Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ያእቆብ

ያእቆብ

ሰሞኑን የህይወት ታሪኩን በማሰላሰል ልቤን በጣም የገዛው ሰው ነው። መቼም ታሪኩን ምንም የማናውቀው ብንሆን እንኳን፥ ወይ በሰዎች ንግግር ውስጥ፥ ወይንም ደግሞ በህብረት ጸሎቶቻችን ውስጥ፥ የአብርሀም የይስሀቅ የያእቆብ አምላክ ተብሎ ሲጸለይ እንሰማለን። ያእቆብ የአብርሀም ልጅ የሆነው ይስሀቅ ከወለዳቸው መንታ ልጆች ውስጥ፥ ሁለተኛ ልጅ ሆኖ የተወለደው ልጅ ነው። እነዚህ መንታ ወንድ ልጆች፥ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ፥ ገና በእናታቸው ማህጸን ውስጥ ሆነው ነው መገፋፋትና በታገል የጀመሩት። እናታቸው ርብቃም ምንም የመጀመሪያዋ እርግዝና ይሁን እንጂ፥ በውስጧ አንድ ያልተለመደ ነገር እየሆነ እንዳለ ተረድታ፥ ግራ ስለገባት እግዚአብሄርን ምን እየሆነ እንዳለ ለመጠየቅ ሄዳ ነበር። “ሁለት ወገኖች በማህጸንሽ ናቸው። ሁለቱም ህዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ። ህዝብም ከህዝብ ይበረታል። ታላቁም ለታናሹ ይገዛል” በማለት የገዛ ሆዷ ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ነገር፥ እግዚአብሄር በግልጽ ነግሯት ነበር። ርብቃ እኮ ታዲያ የምታውቅ የነበረው፥ ሁሉም ሴት ልጅን ለመውለድ እርጉዝ እንደሚሆነው እሷም እንዳረገዘች እንጂ፥ ሁለት ትልልቅ ሰራዊት የሚሆኑና ከአብርሀም ጀምሮ እግዚአብሄር ለአመታት ሲገባ የነበረውን ኪዳን የሚፈጽምባቸው፥ እንዲሁም ሁለት ትልልቅ ህዝብ የሚሆኑ ሰዎች በውስጥዋ እንዳሉ አታውቅም ነበር። አይገርማችሁም፥ አንዳንድ ጊዜ እኮ እግዚአብሄር ውስጣችን ምን እንዳስቀመጠ አናውቅም። የሚገርመው ታዲያ፥ እነዚህ ገና በእናታቸው ማህጸን ውስጥ መገፋፋትና መታገል የጀመሩ አራስ ልጆች፥ በተወለዱበትም ጊዜ፥ ታናሹ የሆነው ያእቆብ የታላቁን ተረከዝ ይዞ ነው ከእናቱ ሆድ የወጣው። እናት ወይንም አባት የሆናችሁ መቼም፥ ልጆቻችሁ ሲወለዱ እንዴት ትንንሾችና ለማቀፍ እንኳን የሚያሳሱ፣ በጣም የሚያሳዝኑ፥ ልባቸው ፍጹም ንጹህ የሆነ፣ በሁሉ ነገራቸው የእናንተን እርዳታና ድጋፍ የሚፈልጉ እንደሆኑ ታውቃላችሁ። ከኤሳውና ከያእቆብ ውጪ ከማህጸን መገፋፋትና መታገል የጀመረ ጽንስ ከዚህ በፊት ታይቶ አይታወቅም። ነገሩ ግን ትንቢታዊ እንደሆነ እና ከፊታቸው ያለውን የትግል ዘመናቶች የሚያሳይ መሆኑን፥ ወላጆቻቸውም በጊዜው አልተረዱም። የታሪኩን አካሄድ እንደምናውቀው፥ እነዚህ ልጆች ካደጉ በኋላ፥ ኤሳው በውጪ በማደን የሚተዳደር ሰው ሲሆን፥ ያእቆብ ደግሞ በቤት ከእናቱ ጋር የሚውል ልጅ ነበር። ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን ያእቆብ የምስር ወጥ በሰራበት ቀን ነው ኤሳው ተርቦ ከውጪ የገባው። በጣም ከመራቡ የተነሳ የሚያስበው ስለ ምግብ ብቻ ነበር። “ያእቆብ በጣም ደክሞኛል፥ ደግሞም ርቦኛል፥ በናትህ ከሰራኸው የምስር ወጥ፥ ትንሽ እንድበላ ፍቀድልኝ።” ያእቆብም መለሰ “ችግር የለውም ወንድሜ። አንድ ነገር ብቻ እንደራደር፥ እኔ ከሰራሁት ቆንጆ የምስር ወጥ የምትበላውን እሰጥሀለሁ። በመጀመሪያ ግን አንተ አንድ ነገር ታረግልኛለህ። ብኩርናህን ትሰጠኛለህ።” ኤሳውም አለ “እኔ ለራሴ በረሀብና በድካም ልሞት ነው፥ ብኩርናዬ ለምኔ ናት?” በማለት ነው በምስር ወጥ ለመለወጥ የተስማማው። ኤሳው በጊዜው በከፍተኛ ድካምና የረሀብ ስሜት ውስጥ ቢሆንም፥ በምስር ወጥ የለወጠው ግን፥ በህይወቱ ላይ የነበረውን የእግዚአብሄርን ዘላለማዊ ኪዳን ነበር። እጁ ላይ የነበረው፥ ትውልዶችን አልፎ ዘላለም የሚቀጥል ትልቅ የእግዚአብሄር ፕሮግራም ነበር። ሰፊ የሆነ የእግዚአብሄር ሀሳብ ነው ከእጁ ያመለጠው። የድካሙና የረሀቡ ስሜት ያልፋል። ተሰጥቶት የነበረው እድል ግን፥ የማያልፍና ዘላለም የሚኖር የእግዚአብሄር በረከት ነበረ። ከዚያ በኋላ ይላል መጽሀፍ ቅዱስ፥ ድካሙ ካለፈ በኋላ፥ ረሀቡ ካለፈ በኋላ፥ በምግብ የለወጠውን ብኩርና በእምባ ቢፈልጋት እንኳን መልሶ አላገኛትም። ለንሰሀም ቦታ አላገኘም” በማለት የእግዚአብሄር ቃል ይነግረናል። አያናድድም? በእጃችን ላይ ያለው የከበረ ነገር፥ ዋጋው የሚገባን ካጣነው በኋላ ሲሆን አያናድድም? ምን አይነት ውድ ነገር እጃችን ላይ እንደነበረ የምናስተውለው ካጣነው በኋላ ሲሆን አያናድድም? ኤሳው በጊዜው አይምሮውን ሁሉ የተቆጣጠረው የረሀብ ስሜት፥ እጁ ላይ ያለውን ነገር ዋጋ እንዳይረዳ አርጎት ነበር። ከዚህ የምንወስደው ትልቁ ትምህርት፥ ውስጣችን ያሉት የተለያዩ ስሜቶች፥ አይምሮአችንን ገዝተው የእግዚአብሄርን ነገር እንዳያቀሉብን በጣም መጠንቀቅ እንዳለብን ነው። ስሜት በባህሪው፥ አይምሮአችንን በሙሉ የመቆጣጠርና በትክክል ማሰብ እንዳንችል የማድረግ ዝንባሌ አለው። አንድ ሰው ስሜታዊ ሲሆን፥ አይምሮው ሌላ ነገር ማሰብ አይችልም። የሚያስበው ስለዛ ስሜታዊ ስለሆነበት ነገር ብቻ ነው። ኤሳው ብኩርናውን ያሸጠው፥ በጊዜው አይምሮውን ተቆጣጥሮት የነበረው የረሀብ ስሜት ነው። ኤሳው በጊዜው ይሰማው የነበረውና አይምሮውን በሙሉ የተቆጣጠረው የረሀብ ስሜት፥ በእጁ ላይ የነበረውን ኪዳን ውድነት ማሰብ እንዳይችል አርጎት ነበር። ሌላኛው የስሜት ባህሪ ደግሞ፥ እንድንወስድ የሚገፋፋን እርምጃ መኖሩ ነው። ሰዎች ስለሆንን ብዙ ስሜቶች በህይወታችን ውስጥ ያልፋሉ። ስሜታዊ በሆንበት ሰአት ግን፥ ምንም አይነት ውሳኔ መወሰን የለብንም። ያ አይምሮአችንን የተቆጣጠረው የትኛውም አይነት ስሜት እስኪያልፍና፥ በትክክል ማሰብ እስክንችል ድረስ ከዚያ ስሜት በቶሎ እንድንወጣ የሚረዱንን ነገሮች እያረግን፥ ዝም ብለን መጠበቅ አለብን። የደስታ ቢሆን የሀዘን፣ የንዴት ቢሆን የብስጭት የትኛውም አይነት ስሜት ያልፋል። የደስታ ስሜት እንኳን ያልፋል። ስሜቱ ውስጥ ሆነን የምንወስናቸው ውሳኔዎች ግን፥ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዱንና፥ በህይወታችን ብዙ ዋጋ የሚያስከፍሉን ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህም በላይ እግዚአብሄር ካልረዳን፥ ስሜታዊ ሆነን የምንወስናቸው ውሳኔዎች፣ ከትልቁ ከእግዚአብሄር ሀሳብና ፕሮግራም ሊያስወጡን ይችላሉ። ነገ ላይ የምንጸጸትባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እግዚአብሄር በእጃችሁ ላይ ያለውን ውድ ነገር እንድታስተውሉ በምትችሉበት ማስተዋል ይባርካችሁ። “እንዲሁም ኤሳው ብኩርናውን አቃለላት” እንደሚለው፥ በእጃችሁ ያለውን ትልቅ የእግዚአብሄር ሀሳብና ፕሮግራም ከማቃለል እግዚአብሄር ይጠብቃችሁ። ህይወታችሁ ላይ ያለውን የከበረ ነገር ውድ መሆን እንድታዩ፥ እግዚአብሄር አይናችሁን ይክፈትላችሁ። የያእቆብ ታሪክ በዚሁ እንዳለ፥ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ደግሞ ፍጹም አምላክ ሲሆን ፍጹም ሰው ሆኖ ወዲህች ምድር የመጣ አንድ ሰው አለ። ምንም የረሀብ ስሜት ቢቆጣጠረውም፥ ይሄ ስሜት ከእግዚአብሄር ሀሳብ ውጪ ያላስወጣው፥ ፍጹም አምላክ ደግሞም ፍጹም ሰው የሆነው  ኢየሱስ። 40 ቀናቶች ሙሉ ከጾመ በኋላ ቢራብም፥ የረሀብ ስሜቱን ለማስታገስ የተሰጠውን ጥሩ የሚመስል ሀሳብ ተቀብሎ፥ ድንጋዩን ዳቦ አላረገውም። የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ይሄንን ድንጋይ ዳቦ እንዲሆን በል በተባለው መሰረት፥ የእግዚአብሄር ልጅ መሆኑን ለማረጋገጥና ለማሳየት፥ አንድም ተጨማሪ ነገር አላረገም። ሰዎች፥ በውስጣችን ያለውን እውነተኛ ማንነት ከተረዱት መልካም ነው። አለበለዚያ ግን፥ እውነተኛ ማንነታችንን ለማሳየት፥ ምንም አይነት ተጨማሪ ነገሮችን እያረግን እንዲረዱን በማድረግ፥ ጊዜ ማቃጠል የለብንም። ልባችን፥ ማንነታችንን ሁሉ በሚያውቀው አምላክ ማረፍ አለበት። ኢየሱስ ድንጋዩን ዳቦ አርጎ በመብላት ረሀቡን ለማስታገስም ሆነ፥ ይሄንን ተአምራት አርጎ የእግዚአብሄርን ልጅ መሆኑን ለማሳየት፥ ስሜት አልገፋፋውም።  ስሜት ከእግዚአብሄር ሀሳብና ፕሮግራም አላስወጣውም። በስሜት ላይ ነገሰ እንጂ ስሜት አልነገሰበትም። 

እንግዲህ የያእቆብን ታሪክ እንደምታውቁት፥ ከኤሳው ብኩርናውን ከተቀበለ በኋላ፥ በተንኮል ገብቶ ኤሳው ነኝ በማለት፥ ከአባቱ ከይስሀቅ ለኤሳው የሚገባውን በረከት ሁሉ በማታለል ተቀብሏል። ለማታለል የሄደበትም መንገድ ሰርቶለት፥ ማግኘት የሚፈልገውን ነገር በሙሉ አግኝቷል። ያእቆብ “ብኩርና” ውስጥ ያለውን በረከት በሙሉ ከአባቱ ተቀብሏል። አሁን ይሄ ኪዳን ኤሳውን አልፎ በያእቆብ ህይወት ቀጥሏል። ያእቆብ በተንኮል በመግባት፥ አንድ በኩር ልጅ ከአባቱ የሚቀበለውን በረከት በሙሉ ተቀብሏል። አላማውን በሙሉ አሳክቷል። ኪዳኑ በህይወቱ ሰርቷል። የእግዚአብሄር ፕሮግራም በህይወቱ ቀጥሏል። እግዚአብሄርም በዘመኑ ሁሉ ከእርሱ ጋር ሆኗል። እግዚአብሄር ጠብቆታል። በተለያየ ጊዜያትም በድምጽና በራእይ አናግሮታል። ምንም የእግዚአብሄር ኪዳን በህይወቱ ቢሰራም ግን፥ መዝራትና ማጨድ የእግዚአብሄር ህግ በመሆኑ፥ ያእቆብ ወንድሙንም ሆነ አባቱን በማታለል የሄደባቸው የማታለል መንገዶች፥ ህይወቱ ላይ እጅግ በጣም ብዙ ዋጋ አስከፍለውታል። የያእቆብን ህይወት ጠቅለል አርገን ስናየው፥ ህይወት ትግል የሆነበት ሰው ነበር። ያእቆብ ታጋይ ነው። ትግል የጀመረው ከእናቱ ማህጸን ሲሆን፥ ይሄ ትግሉ ዘመኑን ሙሉ ቀጥሏል። ከወንድሙ ጋር ይታገላል። ከአጎቱ ከላባ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ይታገላል። ኸረ ያእቆብ ከእግዚአብሄርም ጋር ታግሏል። ወንድሙን ኤሳውን በመሸሽ ወደ አጎቱ ወደ ላባ ቤት ሲሄድ ታዲያ፥ ከላባ ጋር ያሳለፋቸው አመታቶች፥ ዘርቶ የመጣውን የማታለል ዘር ያጨደበት ቦታ ሆኖበታል። ላባ ያእቆብን አስር ጊዜ ደሞዙን እየቀያየረ አታሎታል። 20 አመታቶችን በሚስቶቹ ምክኒያት ገዝቶታል። ያእቆብ አንዴ በበጎቹ፥ አንዴ ደግሞ በፍየሎቹ፥ ከላባ ጋር ባለመስማማት፥ ብዙ ከተማረረ በኋላ፥ ከወንድሙ ከኤሳው እንደኮበለለ፥ እንዲሁ ደግሞ ከአጎቱም ከላባ ኮብልሎ ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ከዘመናት በፊት አታሎ የተለየውን ወንድሙን ኤሳውን እንደገና ለመገናኘት፥ በጣም በብዙ ጭንቀት ውስጥ አልፏል። የዚህን ጭንቀት መጠን ሲያስረዳ፥ “ሰው የእግዚአብሄርን ፊት ለማየት እንደሚፈራ ያህል” የወንድሙን የያእቆብን ፊት ለማየት እንደፈራና እንደተጨነቀ ይናገራል። ከዚህ የተነሳ፥ ልጆቹንና ከብቶቹን ሁሉ ግማሽ በግማሽ ሲከፋፍል፣ የሚወዳቸው ቶሎ እንዳይሞቱበት ወደ ኋላ እስኪያሰልፍ ድረስ በብዙ ፍርሀትና ጭንቀት ውስጥ አልፏል። የያእቆብ ህይወት ክብደት በዚህ ብቻ አላበቃም። እዛው መንገድ ላይ እየሄደ እንዳለ በጣም ይወዳት የነበረችውንና እሷን ለማግኘት ለብዙ አመታቶች ለአባቷ ለላባ የተገዛባትን ሚስቱን በሞት በማጣት፥ ከባድ የሆነ ሀዘን ውስጥ አልፏል። ይሄ ሀዘን ሳያንስ ደግሞ “በእርጅናዬ ከነ ሀዘኔ ወደ መቃብር እወርዳለሁ” እስከሚል ድረስ ክፉኛ ልቡ ያዘነበትና የተጎዳበትን ዜና አስተናግዶ ነበር። በጣም የሚወደው ልጁ የዮሴፍ የሀሰት የሞት ዜና። ይሄ ዜና ውሸት መሆኑ፥ ለእኛ ታሪኩ አልፎ ለምናነበው ሰዎች የታወቀ ይሁን እንጂ ለያእቆብ፥ የልጁን ሞት በደም በተጨማለቀ የልብስ ማስረጃ፥ እውነት መምሰሉን አስረግጠው የነገሩበት፥ በከፍተኛ የነፍስ ሀዘን ውስጥ ያለፈበት በጣም ከባድ የህይወቱ ምእራፍ ነበር።  ያእቆብ ልጁን ዮሴፍን ከብዙ አመታቶች በኋላ በህይወት ቢያገኘውም፥ አንድ ወላጅ የወለደው ልጁ ሲሞትበት የሚያልፍበትን የሀዘን ጥልቀት በሙሉ ያእቆብ አልፎበታል። ልጄን ክፉ አውሬ በልቶታል በማለት፥ ልብሱን ቀዶ፥ ማቅ ለብሶ፥ መጽናናትን እምቢ ብሎ፥ ብዙ ቀን ለልጁ አልቅሷል። ታዲያ ያእቆብ ልጁ ዮሴፍ በህይወት መኖሩን ከሰማና ሊገናኘው ወደ ግብጽ ከሄደ በኋላ፥ በፈርኦን ፊት ቆሞ 130 አመታቶችን ኖሮ ሊሞት 17 አመታቶች ብቻ ሲቀሩት፥ ስለ ጠቅላላ ህይወቱ የተናገረውን አንድ ነገር ከዘፍጥረት ምእራፍ 47 ላይ ላንብብላችሁ። ያእቆብ ስለ ጠቅላላ ህይወቱ እንዲህ ሲል ተናገረ፥ “የእንግድነቴ ዘመን መቶ ሰላሳ አመት ነው። የህይወቴ ዘመኖች ጥቂትም፥ ክፉም ሆኑብኝ። አባቶቼ በእንግድነት የተቀመጡበትንም ዘመን አያህሉም።”  በማለት ህይወት እንደከፋበት፣ ዘመናቶቹም ጥቂት እንደሆኑበት ተናግሯል። ያእቆብ በዚህች ምድር፥ አባቶቹ የኖሩትን ዘመን ብዛት የመኖርን እድል አላገኘም። ከአባቶቹ ከአብርሀምና ከይስሀቅ ጋር ሲነጻጸር፥ ያእቆብ የኖረው እድሜ ያጠረ ነበር። አባቱን እንዳታለለ፥ እሱም እንዲሁ በገዛ ልጆቹ ተታሏል። ወንድሙን እንዳታለለ በአጎቱ በላባ ብዙ ጊዜ ተታሏል። የዘራውን በሙሉ አጭዶ ነው የሄደው። በህይወታችን ለጊዜው ራሳችንን የጠቀምን መስሎን የምንሄድባቸው የማታለል መንገዶች፥ ወደፊት ላይ፥ ብዙ ዋጋ የምንከፍልባቸው ነገሮች ናቸው። ምክኒያቱ ደግሞ የእግዚአብሄር ቃል እንደሚለው፥ መዝራትና ማጨድ፣ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት በምድር ላይ፥ የማያቋርጡ ነገሮች ስለሆኑ ነው።

ከያእቆብ ህይወት ከምንማራቸው ትልልቅ ነገሮች አንዱ፥ እግዚአብሄር በረከትን ለእኛ ካለው፥ በእግዚአብሄር በራሱ ጊዜና በእግዚአብሄር መንገድ ሲመጣ፥ ዋጋ የማንከፍልበት እውነተኛ በረከት ይሆንልናል። በረከትን ግን በራሳችን ጥበብ ወይንም ማታለል ለማግኘት ሞክረን ብናገኘውም እንኳን፥ ብዙ ዋጋ የምንከፍልበት ነገር ሊሆንብን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ በህይወታችን፥ እግዚአብሄር ተስፋ ይሰጠናል። ወደፊት በህይወታችን ሊያደርግ ያሰበውን ነገር አስቀድሞ ይናገራል። ታዲያ የበዛውን ጊዜ እግዚአብሄር የተናገረውን ነገር፥ በራሳችን ጊዜ እንዲሁም በራሳችን ጥበብ ለማስፈጸም ስንሯሯጥ ይታያል። ተስፋን የሰጠው እግዚአብሄር፥ ተስፋውን የሚፈጽምበት የራሱ ጊዜ አለው። ተስፋውን የሰጠው እግዚአብሄር፥ ተስፋውን የሚፈጽምበት የራሱ መንገድ አለው። እግዚአብሄር የተናገረውን ነገር ወደ ፍጻሜ ለማምጣት፥ የእኛን እርዳታና ትብብር አይፈልግም። ብቻውን ድንቅና ተአምራትን የሚያደርግ አምላክ ነው። እግዚአብሄርን መቅደም በህይወታችን የሚያስከፍለን ዋጋ አለ። 

ጠቢብ

ጠቢብ

ፍጹም መውደድ 

ፍጹም መውደድ