አላማ
አንዳንድ ጊዜ፥ የሰው ልጆችን ህይወት ቆም ብላችሁ ብታስቡት፥ በተመሳሳይ ነገሮች የተሞላ ነው:: ሰው ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይማራል፣ ያገባል፣ ይወልዳል፣ ለኑሮው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ይሞክራል፣ እድሜ ከሰጠው ኖሮ፥ ካልሰጠውም ደግሞ በጊዜ ወደ አምላኩ ይሄዳል። ይሄ፥ የአብዛኛው ሰው ህይወት የሚያልፍበት ስርአት ነው። የየትኛውም ሰው ህይወቱ፥ ከዚህ ተመሳሳይ ድግግሞሽ አያመልጥም:: እግዚአብሄር የጥበብን መንፈስ የሞላበት ሰው ጠቢቡ ሰለሞን ህይወትንና የሰው ልጆችን እንቅስቃሴ ሁሉ አስተውሎ ከተመለከተ በኋላ ያለው ነገር ይገርመኛል:: “... ከንቱ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ሁሉ ከንቱ ነው…” (መክብብ 1፡2)
ታዲያ ይሄ ድግግሞሽ የሞላበትን የሰው ልጆች እንቅስቃሴ ቆም ብላችሁ ስታስቡት፥ “የህይወት ትርጉሙ ታዲያ ምንድነው?” ብላችሁ አስባችሁ አታውቁም? ሁሉም ሰው የሚያረገውን አድርጌ፥ ሁሉም ሰው የደጋገመውን ደጋግሜ ለመሞት ነው የተፈጠርኩት? የመፈጠሬ ትርጉሙ ምንድነው? የተፈጠርኩበት ዓላማው ምንድነው ብላችሁ ጠይቃችሁ አታውቁም? ይሄንን አስፈላጊ ጥያቄ ለመመለስ ይረዳን ዘንድ፥ እስኪ በአንድ ጥሩ ምሳሌ እንጀምር።
አንድ ሸክላ ሰሪ፥ ቡና የሚያፈላበትን እቃ መስራት ቢፈልግ፥ የሚሰራው ጀበናን ነው። ይሄንን ጀበና ለመስራት የሚያነሳሳው፥ ቡና ለማፍላት ያለው ፍላጎቱ ነው። ስለዚህ ይሄንን ጀበና የሚሰራበት ምክኒያት አለው ማለት ነው። በሌላ አማርኛ ደግሞ፥ ቡና የሚያፈላበት እቃ ባያስፈልገው፥ ይሄንን ጀበና አይሰራውም። ለሰራው ጀበናም የሚሰጠው ቅርፅ፥ ቡና ለማፍላት የሚያመቸውን ቅርፅ ነው:: እንግዲህ ይሄ ጀበና የተፈጠረበትን አላማ አሳክቷል የሚባለው፥ በዘመኑ ሁሉ ቡና በማፍላት የሰራውን ሰው ሲያገለግል ነው::
ሸክላ ሰሪ፥ አንድ ህይወት የሌለውንና ከጭቃ የሚሰራውን ጊዜያዊ እቃ ለመስራት ምክኒያትና አላማ ካስፈለገው፥ በራሱ ምስልና እስትንፋስ ህያው አርጎ የፈጠረውን ሰው፥ እግዚአብሄር እንዴት ያለ ምክኒያት ይፈጥረዋል? እንዴትስ ያለ አላማ ይፈጥረዋል? እግዚአብሄር እኮ የአላማ አምላክ ነው:: የሚያደርገውን ሁሉ የሚያደርገው ከዘላለም ሀሳቡ አንፃር ነው:: ጊዜ ለማባከን ወይንም ሰአት ለመግደል ብሎ ማንንም አይፈጥርም:: ሰማይና ምድርን እንዲሁም እስትንፋስ የሌላቸውን ግኡዝ ፍጥረታት እንኳን የፈጠራቸው ክብሩን ሊናገርባቸው ነው::
“ሰማያት የእግዚአብሄርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ስራ ያወራል።” (መዝ 19:1)
አላማ ማለት፥ እግዚአብሄር እያንዳንዳችንን ከመፍጠሩ በፊት ልቡ ውስጥ የነበረ ሀሳብ ማለት ነው:: አላማ ማለት፥ እግዚአብሄር እያንዳንዳችንን ለመፍጠር ያነሳሳው ምክኒያት ማለት ነው:: ከፈጠረን በኋላ አይደለም አላማችንን የወሰነው:: ዓላማችንን ከፈጠረ በኋላ ነው የእኛን መፈጠር የወሰነው:: ዓላማችን ነው ቀድሞ የተፈጠረው:: ለዛ ነው እግዚአብሄር ኤርምያስን “በሆድ ሳልሰራህ አውቄሀለሁ፥ ከማህፀንም ሳትወጣ ቀድሼሀለሁ፥ ለአህዛብም ነቢይ አድርጌሀለሁ” (ኤርምያስ 1፡5) በማለት፥ ገና ሳይፈጥረው በፊት እንዳወቀውና፥ ከእናቱ ማህጸን እንኳን ሳይወጣ፥ በነቢይነት አገልግሎት እንዲያገለግል መወሰኑን እግዚአብሄር አስቀድሞ የተናገረው። እንዲሁም ከብሉይ ኪዳን የሳምሶንን፥ ከአዲስ ኪዳን ደግሞ የመጥምቁ ዮሀንስን ታሪክ ብንወስድ፥ ገና ከማህፀን ሳይፈጠሩ፥ እግዚአብሄር አስቀድሞ በእነርሱ ህይወት ውስጥ ያለውን አላማ ነው ለወላጆቻቸው የነገራቸው:: እኛንም እያንዳንዳችንን እንዲሁ፥ አለም ሳይፈጠር፥ እግዚአብሄር በልጁ በክርስቶስ ለራሱ አላማ ወስኖናል:: (ኤፌሶን 1:4) እግዚአብሄር፥ እኔን ከመፍጠሩ በፊት፥ በእኔ ህይወት ሊሰራ ያሰበውን ዓላማ ነው የፈጠረው:: እስኪ ቆም ብላችሁ ለራሳችሁ፥ ይሄንን አስደሳች እውነት ንገሩት:: ወንድሜ፥ እግዚአብሄር አንተን የፈጠረበት ልዩ የሆነ አላማ አለው። ህይወትህ ትክክለኛውን ትርጉምና እርካታ ማግኘት የሚጀምረው፥ ይሄንን እውነት መረዳት ስትጀምር ነው። እህቴ፥ እግዚአብሄር አንቺን የፈጠረበት ልዩ የሆነ አላማ አለው። ህይወትሽ ትክክለኛውን ትርጉምና እርካታ ማግኘት የሚጀምረው፥ ይሄንን እውነት መረዳት ስትጀምሪ ነው።
“ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ።” (መዝ 139̏፡16)
እንግዲህ እያንዳንዳችን በዚህች አጭር የምድር ቆይታችን፥ እግዚአብሄር እኛን ከመፍጠሩ በፊት ልቡ ውስጥ የነበረ፥ አገልግለነው እንድናልፍ የሚፈልገው የተለየ ስራ አለ ማለት ነው:: እግዚአብሄር ከዘላለም ሞት ያዳነንና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የመረጠን፥ አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ስራ እንድንሰራ ነው:: ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ሊያገለግል እንደነበረ ሁሉ፥ እኛም ወደ ምድር የመጣነው ለአገልግሎት ነው:: ለስራ ነው:: እግዚአብሄር በህይወታችን ውስጥ ያለውን ልዩ ሀሳብ ለማገልገል ነው:: አላማን ማወቅ፥ ለስራና ለአገልግሎት እንደተፈጠርን ከመረዳት ይጀምራል። ስራ አለብን። ሌሎች ትርፍ እና አላማ ተኮር ያልሆኑ ነገሮችን ለማድረግ ጊዜ የለንም!
“እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን።” (ኤፌሶን 2፡10)
የአላማ ሌላው ትርጉሙ፥ “እግዚአብሄር ህይወታችንን የሚመራበት የእግዚአብሄር ስርዓት ማለት ነው::” በህይወታችን ውስጥ ካየነው፥ እንዲሁም በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ በተለያዩ ቦታዎች ካነበብናቸው የእግዚአብሄር ባህሪያቶች እንዱ መሪነቱ ነው። እግዚአብሄር መሪ ነው። ህዝቡን ይመራል። ልጆቹን ይመራል። ወደ ሀሳብና ወደ ፈቃዱ ይመራል። የእግዚአብሄርን ፈቃድ በየእለቱ መለማመዳችን አስፈላጊ እንደሆነ ሆኖ፥ አጥብቀን የእግዚአብሄርን ፈቃድ የምንፈልግባቸው ጊዜያቶች ህይወቶቻችን ላይ አሉ። ትልልቅ የህይወት ውሳኔዎችን ለመወሰን ስንነሳ፣ የምናገባውን ሰው ለመወሰን ጊዜው ሲደርስ፣ ሀገር ወይንም ስራ ለመቀየር ስናስብ፣ አገልግሎት ለመቀየር ስንፈልግ እና በመሳሰሉት ከህይወታችን ጋር በተያያዙ ጉዳዮቻችን ውስጥ የእግዚአብሄርን ፈቃድና ምሪት አጥብቀን በምንፈልግባቸው ጊዜያቶች እግዚአብሄር እነዚህን ጥያቄዎቻችንን የሚመልሰው፥ ህይወታችን ላይ ካለው አላማና ስለ ህይወታችን ከጻፈው ዘላለማዊ ሀሳቡ ተነስቶ ነው። ለጥያቄዎቻችን የሚሰጠን መልሶች በሙሉ ወደ አላማዎቻችን የሚመሩን ናቸው:: የሚመራን፣ በውስጣችን ያስቀመጠውን አላማ ለማገልገል ወደሚረዳን ትዳር ነው። የሚመራን፣ በውስጣችን ካስቀመጠው አላማ ጋር ተዛምዶ ወዳላቸው ቦታዎች ነው። የሚመራን፣ በህይወታችን ያለውን ዘላለማዊ ሀሳብ ወደምናገለግልባቸው አገልግሎቶች ነው።
አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሄር መልሶች ወይንም ህይወታችንን የሚመራባቸው መንገዶች ለጊዜው የማይገቡን ለዚሁ ነው። እግዚአብሄር አብርሀምን ከተወለደበትና 75 አመታቶች ሙሉ ከኖረበት ሀገር አውጥቶ የመራው፥ በህይወቱ ላይ ያለው አላማ ወደሚፈጸምበት የኪዳን ቦታ ነው። አብርሀም ግን በእምነት ታዘዘ እንጂ በጊዜው የእግዚአብሄር ሀሳብ ገብቶት አልነበረም። ባይገባውም፣ የሚሄድበትን ሳያውቅ የእግዚአብሄርን ምሪት አምኖ ወጣ። የእግዚአብሄር ምሪቶች ብዙ ጊዜ የማይገቡን፥ ህይወቶቻችን ላይ ካለው ዘላለማዊ ሀሳቦቹ ወይንም አላማዎቹ ጋር የተያያዙ ስለሆኑ ነው። ሀሳቡ ከሀሳቦቻችን፣ መንገዶቹ ከመንገዶቻችን ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እንዲሁ ከፍ ያሉ ናቸው:: የእኛ አካሄዶች ምድር እና ስሜት ተኮሮች ሲሆኑ፥ የእግዚአብሄር አካሄዶች ደግሞ ዘላለም እና አላማ ተኮሮች ናቸው:: በስሜት ተገፋፍቶ አይወስንም። ሀሳቡንም አይለዋውጥም:: አንድ ጊዜ ወስኖታል:: ዘላለማዊ አምላክ ስለሆነ ሀሳቦቹና አላማዎቹ ሁሉ ፅኑዎች ናቸው:: ይሄ ማንነቱ ደግሞ ዘላለም የታመነ እንዲሆን ያደርገዋል:: ባለመለወጡ ላይ ልባችን ሙሉ በሙሉ እንዲያርፍ እና እንድንደገፍበት ያደርገናል:: የክርስቶስን የምድር ቆይታ ካስተዋላችሁት፥ በእያንዳንዱ ቀን እና ሰአት፥ የመጣበት አላማ ላይ በማተኮር የተሞላ ነበር:: የሚሄድባቸው ቦታዎች፥ የሚሰራቸው ስራዎች፥ የሚቆይባቸውና ጊዜውን የሚያሳልፍባቸው ነገሮች በሙሉ፥ ከመጣበት አላማ ጋር በቀጥታ የተገናኙ ናቸው።
ይሄን የተፈጠርንበትን አላማ ስንረዳ፥ ጠባብ ከሆነ ምድራዊ አስተሳሰብ ተላቀን፥ ወደ ሰፊ ስፍራ እንወጣለን:: ነገሮችን ሁሉ እግዚአብሄር እንደሚያያቸው ከዘላለም አንፃር ማየት እንጀምራለን:: ብድራታችንን ወይንም እግዚአብሄር ያዘጋጀልንን ሽልማት ሁልጊዜ ስለምናስብ፥ ቅድሚያ የምንሰጠው የእግዚአብሄርን ሃሳብ ማገልገል እንጂ ጊዜያዊ ምቾት አይሆንም:: የተፈጠርንበትን አላማ በማገልገል ውስጥ መከራ ቢመጣ እንኳን ያንን መከራ የምናልፍበትን አቅም እናገኛለን::ኢየሱስንም የመስቀሉን መከራ እንዲታገስ ሀይል የሰጠዉ ከፊቱ ያለው ደስታ ነዉ:: (ዕብራውያን 12:1-2) ለምቾት ሳይሆን ለአላማ መኖር እንጀምራለን:: እግዚአብሄር በጠራን ቦታዎች ሁሉ ለመቆም ሀይል እናገኛለን::
እውነተኛውን የህይወት ሀሴትና እርካታ መለማመድ የምንጀምረው፥ የተፈጠርንበትን ምክኒያት ስናውቅ እና ያንን አላማ ስናገለግል ነው:: እውነተኛ ሰላማችን፥ ትክክለኛ ደስታችንና ሰማያዊ በረከቶቻችን ያሉት በዚህ ህይወት ውስጥ ነው:: አላማችንን ማወቅ ስንጀምር ብዙ ነገሮች ህይወታችን ላይ ትርጉም ሊሰጡን ይጀምራሉ:: የእግዚአብሄርን ሃሳብና ፈቃድ በማገልገል ውስጥ ያለውን በረከት መለማመድ እንጀምራለን:: ሰይጣንም የሚፈራው ዐላማ ይዞ የሚንቀሳቀስን ሰው ነው:: ለዛ ነው መፅሀፈ መሀልየ መሀልይ ምእራፍ 6፡10 ላይ “ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሰራዊት የምታስፈራ ማን ናት?” ያለው:: ይሄ ብቻ አይደለም ኸረ ዋናውን በረከት መቼ አወራነው! በምድር ላይ ካለ ነገር ሁሉ የሚበልጥ ሰማያዊ አክሊልና የዘላለም ደስታ ይጠብቀናል:: ጳውሎስ እንዳለው፥ በዚህች ምድር ከምናልፍበት መከራ ጋር ሊወዳደር የማይችል ሰማያዊ ክብር ተዘጋጅቶልናል:: አይን ያላየው፥ ጆሮ ያልሰማው በሰው ልብ ያልታሰበው፥ እግዚአብሄር ለሚወዱት ያዘጋጀውን ክብር ከእግዚአብሄር እጅ እንቀበላለን::
እግዚአብሄር ለግል ህይወቴ ያለውን አላማ ወይንም አገልግሎት የማውቀው እንዴት ነው? ብለን እንጠይቅ ይሆናል:: አላማችንን የምናውቅባቸውን መንገዶች በሚቀጥለው ክፍል እግዚአብሄር ቢፈቅድ እና ብንኖር አብረን እናየዋለን ብዬ አስባለሁ::
ስለ አላማ ጥቂት ነገር ካልን፥ ከአላማዎች ሁሉ በላይ ስለሆነው ትልቁ የእግዚአብሄር አላማ በጥቂት ቃላቶች ጥቂት ነገር እንበል። ከሁሉ ነገር በላይ፥ እግዚአብሄር እስትንፋስ ለሰጠው የሰው ልጆች በሙሉ ያለው የዘላለም አላማው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሀጢያት የከፈለውን ዋጋ በእምነት ተቀብሎ፣ ከሀጢያቱ እንዲድን ነው። ሰው ሁሉ ከሞት በኋላ ያለውን የዘላለም ህይወት እንዲወርስ ነው። ኢየሱስ ለሀጢያታችን የከፈለውን የመስቀል ሞት በማመን ብቻ የዘላለም ህይወት ይገኛል። ከሞት በኋላ ለዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር በደስታ መኖር ይቻላል። ለነፍሳችን እረፍት የሚሰጣት ይሄንን አምና የእግዚአብሄር ልጅ ስትሆን ብቻ ነው። ይሄ ፥ አምላክ ሰው በመሆን ራሱን ያዋረደበት ትልቁ የእግዚአብሄር ጥሪና አላማ ነው።
ለተጨማሪ ምክርና እርዳታ፥ hanaelias10@gmail.com ብለው በኢሜል መልእክት ቢጽፉልን፥ ለመርዳት ፈቃደኞች ነን።