ጥንቃቄ
ከህይወታቸው እንማረባቸው ዘንድ በመጽሀፍ ቅዱሳችን ላይ ከተጻፉልን ሰዎች መካከል ነው። ብዙ ጊዜም በየመድረኮቻችን ላይ ታሪኩ ለትምህርታችን ሲሰበክ እናውቀዋለን። ሳምሶን። የተቀባ በጣም ትልቅ የእግዚአብሄር አላማ ያለበት ሰው። ይህ ትልቅ የእግዚአብሄር ሀይል የተገለጠበት ሰው ታዲያ ታሪኩን ብዙዎቻችን እንዳነበብነውና እንደተማርነው፣ ብዙም ሳይቀጥል በጠላቶቹ እጅ በመውደቅ፥ ሙሉውን የእግዚአብሄርን ሀሳብ አገልግሎ ሳይጨርስ አገልግሎቱ እንዳበቃ ብዙዎቻችን እናውቃለን። የሳምሶን ታሪክ በመሳፍንት ምእራፍ 13 ላይ ሲጀምር፥ ከሳምሶን ታሪክ አይጀምርም። ይልቁንም የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሄር ፊት እንደ ገና ክፉ ስራ እንደሰሩ፥ እግዚአብሄርም በፍልስጥኤማውያን እጅ አርባ አመት አሳልፎ እንደሰጣቸው በመናገር ነው የሚጀምረው። ሳምሶን የተወለደበት ወቅት፥ እግዚአብሄር የእስራኤልን ህዝብ በፍልስጥኤም ግዛት ስር የጣለበት፥ እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው እጅ ተላልፈው የተሰጡበት ከባድ ወቅት ነበር። ታዲያ ሳምሶን ከመጸነሱ በፊት፥ የእግዚአብሄር መልአክ ማኑሄ ለሚባል ሰውና መካን ለነበረችው ሚስቱ ተገልጦ፥ ይህቺ መካን ሴት ወንድ ልጅ እንደምትወልድ፥ ይሄ ልጅም፥ በየጊዜው ከሚወለዱት ልጆች ለየት ያለ እንደሆነ፥ ከእናቱ ማህጸን ጀምሮ ለእግዚአብሄር የተለየ ናዝራዊ እንደሚሆን፥ በራሱ ላይ ምላጭ እንደማይደርስበት፥ ይሄንን ለእግዚአብሄር የተለየ ልጅ ለመውለድ ደግሞ መብላትና መጠጣት ስለሌለባት ነገር ጭምር ነው የነገራት። ሳምሶን እኮ እናቱ እንኳን ስለ እርሱ የተቀደሰችለት አስደናቂ የእግዚአብሄር አላማ ያለበት ሰው ነበር። መልአኩ ታዲያ ቀጠል አረገና “ይሄ ከአንቺ የሚወለደው ልጅ፥ የእስራኤልን ህዝብ ከፍልስጥኤማውያን እጅ ማዳን የሚጀምር ነው” በማለት እግዚአብሄር በዚህ ልጅ ህይወት ላይ ያለውን ዋናና ትልቁን አላማ ሳይነግራት አልሄድም። አይገርማችሁም? እግዚአብሄር እኮ እኛ እንኳን በእናታችን ማህጸን ከመጸነሳችን በፊት ነው በህይወታችን ሊሰራ ያሰበውን አላማ ያቀደው። ሁላችንም ከመወለዳችን በፊት፥ እግዚአብሄር በህይወታችን ሊሰራ ያሰበውን አላማ በሙሉ ጽፎታል። አላማን ማወቅ ማለት፥ ይሄ እግዚአብሄር ሳይፈጥረን በፊት በህይወታችን ሊሰራ ያሰበውን ሀሳቡን ማግኘት ማለት ነው። ህይወታችን ትክክለኛውን እርካታ የሚያገኘው፥ ይሄንን አላማ አግኝቶ፣ በዚህ አላማ መመራት ሲጀምር ነው። በዚሁ አጋጣሚ፥ እዚሁ ዌብ ሳይቴ ላይ “አላማ” በሚል ርእስ የጻፍኩትን ጽሁፍ፥ ፈልጋችሁ እንድታነቡት እጋብዛችኋላሁ። ታዲያ ከላይ እንደተነጋገርነው፥ እግዚአብሄር የእስራኤልን ህዝብ አሳልፎ ከሰጣቸው ከፍልስጥኤማውያን ግዛት ለማዳን ሲያስብ፥ ይሄንን ሀሳቡን ለመፈጸም የፈጠረው ሰው ሳምሶን ነበር። የሳምሶን ትልቁ የህይወት አላማ፥ ለእግዚአብሄር ራሱን ለይቶ ናዝራዊነቱን በመጠበቅ፥ የእስራኤልን ህዝብ፥ ተላልፈው ከተሰጡበት ከፍልስጥኤም ህዝብ ባርነት ነጻ ማውጣት ነው። ሳምሶን ናዝራዊ ነው። ናዝራዊ ማለት ለእግዚአብሄር የተለየ ማለት ሲሆን፥ በዘሁልቁ ምእራፍ 6 ላይ፥ እግዚአብሄር ለእስራኤል ህዝብ በሰጣቸው ህግና ስርአት መሰረት፥ ናዝራዊ የሆነ ሰው፥ በጸጉሩ ላይ ምላጭ የማይደርስበት፣ ወይን ጠጅና የሚያሰክር ነገር የማይጠጣ፣ በፍጹም የሞተ ነገር ጋር የማይቀርብ፥ እንዲሁም ብዙ ከናዝራዊነት ጋር እግዚአብሄር ለእስራኤል ህዝብ የሰጣቸውን ትእዛዛት የሚጠብቅ ሰው መሆን አለበት። እነዚህ እንግዲህ ከአንድ ናዝራዊ ከሆነ ሰው የሚጠበቁ የህይወት ስርዓቶች ናቸው። እኛ የህይወት ዘመን ናዝራውያኖች ነን። ለእግዚአብሄር የተለየን ህዝቦች ነን። ልክ እግዚአብሄር በዘሁልቁ መጽሀፍ ላይ ናዝራዊ ለሆኑ ሰዎች እንደሰጠው ስርአትና ህግ፥ ለእኛ ደግሞ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሰጠን ህይወት ጋር የምንተዳደርባቸው ህጎች አሉን። ሳምሶን ናዝራዊ ነህ የተባለው፥ ላዩ ላይ ከነበረው ትልቅ የእግዚአብሄር መንፈስና ሀይል የተነሳ ነው። ዛሬ ልክ እንደ ሳምሶን ዘመን የእግዚአብሄር መንፈስ በላያችን እየመጣ የሚሄድ ሳይሆን፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ስራ፥ በውስጣችን ሊኖር የዘላለም መኖሪያዎቹ አርጎናል። በየቀኑ በውስጣችን ተሸክመን የምንንቀሳቀሰው፥ ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሄርን መንፈስ እንደሆነ በማወቅ፥ በውስጣችን ላለው ለዚህ የከበረ መንፈስ ክብር እየሰጠን፥ በዚህች ምድር እንድንመላለስ ፍጹም የሆነው የእግዚአብሄር ሀሳብና ፈቃድ ነው። ሀያ አራት ሰአት በውስጣችን የሚኖር፣ የእግዚአብሄርን ቃል የሚተረጉምልን፣ የሚያስተምረን፣ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራን፣ የሚቀድሰን፣ ከስህተት መንገድ ሁሉ የሚመልሰን፣ ከሀዘናችን የሚያጽናናን፣ በነገር ሁሉ የሚረዳን የእግዚአብሄር መንፈስ በውስጣችን አለ። በላያችን የተሸከምነው የእግዚአብሄርን ስም ነው። በውስጣችን የተሸከምነው ደግሞ፥ የእግዚአብሄርን መንፈስ ነው። በጣም ውድ ውድ ነገሮችን ተሽክመን፥ ርካሽ ቦታዎች ራሳችንን ማስገኘት አያዋጣንም። እግዚአብሄር፥ በተለያዩ ሰዎች ልዩ ልዩ ባህሪውን የገለጠ ሲሆን፥ በሳምሶን ውስጥ፥ ብርታቱንና ሀይሉን እንዲሁም ማስፈራቱን ገልጦአል። መጽሀፍ ቅዱሳችን ላይ ስናነብ፥ አንዳንድ ሰዎች፥ የእግዚአብሄር መንፈስ ሲወርድባቸው ትንቢትን ይናገራሉ። አንዳንዶች ደግሞ መገለጥና ራእይን ያያሉ:: ሌሎች ደግሞ ልዩ ልዩ በሆነ ልሳንና ሰማያዊ ቋንቋዎች ያወራሉ። ሳምሶን ግን የእግዚአብሄር መንፈስ ሲወርድበት፥ ሀይለኛ ነበር የሚሆነው። በእግዚአብሄር መንፈስ ውስጥ ወደ ሳምሶን ይወርድ የነበረው መለኮታዊ የሆነ የእግዚአብሄር ሀይል ነበር። አይታችሁት ከሆነ፥ ልክ የእግዚአብሄር መንፈስ በላዩ ላይ ሲወርድ፥ ይነሳና ሰው ጠቦትን እንደሚቆራርጥ፥ ያለ ምንም መሳሪያ በእጁ ብቻ አንበሳውን ይቆራርጠው ነበር። ይሄድና የእግዚአብሄር ህዝብ ጠላቶች የሆኑትን ፍልስጥኤማውያንን ይጨርሳቸው ነበር። የእግዚአብሄር መንፈስ ወደ እኛ በሀይልና በሙላት የሚመጣው፥ የተፈጠርንበትን አላማ እንድናገለግል ሀይል ሊሰጠን ነው። የእግዚአብሄር መንፈስ በሀይልና በሙላት ወደ እኛ የሚመጣው የእግዚአብሄርን ሀሳብ በእኛ ውስጥ ለመፈጸም ነው። መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ በሀይልና በተለየ መንገድ ሲመጣ የምናረጋቸው ነገሮች፥ አላማዎቻችንን የሚያመለክቱ ናቸው። ይሄ የእግዚአብሄር መንፈስ በሀይል ወደ እኔ ሲመጣ ወዴት ነው የሚወስደኝ? በዝማሬ ነው የሚሞላኝ? አይኖቼን ከፍቶ መንፈሳዊ ሚስጥራትን ነው የሚያሳየኝ? የቃሉን መገለጥ ነው የሚሰጠኝ? ምን ሳረግ ነው ራሴን የማገኘው? ብለን መጠየቃችን እግዚአብሄር በህይወታችን ሊሰራ ያሰበውን ነገር፥ ከሚያመለክቱን ትልልቅ ምልክቶች ውስጥ አንዱ ነው። “እግዚአብሄርም የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በሀይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያቢሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፣ እግዚአብሄር ከእርሱ ጋር ነበረና።” ሀዋ ስራ 10:38
ሳምሶን በህይወቱ ላይ እግዚአብሄር ካለው አላማ አንጻር፥ በህይወቱ ላይ የተገለጠው የእግዚአብሄር ሀይል፥ በዙሪያው ያሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ የፍልስጤም ህዝቦች ያንቀጠቅጥ ነበር። አይገርማችሁም? እግዚአብሄር እኮ ለመስራት አንድ ሰው ነው የሚበቃው። አንድ የእስራኤልን ህዝብ ወክሎ በቆመ ሰው ውስጥ፥ አንድ ሙሉ ሀገርን ያናውጣል። እግዚአብሄር ጠላቶቹን ለመበቀል ሲነሳ፥ የሚፈልገው አንድ ሰው ነው። ብዙ ሆነን ሀይልና ብርታት እንድናዋጣለት አይፈልግም። ይልቁንም አንድ በእርሱ ትእዛዝና ፈቃድ ውስጥ ለመኖር በቆረጠ ሰው ህይወት፥ ሀገር የሚያንቀጠቅጠውን ሀይሉን ይገልጣል። ከዚያ ሙሉ ክብሩን እራሱ ይወስዳል። ሳምሶንን እንደምታውቁት፥ ላዩ ላይ ከነበረው የእግዚአብሄር ሀይል የተነሳ፥ የከተማን በር ገንጥሎ ከተሸከመ በኋላ፥ ቁልቁለት ሳይሆን ተራራ ላይ በመውጣት የከተማውን በር ተራራው ጫፍ ላይ ወስዶ የሚጥል፥ አስረነዋል ሲሉ ያሰሩበትን ጠንካራ ገመድ፥ እሳት እንደ ሸተተው የተልባ እግር ማሰሪያቸውን በጣጥሶ የሚነሳ፥ የእግዚአብሄርን ህዝብ ጠላቶች ግራ አጋብቶ፥ ራስ ምታት የሆነባቸው ሰው ነበር። ይሄ ህዝብ ተሰብስቦ ያልቻለው እግዚአብሄር ሀያል አርጎ ሀይሉን የገለጠበት እልፍ ገዳይ፥ በአንዲት ሴት እጅ መውደቁና ታሪኩ እንዲህ ማብቃቱ አይገርማችሁም? የሳምሶን ህይወት መጨረሻው በደሊላ እጅ ይለቅ እንጂ፣ የሳምሶን ውድቀት ግን የጀመረው ደሊላ ጋር አይደለም። ታሪኩ የተጻፈልን ለትምህርታችን እንደመሆኑ መጠን፥ ከሳምሶን ህይወት የምንማረው ትልቁ ትምህርት ጥንቃቄና ማስተዋል ምን ያህል ህይወታችንን እንደሚጠብቅ ነው። ሳምሶን፥ የህይወቱን አካሄድ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በደምብ ስታዩት፥ የተጠራበት ናዝራዊ የመሆን ህይወት የሚጠይቀውን ስርዓት፥ በአግባቡ እየተከተለ የሚሄድ ሰው አልነበረም። ከላይ በዘሁልቁ መጽሀፍ ላይ እንዳነበብነው፥ እግዚአብሄር ለህዝቡ ከሰጣቸው የናዝራዊነት ህጎች አንዱ፥ የሞተ ነገር ጋር ወይንም ሬሳ ጋር አለመቅረብ ነው። ታሪኩን ካስታወሳችሁት፥ ሳምሶን የእግዚአብሄር መንፈስ ወርዶበት የቆራረጠውን የአንበሳ ሬሳ ለማየት ፈቀቅ በማለትና፥ የሞተው የአንበሳ ሬሳ ውስጥ ያየውን ማር በእጁ በመውሰድ፥ መንገድ ለመንገድ እየበላ እንደሄደ መጽሀፍ ቅዱስ ጽፎልናል። እቤቱ ሲደርስ ደግሞ፥ ማሩን ለእናትና ለአባቱ ቢሰጣቸውም፣ ማሩን ከሞተ የአንበሳ ሬሳ ውስጥ እንዳመጣው ግን አልነገራቸውም በማለት መጽሀፍ ቅዱስ በግልጽ ጽፎልናል። ብዙ ጊዜ ስናወራ “ከሞተ አንበሳ ውስጥ ማርን የሚያወጣ አምላክ” እያልን እናወራለን እንዘምራለን። እውነት ነው፥ እግዚአብሄር ምንም የማይሳነው አምላክ ነው። ከዚህ ነገር ውስጥ የምንማረው ትልቁ ነገር ግን፥ ሰይጣን እኛን ወደ ተሳሳተ ቦታ ለመሳብ፥ ትክክል ያልሆኑ ነገሮች ውስጥ፥ ሊስቡን የሚችሉ ነገሮችን ሊያስቀምጥ መቻሉ ነው። ሳምሶን ወደ ሬሳው ጋር ባይቀርብ ማሩን ባላየው፣ ለመብላትም ባልተመኘው ነበር። ትልቁ ስህተቱ አትቅረብ ወደ ተባለው ቦታ መቅረቡ ነው። ወደ አንበሳው ሬሳ መቅረቡ ነው። እኛ አንድ እርምጃ እንቅረብ እንጂ፥ ሰይጣን እንዴት አርጎ እንደሚስበንና እንደሚያነካካን ያውቃል። አንዳንድ ጊዜ፥ ይሄ እኮ ምንም ችግር የለውም ብለን የናቅነው አንድ እርምጃ፥ ወደ ስህተት ጎዳና የሚያቀርበንና፥ ነገ ላይ ለሚመጣው ትልቅ ውድቀት መንገድ ከፋች ሆኖ ሊገኝ ይችላል። እኛ ክርስቲያኖች ጠላት አለን። ዲያቢሎስ የሚባል ጠላት አለን። ይሄ ጠላታችን የሚመጣው ደግሞ፥ እኛ እንደምናስበው በምንፈራቸው ነገሮች ውስጥ አይደለም። በምንፈራቸው ነገሮች ውስጥ ቢመጣማ፣ ቶሎ ሮጠን እናመልጣለን። የሚመጣው፥ በምንወዳቸው፥ እኛን ሊስቡን በሚችሉና ጊዜያዊ ደስታ ሊሰጡን በሚችሉ ነገሮች ውስጥ ነው።
ሌላው በጣም የሚገርመኝ፥ ሳምሶን ከደሊላ ጋር የነበረው ግንኙነት ነው። ደሊላ እስራኤላዊ አይደለችም። ፍልስጥኤማዊ ናት። የእግዚአብሄር ህዝብ ጠላቶች ወገን ናት። ማለትም በሌላ አማርኛ፥ ሳምሶን የፍቅር ግንኙነት ውስጥ የገባው ከጠላቱ ጋር ነው። ይሄ ነገር ሁሌ ይገርመኛል። ከጠላት ጋር ወዳጅነት። እግዚአብሄር “ጠላት ነው” ካለው ወገን ጋር ወዳጅ ለመሆን መሞከር። እንዴት ያለ አደገኛ ጨዋታ ነው! ሳምሶን ሀይሉ የሚደክምበትንና እንደ ማንኛውም ተራ ሰው ሊሆን የሚችልበትን ከፍተኛ የሆነ ሚስጥር ያጫወተው፥ ለጠላቱ ነው። ከዚህ ብዙ ነገሮችን እንደምንማር አስባለሁ። የሆነን ሰው ልውደደው እንጂ እግዚአብሄር ፍቅር ስለሆነ፥ ፍቅር ሁሉ ከእግዚአብሄር ነው ብለን የምናምን ሰዎች ካለን፣ ከሳምሶን ህይወት በላይ ሊያስተምረን የሚችል ነገር ያለ አይመስለኝም። ልባችንን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ፥ ህይወታችንን ወዳልፈለግነው አቅጣጫ ሊወስድ የሚችል ስሜት ውስጥ ከመግባታችን በፊት፥ ያ ሰው ማን እንደሆነ በደምብ ማሰብና መጸለይ መልካም ነው። ሳምሶን ወዳጅነት የጀመረው ከጠላቱ ጋር ነው። ማለትም እሱ እስራኤላዊ፥ የኪዳን ህዝብ የእግዚአብሄር ህዝብ ወገን ሲሆን፣ ፍቅር የጀመረው ደግሞ ከእግዚአብሄር ህዝብ ጠላቶች ወገን ጋር ነው። አሁን ዋናው የሳምሶንና የደሊላ ፍቅር አይደለም። ዋናው፥ ህይወታቸው የሚመራበት አምላክ ጠላትነት ነው። እሱ በሚያመልከው አምላክና እሷ በምታመልከው ጣኦት መካከል ያለው ጠላትነት ነው። ነገሩ ለእነርሱ በተለይም ደግሞ ለሳምሶን፥ ፍቅር ይምሰል እንጂ፣ ነገሩ በሙሉ፥ ስውር የጠላት እጅ ያለበት መንፈሳዊ አሰራር ነበር። ወጥመድ ነበር። እዚህ ነገር ውስጥ፥ ምንም አይነት ፍቅር የለም። ፍቅርማ እግዚአብሄር ነው። የእግዚአብሄር ፍቅር ደግሞ፥ ከፈቃዱና ከሀሳቡ ውጪ ሊሰራ አይችልም። በጊዜው፥ ሳምሶንን ሄዳችሁ “ይሄ ነገር ሳምሶን፥ ፍቅር አይደለም ወጥመድ ነው” ብትሉት እሱ በጊዜው ስለ ደሊላ ይሰማው ከነበረው ከፍተኛ የሆነ የፍቅር የሚመስል ስሜት ተነስቶ፥ ምናልባት ሊጣላችሁ ይችላል። ፍቅር ግን በስሜት ውስጥ ሊገለጥ ይችላል እንጂ ስሜት አይደለም። መጽሀፍ ቅዱስ ፍቅር ብሎ ሊያስተምረን በአንደኛ ቆሮንቶስ 13 ላይ ሲጀምር፥ በፍቅር ውስጥ ስለሚገለጡት ባህሪያቶች ጻፈ እንጂ፥ ፍቅር ሲይዘን ሊሰሙን ስለሚችሉት የስሜት አይነቶች አልዘረዘረም። ፍቅር ታጋሽ ነው፣ ይቅር ባይ ነው፥ ፍቅር ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል አለ። ፍቅር ከእውነት ጋር ወይንም ከእግዚአብሄር ቃል ጋር ይደሰታል፣ ከእግዚአብሄር ሀሳብና ፈቃድ ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ከአመጻ ጋር፥ ከእግዚአብሄር ፈቃድ ተቃራኒ ከሚሄዱ ነገሮች ጋር፥ በፍጹም አይደሰትም። ምን ጊዜም ስለ ፍቅር ስናስብ፥ ይሄ ነገር እውነተኛ ፍቅር ነው ወይንም አይደለም የማለት መስፈርታችን፥ የእግዚአብሄር ቃል እንጂ የሚሰሙን ስሜቶች መሆን የለባቸውም። ስሜቶቻችንን ብቻ እየተከተልን ከሄድንማ፥ መጨረሻ ላይ እራሳችንን ገድል ውስጥ እንደምናገኘው መጠራጠር የለብንም። ይሄ እኛ ፍቅር እያልን የምንጠራው ጠንካራ ስሜት፥ ሰይጣን የብዙ ሰዎችን፥ በተለይም የብዙ የተቀቡና ለእግዚአብሄር የተለዩ ሰዎችን ህይወት ገደል የከተተበት ዋነኛ መሳሪያው ነው። በፍቅር ስም፥ ስንትና ለብዙ ህዝብ ሊተርፍ የሚችል ጸጋቸው የተላጨ ብዙ ሰዎች አሉ። ሳኦልም ልጁን ሚልኮልን ወጥመድ ትሆነው ዘንድ ለዳዊት ሰጠው ብሎ መጽሀፍ ቅዱስ እንደሚነግረን በትዳር ስም ስንት አይነት ዘመናቸውን የሚያለቅሱበት ወጥመድ ውስጥ ሰይጣን የከተታቸውን ሰዎች እኔ በግሌ አውቃለሁ። እግዚአብሄር አላማችንን ለማገልገል እርዳታ እንድናገኝበት የሰጠንን በረከት ወይንም ትዳር፥ ሰይጣን የአገልጋዮችን ህይወት ለማጥመድ ሲጠቀምበት አይቻለሁ። ስለዚህ እንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ ስንገባ፥ በብዙ ማስተዋልና ጥንቃቄ የእግዚአብሄርን ድምጽና ምሪት እየተከተልን መሄዳችን፥ ህይወታችንን ከብዙ ጸጸት ሊያድን እንደሚችል፥ የሳምሶን ውድቀት ያስተምረናል።
ከሳምሶን ህይወት ሌላው የሚገርመው ነገር፥ በተለያየ ስህተት ውስጥ እራሱን ያስገኘ ቢሆንም፥ እስከ መጨረሻው አይኑ እስከወጣበት ደቂቃ ድረስ፥ የእግዚአብሄር መንፈስ በእርሱ ላይ መስራቱን አለማቆሙ ነው። አንድ ናዝራዊ ሰው ሊያረግ የማይገባውን ነገር እያረገም፥ እግዚአብሄር በህይወቱ ይሰራ ነበር። ራሱን ሊያስገኝ በማይገባው ቦታዎች እያስገኘም፥ የእግዚአብሄር መንፈስ በእርሱ ላይ በሀይል ይመጣ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ህይወታችን፥ በስህተት መንገድ እየሄደ ቢሆንም፥ እግዚአብሄር ሊያገለግል ስለወደደው ስለ ህዝቡ ሲል፥ በህይወታችን መስራቱን ይቀጥላል። የእግዚአብሄር ስራ በህይወታችን መቀጠል ግን፥ የህይወታችንን ትክክለኛ አካሄድ ላያረጋግጥ ይችላል። ሁልጊዜ መርሳት የሌለብን፥ እግዚአብሄር ህይወታችንንና አገልግሎታችንን የሚመዝናቸው ለያይቶ እንደሆነ ነው። እግዚአብሄር በአገልግሎቶቻችን ውስጥ በሚገለጠው ጸጋ አይደነቅም:: ዋው አይልም። ምክኒያቱም ስጦታውም ጸጋውም የእርሱ የራሱ ነው። ሀይሉም ብርታቱም፣ የእርሱ የራሱ ነው። ነገር ግን በህይወታችን አካሄድ፣ እሱን ልናስደስተው በምንከፍላቸው ዋጋዎች ግን ይደነቃል። እግዚአብሄር ልክ እንደ እኛ እንደ ሰዎች፥ በአገልግሎታችን ታዋቂነትና አስደናቂነት ራሱን እየነቀነቀ አይደነቅም። “ዛሬ መቼም የሚገርም ዝማሬና ሙዚቃ ነው ያቀረቡልኝ” አይልም። ስለ ዝማሬ ካወራን ሺ ጊዜ ሺ፥ እልፍ ጊዜ እልፍ የሆኑ መላእክቶች ሀያ አራት ሰአት በትጋትና በብዙ መንቀጥቀጥ የሚያመልኩት አምላክ ነው። የእኛን ዝማሬ ለመስማት ቢመጣ፥ እንዲሁ ከራሱ ማንነት የተነሳ ወዶና አክብሮን እንጂ፥ ዝማሬዎቻችን የክብሩን ጫፍ እንኳን መግለጥ ስለቻሉ ተገርሞ አይደለም። ስለዚህ ብዙ አገለገልን፥ ህዝቡን በአገልግሎታችን አስደነቅን ማለት፥ ህይወታችን በትክክል እየሄደ ነው ማለት ላይሆን ስለሚችል፥ አገልግሎታችንን ወደ ጎን እያስቀመጥን፥ ህይወታችንን በየጊዜው በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ መመርመር በጣም መልካም ነው።
የሳምሶን ህይወት በጠላቶቹ እጅ ብቻ ወድቆ አለቀ ብለን ብንዘጋው፥ ከህይወቱ ልንማር የሚገባንን ግማሹን ትምህርት እናጣዋለን ብዬ አስባለሁ። ከሁሉ በላይ ዘወትር የምገረምበት የእግዚአብሄር ምህረት፥ ሳምሶን አይኑ ቢጠፋም በህይወቱ ከገደላቸው ጠላቶቹ ይልቅ፥ እግዚአብሄርን አንዴ አስበኝ ብሎ ሲለምንና እግዚአብሄር በምህረቱ ውስጥ ሲያስበው የገደላቸው ጠላቶቹ ብዛት፥ የእግዚአብሄርን ምህረት ትልቅነት ያስረዳኛል። በእግዚአብሄር ምህረት በጣም እደነቃለሁ። በሳምሶን ውድቀት ውስጥ በተገለጠው በእግዚአብሄር ምህረት እደነቃለሁ። ሰው እንደሚፈርድ የማይፈርድብን፣ በብዙ ውድቀት ውስጥ እንኳን ብንሆን የሚራራልን አምላክ ነው። እግዚአብሄር በምህረቱ ባለጠጋ ነው። የምህረት ባለጠጋ ነው። የምህረት ሀብታም ነው። ብዙ ምህረት ያለው፥ በዙፋኑ ላይ ቁጭ ብሎ ለሚለምኑት ሁሉ ምህረቱን የሚሰጥ። በመስጠቱ ደግሞ እጅግ በጣም ደስ የሚሰኝ። አለማትን በቸርነቱ እየደገፈ፥ ፍጥረታትን ሁሉ በምህረቱ ውስጥ እያስወጣ የሚያስገባ። ያልጠፋነው ከምህረቱ የተነሳ እንደሆነ፥ አለመጥፋትን በምህረቱ ውስጥ ያደረገ። ምህረቱ ከህይወት ይሻላል ተብሎ እንደተጻፈ፣ ከብዙ ምህረቱ ውስጥ ህይወትን የወለደ፥ ህይወትን ያወጣ፥ የምህረት ባለጠጋ፣ የምህረት ሀብታም ነው እግዚአብሄር። ምህረት እኮ ለሀጢያታችን ብቻ የሚያስፈልገን ነገር አይደለም። በምህረትህ ወደ ቤትህ እገባለሁ ብሎ ባሪያው እንደተናገረ፣ ሀጢያት ውስጥ የሌለንበት መስሎ በተሰማን ሰአት እራሱ፥ ወደ እግዚአብሄር ቤት ለመግባት፣ የእግዚአብሄር መሰዊያ ላይ ለመቆም፥ ቅዱስ የሆነውን ስሙን ለመጥራት የእግዚአብሄር ምህረት ያስፈልገናል። ለመኖርና ለመተንፈስ፣ ላለመጥፋት የእግዚአብሄር ምህረት ያስፈልገናል። ተኝተን፣ በሰላም አድረን ጠዋት በማለዳ ስንነሳ፥ ከተኛንበት ያነቃንን የእግዚአብሄርን ምህረት ማመስገን አለብን። በሳምሶን የህይወት መጨረሻ ላይ ከበዛው የእግዚአብሄር ምህረት በመነሳት እንዲህ እላለሁ፣ በዚህ ሰአት በተለያየ የአለም ክፍል ሆናችሁ ይሄንን ጽሁፍ የምታነቡ ወይንም የምትሰሙ፣ እስከዛሬ እግዚአብሄርን ከበደላችሁበት ብቻ ሳይሆን በህይወት ዘመናችሁ ሁሉ ከምትሰሩት ስህተት ይልቅ የእግዚአብሄር ምህረት ይሰፋል። የእግዚአብሄር ምህረት ይበልጣል። እግዚአብሄር ለእኛ አለመራራት ወይንም ምህረትን ለለመኑት አለመስጠት አይችልም። ምክኒያቱ ደግሞ ማንነቱና ባህሪው ስላልሆነ ነው። “ወንድምህ ቢበድልህ “ሰባ ጊዜ ሰባት” ማለትም አራት መቶ ዘጠና ጊዜ ይቅር በለው” ብሎ ያዘዘን አምላክ፥ እኛ ደጋግመን እንኳን በበደል ውስጥ ብንገኝ፥ ይቅር አለማለት ያስችለዋል? እግዚአብሄር የራሱን ስም ለሙሴ አውጃለሁ ብሎ በተነሳ ጊዜ፣ ካሉት ባህሪያቶች ሁሉ ስሙን “እግዚአብሄር እግዚአብሄር መሀሪ፣ ሞገስ ያለው ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ አበሳንና መተላለፍን ሀጢአትንም ይቅር የሚል” ብሎ በስሙ ውስጥ ያለውን ቸርነትና ምህረት አላወጀም? በእግዚአብሄር ምህረት በፍጹም ተስፋ አይቆረጥም። ከማረን በኋላ ደግሞ፥ ያለፈውን ስህተታችንን ማስታወስ የሚወደው ሰይጣን ብቻ ነው። እግዚአብሄር አንድ ብሎ እንደገና ይጀምራል እንጂ፥ ባለፈው ስላረጉት ዛሬም በተመሳሳይ ሁኔታ ያሳዝኑኛል ብሎ ልቡን አይጠብቅም። ስናሳዝነውም ያሁኑን ስህተታችንን ከትላንትናው ጋር አይደምረውም። እግዚአብሄር የምህረት ባለጸጋ፥ የምህረት ሀብታም ነው።