Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ምስጋና 

ምስጋና 

በህይወቴ ላይ በተለያዩ ስሜቶች ውስጥ ያለፍኩባቸው የተለያዩ ቀናቶች አሉ። በጣም ደስተኛ የሆንኩባቸው፥ እግዚአብሄር ግን እንዴት መልካም አምላክ ነው ያልኩባቸው፣ የዘመርኩባቸውና እግዚአብሄርን የባረኩባቸው ብዙ ቀናቶች ህይወቴ ላይ አሉ። ልክ እንደዚሁ ደግሞ፥ በጣም ያዘንኩባቸው፥ ልቤ የተሰበረባቸው፣ እግዚአብሄርን ለምን ብዬ ለመጠየቅ የተነሳሁባቸውና ልቤ ከምስጋና እጅግ በጣም የራቀባቸው ቀናቶችም ህይወቴ ላይ ነበሩ። የእነዚህ ቀናቶች ክብደት፥ እግዚአብሄርን ብዙ ነገር እንድለው አርገውኝ ያውቃሉ። “እኔ አንተን የማመልክ፣ አንተን የምከተል፣ አንተን የማገለግል ሰው ሆኜ፥ ለምን በዚህ ውስጥ ታሳልፈኛለህ? እኔ እንደዚህ ይሄ ነገር ሲከብደኝ፥ ለምን አንድ ነገር አታረግም?” ብዬ እግዚአብሄር ላይ እንደ መናደድም፥ እንደ መቆጣትም፥ እንደ ማኩረፍም እሆንና ለመጸለይ ብንበረከክም፥ ስላኮረፍኩ እግዚአብሄርን ዘግቼው ከተንበረከኩበት የተነሳሁባቸው ቀናቶች ነበሩ። ለምንድነው እግዚአብሄር ላይ እናደድና፣ አኮርፍ የነበረው ብዬ እነዚህ ስሜቶቼ ውስጥ ያሉትን እውነተኛ ምክኒያቶች ስመረምራቸው፥ አንድ ዋና ምክኒያት አገኘሁ። ያገኘሁት ዋና ምክኒያት ይሄ ነበር። ህይወቴ ያልፍ ለነበረባቸው ከባድ ነገሮች ተጠያቂ የማደርገው፥ እግዚአብሄርን ነበር። ህይወቴ ላይ ላለፉት ነገሮች እግዚአብሄርን ተጠያቂ ማድረጌን በተያያዝኩባቸው በእነዚያ ወቅቶች ነበር አንድ አካላዊ ህመም ወይም Physical pain ውስጥ አልፍ የነበረው። ህመሙ ለህይወቴ የሚያሰጋ ባይሆንም፥ የህመሙ መጠን ትንሽ ከፍ ያለ ስለነበር፥ ድሮ አደርጋቸው የነበሩትን አንዳንድ ነገሮች ማድረግ አለመቻሌን፥ እንዲሁም ከነገሩ ጋር የተያያዙትን አንዳንድ ነገሮች በማሰብ ስሜታዊ ሆኜ በእግዚአብሄር ፊት በነበርኩበት በአንድ አመሻሽ ላይ ነበር አንድ ህይወቴን የቀየረ መረዳት ወደ መንፈሴ ውስጥ የፈሰሰው። ይሄ የተሸከምኩት ስጋ ምድራዊ ነው። ይታመማል፣ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል፣ በህመምና በስቃይ እንዲሁም በመከራ ውስጥ ሊያልፍ ተፈርዶበታል። ጌታን ማምለኬ፣ እግዚአብሄርን በህይወቴ መከተሌ ላለመታመሜ ወይንም በችግሮች ውስጥ ላለማለፌ ምክኒያት ሊሆን አይችልም። ኢየሱስ እራሱ እንኳን በምድር ሳላችሁ መከራ አለባችሁ በማለት፣ ይህቺ ምድር ከመከራ ውጪ ልትሆን እንደማትችል ግልጽ አድርጎ ተናግሯል። ህመም በዚህች ምድር ስኖር ላልፍ የምችልበት አንዱ ነገር ነው። ህይወት በዚህች ምድር ከመከራ ውጪ ልትሆን አትችልም። ከችግር ነጻ ልትሆን አትችልም። ከችግር፣ ከመከራና ስቃይ ነጻ የምሆነው ዘላለማዊ ቤቴ ስሄድ እዛ ስደርስ ነው። አሁን ምድር ላይ ነኝ ያለሁት። ስለዚህ ይሄ የተሸከምኩት ስጋ ላይ ህመም፣ ችግርና መከራ ሊደርስበት ይችላል። ይሄ ሁላችንም የምናውቀውና አዲስ ያልሆነ ነገር ይሁን እንጂ በደምብ እራሳችንን ስንመረምር፥ እኔን እራሴንም ጨምሮ የብዙ ማጉረምረማችንና እግዚአብሄርን ለምን ብለን የመጠየቃችን ምክኒያት ይሄንን እውነት መረዳት ባለብን መጠን አለመረዳታችን ነው። ለምሳሌ አንድ ትምህርት ቤት ለመግባትና ለመማር የፈለገ ሰው፥ ትምህርት የሚጠይቃቸውን ነገሮች ስለሚያውቅ፥ የቤት ስራ በተሰጠው ቁጥር፣ የሚያጠናው ብዙ የትምህርት ቤት ስራዎች በተሰጡት ቁጥር፣ ፈተና በተፈተነ ቁጥር ግራ አይገባውም። ምክኒያቱም ትምህርት ለመጀመር ሲያስብ እነዚህ ነገሮች ከትምህርቱ ጋር አብረው ሊመጡ የሚችሉ ህጎች እንደሆኑ አውቆና አይምሮውን አዘጋጅቶ ስለሚገባበት ነው። ስለ ትምህርት እና ትምህርት ስለሚጠይቃቸው ነገሮች ምንም መረጃ የሌለው ሰው ግን ከላይ የዘረዘርናቸው ትምህርቱ የሚጠይቃቸው ነገሮች በመጡበት ሰዐት ግራ ነው የሚገባው። የትምህርት ህግ አልገባውም። ያልጠበቃቸው ነገሮች ስለሆኑ፣ አይምሮውን ያላዘጋጀባቸው ነገሮች ስለሆኑ ይናደዳል፣ ይበሳጫል፣ ያጉረመርማል የሚሰጡትንም ፈተናዎች ይወድቃል። በትምህርቱም ፈጽሞ ስኬታማ ሊሆን አይችልም። ምክኒያቱ ምንድነው? የትምህርት ህጉ ስላልገባውና ለህጉ አይምሮውን ስላላዘጋጀ ነው። ከአዳምና ሄዋን ውድቀት በኋላ፥ እኛ የሰው ልጆች ወደዚህች መከራ ወደ ሞላባት ምድር መጥተናል። የመጣንባት ምድር መከራ ያለባት፣ ህመም ያለባት፣ ልዩ ልዩ ፈተናዎች ያሉባት ምድር ናት። ደስ የሚለው ነገር ጊዜያዊ መቆያችን እንጂ ዘላለም መኖሪያችን አለመሆኗ ነው። እግዚአብሄር ስሙ ይባረክ፣ ልጁን ኢየሱስን ወደ ምድር ልኮ የዘላለማችንን አድራሻ ቀይሮታል። ችግሮቻችንን እና መከራዎቻችንን አጭር አድርጎታል። ዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር እንድንኖር፥ የእንደገና አምላክ እንደገና እድል ሰጥቶናል። ይህቺ ለጊዜው የመጣንባት ምድር ግን የመከራ ምድር ናት። አጭርና መከራ የሞላባት ምድር ናት። ስለዚህ በዚህች ምድር ላይ ቁጭ ብለን፥ ምቾትን አልጋ በአልጋ መሆንን የምንጠብቅ ከሆንን በሚገጥመን ችግር ቁጥር እግዚአብሄርን ለምን ለማለት የምንቸኩልና ለማማረር የምንፈጥን ሰዎች ነው የምንሆነው። ስለዚህ ይሄ ምድራዊ መከራ በራሳችን አለመታዘዝ ምክኒያት የመጣንባት የዚህች ምድር ሁኔታ እንጂ የስቃያችን፣ የመከራችን የህመማችን ምክኒያቱ እግዚአብሄር አይደለም። እግዚአብሄር የምናልፍበት የትኛውም ምድራዊ ችግር ምክኒያት አይደለም። በመከራዎቻችንና በስቃዮቻችን ውስጥ በፍጹም የእግዚአብሄር ትብብር የለበትም። እንዲያውም እግዚአብሄር ችግራቸው የእኔ ጥፋት አይደለም፥ ችግራቸው ውስጥ እጄ የለበትም ብሎ አንድም ጊዜ እኛን ከመርዳት እጁን አጣጥፎ የተቀመጠበት ቀን የለም። ባለፍንባቸው ጥቂትም ሆነ ብዙ ዘመናቶች፥ እኛን ለመርዳት እግዚአብሄር እጁን ያልዘረጋበት ጊዜ የለም። በምናልፍበት ሁሉ ውስጥ በገዛ ፍቃዱና ፍቅሩ አብሮን እያለፈ የእሳቱን ሀይል በማጥፋት እንዳያቃጥለን ያረግልናል እንጂ። በውሀ ውስጥ ስናልፍ፥ በገዛ ፍቃዱ አብሮን እያለፈ ውሀው እንዳያሰጥመን ይጠብቀናል እንጂ። መቼ ነው እግዚአብሄር የእኛን ጉዳይ ተመልክቶ፥ አያገባኝም ብሎ የተቀመጠው? በመከራዎቻችን ሁሉ የጸጋውን ብርታት በህይወታችን  እያሳለፈ፥ እስከዛሬ ድረስ አጽንቶ አቆመን እንጂ:: እንዲያውም ችግሮች ከምንችለው በላይ ሆነው ወደ ህይወታችን እንዳይመጡና ከምንችለው በላይ እንዳንፈተን ለመፍቀድ ህይወታችን ላይ ጣልቃ ይገባል እንጂ! ይህቺ ምድር የምታመጣብንን መከራ ከእኛ አቅም ጋር በማስተያየት እየመጠነና እየለካ እምነታችንን ለማሳደግ፣ ትእግስታችንን ለመጨመር፣ ስለ እርሱ ያለንን እውቀት ለማሳደግ እየተጠቀመ እየመጣ ላለው የዘላለም ክብር ተስፋ እኛን ያዘጋጅበታል እንጂ፥ የሚጠቅሙንን ባህሪያቶች በእኛ ውስጥ ያሳድግበታል እንጂ፣ ልጁን ኢየሱስን በእኛ ውስጥ ይስልበታል እንጂ፥ የራሳቸው ጉዳይ ነው አያገባኝም ብሎ ገለል ያለው መቼ ነው? እግዚአብሄር በፍጹም የመከራችን አካል አይደለም። 

አሁን ጽፌ ከማነብላችሁ በላይ፥ ይሄ መረዳት ችግሮችንና መከራዎችን የማይበት አመለካከቴን የማስተካከልና የመቀየር ከፍተኛ የሆነ ሀይል ነበረው። በዚህች ምድር ስኖር ለማልፍበት ለየትኛውም ችግር እግዚአብሄር ምክኒያቱ እንዳልሆነ፣ የእኔ የትኛውም ጉዳት ውስጥ የእግዚአብሄር እጅ እንደሌለበት መረዳቴ “ለምን” የሚለውን ትልቅ ጥያቄ ከልቤ ውስጥ ሻረልኝ። አሁን ላይ ነገሮች ሲከብዱኝ ባለቅስ እንኳን፣ የእግዚአብሄርን እርዳታ ፈልጌ እንጂ እርዳታን ከእሱ እየለመንኩ እንጂ እግዚአብሄርን ተጠያቂ አድርጌው አይደለም። እግዚአብሄርን ለብቻው፥ የራሴን ችግሮች ለብቻ ለያይቼ ነው የማያቸው። ይሄ መረዳት ልቤን ቀየረልኝ። ምስጋናዬን ቋሚ አደረገልኝ። በሁሉ አመስግኑ የሚለውን ቃል ህያውነት ከህይወቴ ጋር አገናኘልኝ። በዚህ መረዳት ውስጥ ስገባ ነው አንኮንዲሽናል ምስጋና ወደማቀርብበት አለም ጥቂት የተጠጋሁት። ይሄንን መረዳት ሳገኘው ነው “እግዚአብሄር መልካም ነው” የሚለው ቃል በደምብ የገባኝና “መልካም ነህ” ብዬ የምዘምረው ዝማሬ በእግዚአብሄር ፊት እውነተኛ የሆነልኝ። እኔ ወደ ከፍታ ስወጣም መልካም እንደሆነ፥ ወደ ሸለቆዎች ውስጥ ስወርድም መልካም አምላክ እንደሆነ፣ እግዚአብሄር ፍጹም ርህራሄን የተሞላ፣ ፍጹም ለሰው ልጆች ሁሉ የሚራራ፣ ለሚለምኑት ሁሉ የእርዳታ እጁን አለመዘርጋት የማይችል፣ የሚለመን፣ ሰዎችን ሁሉ መርዳት የሚወድ፣ መልካምነትን የተሞላና መልካምነት ማንነቱ የሆነ አምላክ እንደሆነ የገባኝ:: ከዚያ ነገር በኋላ፥ የማልፍበትን ሁሉ በዚህች ምድር ላይ በመኖሬ ላልፍበት የሚገባኝ ነገር እንደሆነ ነው የምቆጥረው። ከዚያ ግን ምህረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ተብሎ እንደተጻፈው፣ በማልፍበት ሁሉ የእግዚአብሄርን እርዳታ፣ የእግዚአብሄርን ጸጋ እለምናለሁ። ሲረዳኝ ታዲያ እግዚአብሄር እኔን የመርዳት ግዴታ እንደሌለበት ለነፍሴ እነግራታለሁ። እግዚአብሄር እኔን የመረዳት ግዴታ እንዳለበት አላስብም። እንኳን እኔን የመርዳት እርዳኝ ብዬ የለመንኩትን ጸሎት እራሱ የመስማት ግዴታ የለበትም። የመመለስ ግዴታም የለበትም። የሚሰማኝ፣ የሚመልስልኝ፣ የሚረዳኝ፣ ግዴታ ስላለበት አይደለም:: በማንነቱ ምህረትን የተሞላ፣ ትእግስትን የተሞላ፣ የፍቅር አምላክ ስለሆነ ብቻ ነው። የሚሰማኝ፣ የሚመልስልኝ፣ የሚወደኝ፣ ልጁ ያደረገኝ ይሄንን ሁሉ የማድረግ ግዴታ ስለነበረበት አይደለም። በማንነቱ የፍቅር አምላክ ስለሆነ ነው። ከራሱ መልካም ተነሳሽነት ብቻ ነው። የማድረግ ግዴታ የሌለበትን ነገሮች ማድረጉና በዚህ ውስጥ የማይገባኝን ነገር ለእኔ መስጠቱ ልቤን በምስጋና ይሞላልኛል። ምስጋናዬንም ብዙ ያደርግልኛል።  

የዚህ ጽሁፍ ዋና አላማ ታዲያ ምንድነው? በህይወታችን እያለፍን ያለንባቸው ከባባድ ጉዳዮች ቢኖሩ፣ ወይንም መንገዳችን ላይ ቢመጡ እነዚህን ነገሮች እግዚአብሄርን ደስ በሚያሰኝ ልብ፣ የእግዚአብሄርን መልካምነት ባለመጠራጠር፣ ባለማጉረምረምና በትክክለኛው መንገድ የእግዚአብሄርን ጸጋና እርዳታ ብቻ እየለመንን ከእውነተኛ ምስጋና ጋር በማለፍ እግዚአብሄርን እንድናከብረው ለማስታወስ ነው። በጣም ከፍተኛ ሀይል ያለው ምስጋና በምቾቶቻችን ሰአት የምናቀርበው ምስጋና አይደለም። ከፍተኛ ሀይል ያለው ምስጋና ልክ እንደ እነ ጳውሎስና ሲላስ በእስር ቤትና በሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነን የምናቀርበው  ምስጋና ነው። ይሄ አይነቱ ምስጋና፥ ልክ እነርሱ በእኩለ ለሊት ህይወት ለሊትና ጨለማ በሆነባቸው ሰአት፥ እግዚአብሄርን በዜማ ሲያመሰግኑ የዚህ ምስጋና ሀይል የወህኒውን ደጅ አናውጧል። የምስጋናቸው ሀይል የእነርሱን ብቻ ሳይሆን አካባቢያቸው ላይ ያሉትን ሰዎች ሁሉ ሳይቀር ነው የፈታው። በነገራችን ላይ እነ ጳውሎስ እግዚአብሄርን አመስግነው የሚያውቁት የዛን ቀን ብቻ አይደለም። በተለያዩ ቀናቶች እግዚአብሄርን አመስግነዋል። የዚያ ቀን ምስጋና ልዩ ሀይል እንዲኖረውና ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ነገር እንዲያደርግ ያረገው፥ የነበሩበት አስጨናቂ ሁኔታና ያልፉ የነበሩበት መከራ ነው። ከእንደዚህ አይነት መከራዎቻችን ውስጥ የሚወጡ ምስጋናዎች ሀይለኞች ናቸው። ብዙ ሰንሰለቶችን የመፍታት፣ ያለንበትን ሁኔታ የማናወጥና የማንቀሳቀስ ሀይል አላቸው። 

በዚህች ምድር ላይ ስንኖር፥ ከመከራ፣ ከችግር፣ ከህመምና ከውጣ ውረድ ውጪ የሆነ ህይወት ተስፋ አልተገባልንም። መከራ የምንኖርባት ምድር አንዱ ክፍል ነው። እግዚአብሄር ግን እንድንቸገርና መከራ ውስጥ እንድንገባ እያደረገ፣ በፍጹም በምናልፍባቸው ችግሮችና መከራዎች የሚደሰት፥ መከራችንን ኢንጆይ የሚያደርግ አምላክ አይደለም። እንደሱ የሚያደርገው አጋንንት ብቻ ነው። በህመማችን፣ በመከራችን የሚደሰተው ሰይጣን ብቻ ነው። እግዚአብሄር ቃሉ እንደሚለው መልካም አምላክ ነው። ለእኛ መልካም መሆን ግን በማንነቱ ውስጥ ያለ ምርጫ እንጂ ግዴታው አይደለም። ይሄንን እየደጋገምን ማሰብና ለነፍሳችን ማስረዳት ያለብን፣ እኛ በማይገባን መልኩ ውስጣችን፥ የሚደረግልንን ነገሮች የእግዚአብሄር ግዴታ እንደሆነ የማሰብ ዝንባሌ ስላለው ነው። እኛ ሰዎች ትክክለኛና ከልባችን የሆነ ምስጋና ልናቀርብ የምንችለው፥ ግዴታውን ለተወጣ ሰው አይደለም። ግዴታ ሳይኖርበት፥ ከራሱ መልካምነት ፍቅርና ርህራሄ ተነስቶ ላረገልን ሰው ነው። ለእኛ የሆነ ነገር ለማድረግ ግዴታ ያለበት ሰውና ምንም ግዴታ ሳይኖርበት ከራሱ መልካምነት ተነስቶ መልካም ነገር ለሚያረግልን ሰው የምናቀርበው ምስጋና የተለያየ ነው። ያ ግዴታ ያለበት ሰው ግዴታው እንደሆነ ስለምናውቅ፥ ነገሩን እንዲያደርግ እንጠብቅበታለን። እንዲያውም ያ ግዴታው የሆነውን ነገር ባያደርግ፥ ግዴታውን ባለመወጣቱ እንናደዳለን። ነገር ግን መልካም ነገርን የማድረግም ያለማድረግም መብት ያለው ሰው፥ መልካም ነገርን ለማድረግ መምረጡንና ግዴታ የሌለበትን ነገር ለማድረግ ልቡን ማቅናቱ ከልባችን እንድናመሰግነው ያደርገናል። እግዚአብሄር በህይወታችን ያደረገውን የትኛውንም መልካም ነገር ግዴታ ስለነበረበት አይደለም ያደረገው። ያደረገው በማንነቱ መልካም ስለሆነ ብቻ ነው። ለእኛ የመራራት፣ አለምን የመውደድ፣ እያንዳንዳችንን ከዚህ ሁሉ የአለም ሰዎች ውስጥ ለይቶ የማወቅ፣ እኛን የመርዳት፣ ጸሎቶቻችንን የመስማት ግዴታ ኖሮበት አያውቅም። ይሄንን ሁሉ ያደረገው መልካምነቱ ነው። ማንነቱ ነው። እግዚአብሄር ልጁን ኢየሱስን ለእኛ ሀጢያት ወደ ሞት ፍርድ እንዲጣል በመስቀል ላይ እንዲውል የማድረግ ግዴታ አልነበረበትም። ግድ ካለውም፥ ግድ ያለው ፍቅር ብቻ  እንጂ የትኛውም ሌላ ሀይል አይደለም። ለዚህ ነው እውነተኛ ምስጋና የሚገባው። 

ማንነት

ማንነት

ይሉኝታ

ይሉኝታ