Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ተዋጊ

ተዋጊ

ሰሞኑን እየተማርኩ ያለሁት ስለ መንፈሳዊ ውጊያ ነው። “እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም ደግሞ እግዚአብሔር ነው” በማለት በዘጸአት 15፡3 ላይ እንደተጻፈው፥ የምናመልከው አምላክ ተዋጊ እንደሆነ ሁሉ እኛም ህዝቦቹ ተዋጊ ሰራዊቶች እንድንሆን ይፈልጋል። አንድ ጊዜ እንዲያውም በመሳፍንት መጽሐፍ ምእራፍ 3 ከቁጥር 1 ጀምሮ ስትመለከቱ፥ እግዚአብሔር ሆነ ብሎ የእስራኤል ልጆች መዋጋትን ይማሩ ዘንድ፥ ሰልፍን ይለማመዱ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ጠላቶቻቸውን ሊያጠፋ እንዳልወደደና ጥቂት ጠላቶችን እንዳስቀረ በክፍሉ ላይ ይናገራል። እግዚአብሔር መዋጋትን እንድናውቅ፥ ሰልፍን እንድንማር ይፈልጋል። ዳዊትም በመዝሙረ ዳዊት 144 ላይ ስለ ጎልያድ በጻፈው መዝሙር ላይ “እግዚአብሔር አምላኬ ይባረክ፥ ለእጆቼ ሰልፍን ለጣቶቼም ዘመቻን የሚያስተምር” በማለት እግዚአብሔር መዋጋትን ያስተምረው እንደነበር ተናግሯል። ዳዊት እንዲያውም ጎልያድ ጋር ሲመጣ አይደለም ውጊያን የተማረው። በምድረበዳ የአባቶቹን በጎች ሲጠብቅ፥ እግዚአብሔር አንበሳና ድብን እየላከ ነው ውጊያን አስቀድሞ ያለማመደው። እንዲያውም ጎልያድን ለመግጠም ወደ ሳኦል ማመልከቻ ሲያስገባ፥ እንደ ልምድ አድርጎ ያቀረበው ምድረበዳ ላይ በአንበሶችና በድቦች ላይ እግዚአብሔር የሰጠውን ድሎቹን ነበር። “ሳኦልም ዳዊትን። አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም አለው። ዳዊትም ሳኦልን አለው። እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር። እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ መታሁ፤ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ የሕያውን አምላክ ጭፍሮች ተገዳድሮአልና ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ዳዊትም። ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል አለ።” (1ኛ ሳሙኤል ምእራፍ 17፡33-37) 

ዳዊት ምድረበዳ ላይ በጎች እየጠበቀ ለእግዚአብሔር ይዘምራል። አንበሳና ድብ ደግሞ በጎን በኩል ይመጡበታል። አንድም ቀን ግን “እግዚአብሔር ሆይ እኔ ለአንተ እየዘመርኩ፥ እኔ አንተን እያመለኩ፥ እኔ ለአንተ እየኖርኩ እንዴት ህይወቴን አደጋ ላይ የሚጥሉ አራዊቶች ሲመጡብኝ ዝም ብለህ ትመለከታለህ?” ብሎ ሲያጉረመርም አንሰማውም። ይልቁንም “እግዚአብሔር ብርሀኔና መድሀኒቴ ነው የሚያስፈራኝ ማነው? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው የሚያስደነግጠኝ ማነው?” እያለ በእግዚአብሔር ላይ በመታመን ይዘምራል። መታገል ሲያቅተው ደግሞ ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እየጠራ ከጠላቶቹ እጅ ይድናል።  

አንድ ሰው አለምን ሰይጣንንና የራሱን ፈቃድ ትቶ ክርስቶስን ለመከተል ሲወስን፥ ወዲያውኑ የሰይጣን መንግስት ጠላት ይሆናል። ስለዚህ ሁልጊዜ ጠላት አለን፥ ሁልጊዜ ውጊያ ውስጥ ነን ማለት ነው። ስለ መንፈሳዊ ውጊያ ስናስብ ውጊያውን ብዙ ጊዜ የምናያይዘው በተለያዩ አጋጣሚዎች መንገዳችን ላይ ከሚመጡ አደጋዎች፣ የጤና መቃወሶች እንዲሁም አለመከናወኖች ጋር ብቻ ነው። ጠላት በእነዚህ መንገዶች ሊዋጋን ቢችልም በየቀኑ እኛን የሚዋጋበትን ዋና መንገድ ግን ቸል ልንለው አይገባም። በኤፌሶን መጽሐፍ ምእራፍ 6 ከቁጥር 10 ጀምሮ እንደተጻፈልን ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን እቃ ጦር እንድንታጠቅ የተነገረን፥ የዲያቢሎስን ሽንገላ እንድንቃወም ነው። ወገባችንን በእውነት እንድንታጠቅ፣ የጽድቅን ጥሩር እንድንለብስ፣ በሰላም ወንጌል እግሮቻችን ተጫምተው እንዲቆሙ፣ የመንፈስን ሰይፍ እንድንይዝ የተነገረን፥ የዲያቢሎስን ሽንገላ እና ውሸት እንቃወም ዘንድ ነው። 

በየቀኑ ሰይጣን ወደ አይምⶂአችን የሚልከውን ውሸቶች የምንቃወምበት ዋና መሳሪያችን ደግሞ፥ እውነት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ነው። ውሸት የሚጋለጠው በእውነት ነው። ውሸት ውሸት መሆኑ የሚታወቀው እውነት ሲመጣ ነው። እውነት ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው። ስለዚህ ጠላት ወደ ሀሳባችን የሚልካቸውን ውሸቶች መቃወም የምንችለው፥ በተጻፈልን የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነው ማለት ነው። እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችሃል በማለት በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 8፡32 ላይ እንደሚናገረው፥ የምናውቀው የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነው አርነት የሚያወጣን።  

ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወታችን ጌታና አዳኝ አድርገን በተቀበልንበት በዚያች ደቂቃ፥ አዲስ ፍጥረት ሆነናል፥ አዲስ ማንነት ተሰቶናል። ነፍሳችን የዳነችው፥ የክርስቶስን ስራ በእምነት በተቀበልንበት በዚያች ቅጽበት ነው። አያችሁ ግን እምነት እንዴት አስፈላጊ እንደሆነ? “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና” ተብሎ በኤፌሶን 2፡8 ላይ እንደተጻፈው፥ የእግዚአብሔር ጸጋ ያዳነን እግዚአብሔር እራሱ በሰጠን እምነት ውስጥ አልፎ ነው። ምንም ኢየሱስ ለሀጢያታችን ዋጋ ቢከፍልም፥ ይሄንን እውነት በእምነት ካልተቀበልነው ልንድን አንችልም። እምነት ዘላለማችንን ከገሀነም አስመልጦ ወደ እግዚአብሔር መንግስተ እንገባ ዘንድ እግዚአብሔር የተጠቀመበት አስደናቂ ነገር ነው። ዘላለማዊ የሆነው የእግዚአብሔር ማዳን የሚያልፈው በእምነታችን ውስጥ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር በእምነት የጀመርነውን ይሄንን መንገድ እስከመጨረሻው የምንቀጥለውም በእምነት ነው። ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር በክርስቶስ ውስጥ የተሰጠንን ነጻነቶች አስጠብቀን የምንኖረው በዚሁ እግዚአብሔር በሰጠን እምነት ውስጥ ነው። 

እግዚአብሔር እንዲሁ በነጻ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ የሰጠን፣ እንደተሰጠን ባለማወቃችን ግን እንዳልተሰጠው ሰው የምንኖርባቸው ብዙ ሁኔታዎች አሉ። በሀገራችን አንድ አባባል አለ “የሌለውና ያለውን የማያውቅ አንድ ናቸው” ሲባል ሰምቻለው። ምንም በጠላት ሀይል ሁሉ ላይ ስልጣን ቢሰጠንም፥ የተሰጠንን ነገሮች ካላወቅን ስለማንጠቀምበት መብት ከሌለው ሰው ጋር ልዩነት ላይኖረን ይችላል።  

ስለዚህ ጠላት እኛን በባርነት ውስጥ ለማስቀመጥ እድል የሚያገኘው በሁለት መንገዶች ብቻ ነው። ወይ ስለ እኛ የተጻፈውን ቃል ባለማወቃችን ነው ወይንም ደግሞ ያወቅነውን ቃል ባለማመናችን ውስጥ ነው። ስለዚህ የሚያደርገው ከሁለቱ አንዱን ነው፥ ወይ እንዳናውቅ ይታገላል። ወይንም ደግሞ ያወቅነውን እንዳናምነው ይታገላል። ምክኒያቱም ፍጹም የሆነው ነጻነታችን ያለው እውነትን በማወቃችን እና ያወቅነውን እውነት በማመናችን ውስጥ ነው። በ1ኛ ዮሐንስ 5፡4 ላይ ሲናገር፥  “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ አለምን ያሸንፋልና፥ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው” በማለት እንደተናገረው እምነት በክርስቶስ የተሰጠንን አሸናፊነት ጠብቀን የምንኖርበት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። እምነት መንፈሳዊ አለም ላይ እጅግ የከበረ ነገር ነው። የጠላት ውሸት ዘልቆ ወደ ውስጣችን እንዳይገባ የምንከላከልበት ጋሻችን ነው። ብርቱ የሆነ የመዋጊያ መሳሪያችን ነው። እግዚአብሔርም በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ሕይወታችንን የሚያሳልፍበት ምክኒያት፥ በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነው እምነታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ ነው። ሰይጣን የፈለገ ሀይለኛ ቢሆን እንካን ከተጻፈው ሕግ አልፎ ሊሰራ አይችልም። ሊሰራ የሚችለው ህጉን ባለማወቃችን ምክኒያት የሚያቀርብልንን ውሸቶች በማመናችን ውስጥ ብቻ ነው። 

ፍርድ ቤት ከሳሽና ተከሳሽ በዳኛው ፊት በቆሙበት የፍርድ ወንበር ፊት ዳኛው የከሳሽንና የተከሳሽን ሀሳብ ካዳመጠ በሓላ ፍርዱን ከመስጠቱ በፊት አንድ ወሳኝ የሆነ ጥያቄ ይጠይቃል። “ህጉ ምን ይላል” ይላል። በጉዳዩ ላይ ቀድሞ የተጻፈው ህግ ምን ይላል? አያችሁ ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ ወደ ፍርድ ቤቱ ሳይመጡ በፊት በሚካሰሱበት ጉዳይ ዙሪያ አስቀድሞ የተጻፈ ህግ አለ። ሊፈርድ የተቀመጠው ዳኛ ፍርዱን የሚሰጠው አስቀድሞ በተጻፈው ህግ መሰረት ነው። ህጉ መተዳደሪያ፣ ትክክለኛ ፍርድ መፍረጃ ነው። ጠበቆችም ለመከራከርና የከሳሹን ወይንም የተከሳሹን መብት ለማስከበር ያላቸው ብቸኛ መንገድ ሕጉ ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል ብለው የተጻፈውን ህግ በመጥቀስ መብታቸውን ለማስከበር መትጋት ነው። መንፈሳዊ አለም ላይ የሚሰራው የእግዚአብሔር ቃል ህግ ነው። ሰይጣንም ህጉን ያውቃል፥ በደምብ ከእኛ የበለጠ ያውቃል። ትዝ አይላችሁም ኢየሱስን ቃል እየጠቀሰ ሊፈትነው ሲሞክር? ለዚያ ነው የእምነትን ጋሻ ማንሳት ያለብን፣ የመንፈስ ሰይፍ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ማንሳት ያለብን። የምንዋጋበትና ነጻ የምንወጣበት ትልቁ መሳሪያችን አምነን የምንዋጋበት የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ነው። 

የብሉይ ኪዳን መጽሀፍን ስናነብ በኢያሱ መጽሐፍ ላይ ኢያሱና ሕዝቡ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከነዓን  ለመግባት መንገዳቸው ላይ ያሉትን የእግዚአብሔር ጠላት የሆኑትን ሕዝብ በመዋጋት እና ምድሪቱን በመውረስ የተስፋ ቃላቸው ጋር መድረስ ነበረባቸው። እግዚአብሔር አስቀድሞ “የእግራችሁ ጫማ የሚረግጠውን ቦታ ለእናንተ ሰጥቻለሁ” በማለት ምድሪቱን እንደሰጣቸው አስቀድሞ ስለተናገረ፣ እነ ኢያሱ እግዚአብሔር ሰጥቻችሁዋለሁ ብሎ በሰጣቸው ምድር ላይ ከተቀመጡት ጠላቶች ጋር ሲዋጉ እምነታቸው ይሄ ነበር “ምድሪቱን እግዚአብሔር ሰጥቶናል፣ ምድሪቱ የእናንተ አይደለችም የእኛ ናት” የሚል ታላቅ እምነት ልባቸው ውስጥ ነበር። የእነ ኢያሱ መፈክር፥ “እግዚአብሔር ምድሪቱን ስለሰጠን እናስለቅቃችሃለን” የሚል ነበር። ምንም በጠላቶች ተይዛ የነበረች ምድር ብትሆንም፥ እነ ኢያሱ እነዚህን ጠላቶች ለማስለቀቅ፥ እግዚአብሔር “ለእናንተ ሰጥቼዋለሁ፣ የእናንተ ነው” ያለውን ቃል አምነው መዋጋት ነበረባቸው። እግዚአብሔር የሰጣቸውን ምድር የራሳቸው ያደረጉት ተዋግተው ነው። 

በምንዋጋበት ሰአት ትልቁ መሳሪያችን፥ እግዚአብሔር የሰጠን ተስፋ ወይንም ከእግዚአብሔር ቃል የሰማናቸውን እውነቶች ማመናችን ነው። እምነት እግዚአብሔር ሰጥቻችሃለሁ ያለንን ነገር የምንቀበልበት፣ ናችሁ ያለንን ነገሮች የምንሆንበት እጅግ በጣም ትልቅ አስፈላጊ የውጊያ መሳሪያችን ነው። “የእግዚአብሔር ቃል ቅን ነውና፥ ስራውም ሁሉ በእምነት ነውና።” በማለት መዝሙረ ዳዊት 33፡4 ላይ እንደሚናገረው መንፈሳዊ አለም ካለ እምነት አይሰራም። ሰይጣን እንኳን በሰዎች ሕይወት ለመስራት ወይንም ተጽእኖ ለማድረግ ሲፈልግ፥ መጀመሪያ ውሸቶቹን እንዲያምኑ ነው የሚያደርገው። ሰይጣን እራሱ በሰዎች ሕይወት ውስጥ እድል የሚያገኘው በእምነታቸው ውስጥ ነው። ካላመኑት መስራት አይችልም። 

በክርስቶስ በተሰጠን በአዲሱ ማንነታችን ውስጥ ያሉትን ነጻነቶች በእምነት ተቀብለን ካልተዋጋን፥ ሰይጣን አሁንም በባርነት ውስጥ እኛን የሚያኖርበትን እድል ሊያገኝ ይችላል። ለምሳሌ አንድ ቀለል ያለ ምሳሌ ወስደን ብንመለከት፥ ክርስቶስን በማመን የተሰጠን ይሄ አዲሱ ማንነታችን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በከፈለው ዋጋ የጸደቀ በጠላት ክስ ውስጥ ሊኖር የማይችል ነው። ይሄ ማለት ግን ሰይጣን እኛን መክሰሱን ያቆማል ማለት አይደለም። ክሱን እያመንን ከተቀበልነው አሁንም በክስ ባርነት ውስጥ ሊያኖረን ይፈልጋል። ሰይጣን መክሰስ ባህሪው ነው፣ መጽሀፍ ቅዱስም የወንድሞች ከሳሽ ብሎ አስቀምጦታል። በክርስቶስ አዲስ የሆንበት አዲሱ ማንነታችን ግን በክርስቶስ የጸደቀ በመሆኑ ሮሜ 8፡33 ት ላይ የተጻፈውን ቃል በማመንና በመጥቀስ የጠላትን ክስ አልቀበልም ብለን ሀሳቡን መቃወምና ነጻነታችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን። ሮሜ 8፡33 ላይ የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር እንዲህ ይላል “እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው የሚኮንንስ ማነው?” ይላል። አያችሁ፥ የሰይጣንን ክስ አልቀበልም የማለት መብት እንዳለው ያላወቀ አማኝ ግን መብቱን የሚያስከብርበት እውቀት ስለሌለው፥ ነፍሱ ብትድንም ነጻነቱን ግን በጠላት ተቀምቶ ዝም ብሎ ሲከሰስ ሊኖር ይችላል። ነጻነት እኮ ተሰጥቶናል፥ በተሰጠን ነጻነት ውስጥ ለመቆየት ግን የሰይጣንን ውሸቶች እምቢ እያልን በእምነት ጸንተን በመቃወም የዚህች ምድር ሩጫችን እንከሚያበቃ ድረስ መልካሙን የእምነት ገድል እየተጋደልን እንኖራለን። 

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።” (ገላትያ 5፡1)

ሸክም 

ሸክም 

ሰላምና ደስታ

ሰላምና ደስታ