Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

የተፈጠርኩበትን ዓላማ የማውቀው እንዴት ነው?

የተፈጠርኩበትን ዓላማ የማውቀው እንዴት ነው?

ብዙ ሰው በህይወቱ መጨረሻ ቁጭቶች ይኖሩታል። ማድረግ ነበረብኝ ወይንም አልነበረብኝም የሚላቸው ነገሮች ይበዛሉ። በመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ፥ በእድሜው መጨረሻ ህይወቱን ዞር ብሎ አይቶ የእርካታና የደስታ ንግግር ከተናገሩ ሰዎች መካከል አንዱ ጳውሎስ ነው። 

“መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፥ ሩጫውን ጨርሻለሁ፥ ሀይማኖትን ጠብቄያለሁ፥ ወደ ፊት የፅድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል ይህንም ፃድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል“ (2ኛ ጢሞ 4፡7)

ጳውሎስ በነበረበት ዘመን የተማረ እና ብዙ ሊመካባቸው የሚችላቸው የህይወት ስኬቶች የነበሩት ሰው ቢሆንም፥ በህይወቱ መጨረሻ  ያገኘው ይሄ እርካታ ግን ከምድራዊ ስኬቶቹ ጋር የተያያዙ አልነበሩም። ይልቁንም ከእናቱ ማህፀን ጀምሮ እግዚአብሄር በህይወቱ ላለው አላማ እሱን መለየቱ፥ በፀጋው ውስጥ የደረሰው የአገልግሎት ጥሪ እና በህይወቱ ውስጥ እግዚአብሄር ልጁን ኢየሱስን ለሌሎች ሊገልጥ የወደደበትን አላማ በመረዳት ይሄን የተሰጠውን አላማ በመስዋእትነት በማገልገሉ ነው።  

የምንኖርባት ምድር ስኬትን ከብዙ አቅጣጫ ትርጉም ብትሰጠውም፥ በእግዚአብሄር እይታ ስኬታማነት ማለት እግዚአብሄር የፈጠረንን አላማ መረዳት እና ያንን አላማ በሚመጥን የህይወት አካሄድ እና በሙሉ ትጋት አገልግሎ ማለፍ ነው። ሰው ይሄንን ሲረዳና በህይወቱ ተግባራዊ ሲያደርገው ነው ትክክለኛ የሆነውን የህይወት ትርጉምና እርካታ ማግኘት የሚጀምረው። 

በባለፈው ክፍል ፅሁፋችን ውስጥ የዓላማን ምንነት ለማየት ሞክረን ነበር። ዓላማ ማለት እግዚአብሄር እኛን ከመፍጠሩ በፊት ስለ እያንዳንዳችን ህይወት ልቡ ውስጥ የነበረ ሀሳብ ማለት ነው። እግዚአብሄር እንደ ልቤ ያለው ሰው ዳዊት የዚህ ምድር ቆይታውን ስኬታማ ያስባለው፥ በራሱ ዘመን የእግዚአብሄርን ሀሳብ አገልግሎ ማለፉ ነው።

እንግዲህ የእግዚአብሄር ቃል እንደሚናገረው፥ የስራ ድርሻችን ይለያይ እንጂ፥ እያንዳንዳችን በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ አብረን ሰራተኞች ልንሆንና የክርስቶስ አካል ልንሆን ነው የተጠራነው። አካልን ዝም ብላችሁ ስታዩት አገልግሎት የማይሰጥ ክፍል የለውም። እያንዳንዱ የአካል ክፍል አገልግሎት የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ለሚያገለግልበት የአገልግሎት ክፍል ተስማሚ ቦታና ቅርፅ  እንዲኖረው ተደርጎ ነው የተሰራው። እጅን ስታዩት ዓላማው መስራት ስለሆነ ልክ አንደ አፍንጫ እና ጆሮ አጭር ተደርጎ አልተሰራም። አይን ፊት ለፊት ስለሆነ ነገሮችን ቶሎ ማየት ይችላል። ሌላው ቀርቶ፥ ቅንድብ እራሱ እኛ እህቶች በርካታ ለሆኑ አገልግሎቶች እናውለው እንጂ ዋና አላማው አይንን ከአቧራ እና ከላብ መጠበቅ ነው። አፍንጫ በመተንፈስ ስለሚያገለግል ለአካሉ የጎላ ጠቀሜታ አለው። ጆሮ ይሰማልናል። እጅ ሰራተኛ ነው፥ እግርም እንዲሁ ወደሚያስፈልገው ስፍራ በመሄድ አካሉን ያገለግላል። የእግዚአብሄር ቃል በአካል የመሰለን፥ የአካል ክፍል  ቅርፅ እና ስራ እንደሚለያይ ሁሉ የተለያየ የተፈጥሮ ባህሪ እና የስራ ድርሻ ቢኖረንም፥ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ሁላችንም ሰራተኞች እና አገልጋዮች እንደሆንን ለማስገንዘብ ነው። 

“እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን።” (ኤፌሶን 2፡10)

አላማን ማወቅ ማለት ባለንበት የክርስቶስ አካል ውስጥ የትኛውን የአካል ክፍል ሆነን ለማገልገል እንደተጠራን ማወቅና መረዳት ነው። ለምሳሌ ብንወስድ፥ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ አንደበት የሆኑ ሰዎች አሉ። ቦታቸው መድረክ ነው። እነዚህ በእግዚአብሄር አደባባዮች ላይ የሚቆሙ የእግዚአብሄር አንደበቶች ናቸው። አስተማሪዎች፥ ሰባኪዎች፥ ወንጌላውያን፥ እንዲሁም የቤተክርስቲያን መሪዎች ናቸው። ያስተምራሉ፥ ይገስፃሉ የእግዚአብሄርን ህዝብ ያገለግላሉ። ጳውሎስ እና አብዛኞቹ ሀዋሪያት በዚህ አገልግሎት ውስጥ አገልግለው አልፈዋል።

በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ አይን ወይንም ጆሮ ሆነው የሚያዩና የሚሰሙ ሰዎች ደግሞ አሉ። ሊመጣ ያለው ነገው ይታያቸዋል ህልምን ወይንም ራእይን አይተው በመናገር የእግዚአብሄርን ህዝብ ያፅናናሉ ወይንም ሊመጣ ካለው ክፉ ነገር ህዝቡን/ልጆቹን ለማስመለጥ እግዚአብሄር ይጠቀምባቸዋል። እነዚህ፥ የጊዜውን የእግዚአብሄርን ሀሳብ የሚያመጡ ነቢያቶች ናቸው። ሙሴ፥ ሳሙኤል፥እምባቆም፥ ኤርምያስ እና ሌሎችም ብዙ የነቢያት ምሳሌዎች በቃሉ ውስጥ ተጠቅሰውልናል። 

እንደ እጅ በመሆን የማገልገል ጥሪ ያላቸው ሰዎች ደግሞ አሉ። ብዙ ጊዜ መድረኮች ላይ ባናያቸውም ግን የትጋት መንፈስ ያለባቸው ለእግዚአብሄር መንግስት ይሄ ነው የማይባል ሚና የሚጫወቱ ሰራተኞች ናቸው። ይሄ በ1ኛ ቆሮ 12፡28 ላይ ከተዘረዘሩት የፀጋ ስጦታዎች ውስጥ “እርዳታ” በማለት አንድ ራሱን የቻለ የፀጋ ስጦታ እንደሆነ መፅሀፍ ቅዱስ ፅፎልናል። እነዚህ ሰዎች ቁጭ ብሎ ከመስተናገድ ይልቅ ማስተናገድ የሚያስደስታቸው፥ በእግዚአብሄር ቤት ውስጥ ለብዙ ሰው የማይታየው የጎደለ ነገር የሚታያቸውና የጎደሉ ቦታዎችን በመሙላት የሚያገለግሉ ናቸው። ይሄ ስጦታ ያላቸው ሰዎች፥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ካላቸው የጠበቀ ህብረት የተነሳ፥ በመንፈስ በመመራትና ሰዎች ቤት ድረስ በመሄድ የሚያፈልጋቸውን ነገር ሲያደርጉ አይቼ አውቃለሁ።  

“….እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ። “ (1ኛ ጴጥ 4፡10) 

ከላይ የተጠቀሱትን ጥቂት አገልግሎቶች ለምሳሌነት አየን እንጂ፥ በውስጣችን  እንደ ልብ፥ ኩላሊት እና ሌሎችም የማናያቸው፥ ነገር ግን አካል ቆሞ ለመሄዱ ወሳኝ የሆኑ የአካል ክፍሎች እንዳሉት ሁሉ፥ ፊት ለፊት የማናያቸው ነገር ግን በጣም አስፈላጊ የሆነ አገልግሎት ያላቸው ሰዎች በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ አሉ። ማስተዋል ያለብን ግን፥ አገልግሎት ቤተክርስቲያን ውስጥ ወይንም መድረክ ላይ ብቻ አለመሆኑን ነው። አገልግሎት በጣም ልዩ ልዩ ነው። መፅሀፍ ቅዱሳችንን ስናጠና፥ የእግዚአብሄርን ቤት ለመስራትና ለመገንባት እግዚአብሄር የጥበብ፥ የእውቀትና የማስተዋልን መንፈስ ያፈሰሰባቸው ሰዎች ነበሩ። (ዘፀ 31፡1-11) ሰዎችን የመምከር ስጦታ የነበራቸው ሰዎች ነበሩ፥ በመስጠት ያገለገሉ ሰዎች ነበሩ፥ እግዚአብሄር የጥበብንና የእውቀትን ስጦታ የሰጣቸው እንዲሁም በሌሎች የተለያየ አገልግሎቶች ውስጥ አገልግለው ያለፉ ሰዎች ነበሩ።

“የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።” (1ኛ ቆሮ 12፡4)

የተሰጠን የፀጋ ስጦታ ወይንም መክሊት አስር ሊሆን ይችላል። ደግሞም አንድ ሊሆን ይችላል። የተጠራነው ለጥቂት ሰው ሊሆን ይችላል፥ ደግሞም ለብዙ ህዝብ ሊሆን ይችላል። ዋናው ግን የተጠራንበትን ትክክለኛ ቦታ ማወቅ እና በዛ ቦታ ላይ በታማኝነትና በትጋት ማገልገል ነው።

የግል አላማዬን የማውቅባቸው መንገዶች ምንድናቸው? 

1፥ አላማችንን ብዙ ጊዜ ግርግርና ጫጫታ ውስጥ አናገኘውም።  እኛን ወደ ትክክለኛው የህይወት አቅጣጫ ለመምራት፥ በፀጥታ ውስጥ የሚፈሰውን የእግዚአብሄርን ድምፅ ለመስማት ወደ ፀጥታ ቦታዎቻችን መግባትን መለማመድ ይኖርብናል። ያ የፀጥታ ቦታችን የመኝታ ክፍላችን ሊሆን ይችላል፣ መኪናችን ሊሆን ይችላል፣ ለብቻችን የምናደርገው የእግር መንገድ ጉዞ ሊሆን ይችላል፣ ወደ ተፈጥሮአዊ ቦታዎች መሄድ ሊሆን ይችላል፥ ለእኛ የሚመቸንን ቦታ መርጠን ያንን ከእግዚአብሄር ጋር ጊዜ የማሳለፊያ ቦታ ልናረገው እንችላለን። ስህተቶቻችንን ለማስተዋል፣ ትክክለኛ የሆኑ የህይወት ውሳኔዎችን ለመወሰን እንዲሁም ወደ አላማችን የሚመራንን የእግዚአብሄርን ድምፅ ለመስማት እድል የሚሰጡን የፀጥታ ቦታዎቻችን ናቸው። የፈጠረን ከአላማ ጋር ከሆነ እኛን ከመፍጠሩ በፊት ልቡ ውስጥ የነበረውን ትክክለኛ ሀሳብ ሊነግረን የሚችለው እግዚአብሄር እራሱ ነው። ይሄ ደግሞ ለእኛ የሚታወቀው ከእሱ ጋር በምናሳልፋቸው ጊዜያቶች ውስጥ ነው። ድምፁን ወደ እኛ በመላክ ወይንም ልባችንን ወደ ፍቃዱ በመምራት አላማችንን ያስታውቀናል። 

2፥ ሁልጊዜ ልባችንን የሚሞላው ስራ ወይም አገልግሎት ምንድነው? ዙሪያችን ባሉ ድምፆች ወይም ግርግሮች ተሸፍኖብን ይሆናል እንጂ፥ የሆነ ጠንካራ መሻት ልባችን ውስጥ አለ። በጎ ፈቃዱን በህይወታችን ለማድረግ ሲል እግዚአብሄር በውስጣችን ያስቀመጠው ፍላጎት አለ። ወይንም ደግሞ፥ በሆነ ነገር ዙሪያ ከሌሎች የተሻለ አቅም ውስጣችን አለ። ያንን ለማወቅ ጊዜ ሰጥቶ ራስን መስማት በጣም አስፈላጊ ነው። የምንኖረው ህይወት ወይንም የምንሰራቸው ስራዎች ደስታንና እርካታን እየሰጡን ካልሆነ፥ ቆም ብለን “እግዚአብሄር የጠራኝን ነገር ነው ወይ እያደረኩ ያለሁት?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ምክኒያቱም  አንዳንድ ጊዜ ለምናገኛቸው ጊዜያዊ ጥቅሞች ብለን የእኛ ያልሆኑና ለህይወታችን የእግዚአብሄር ሀሳብ የሌለባቸው ቦታዎች ውስጥ ዘመናችንን ልንጨርስ እንችላለን። 

3፥ ስናደርገው ሰዎች የሚጠቀሙበት ነገር ምንድነው? በተደጋጋሚ ሰዎች የሚሰጡንን አስተያየቶች ማስተዋል የአገልግሎት ቦታችንን ለማወቅ ከሚያግዙን ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው። እግዚአብሄር ፀጋዎችን በውስጣችን የሚያስቀምጥበት ዋነኛ አላማ ሌሎችን ለማገልገል ስለሆነ እኛ ስናደርገው ሰዎች እንደተጠቀሙ የነገሩን ተደጋጋሚ አስተያየቶች ካሉ፥ ያንን ማስተዋል፥ ስለዚያ ነገር መፀለይና የእግዚአብሄርን ምሪት መፈለግ መልካም ነው። 

በመጨረሻ እኔም እራሴ የተጠቀምኩበት እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች አካፍዬው በውስጣቸው የተቀመጠውን የፀጋ ስጦታ እንዲያስቡ የጠቀማቸውን የYoutube video share አረጋችኋለሁ። እንደሚረዳችሁ እምነት አለኝ። 

https://www.youtube.com/watch?v=-NXft0yyWT8&t=3037s 

alisa-anton-u_z0X-yrJIE-unsplash.jpg
How do I know the will of God in my romantic relationship?

How do I know the will of God in my romantic relationship?

አላማ

አላማ