Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

መዳኔ

መዳኔ

ዛሬ ከወትሮዬ ለየት ባለ መንገድ በክርስቶስ ውስጥ ስላገኘሁት የዘላለም መዳን ልቤ ሲገረምና ሲደነቅ ቆይቷል። አንዳንድ ቀን መዳኔ ልክ ስለሰራሁት መልካም ስራ የሚገባኝ ተመጣጣኝ ክፍያ ይመስል፣ በእግዚአብሄር ውስጥ እየኖርኩት ያለሁት ህይወት የማይገባኝና ከእግዚአብሄር ምህረት ብዛት የተሰጠኝ መሆኑን ልቤ ይዘነጋዋል:: በክርስቶስ ደም ተቀድሼ አንደበቴ ስለ ጽድቅ የማወራትን ድፍረት ማግኘቱን፣ የእግዚአብሄር ባሪያ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሄር ልጅ ተብሎ የመጠራትን እድል ማግኘቴ ፈጽሞ የማይገባኝ ነገር መሆኑ ይረሳኛል። ግን እኮ አሁን እየኖርኩ ያለሁትና በክርስቶስ ውስጥ ያገኘኋቸው በረከቶች በሙሉ የሚገቡኝ አይደሉም። የሚገባኝማ ለሀጢያቴ የሚከፈለኝ ዋጋ ነበር። ለምሳሌ፥ የአሜሪካን ፕሮዚደንት የሆነው ባይደን እኔን በጣም ከመውደዱ የተነሳ፥ አዳብት አሮጎ ልጁ ቢያረገኝ እሱም ሰው ስለሆነ፣ እሱም ልክ እንደ እኔ አይነት ተፈጥሮ ያለው ስለሆነ ብዙም የሚገርም ላይሆን ይችላል። አይ ኸረ በጣም ይገርማል እንጂ። እንዴት የአንድ ሀያል የተባለች ሀገር መሪና አስተዳዳሪ ከመሬት ተነስቶ አንድ ምንም ውለታ ያልሰራችለትን ሴት፥ እንዴት ነው ልጄ ብሎ የሚጠራት? በየ ጋዜጣውና በየ ቢቢሲ ኒውሱ ላይ ነበር ታሪኬን የምታገኙት። እሺ ቆይ ሰማይና ምድርን ፈጥሮ፣ ዩኒቨርስን የሚያስተዳድር፣ ጸሀይን እያስወጣ የሚያስገባ፣ ነፋሳትን ወደ ወደደው ቦታ የሚልካቸው፣ በፊቱ በድፍረት መቆም የሚችል የሌለና ማንንም ሳይፈራ በጉልበቱ ጽናት የሚራመደው አምላክ እግዚአብሄር፥ በምን አይነት ተአምር ነው እኔን ልጄ ናት ብሎ የዘላለማዊ መንግስቱ ተካፋይና ወራሽ ያያረገኝ? እንዴትስ ነው አድነኝ ብዬ እንኳን ሳልጠይቀው አንድ ልጁን ለጽድቄ አይደለም፥ ለሀጢያቴ ለመሞት አሳልፎ የሰጠው? እንዴት የኪዳን ልጁ አደረገኝ? እንዴትስ ብሎ ነው ቆይ ለዘላለም ላይጥለኝና ላይረሳኝ በራሱ የማለው? ቆይ እኔ ምንድነኝ? እኔ ማነኝ? ይሄ ቃል አሳጥቶ ቃል አልባ ካላደረገኝ ሌላ ምን ያደርገኛል? ይሄ አሁን ከእግዚአብሄር ጋር የምኖረው ህይወት እኮ የሚገባኝ ህይወት አይደለም። በየቀኑ ልቤን በመደነቅ የሚሞላልኝና  ቃላቶች የማጣበት አስደናቂ ስጦታዬ ነው። ለዚህ አስደናቂ ህይወት ደግሞ፥ እኔ ያዋጣሁት ትንሽ እንኳን መልካም ነገር ቢኖር የመገረሜን ደረጃ በጥቂቱ እንኳን ሊቀንሰው በቻለ፣ መቶ በመቶ ከራሱ በሆነ ምህረት ውስጥ ከህይወት ወደ ተሻለ ህይወት አይደለም ያሻገረኝ። ከዘላለም ሞት ወደ ወደ ዘላለም ህይወት ነው ያሻገረኝ። ከብርሀን ወደ ተሻለ ብርሀን አይደለም ያሻገረኝ። ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሀን ነው ያሻገረኝ። ካሻገረኝ በኋላ ደግሞ በይ በቃ አንዴ አድኜሻለሁ፥ ካንቺ ጋር ያለኝን ጉዳይ ጨርሻለሁ አለማለቱ። ከሱ ጋር መነጋገርና መጫወት እንድችል 24 ሰአት ራሱን ለኔ ማስገኘቱ። ሰው እኮ በጥቂት ስራዎች ሲጠመድ፣ “ይቅርታ ቢዚ ስለሆንኩኝ አሁን ላናግራችሁ አልችልም” ብሎ ይመልሳል። አለምን የሚያስተዳድረው አምላክ እግዚአብሄር፥ እንዴት ብሎ ነው እኔን ለማናገር ልቡንና ትኩረቱን የሰጠኝ? ከሱ ጋር የምነጋገረው ደግሞ እሱ በፈለገበት ሰአት ብቻ ሳይሆን፥ እኔም በፈለኩት ሰአት ላናግረው ብፈልግ ራሱን ሁሌ ለኔ ማስገኘቱ በጣም ይደንቀኛል። እንዴት ነው እሱን ለማናገር ቀጠሮ ያላስያዘኝ? እንዴት ወረፋ ጠብቂ አላለኝም? ትንሽ ስልጣን አለን የሚሉ ሰዎችን እኮ በፈለኩት ሰአት ገብቼ አናግሬያቸው አላቅም። የማገኛቸውም በሰዎች በኩል እንጂ ቀጥታ ገብቼ ለማናገር እድሉ ኖሮኝ አያውቅም። እግዚአብሄር እንዴት ራሱን አሳንሶ ልቤና ቤቴ ውስጥ ገባ? ይሄን ነገሬን ወዶ ነው እንዳልል ምንም የለም። ምንድነው ያለው? እኔ በዚህች ጥቂት ዘመናቶቼ እንደዚህ አይነት ነገር አይቼ አላውቅም። አይታችሁ ታውቃላችሁ? 

የመዳኔን ውድነት በቃላት ሳይሆን ልቤ ውስጥ በሚያፈሰው እውቀቱ ያስረዳኝና ያብራራልኝ የእግዚአብሄር መንፈስ ይባረክ። መንፈስ ቅዱስ አንተ ባትሰጠን ኖሮ ማን እግዚአብሄርንና ከእሱ በነጻ ያገኘናቸውን በረከቶች በቃላቶቹ ያብራራልን ነበር? ማን ነበር የሚያስረዳን? ለነገሩ የልቦናችንን አይኖችስ ቢሆን አንተ ስላበራሀው አይደል ለዚህች ምድር ሀያላንና ጠቢባን ያልተገለጠውን የወንጌል ሚስጥር ማመን የቻልነው። እንጂ እኮ እኛ ከሰዎች ሁሉ የተሻለ አማኝ ልቦና ስላለን ወይንም በቀላሉ ነገሮችን የምናምን ስለሆንን አይደለም። አሁን ያለን እምነት እራሱ ያንተ ስጦታ ነው። የእምነትን ስጦታ ሰተህ ነው ያዳንከን። ስለዚህ በእምነታችንም ቢሆን አንመካም። ኢየሱስ በምድር እያለ ስላንተ ብዙ ነገር ነግሮናል፣ አጽናኝ እንደሆንክ፣ ኑሩ ያለንን ህይወት ለመኖር ካንተ ልናገኝ ስለምንችለው እርዳታ ሁሉ ሳይቀር ነው ያጫወተን። አንተ የእውነት መንፈስ፣ ኢየሱስ የኖረውን ህይወት የምታኖረን፣ ቀድሰህ ቅዱስ ህዝቦች ያረከን። ሁሌ ከእኛ ጋር መኖርህ፣ በበደላችን ባይቸገርንህ ሰአት እንኳን ጥለኸን አለመሄድህ። ትግስትና መቻልህ። በብዙ ምክሮችህ ያጸናኸንና፣ ነገም መንገዳችን ላይ ሊመጡ የሚችሉትን ነገሮች ሁሉ እንዳንፈራ የምታረገን ብርቱ መታመኛችን ነህ።  የእግዚአብሄር መንፈስ ሆይ እናመሰግንሀለን። መዳናችን በዚህ ምድር ካገኘነው ከየትኛውም ውድ የሆነ ነገር ይበልጣል። ይሄ አለም እና ውስጥዋ ያሉት ነገሮች ቢሰበሰቡ፥ የዳንበትን መዳን ሊያክሉት አይችሉም። መዳናችን በጣም ውድ ነው። ምንም ነገር ሊከፍለው አይችልም። በጣም ውድና ልንከፍለው የማንችለው ነገር ስለሆነ ነው በነጻ የሆነው። አንዳንድ ጊዜ እኛ ሰዎች፥ ዋጋ የከፈልንባቸውንና ለፍተን ያገኘናቸውን ነገሮች በጣም የመንከባከብና ትኩረት የመስጠት፥ በነጻና ምንም ሳንለፋ ያገኘናቸውን ነገሮች ደግሞ ችላ የማለት ዝንባሌ አለን። ይሄ የእኛ የሰዎች ባህሪ ነው። መዳናችን ነጻ የሆነው፥ የገንዘብ ተመን ውስጥ የማይገባና በእኛ አቅም ሊከፈል የማይችል ነገር ስለሆነ ነው። ይሄ መዳናችን ታዲያ ነጻ የሆነው ለእኛ እንጂ፣ ኢየሱስን ግን ያላስከፈለው ዋጋ አልነበረም። የአምላክነቱን ክብር ወደ ጎን አስቀምጦ ሰው ሆኖበታል። የሰው ልጆች በምድር ላይ የሚከፍሉትን ዋጋ በሙሉ ከፍሎበታል። በከብቶች በረት ውስጥ ከመወለድ ጀምሮ እስከ መርገም ሞት ድረስ እያንዳንዱን የውርደት ጥግ ከፍሎበታል። መዳናችን ከአይምሮአችን በላይ የሆነ ዋጋ ተከፍሎበታል። እግዚአብሄርን በጣም የምትወደው ነገር ምንድነው ብትሉት የሰውን ልጆች ይላል። በጣም የምትጠላውስ ነገርስ ብትሉት ሀጢያትን ይላል። ታዲያ በጣም የሚወደውን የሰው ልጅ በጣም ከሚጠላው ሀጢያት ጋር ለመለያየት መስቀሉ እግዚአብሄር ያመጣው የእግዚአብሄር ጥበብ ነው። ታዲያ ይሄ የተሰጠን ከየትኛውም ነገር በላይ ውድ የሆነው ስጦታችን፣ በጣም ውድና የዋጋ ተመን የሌለው በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። አንድ በጣም የምንወደውና የምናከብረው ሰው የሆነ ውድ ስጦታ ቢሰጠን፣ ስጦታው የመጣው በጣም ከምናከብረው ሰው በመሆኑና ውድ በመሆኑ በጣም በጥንቃቄ እንደምን ይዘው ሁሉ፣ በክርስቶስ በኩል የተሰጠን ይሄ ውድ ስጦታ፥ የሚጠይቀን ጥንቃቄ አለ። ጥንቃቄ የሚያስፈልገን ደግሞ ይሄንን ውድ የሆነ ስጦታ የምናጣባቸው ሁኔታዎች ስላሉ ነው። አሁን ውስጣችን ያለው የዘላለም ህይወት ነው። ውስጣችን ያለው ጽድቅና ቅድስና ነው። ውስጣችን ያለው የከበረ ነገር ነው። ውስጣችን ያለው ገንዘብና የአለም ሀብት የማይገዛው ነገር ነው። አሁን ያለነው አዲስ ህይወት ውስጥ ነው። አንደበቶቻችን ስለ ጽድቅና ቅድስና የማውራትን ድፍረት በክርስቶስ ውስጥ አግኝተዋል ስሙ ለዘላለም ይባረክ። አሁን ባሪያዎች አይደለንም። የእግዚአብሄር ልጆች ነን። ቅዱስ ህዝብ ነን። አሁን ቅድስና ለመያዝ የምንጣጣረው ነገር ሳይሆን፥ የአዲሱ ተፈጥሮአችን ማንነት ሆኗል። ተፈጥሮአችን ሆኗል። አሁን ውስጣችን ቢፈተሽ ያለው በጣም ውድ ውድ ነገር ነው። ምድራዊ ብርና ወርቅ እንዲሁም የትኛውም ውድ ነገር ሊገዛ የማይችለው ነገር ነው ውስጣችን ያለው። ይሄንን ሁልጊዜ ማሰብ መልካም ነው። ኤሳው እኮ ብኩርናውን ያቃለላት፣ ውድ መሆኗ በጊዜው ስላልገባው ነው። ለጊዜው ይሰማው ከነበረው የረሀብ ስሜት በልጣ ስላልታየችው ነው። ውድነቷን ቢሸፍንበት፥ አንዴ በምስር ወጥ ከሸጣትና ከለወጣት በኋላ ነው እጁ ላይ የነበረች ዘላለማዊ የእግዚአብሄር ኪዳን መሆኗ በትክክል የገባው። የሚያሳዝነው ደግሞ ከዚያ በሀዋላ ቢፈልጋት እንኳን እንዳላገኛትና ለንሰሀ እንኳን ቦታ እንዳላገኘ ቃሉ ይናገራል። ሰው የዘላለም ህይወቱን አጥቶ አለምን ሁሉ ቢያተርፍ ትልቅ ኪሳራ ውስጥ ነው ያለው። ውስጣችን ያለው ህይወት፣ ውስጣችን ያሉት ስጦታዎች አለም ላይ ውድ የተባሉ ነገሮች ቢሰበሰቡ ሊወዳደሩት አይችሉም። በጣም ውድ ውድ ነገር ይዞ የሚንቀሳቀስ ሰው ደግሞ የሌባ አይን ውስጥ መግባቱ አይቀርም። ሌባው ደግሞ ዲያቢሎስ ነው። ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ የሚመጣ ሌባ አለ። ለዚያ ነው ከእግዚአብሄር ያገኘናቸውን ውድ ስጦታዎች በጣም በጥንቃቄ መያዝ ያለብን። ውድ ውድ ዳይመንድ ወርቅና ኤልክትሮኒክሶች ይዘን፥ ሌባ ያለበት ከተማ ውስጥ በጥንቃቄ እንደምንመላለሰው ሁሉ፣ እግዚአብሄር የሰጠንን ውድ ስጦታዎች የዘላለም ህይወታችንን፣ በክርስቶስ ያገኘነውን ጽድቅ፣ ቅድስና ለማስጣልና ለመስረቅ የተሰማሩ ሌቦች አሉ። ኢየሱስም አለ። እኔ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ። ስለዚህ እንደ እርግብ የዋሆች፥ እንደ እባብ ደግሞ ልባሞች ሁኑ እንዳለው። ይሄ የእግድነት ዘመናችን በብዙ ጥንቃቄ ልንኖር የሚያስፈልገን ነው። 

“እንግዲህ በጌታ እስር የሆንኩ እኔ፥ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ።” (ኤፌሶን 4:1)  ከእግዚአብሄር ስለ ተሰጠን የዘላለም ህይወት ተስፋ ስናስብ፣ ተስፋው ጋር ለመድረስ መንገድ ላይ ነን እንጂ ገና አልደረስንበትም። ሁላችንም እየሄድን ነው። መንገድ ላይ ነን። የትኛውም ከእግዚአብሄር የሚመጣ ተስፋ፣ ተስፋው ጋር የመድረሻ መመሪያ አለው። ተስፋው ጋር ለመድረስ የምንሄድባቸው መንገዶች አሉ። የእስራኤል ህዝቦች፥ እነሱ በፈለጉበት መንገድ ሄደው አይደለም የተስፋይቱን ምድር የወረሱት። እግዚአብሄር በመራቸው መንገድ ሄደው ነው የተስፋይቱን ምድር የወረሱት። እግዚአብሄር የተስፋን ቃል ሲሰጠን፣ ተስፋው መፈፀሙን አንደምንጠብቅ ሁሉ፣ እግዚአብሄርም ከእኛ የሚጠብቃቸውና ተስፋው ጋር እንደርስ ዘንድ የሚሰጠን መመሪያዎች ወይንም ስርአቶች አሉት። እነዚህ መመሪያዎች ተስፋችን ጋር የሚያደርሱን መንገዶች ናቸው። እንደፈለግን መኖራችን ተስፋው ጋር ላያደርሰን እንደሚችል ማሰብ በጣም መልካም ነው። ስለተስፋይቱ ምድር ስለ ከነአን እግዚአብሄር የተናገረው፥ ለኢያሱና ለካሌብ ብቻ አልነበረም። የተናገረው ለመላው ከ600 ሺህ በላይ ለሆኑት ህዝብ በሙሉ ቢሆንም ከ600 ሺህ ህዝብ ውስጥ፥ 2 ሰው ብቻ የተስፋይቱን ምድር መውረስ የሚነግረን የሆነ ነገር የለም? እግዚአብሄርማ ፈቃዱንና ስርአቱን የጠበቁትን ሰዎች የተናገረውን ምድር አውርሷል። ለእስራኤል ቤት ከገባው የተስፋ ቃል ያልተፈጸመ አንድም እንደሌለ ቃሉ እራሱ ያረጋግጥልናል። እግዚአብሄር የተናገረው ነገር በሙሉ ተፈጽሟል። እንደተናገረው የእስራኤልን ህዝብ ወደ ተናገራቸው የተስፋ ምድር በማስገባት ታማኝነቱን ጠብቋል። በዚህ የተስፋ ቃል ውስጥ ግን የገቡት እንደ ፈቃዱ የሄዱትና ስርአቱን የጠበቁት ሰዎች ብቻ ነበሩ። የተገባላቸውን ተስፋ ሳያዩ በምድረበዳ የቀሩ፥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ነበሩ። ይሄንን በዚህ ዘመን ለእኛ ትምህርት አርገን መውሰድ በጣም መልካም ነው። እግዚአብሄር ለሁላችንም የዘላለም ህይወት ተስፋን ሰጥቷል። የእግዚአብሄር ፈቃድ የሰው ልጆች በሙሉ ከዘላለም ጥፋት እንዲድኑና መንግስቱን እንዲወርሱ ነው። ለዚህም ነው ልጁን ኢየሱስን ዋጋ እንዲከፍል የላከው። ለዚህም ነው የመዳንን መንገድ ለሰው ልጆች በሙሉ ያዘጋጀው። ነገር ግን ይሄ የዘላለም ህይወት ተስፋ የሚጠብቅብን የህይወት መንገዶች ወይንም ስርአቶች አሉት። እንደፈለግን እየኖርን ተስፋችን ጋር መድረስ አንችልም። የተሰጠን ተስፋ ጋር የምንደርሰው ፈቃዱን በመኖር ነው እንጂ ፈቃዳችንን በመኖር አይደለም። የእግዚአብሄርን ፈቃድ እያደረግን የተሰጠንን ተስፋ እንድናገኝ እግዚአብሄር በረዳን መጠን፥ በቃሉ ውስጥ መጽናት ያስፈልገናል። ፈቃዳችንን ሳይሆን የእግዚአብሄርን ፈቃድ በማድረግ መጽናት ያስፈልገናል። ያዳነን ጸጋ የእግዚአብሄርን ፈቃድ እንድንኖር የሚረዳን ነው። ያዳነን ጸጋ አለማዊ ምኞትን አስክዶ የሚቀድስ ነው። ያዳነን ጸጋ ኢየሱስን እንድንመስል የሚረዳን ነው። የክርስቶስን መምጣትና የዘላለምን ህይወት ተስፋ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ እየኖርን እንድንጠብቅ አቅም የሚሰጠን ነው። እግዚአብሄር በራሳችን ስራ የዘላለምን ህይወት እንድንወርስ አይጠብቅብንም ምክኒያቱም በስራችን እንደማናገኘው ያውቃል። ነገር ግን በክርስቶስ ስራ የዘላለምን ህይወት ተስፋ ከሰጠን በኋላ፥ ይሄንን ተስፋ እንድንጠብቀውና ፈቃዱን እያረግን በመጽናት እንድንወርሰው ይፈልጋል። እግዚአብሄር በገዛ ስራችን እንደማንቀደስ ያውቃል። ዳግም በልጁ ከወለደንና ቅድስናን ማንነታችን ካረገው በኋላ ግን፣ በዚህ በሰጠን አዲስ ማንነት ውስጥ እንድንመላለስ ሊያረክሱን ከሚችሉ ነገሮች በመራቅ ይሄንን የሰጠንን ውድ ስጦታ እንድንጠብቀው ይጠብቅብናል። እግዚአብሄር በራሳችን እንድንጸድቅ አይጠብቅብንም፣ በልጁ ስራ ውስጥ በሰጠን ጽድቅ ውስጥ ግን  እንድንመላለስ ይጠብቅብናል። ያልሰጠንን ግን አይጠብቅብንም። የዛኔ በእግዚአብሄር ፍርድ ፊት እኮ ስንቆም ምክኒያቶች ከጥቅም ውጪ የሚሆኑት ለዚህ ነው። እግዚአብሄርን ለመምሰል የሚሆነውን ሁሉ፥ እግዚአብሄርን ለመምሰል የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሰጠን ቃሉ ላይ ይናገራል።  “የመለኮቱ ሀይል በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ ለህይወትና እግዚአብሄርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሄርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ::” (2 ጴጥሮስ 1:2-3)

ከእግዚአብሄር የሚመጡና የምንጠብቃቸው ተስፋዎች ከእኛ የሚጠብቁት ነገር አለ። እግዚአብሄር አብርሀምን አለው ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ህዝብ አደርግሀለሁ። እባርክሀለሁ፥ የሚረግሙህን እረግማለሁ። የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ። ስለዚህ የአብርሀም መባረክ እግዚአብሄር ውጣ ወዳለው ምድር በመውጣትና እግዚአብሄርን አምኖ በመታዘዝ መንገድ ሄዶ ያገኘው ነው። እግዚአብሄር የዳዊት ልጅ የሆነውን ሰለሞንን ደግሞ አለው። አባትህ ዳዊት እንደሄደ ስርአቴንና ትእዛዜን ትጠብቅ ዘንድ በመንገዴ የሄድክ እንደሆነ እድሜህን አረዝመዋለሁ። ዳዊትም አባትህ በየዋህ ልብና በቅንነት እንደ ሄደ አንተ ደግሞ በፊቴ ብትሄድ፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ስርአቴንም ፍርዴንም ብትጠብቅ፥ እኔ ከእስራኤል ዙፋን ከዘርህ ሰው አታጣም ብዬ ለአባትህ ለዳዊት እንደ ተናገርሁ፥ የመንግስትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ። ሰለሞን ተስፋው የሚጠበቅለት እግዚአብሄር ባሰመረለት መስመር የሄደ እንደሆነ ብቻ ነው። ታሪኩን ግን አንባችሁት ከሆነ፣ ንጉስ ሰለሞን እግዚአብሄር የሰጠውን ትእዛዛት ባለመጠበቁ ምክኒያት መንግስቱ ከልጁ እጅ እንደተቀደደ የእግዚአብሄር ቃል ይናገራል። አባቶቻችን ስለወረሱት የተስፋ ቃል ካሰብን፥ ተስፋቸውን የወረሱት፥ ከተስፋው ጋር የመጣውን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ኖረውና ታዘው ነው። ስለ ተስፋችንን ብቻውን ማሰቡ ተስፋው ጋር አያደርሰንም። ከተስፋው ጋር አብረን እግዚአብሄር ከእኛ የሚጠብቀውን ማሰብና መኖር በጣም አስፈላጊ ነው። ስለ ዘላለም ህይወታችን ማሰባችን በጣም አስፈላጊ ነው። ይሄንን መከራ የሞላበት ምድር የምንወጣበት አቅም ይሰጠናል። ነገር ግን ከተስፋው ጋር ይሄ ተስፋ ስለሚመጥነው የህይወትና የኑሮ አይነት ካላሰብንና ካልኖርነው ተስፋችን አደጋ ላይ ሊወድቅ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ማሰብ በጣም መልካም ነው። እስከመጨረሻ የሚጸና ይድናል እኮ የተባለው፣ በመንገዳችን መሀል ላይ ጽናታችንን የሚፈትኑ ነገሮች ስላሉ ነው። እግዚአብሄር ሁላችንንም ይርዳን።

ጥንቃቄ

ጥንቃቄ

ሩት

ሩት