚያስብበት ጊዜ የለውም። ከዚህም የተነሳ በዘመኑ ሁሉ እግዚአብሄር ካዘዘው ነገር ፈቀቅ ሳይል እንዳለፈ፥ የእግዚአብሄር ቃል እራሱ በአንደኛ ነገስት ምእራፍ 15:5 ላይ መስክሮለታል። ይሄ ያነበበውና ያሰላሰለው ቃል፥ ለህይወቱ ብዙ ጥበብን እየሰጠ፥ እግሮቹን ከብዙ የጥፋት መንገዶች ጠብቆለታል። ከዚህ ካሰላሰለው ቃል፥ ብዙ እግዚአብሄርን የመፍራትን ጥበብ አግኝቷል። የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሀደ አልጠቀማቸውም እንደሚለው፥ የሰማነው ወይንም ያነበብነው ሁሉ ቃል ከእኛ ጋር ይዋሀዳል ማለት አይደለም። አንዳንዴ ቃሉን ሰምተነው በኢንፎርሜሽን ደረጃ ብቻ አይምሮአችን ውስጥ ሊቀመጥ ይችላል። ይሄንን ኢንፎርሜሽን እያወጣን ጥቅስ ልንጠቅስበትም የመዝሙር ግጥም አርገን ልንዘምረውም፥ ልናስተምርበትም ሁሉ እንችላለን። ግን ይሄ የሰማነው ቃል ውስጥ ያለውን መንፈስ የምናገኘውና በህይወታችን በትክክል የሚጠቅመን፥ ስናሰላስለውና በእምነት ከእኛ ጋር ሲዋሃድ ነው። ስናሰላስለውና ቃሉ ውስጥ ያለውን መንፈስ ስናገኝ ነው። እዚሁ የቃሉ መንፈስ ውስጥ ነው ጥበብ ያለው። እዚሁ የቃሉ መንፈስ ውስጥ ነው ማስተዋልና እውቀት ያሉት። መንፈሳዊ ህይወታችን እራሱ በፍጥነት የሚያድገው፥ እንዲሁም በየቀን ህይወታችን ውስጥ ቀናቶቻችንን በትክክል ለማለፍ ጥበብን የምናገኘው፥ በምናሰላስለው ቃል ውስጥ የምናገኘው የእግዚአብሄር ቃል መንፈስ ነው። መንፈስ ነው እኛን የሚለውጠን። መንፈስ ነው አይምሮአችንን ሀሳባችንን በሙሉ የሚቀድሰው። ቃሉ ከተጻፈ በጣም ብዙ ሺህ አመታቶች ቢቆጠሩም፥ ያ እነርሱ መጽሀፍ ቅዱስን የጻፉበት መንፈስ ግን፥ አሁንም ህያው ሆኖ በቃሎቹ ውስጥ ይኖራል። መጽሀፍ ቅዱስን ማንበባችን ስኬታማ ሆነ የምንለው ታዲያ፥ የእምነት አባቶቻችን ቃሉን የጻፉበትን መንፈስ እኛ ስናገኘው ነው። ያ ነው ህይወታችንን የሚቀይረው። እዛ መንፈስ ውስጥ ነው ጥበብ ያለው፥ እዛ መንፈስ ውስጥ ነው እውቀትና ማስተዋል ያሉት። የቃልህ ፍቺ ያበራል ህጻናትንም አስተዋዮች ያደርጋል እንደሚለው። ማስተዋል ያለው፥ የእግዚአብሄር ቃል ፍቺ ውስጥ ነው። ፈቺው ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ነው። በዚህ በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ያለው መንፈስ ነው ከጠላቶቻችን ይልቅ አስተዋዮች እና ጥበበኞች የሚያደርገን።

  2. ሌላው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ህብረት ማድረግ ነው። ሰው በጸሎት ከእግዚአብሄር መንፈስ ጋር ጊዜ እያሳለፈ ሲመጣ ጥበበኛ እየሆነ ነው የሚመጣው። አስተዋይ እየሆነ ነው የሚመጣው። ማንም የተጠማ ቢኖር አለ ኢየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር፥ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ አለ። ወደ እኔ መጥቶ ይጠጣ ያለው የተጠማን ሰው ነው። አለመጠማታችን ከስንት የመንፈስ ቅዱስ ሙላት አጎደለን። ለምሳሌ ብዙ ውሀ መጠጣት የሚችለው፥ ብዙ የተጠማ ሰው ነው። እንደተጠማው መጠን፥ ብዙ የመጠጣት ችሎታ አለው። ብዙ ያልተጠማ ሰው ግን ብዙ ውሀ መጠጣት አይችልም። ኢየሱስ አንደሆነ በባህሪው ሰጪ ነው። ቢሰጥ ቢሰጥ አያልቅበትም። ለእኛ የሚሰጠው መጠን የሚወሰነው ግን፥ በጥማታችን ጥልቀት ወይንም በጥማታችን መጠን ነው። ብዙ የተጠማ ሰው፥ ብዙ ይጠጣል። መጠማት፥ መንፈሳዊ አለም ላይ ትልቅ ሀብት ነው። ብዙ መውሰድ የምንችልበት ገንዘብ ነው። በጸሎት ውስጥ የምንጠማው የእግዚአብሄር መንፈስ ውስጥ፥ ሁሉ ነገር አለ። እግዚአብሄር እኛን በጣም ከመውደዱ የተነሳ ከሰጠን ትልልቅ ስጦታዎች ውስጥ አንዱ፥ መንፈስ ቅዱስን ነው። መቼም መንፈስ ቅዱስ በእኛ ህይወት ውስጥ የሚሰራውን ስራ፥ አንድና ሁለት ብለን ዘርዝረን ልንጨርሰው አንችልም። የእግዚአብሄር መንፈስ የጥበብ፣ የማስተዋል፣ የእውቀት መንፈስ እንደመሆኑ፥ ህይወታችንን የምንመራበትንም ሆነ የምንኖርበትን ጥበብ የምናገኘው በጸሎት ውስጥ ወደ እኛ ከሚለቀቀው ከመንፈስ ቅዱስ ነው። ከላይ በኢሳይያስ መጽሀፍ ላይ ተጽፎ እንዳየነው፥ የእግዚአብሄር መንፈስ የጥበብ የእውቀት የማስተዋል የምክር መንፈስ መሆኑን አንብበናል። ይሄ መንፈስ ታዲያ እኛ ውስጥ በሙላት አለ ማለት፥ በሌላ አማርኛ፥ ጥበብ እኛ ውስጥ በሙላት አለ ማለት ነው። መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ በሙላት አለ ማለት፥ በሌላ አማርኛ እውቀትና ማስተዋል እንዲሁም ምክር በእኛ ውስጥ በሙላት አለ ማለት ነው። በህይወታችን ከራሳችን አልፈን ለሌሎች ጥበብን አስተማሪ የምንሆነው፥ ይሄ ጥበብን የተሸከመው የእግዚአብሄር መንፈስ በእኛ ውስጥ በሙላት ሲኖር ነው። መንፈስ ቅዱስን የምንሞላው ደግሞ በመጠማት ነው። በጸሎት ውስጥ ነው። 

  3. ሌላኛው ጥበብን የምናገኝበት ዋና መንገድ አይኖቻችንን ከፍተን አካባቢያችንን በመመልከት ነው። አይኖቻችንን ከፍተን በማስተዋል ለማየት ስንሞክር፥ አካባቢያችን ካሉ ነገሮች ብዙ የምንማረው ጥበብ አለ። መጽሀፍ ቅዱስ ስለ ጥበብ ሊያስተምረን ሲነሳ፥ በጣም ትንሽ ከሆነችው ጉንዳን ይጀምራል። “አንተ ታካች እስከመቼ ትተኛለህ? ይላል ምሳሌ መጽሀፍ ምእራፍ 6 ላይ ሲናገር። “እስኪ ወደ ገብረ ጉንዳን ሂድና መንገድዋን ተመልክተህ ጠቢብ ሁን” ይለዋል። ጉንዳን ምን እንደምታረግ፥ ክረምት ሳይመጣ በበጋ ምግቧን እንዴት አዘጋጅታ እንደምታስቀምጥ በማስተዋል ተመልክተህ ብቻ፥ ጥበብን ተማር ይለዋል። ከጉንዳን ቀድሞ የመዘጋጀትን ጥበብ እንማራለን። ጊዜን የማወቅን ጥበብ እንማራለን። መትጋት ባለብን ጊዜ በመትጋት ውስጥ የሚገኘውን እረፍት እንማራለን። ጊዜን ለይታ ታውቃለች ጉንዳን። መቼ በትጋት መስራት እንዳለባት፥ ገና የክረምት ጊዜ እንደሚመጣ አውቃ፥ በበጋ ጊዜ ምግቦቿን እየሰበሰች ታስቀምጣለች። እንዲሁ ደግሞ አይኖቻችንን ከፍተን ብንመለከት፥ በጣም ብዙ ነገር የምንማርባቸው ሰዎች አካባቢያችን ላይ አሉ። በአገልግሎቶቻችን መሰጠትን፣ ጽናትን፣ መታዘዝን የምንማርባቸው ሰዎች አካባቢያችን ላይ አሉ። ሰራተኞች ከሆንን ደግሞ፥ ትጋትን የምንማርባቸው ሰዎች ህይወታችን ላይ አሉ። ባለ ትዳሮች ከሆንን፥ የትዳርን ጥበብ የምንማርባቸው ሰዎች አካባቢያችን ላይ አሉ። ሲንግሎች ከሆንን በሁለንተናችን እግዚአብሄርን ማክበርን የምንማርባቸው ሰዎች አካባቢያችን ላይ አሉ። መጽሀፍ ቅዱስ እራሱ ሲናገር፥ “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፥ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” በማለት በምሳሌ መጽሀፍ ምእራፍ 13 ላይ ይናገራል። ታዲያ መጽሀፍ ቅዱሳችን ሲያስተምረን፥ ጥበብን ከተሳካላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን፥ በራሳቸው ስንፍና ምክኒያት ነገሮቻቸው ከተበላሹባቸው ሰዎችም ብዙ ጥበብን መማር እንደምንችል ይነግረናል። እዚያው ምሳሌ መጽሀፍ ምእራፍ 24 ከቁጥር 30 ጀምሮ እንዲህ ይላል። “በታካች ሰው እርሻ፥ አእምሮ በጎደለውም ሰው ወይን ቦታ አለፍኩ። እነሆም ሁሉ እሾህ ሞልቶበታል። ፊቱንም ሳማ ሸፍኖታል። የድንጋዩም ቅጥር ፈርሶአል። ተመለከትኩና አሰብኩ። አየሁትና ተግሳጽን ተቀበልኩ።” ይላል። ይሄ የተበላሸ፣ እሾክ የሞላበት፣ ሳማ የሞላበትና ቅጥሩ በሙሉ የፈራረሰው፥ የታካች ሰው እርሻ ነው። ታካች ስለሆነ እጁ ላይ ያለውን እርሻ በትክክል እየተንከባከበ አይደለም። ይሄ እርሻ በትክክል እንዳያፈራና ፍሬ እንዳይሰጥ፥ ይሄ ሰው ማድረግ ያለበትን የሚጠበቅበትን ነገር እያረገ አይደለም። በዚህም ምክኒያት፥ እርሻው በአረምና በአላስፈላጊ ነገሮች መሞላቱን፥ እንዲሁም የእርሻው ቅጥሮች በሙሉ መፍረሳቸውን በመመልከት ብቻ፥ ይሄ ሰው ተግሳጽንና ጥበብን መቀበሉን ይነግረናል። ይሄ በታካች ሰው እርሻ መካከል አልፍኩ ያለው ሰው። እርሻውን አይቼ በማየት ብቻ ተግሳጽን ተቀበልኩ እንዳለ፥ አካባቢያችን ያሉ የፈራረሱ ነገሮችን አስተውለን በማየት ብቻ የምቀበለው ተግሳጽ አለ። የፈረሱ ነገሮችን አስተውለን በማየት ብቻ የምናገኘው ጥበብ አለ። አካባቢያችን የፈረሱ ትዳሮች አሉ? ከዚያ ከፈረሰው ነገር ጥበብን መማር እንችላለን። አካባቢያችን ከእግዚአብሄርም ሆነ ከሰዎች ጋር የፈረሱ ህብረቶች አሉ? እነዚያ የፈረሱ ህብረቶችን አይተን ብቻ ተግሳጽን መቀበል እንችላለን። ጥሩና እጁ ላይ የነበረውን ስራ በራሱ ስንፍና ያጣ ሰው አካባቢያችን አለ? የዚያን ሰው ህይወት በማየት ብቻ ተግሳጽን መቀበል እንዲሁም ጥበብን ማግኘት እንችላለን። አካባቢያችን ያሉ ነገሮችን አስተውሎ በማየት ብቻ፥  የምናገኘው ብዙ ጥበብ አለ። 

	አንዲቷ  ልመና

አንዲቷ  ልመና

ያእቆብ

ያእቆብ