Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ምርጫ 

ምርጫ 

መቼም ህይወታችን የየቀን ምርጫዎቻችን ውጤት መሆኑን ብዙዎቻችን እናስተውላለን። አብዛኞቹ ህይወታችን ላይ ያሉት ነገሮች፥ የእኛ ምርጫ ውጤቶች ናቸው። ለምሳሌ የምንሰራበትን መስሪያ ቤት መርጠን ማመልከቻ አስገብተን ነው የገባነው። የምሄድበትን ቤተክርስቲያን መርጠን ነው የምንሄደው። ቀናችንን በምን አይነት ሁኔታ እንደምናሳልፍ፣ የት መሄድ እንዳለብን፣ ከማን ጋር ጓደኛ መሆን እንዳለብን ጨምሮ በጣም ብዙ ህይወታችን ላይ ያሉት ነገሮች፥ የእኛ ምርጫ ውጤቶች ናቸው። እግዚአብሄርም የሰው ልጆችን ምርጫ የሚያከብር አምላክ ሲሆን፥ የተሰጠንን ነጻ የምርጫ ፈቃድ ተጠቅመን መልካም ምርጫዎችን እንመርጥ ዘንድ ይመራናል። ምርጫችንን ተጠቅመን ህይወታችንን ወደ ተሻለ ቦታ እንድንወስድና ከክፉ ሁሉ እንድናመልጥ፥ ከፊታችን ካሉት ምርጫዎች ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ጥሩም ሆነ መጥፎ ውጤት እያስቀደመ ይናገራል። ዘዳግም 30 ላይ ሙሴ ከመሞቱ በፊት የእስራኤልን ህዝብ እየደጋገመ የእግዚአብሄርን ሀሳብ መምረጥ እንዳለባቸው እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃቸው ነበር። 

በሕይወትም እንድትኖር እንድትበዛም፥ አምላክህም እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እንዲባርክህ፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ ትእዛዙንና ሥርዓቱን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ እኔ አዝዝሃለሁ።” ይልና ቁጥር 19 እና 20 ላይ፥ “በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንዲሰጣቸው በማለላቸው በምድሪቱ ትቀመጥ ዘንድ፥ እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።” በማለት ትክክለኛውን ምርጫ እንዲመርጡ ሙሴ ህዝቡን ያበረታታ ነበር።   

ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ ስትመለከቱ፥ እግዚአብሄር በኤደን ገነት ውስጥ ስላለችው የሞት ዛፍ ለአዳም ነገረው እንጂ እጁን ጠምዝዞ እንዲበላ አላደረገውም። እጁን ጠምዝዞ እንዳይበላም አላደረገውም። የዛፉን ፍሬ ለመብላትም ሆነ ላለመብላት በልቡ ውስጥ ያስቀመጠው ምርጫ ብቻ ነው። ምርጫ በጣም ፖወር ፉል ነው። ለዚህ ነው በሕይወታችን የምንመርጠውን እያንዳንዱን ምርጫ በማስተዋል ማድረግ ያለብን። እግዚአብሔር ለአዳም ምርጫን ከሰጠው በሁዋላ፥ ፍሬውን ለመብላት ከመረጠ፥ ከዚህ ምርጫ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ውድቀትና ሞት ገና ሳይበላ በፊት አስቀድሞ ነግሮታል። እግዚአብሄር የአዳምንና የሄዋንን እጅ ጠምዝዞ ፍሬውን እንዳይበሉ ቢያደርግ ኖሮ፥ የፈቃድ አምላክ አይባልም ነበር። እግዚአብሔር ለአዳም ፍቅሩን የገለጠው እጁን ጠምዝዞ በኤደን ገነት ውስጥ የተተከለውን ፍሬ እንዳይበላ በማድረግ ሳይሆን፥ ፍሬውን ቢበላ የሚመጣውን ውጤት በመናገር ነው። እግዚአብሔር ሊመርጥ የሚችለውን ምርጫ ውጤት ሳይናገር ዝም ይል ዘንድ ልቡ ውስጥ ያለው ፍቅር አላስቻለውም። ዛሬም እንደገና የሰው ልጆችን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ መንግስቱ ለማስገባት የሰዎችን እጅ አይጠመዝዝም። ይልቁንም በእኛ በብርሀን ልጆች እየተጠቀመ ለዓለም ሁሉ ኢየሱስን ምረጡ እያለ ይጮሀል። ኢየሱስን ብትመርጡ የዘላለምን ህይወት ታገኛላችሁ። ሌላኛው ምርጫችሁ ግን የዘላለምን ሞት ያመጣባችሁዋል እያለ ዓለም ልጁን ትመርጥ ዘንድ ለዓለም ወንጌልን ይመሰክራል።  

ያው ሁላችንም እንደምናውቀው፥ አዳም የመረጠው ምርጫ ሞትን አምጥቶበታል፥ ከእግዚአብሄር መለየትን አምጥቶበታል። አይገርማችሁም ግን አዳም ፍሬውን ከበላ በኋላ ይሄንን የተሳሳተ ምርጫ የመረጥኩት የሰጠኸኝ ሚስት አሳስታኝ ነው፥ ሄዋን ደግሞ እባቡ አሳስቶኝ ነው ብላ ምክኒያት ብታቀርብም፥ እግዚአብሄር የትኛውንም አይነት ምክኒያት አልተቀበለም። አይገርማችሁም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስንተላለፍ እኮ በፊቱ ቀርበን ምህረትን ከመለመን ውጪ ለስህተታችን የምንደረድራቸው ምክኒያቶችና ሰበቦች እግዚአብሄርን ሊያሳምኑት አይችሉም። የመረጥነውን ምርጫ ውጤት በደስታም ሆነ በጸጋ የመቀበል ግዴታ አለብን። አዳምና ሄዋን የዛሬ ስንትና ስንት ሺህ አመት በመረጡት ምርጫ ዛሬ የዓለም ህዝብ በሙሉ ዋጋ እየከፈለ ነው። አንዳንድ ምርጫዎች ጉዳታቸው ለረጅም ጊዜ በሕይወታችን የሚቀጥል ሊሆን ይችላል። “እነርሱ ባጠፉት እኔ ለምን እቀጣለሁ?” ብለን የምናስብ ሰዎች ካለን፥ እኛም በእነርሱ ቦታ ብንሆን ከእነርሱ የተለየ ምርጫ ልንመርጥ እንደማንችል እርግጠኞች ሁኑ። ምክኒያቱ ደግሞ እኛም ልክ እንደ እነርሱ ሰዎች የሆንን፣ ልክ እንደ እነርሱ ስሜት ያለን፣ የስጋ ምኞትና አምሮት ያለን፣ ልክ እንደ እነርሱ በጠላት የምንታለን ሰዎች ስለሆንን ነው። እግዚአብሄር ግን ደግ ነው። እኛ ባጠፋነው የራሱን ልጅ ኢየሱስን ዋጋ አስከፍሎታል። እንዲያውም እኮ “እነርሱ ባጠፉት እኔ ለምን እቀጣለሁ?” ማለት የነበረበት ክርስቶስ ነበረ። ምክኒያቱም እርሱ ምን አጠፋ? ለመታዘዝ መርጦ የሰው ልጆችን ሆነ እንጂ፥ ከመጀመሪያ መች የሰው ልጅ ነበረ? እርሱ ጻድቅ በመሆኑ፥ ስለ ሀጢያት ዋጋ የመክፈል ግዴታ መች ደረሰበት? ግድ ቢለው ፍቅር ብቻ እንጂ፥ ማን ስለ ሀጢያት ሊከሰው ይችላል? ይሄ ሁሉ ፍቅርና ምህረት ለማይገባን ለእኛ የበዛው የእግዚአብሄር ፍቅር እጅግ በጣም አስደናቂ ነው። ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የከፈለውን ዋጋ በማመን ብቻ የዘላለምን ህይወት አገኘን። ድጋሚ ወደ እግዚአብሄር መንግስት ለመግባት እድል ተሰጠን። ምህረት ተደረገልን፥ እንደገና ተባልን። እግዚአብሄር ጽድቁን፣ ቅድስናውን፣ መንግስቱን አወረሰን። አካፈለን። ምህረቱ በእኛ ላይ ተገለጠ። ታዲያ ግን እዚህ ጋር ልብ ማለት ያለብን፥ በስጋ እስከምንሞት ወይንም ወደ ጌታ እስከምንሄድ ድረስ ይህቺ የተጣልንባት የመከራ ምድር ልታመጣብን የምትችለውን መከራ መቀበላችን የግድ እንደሆነ ነው። ኢየሱስ ዋጋ የከፈለው ከሞት በኋላ ያለውን ዘላለማችንን ለማስተካከል ነው እንጂ ምድራዊ ህይወታችን አልጋ በአልጋ እንዲሆን አይደለም። አዳምና ሄዋን የሰሩት ሀጢያት ምህረትን አግኝቶ የዘላለምን ህይወት ለመውረስ ድጋሚ እድል ቢሰጠንም፥ አንዴ በሰራነው ሀጢያት ምክኒያት የተጣልንባትን የዚህችን ምድር መከራ መቀበላችን ግን ግድ ነው። ሀጢያት ሁልጊዜም ቢሆን የሚያመጣብን መዘዝ አለው። አሁን ሀጢያት ሰርቼ በኋላ ንሰሀ እገባለሁ የሚባል ነገር የለም። አዎ እግዚአብሄርማ እኮ ይቅር ይላል። በዘራነው የሀጢያት ዘር ውስጥ ያለውን ዋጋ ግን መክፈላችን አይቀርም።           

ይሄንን ለመረዳት እግዚአብሄር እንደ ልቤ ያለውንና ታላቅ የእግዚአብሄር ሰው የሆነውን የዳዊትን ህይወት ማጥናት በቂ ነው። ዳዊት እጅግ በጣም በእግዚአብሄር የተወደደ ሰው ነው። በዘመኑ ሁሉ የእግዚአብሄርን ሀሳብ አገልግሎ እንዳለፈ የተጻፈለት፥ እግዚአብሄርን አብዝቶ የሚወድና የሚፈልግ አስደናቂ ልብ የተሰጠው ሰው ነበር። ምንም በእግዚአብሄር እጅግ በጣም የተወደደ ትልቅ ሰው ቢሆንም ግን፥ የዳዊትን አጠቃላይ ህይወት ስትመለከቱ፥ ሕይወቱ በጣም በብዙ ፈተናዎችና መከራዎች የተሞላ የሰልፍ ሕይወት ነበር። በተለይ ደግሞ የሁለተኛ ሳሙኤል መጽሀፍን ስትመለከቱ፥ የንግስና ወንበሩን ትቶ እስኪሸሽ ድረስ ያደረሱት ከባባድ ፈተናዎች በህይወቱ አልፈው እንደነበር ትገነዘባላችሁ። እነዚህ እጅግ በጣም ብዙ ዋጋ ያስከፈሉት ፈተናዎች፥ ዳዊት ከሰው ሚስት ጋር በመተኛቱና ንጹህ ሰው በማስገደሉ በሰራው ሀጢያት ምክኒያት ህይወቱ ላይ የመጡ የሀጢያት ዘር ውጤቶች ነበሩ። ዳዊት ምንም በእግዚአብሄር የተወደደ ሰው ቢሆንም፥ በሰራው ሀጢያት የበቀሉትን ዘሮች ማጨዱ ግን አልቀረም። የዳዊትን ህይወት በጣም ካከበዱት ነገሮች ውስጥ አንዱ፥ በዘራው የሀጢያት ዘር ምክኒያት የበቀሉት የመከራ ውጤቶች ነበሩ። ሀጢያት ልክ እንደ ዘር ነው፥ ጊዜ ጠብቆ ይበቅላል። ብዙ ዋጋንም ያስከፍላል። መጽሀፍ ቅዱስ በዘፍጥረት መጽሀፍ ምእራፍ 8 ቁጥር 22 ላይ ሲናገር “በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም።” በማለት የምዘራው ጥሩም ሆነ መጥፎ ዘር ጊዜ ጠብቆ እንደሚበቅልና ይሄ ህግ አንዴ በእግዚአብሄር የተወሰነ እንዲሁም ሊቀየር የማይችል ህግ እንደሆነ ይናገራል።  ዳዊት ስለሰራው ሀጢያትና እግዚአብሔርን ስለበደለበት በደል ንሰሀ በመግባት ወዲያውኑ የእግዚአብሔርን ምህረት አግኝቷል። እግዚአብሔር ምህረት አድርጎለት፥ ሀጢያቱን በሙሉ ይቅር ብሎታል። በሰራው ሀጢያት ውስጥ የተመደበውን ቅጣት ግን ሳይከፍል ፈጽሞ ከዚህች ምድር አላለፈም። እግዚአብሄር ምህረቱ ብዙ የሆነ መሀሪና ታጋሽ አምላክ ነው። ምህረቱን ለለመኑት ሁሉ አይከለክልም። እኛን በመማርና ይቅር በማለት ይደሰታል። ስለሰራናቸው ሀጢያቶች ግን የምንከፍላቸው ዋጋዎች አሉ። በዚህ በስጋችን የሰራናቸውን ሀጢያቶች ዋጋ ሳንከፍል ማናችንም ከዚህች ምድር አንሄድም። ምንጊዜም እግዚአብሄርን ያለመታዘዝ መንገዶችን ስንመርጥ፥ ያ የምንመርጠው መንገድ ዋጋ እንደሚያስከፍለን እያወቅን ቢሆን ምናልባት መንገዳችንን እንድናስተካክል ይረዳን ይሆናል። ምናልባት ከብዙ ዋጋ መክፈሎች ያድነን ይሆናል። ምናልባት የእግዚአብሄርን ምህረት እንደ ፈቃድ በመጠቀም ከምንገባባቸው ትልልቅ ስህተቶች ያድነን ይሆናል።  

ሰላምና ደስታ

ሰላምና ደስታ

 መወደድ 

መወደድ