Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

 መወደድ 

መወደድ 

በልጅነቱ እንደ እኔ ጨዋታ የሚወድ ሰው ያለ እስከማይመስለኝ ድረስ መጫወት በጣም ነበር የምወደው። ገና ከትምህርት ቤት ስንወጣ ልቤ የሚቸኩለው፥ ቶሎ ብዬ ቤት በመሄድ ልብሴን ቀይሬ ከሰፈር ጓደኞቼ ጋር አባሮሽ እስክንጫወትና ሩጫ እስክንወዳደር ነበር። ታዲያ ገና እኔና እህቴ ከትምህርት ቤት እንደገባን፥ እናታችን ከስራ ትመጣና ለእኔና ለእህቴ መስራት ያለብንን የቤት ስራ አከፋፍላን መሄድ ወዳለባት የማህበራዊ ህይወት ጉዳዮች ትሄዳለች። አብዛኛውን ጊዜ የእህቴ ስራ እቃ ማጠብ ሲሆን፥ የእኔ ስራ ደግሞ ቤቱን ማጽዳት ነው። “በቃ ቶሎ ቶሎ ሰርቼው ሄጄ ልጫወት” እልና ገና ቤቱን መጥረግ እንደጀመርኩ፥ የሰፈር ጓደኞቼ በአጥሩ በኩል ስሜን እየጠሩ ጊቢውን ይደባልቁታል። ድሮም ለመጫወት የቸኮለው ልቤ “በቃ ትንሽ ልጫወትና ቶሎ ተመልሼ እጨርሰዋለሁ” በማለት፥ ጓደኞቼን ለማግኘት ወደ ውጪ እሮጣለሁ። ከጓደኞቼ ጋር ስንሮጥ፣ ስንስቅ፣ ስንቀልድና ስንጫወት ቆይተን ቆይተን ልክ ቀኑ እየመሸ ሲመጣ፥ እናቴና የሰፈር ጎረቤቶቿ ነጭ ነጠላቸውን አንደለበሱ ሰፈር ውስጥ ከነበረ ለቅሶ ቤት ሲመለሱ ከሩቅ አያቸዋለሁ። “ወይኔ ስራዬን ሳልጨርስ እናቴ እየመጣች ነው” ብዬ በሩጫ ወደ ቤት በመመለስ የጀመርኩትን ቤት ጠርጌ ሳልጨርስ ውዷ እናቴ ትገባለች። “ቀጥ ብለሽ መኝታ ቤት ሄደሽ ጠብቂኝ” ማለት በእኛ ቤት አማርኛ፥ መኝታ ቤት ቁጭ ብለሽ እየመጣ ያለውን ዱላ ጠብቂ ማለት ነው። ዱላው ደግሞ እዛው መኝታ ቤት አልጋ ስር ስለሚቀመጥ፥ አንዳንድ ጊዜ ሰባብሬ ብጥለው እራሱ ደስ ይለኛል። በ4 አመት ከእኔ ታናሽ የሆነችው እህቴ ደግሞ በጣም በሚገርም ሁኔታ እንደ እኔ ጨዋታ የማያታልላትና የተሰጣትን ስራ ሳትሰራ የትም ቦታ ለመጫወት የማትሄድ ልጅ ነበረች። ኸረ አንዳንዴ እንዲያውም ስራውን እየሰራች ሳትጫወት ቀኑ ሊመሽባት ይችላል። አሁን ላይ ስለ ልጅነታችን ስናወራ ታዲያ፥ እህቴ የጨዋታ ጊዜዋን በአግባቡ ስላልተጠቀመችበትና መጫወት ባለባት ጊዜ ስላልተጫወተች ሲቆጫት እመለከታለሁ። “እንዴት ነው ታዲያ ጨዋታ ሊያታልልሽ በሚችልበት እድሜ ላይ ሆነሽ ስራን ልታስቀድሚ የቻልሽው?” ብዬ ስጠይቃት፥ የሰጠችኝ መልስ ይሄ ነው። “የተሰጠኝን ስራ ካልሰራሁ እናቴ የምትወደኝ አይመስለኝም። የምሰራው እናታችን በጣም እንድትወደኝ ብዬ ነው” በማለት መልሳልኛለች። እናታችን አሁን ላይ ሆነን የምናነሳውን ይሄንን ትዝታ ስትሰማ “ድሮ ልጅ እያላችሁ የተሰጣችሁን ስራ ያልሰራችሁ ቀናቶችም እኮ እወዳችሁ ነበር።” ስትለን “ታዲያ ለምን የዛኔ አልነገርሽንም ነበር” በማለት ምላሽ እንሰጣታለን። የእህቴን ምላሽና እኔ የተሰጠኝን ስራ ባልሰራሁባቸው ቀናቶች ይሰማኝ የነበረውን ያለመወደድ ስሜት እያሰብኩ ጥቂት ቆየሁ። ስሜቱ በጣም ያስጠላል። ያለመወደድ ስሜት በጣም ከባድ ነው። ይሄ ስሜት ከልጅነታችንም ስላደገብኝ፥ ወደ እግዚአብሄር አባትነት ስመጣ በተለያዩ ቀናቶች ተመሳሳይ ስሜት ሲሰማኝ እራሴን አገኘዋለሁ። አንዳንድ ቀን እግዚአብሄር የሚወደኝ ስለታዘዝኩትና ስላገለገልኩት መስሎ የሚሰማኝ ቀናቶች አሉ። እራሴን ታዲያ ባለመታዘዝ ውስጥ ያገኘሁት ቀን፥ ለእኔ ያለው ፍቅር የሚቀንስ እየመሰለኝ ውስጤ ይረበሻል። ነፍሴ እግዚአብሄር ከሰው ፍጹም የተለየ አስተሳሰብ እንዳለው እስኪገባትና እስክትረዳ ድረስ፥ ዘላለማዊ የሆነውንና ያለ ምንም ምክኒያት ስለወደደኝ በምንም ምክኒያት ሊጠላኝ የማይችል አምላክ እንደሆነ እስክረዳው ድረስ ነው። 

በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 15 ላይ፥ ኢየሱስ ስለ ጠፋው ልጅ ምሳሌ እንዲህ በማለት ይናገራል። አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን፦ አባቴ ሆይ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከእነዚህ ሁለት ወንድማማቾች ታናሽ የሆነው ወንድም ታዲያ፥ ከአባቱ የሚደርሰውን ክፍል በመቀበል ወደ ሩቅ አገር እንደሄደና ገንዘቡን አባክኖ እንደጨረሰ፥ ከዚያም በብዙ ረሀብና ችግር ውስጥ ካለፈ በኋላ ወደ ልቡ እንደተመለሰ ይናገራል። ይሄ ልጅ በዚህ ሁሉ መባከንና ማባከን ውስጥ ሲያልፍ በልቡ አልነበረም። በመጨረሻ ግን በምእራፉ ቁጥር 17 ላይ እንደሚናገረው፥ ወደ ልቡ ተመልሶ “እንዴ ቆይ ግን ምግብ የሚተርፋቸው በጣም ብዙ ሰዎች በአባቴ ቤት አሉ አይደል እንዴ? እኔ ታዲያ ለምንድነው እዚህ የአሳማዎችን ምግብ ለመብላት እስከምፈልግ ድረስ በዚህ ከባድ ረሀብ ውስጥ የማልፈው?” ብሎ በማሰብ ወደ አባቱ ቤት ለመመለስ ይወስናል። በጣም የሚገርመው፥ ይሄ ልጅ ቢጠፋም አባቱ ለእርሱ ያለውን ፍቅር ጠንቅቆ የተረዳ ልጅ ነበር። ለዚያ ነው ያለውን ድርሻ አባክኖ ከጨረሰ በኋላ ወደ አባቱ የሚመለስበትን ድፍረት ያገኘው። አብዛኞቻችሁ ታዲያ ታሪኩን እንደምታውቁት፥ የልጁን ወደ እርሱ መመለስ የተመለከተው አባት፥ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ደስታ ውስጥ ገብቶ ባሪያዎቹን እንዲህ በማለት ሲያዛቸው እንመለከታለን። “ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት። ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፥ የሰባውን ፍሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላ ደስም ይበለን፥ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ህያው ሆኗል ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም” በማለት ይናገራል። በሌላ ገጽ ደግሞ በቤት ውስጥ ብዙ የሚለፋና የሚደክመው የዚህ የጠፋው ልጅ ታላቅ ወንድም፥ በጣም ብዙ ስለሰራና አባቱን ስላገለገለ ከወንድሙ በተሻለ መልኩ የሚወደድ ይመስለው ነበር። ይሄንንም የሚያስረግጥልን በምእራፉ 29ነኛ ቁጥር ላይ፥ አባት የጠፋውን ልጁን አስመልክቶ ባደረገው የደስታ ዝግጅት ላይ በመናደድ የተናገረው ንግግር ነው። “እነሆ ይህን ያህል አመት እንደ ባሪያ ተገዝቼልሀለሁ፥ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍኩም፥ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጠቦትስ እንኳን አልሰጠሀኝም።” በማለት ለአባቱ ያለውን መገዛትና መታዘዝ ከወንድሙ በተሻለ መልኩ ሊወደድበት የሚገባ ምክኒያት አድርጎ ያስቀምጣል። ይሄ ልጅ መገዛቱ መልካም ነው። የአባቱን ትእዛዝ በትክክል አክብሮ ማገልገሉም እጅግ በጣም መልካም ነው። አንድ የሳተው ትልቅ ነገር ግን ምንድነው? ለአባቱ የሚሰጠው ይሄ ሁሉ አገልግሎት፥ አባቱ እርሱን የወደደባቸው ምክኒያቶች አለመሆናቸውን አለመረዳቱ ነው። አባታቸው እርሱንም ሆነ ወንድሙን የወደዳቸው፥ ስለሰሩና ስላገለገሉት አይደለም። የወደዳቸው ልጆቹ ስለሆኑ ነው። የወደዳቸው ስለወለዳቸው ነው። ሰው ልጁን የሚወደው፥ ስለሰራና ስላገለገለው አይደለም። ሰው ልጁን የሚወደው፥ ስለወለደው ነው። 

እኔ ገና ልጅ ባለመውለዴ ስሜቱ በትክክል ባይገባኝም፥ አንድ ወዳጃችን የመጀመሪያ ልጇን ከወለደች በኋላ የነገረችን አንድ ነገር ልቤ ውስጥ ቀርቷል። “ልጄን ወልጄ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ ሳያት አለቀስኩ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ተሰምቶኝ የማያውቅ ስሜት ተሰማኝ። ገና ሳያት በጣም ወደድኳት። ድንገት ወደ ህይወቴ መጥታ፥ በህይወቴ ከማውቃቸው ሰዎች ሁሉ በለጠችብኝ። በዚህ መጠን ሰውን መውደድ የምችል እራሱ አይመስለኝም ነበር” እያለች ስትናገር አስታውሳለሁ። እኛ ሰዎች፥ ሌሎች ሰዎችን ስንወድ ሁልጊዜ ምክኒያት አለን። ልጆች ስንወልድ ግን ልጆቻችንን የምንወድበት ምክኒያት የለንም። የምንወዳቸው ስለወለድናቸው ብቻ ነው። ስለወለድነው ብቻ ልጃችንን ዳይፐሩን እየቀየርን፣ እያበላንና እያጠጣን፣ የራሳችንን እንቅልፍና እረፍት እየቀነስን የወለድነውን ልጅ እናሳድጋለን። ይሄንን ሁሉ ዋጋ ስንከፍል፥ ለልጁ ውለታ እያደረግንለት እንደሆነ አይሰማንም፥ ምክኒያቱም ሁሉንም ነገር የምናረገው ውስጣችን ካለው ፍቅር ተነስተን ነው። ለወለድነው ልጅ የሚያስከፍለውን ዋጋ ብቻ ሳይሆን፥ አንዳንዴም ከሚያስከፍለው ዋጋ በላይ ማድረግ ትልቁ ደስታችን ነው። እንዲያውም እነዚህን ነገሮችን ለወለድነው ልጅ አለማድረግ አንችልም። በተለያዩ ከባባድ ምክኒያቶች ይሄንን ለልጆቻችን ማድረግ ባንችል ደግሞ፥ እጅግ በጣም ትልቁ ሀዘናችን ነው። ይሄ የጠፋው ልጅ ወንድም፥ አባታቸው ስለሰሩለትና ስላገለገሉት ሳይሆን ልጁቹ ስለሆኑ ብቻ፥ ከእርሱ ስለተወለዱ ብቻ እንደሚወዳቸው ቢረዳና ቢገባው ኖሮ፥ የወንድሙን መመለስ አስመልክቶ እየሆነ ባለው ደስታ ላይ ተባባሪ ይሆን ነበር። ሌላው፥ ይሄ ታላቅ ወንድም አባቱ ለእርሱ ያለውን ከምንም ነገር ጋር ያልተያያዘ ፍቅር ቢረዳ ኖሮ፥ አባቱን የሚያገለግልበት ምክኒያት ይቀየር ነበር። አገልግሎቱ ባይቋረጥም፥ የሚያገለግለውና የሚታዘዘው እንዲወደድ ሳይሆን ስለተወደደ ይሆን ነበር። አገልግሎቱ በአባቱ የሚወደድበት ምክኒያት ሳይሆን፥ በአባቱ ለተወደደበት ፍቅር የሚሰጠው ምላሽ ይሆንለት ነበር።

ሁላችንም እግዚአብሄርን ለማገልገል የተጠራን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን፥ በአገልግሎት ቦታችን ላይ ሆነን ማወቅ ያለብን፥ እግዚአብሄር እኛን የሚወደን ስላገለገልነው አለመሆኑን ነው። ይሄንን ደጋግመን ለራሳችን መንገር አለብን። የእግዚአብሄር ፍቅር እኛ ባገልገልነው መጠን ቢሆን ኖሮ፥ ፍቅሩ በጣም ትንሽ ይሆን ነበር። ሌላው ቀርቶ እግዚአብሄር የሚወደን ቃሉን እየጠበቅን በመታዘዝ ስለምንኖር አይደለም። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሄር አስተሳሰቡ እንደ እኛ እንደ ሰው ስለሚመስለን፥ በፊቱ ጥሩ ህይወት ያለን የመሰለን ሰሞን ለእኛ ያለው ፍቅር የጨመረ ይመስለናል። ነገር ግን ባለመታዘዝና በጨለማ ውስጥ ሆነን የስጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን ስንሄድ፣ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ሆነን የስጋችንን ምኞቶች እየተከተልን በነበርንበት የህይወት ጎዳና፥ በእኛ ላይ የነበረው ፍቅር ልክ እንደ ዛሬው ሀያል ነበር። እግዚአብሄር እኛን የሚወድበት ከእኛ ጋር የተያያዘ ምንም አይነት ምክኒያት የለውም። የሚወደን ጥሩ ስለሰራን አይደለም። አምነን ስለተከተልነውም አይደለም። ስላገለገልነውም አይደለም። በቃ ዝም ብሎ ነው የሚወደን። እኛን የወደድክበትን ምክኒያት ስጥ ከተባለ፥ ሊሰጥ የሚችለው የራሱን ማንነት እንጂ፥ ከእኛ ጋር የተያያዘ ምንም የሚሰጠው ምክኒያት የለውም። ምን አይነት ነገር ነው ግን? ምድር ላይ የሌለ፥ በሰዎች መካከል የሌለ ነገር እኮ ነው። በምናረገው በየትኛውም ነገር የእግዚአብሄርን ፍቅር ከፍም ሆነ ዝቅ ልናረገው አንችልም። እግዚአብሄር የሰው ልጆችን ሁሉ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ወዷል። እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ፍቅር ልንወስነው አንችልም። እግዚአብሄር በእኛ ህይወት ላይ ያለውን ደስታ ግን የምንወስነው እኛው እራሳችን ነን። እግዚአብሄር እንዳይወደን ልናረግ ባንችልም፥ በእኛ እንዳይደሰት ልናረግ ግን እንችላለን። እግዚአብሄር የሚወደውና የሚጠላው ሰው የለም። የሚደሰትበትና የማይደሰትበት ሰው ግን አለ። የምንሰራው ለእግዚአብሄር ፍቅር አይደለም። የምንሰራው ለእግዚአብሄር ደስታ ነው። 

የእግዚአብሄርን ፍቅር የተረዳ ሰው፥ እግዚአብሄር ያለ ምንም ምክኒያት እንደወደደው የተረዳ ሰው የሚያገለግለው አገልግሎትና ይሄንን የእግዚአብሄርን ፍቅር ያልተረዳ ሰው የሚያገለግለው አገልግሎት አንድ አይነት ሊሆን አይችልም። የአገልግሎቱ ፍሬና ውጤትም አንድ አይነት አይደለም። እነዚህ ሁለት ሰዎች የሚኖሩበትና የሚያገለግሉበት ስሜትም አንድ አይነት አይደለም። እግዚአብሄር በእኛ ላይ ያለው የአገልግሎት አላማ፥ በእኛ ላይ ካለው የፍቅር አላማ ቀጥሎ የሚመጣ ነገር ነው። እግዚአብሄር መጀመሪያ የሚፈልገው ለእኛ ያለውን ፍቅር እንድንረዳና እንድናውቅ እንዲሁም በዚህ ፍቅር ውስጥ እንድንኖር ነው። በፍቅሩ ውስጥ እንድንኖር፥ በቃ አብረነው እንድንኖር ነው የሚፈልገው። ይሄንን አስመልክቶ በማርቆስ ምእራፍ 3 ከቁጥር 13 ጀምሮ እንዲህ በማለት ይናገራል። ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። ይልና ቀጥሎ እንዲህ ይላል። “...ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ስልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አስራ ሁለት አደረገ..” ይላል። ከዚህ ቃል እንደምንረዳው፥ ኢየሱስ 12ቱን ሀዋሪያት ወደ እርሱ የጠራበት የመጀመሪያው አላማ፥ ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ነው። ለዚያ ነው “ከእርሱም ጋር እንዲኖሩ ለመስበክ እንዲልካቸው…” የሚለው። መጀመሪያ የፈለገው ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ነው። ቀጥሎ ነው ለአገልግሎት የሚልካቸው። ጌታ መጀመሪያ ከአገልግሎቶቻችንም በፊት የሚፈልገው፥ ከእኛ ጋር መኖር ነው። መጀመሪያ አላማው ፍቅር ነው። መጀመሪያ የሚፈልገው ከእኛ ጋር ህብረት ማድረግ ነው። እነዚህ በሉቃስ 15 ላይ የምናያቸው ሁለት ወንድማማቾች፥ በአንድ ቤት የሚኖሩ፥ ነገር ግን በሁለት የተለያየ ስሜት ውስጥ ያሉ ልጆች ናቸው። ታናሹ ወንድም ሄዶ ገንዘቡን ሁሉ ቢያጠፋም፥ ወደ አባቱ ተመልሶ እንዲመጣ ያደረገው፥ አባቱ ለእርሱ ያለውን ፍቅር ማወቁ ነው። ቤት ውስጥ ያለው የመጀመሪያ ልጅ ግን በብዙ አገልግሎት ውስጥ የተጠመደ ልጅ ቢሆንም፥ የአገልግሎቱ ምክኒያት ፈጽሞ የተሳሳተ ነበር። ምናልባትም ድርሻውን ይዞ የጠፋው ይሄ ታላቅ ወንድም ቢሆን ኖሮ፥ ገንዘቡን ከጨረሰ በኋላ ወደ አባቱ የሚመለስበት ድፍረት አይኖረውም ብዬ እገምታለሁ። ምክኒያቱም የተወደደበት ምክኒያት በትክክል የገባው ልጅ አልነበረም። ጥፋት ስናጠፋና የእግዚአብሄርን መንገድ ስንስት፥ የእግዚአብሄርን ከምክኒያት ውጪ የሆነ ፍቅር መረዳት፥ ወደ እግዚአብሄር መመለሳችንና አለመመለሳችን ሊወስን የሚችል ነገር ሆኖ ሊገኝ ይችላል። የእግዚአብሄርን ፍቅር ስንረዳ፥ አገልግሎት ከባድ ሸክም ሳይሆን በብዙ ፍቅር የምናደርገው ነገር ይሆንልናል። እግዚአብሄር የሚፈልገው አገልግሎታችን ከፍቅር እንዲጀምር ነው። እርሱ ለእኛ ያለውን ፍቅር በመረዳት እንዲሁም እኛ ለእርሱ ያለንን ፍቅር በማቅረብ፥ በፍቅር ላይ የተመሰረተውን አገልግሎት እንድናገለግል ነው።

ምርጫ 

ምርጫ 

ፍለጋ

ፍለጋ