ረሀብ
በማመልክበት ቤተክርስቲያን ውስጥ አገልጋይ የሆነ አንድ ወንድም የእግዚአብሔርን ቃል በማስተማር ላይ እያለ አንድ ጥያቄ ጉባኤውን ጠየቀ። ለተወሰነ ጊዜ ብትታሰሩና ከመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች ውስጥ ይዛችሁ መግባት የምትችሉት አንድ መጽሐፍ ብቻ ነው ብትባሉ፥ የትኛውን መጽሐፍ ትመርጣላችሁ? በማለት ጉባኤውን ይጠይቃል። ይሄ ወንድም ጥያቄውን እየጠየቀ፥ በልቤ ጥቂት ካሰብኩ በኃላ ከመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች ውስጥ አንድ መጽሐፍ ብቻ ነው መምረጥ የምትችይው ብባል የሐዋሪያት ስራ መጽሐፍን እንደሆነ ማሰብ ጀመርኩ። የሐዋሪያት ስራ መጽሐፍ በጣም የምወደው መጽሐፍ ነው። ከመጽሐፎች ሁሉ ውስጥ ለምን የሐዋሪያት ስራ መጽሐፍን መረጥሽ ከተባልኩ፥ መጽሐፉን የመረጥኩበት ዋና ዋና ምክኒያቶች እነዚህ ናቸው። የሐዋሪያት ስራ መጽሐፍ መንፈስ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ምድር ሲወርድ የተከሰቱትን ነገሮች የሚናገር ልዩ መጽሐፍ ነው። መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድር ሲወርድ፥ ፈሪ የነበሩት እነ ጴጥሮስ በብዙ የመንፈስ ቅዱስ ድፍረት ሲያገለግሉ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ በልዩ ልዩ ድንቅና ታምራቶች ቃሉን በመካከላቸው እያጸና በሚታይና በሚዳሰስ መልኩ አብሯቸው ሲሰራ የምትመለከቱበት፥ ከዚህም የተነሳ የወንጌል እሳት እየነደደ ብዙዎች በክርስቶስ በማመን ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር ሲሰጡ የምታዩበት አስደናቂ መጽሐፍ ነው። በተጨማሪም፥ ሐዋሪያቶቹ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ታግዘው በብዙ ሲተጉ እና ዋጋ ሲከፍሉ የምትመለከቱበት፥ እነ ሳኦል ጳውሎስ ወደመሆን የተቀየሩበት የጳውሎስን የአገልግሎት ጉዞ እና አስደናቂ የሕይወት ምስክርነት እያነበባችሁ የምትደነቁበት መጽሐፍ ነው። የሐዋሪያት ስራ መጽሐፍን በአጠቃላይ ስትመለከቱ፥ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሰዎች ድካም ውስጥ ሲያልፍ የሚሆኑትን አስደናቂ ነገሮች ትማሩበታላችሁ።
የእግዚአብሔርን ቃል ከትላንት ዛሬ በተሻለ መንገድ እየተማርኩ ስመጣ፥ በዘመናቶች መካከል እግዚአብሔር ትልልቅ የሆኑ አላማዎቹን በምድር ላይ የፈፀመው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደሆነ እየተረዳሁ መጣሁ። የአዲስ ኪዳን መጽሐፍትን ብቻ ሳይሆን፥ የብሉይ ኪዳን መጽሐፎችንም ስትመለከቱ እግዚአብሔር በነገስታቶች፣ በመሳፍንቶችና በነቢያቶች ሕይወት ለመስራት እና በጊዜው የነበረውን ዓላማ ለመፈጸም የቀባቸው በመንፈስ ቅዱስ ቅባት ነበር። ሳምሶን የእስራኤልን ሕዝብ ተገዝተው ከነበረበት ከፍልስጥኤም ግዛት ለማዳን ተቀብቶ ነበር፥ በመሳፍንት መጽሐፍ ላይ እያነበብን የምንደነቅበት የሳምሶን ልዩ የሆነ ሀይል፥ የሳምሶን የጡንቻ ሀይል አይደለም የእስራኤልን ሕዝብ ከጠላቶቻቸው እጅ ያድን ዘንድ በሳምሶን ውስጥ የተገለጠ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። ሌላ ምሳሌ እንመልከት ካልንም ኢዩ ኤልዛቤልን ለመበቀል ተቀብቶ ነበር ከእግዚአብሔር ቃል እንረዳለን፣ በእስራኤል ላይ ለመንገስ የተጠሩትን የሳኦልን እና የዳዊትን አገልግሎትም ስንመለከት፥ የእስራኤልን ሕዝብ ለመምራት እና ለመጠበቅ በንግስና ቅባት ተቀብተው ነበር። ሳኦልና ዳዊት በንግስና ቅባት የተቀቡት፥ የእግዚአብሔር መንፈስ በእነርሱ ውስጥ አልፎ ሕዝቡን ይመራ እና ይጠብቅ ዘንድ ነው። ይሄንን በራሳቸው ኃይል ማድረግ ቢችሉ ኖሮ መቀባት አያስፈልጋቸውም ነበር። የሳኦልንና የዳዊትን የንግስና አገልግሎት እኮ ልዩ ልዩ ያደረገው የሳኦል ከሁለት አመት በላይ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አለመቀጠል እና የዳዊት ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እስከመጨረሻው መቀጠል ነበር። ሳኦል ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተጓዘው ለሁለት አመታቶች ብቻ ነበር። የዳዊትን አገልግሎት ውብ ያደረገው፥ በሕይወቱ ከፍታዎችም ሆነ ዝቅታዎች ውስጥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አብሮ መጓዙ ነበር። የእግዚአብሔር ቃል በኢዮብ መጽሐፍ 26፡13 ላይ ሲናገር “በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ” በማለት ይናገራል። ሰማያቶች እንኳን እኮ የተዋቡት፥ ውበትን ያገኙት በእግዚአብሔር መንፈስ ነው። የእኛም ሕይወታችን የሚዋበው፥ እያንዳንዱ ነገራችን ውበትን የሚያገኘው በእግዚአብሔር መንፈስ ነው። የነገሮቻችን ሁሉ ውበት ያለው በመንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር መሆን ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የምድር አገልግሎትም እንዲሁ ስንመለከት በምድር የነበረውን አገልግሎቶች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንዳገለገለ የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል። እንዲያውም በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 4 ላይ እንደሚናገረው፥ በሰንበት ወደ ምኩራብ ገብቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊያነብ ሲነሳ በነቢዩ በኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ ስለ እርሱ የተጻፈውን ቃል እንዲህ በማለት በፊታቸው ቆሞ አንብቦ ነበር። “የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፥ ለታሰሩትም መፈታትን ለእውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” በማለት አንብቦ ነበር። በሐዋሪያት ስራ ምእራፍ 10፡38 ላይም ስለ ኢየሱስ የምድር አገልግሎት ሲናገር፥ እንዲህ ይላል። “እግዚአብሔር የናዝሬቱ ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና..” በማለት የኢየሱስ የምድር አገልግሎት በመንፈስ ቅዱስ ሙላት ውስጥ እንደነበረ ይናገራል። ታዲያ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ ካገለገለ የእኛ አገልግሎት እንዴት ከመንፈስ ቅዱስ ውጪ ሊሆን ይችላል? እንዲያውም መንፈስ ቅዱስ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ኢየሱስ ሲናገር በዮሐንስ ወንጌል 16፡7 ላይ እንዲህ ብሎ ነበር። “እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።” በማለት መሄዱን የተሻለ አድርጎ የተናገረበት ዋና ምክኒያቱ የመንፈስ ቅዱስ ወደ ምድር መምጣት እና ከእኛ ጋር መሆን ነው።
ብዙ ጊዜ ስለ መንፈስ ቅዱስ ስናስብ፥ ቶሎ ወደ ሀሳባችን የሚመጣልን፥ በኃይል የተሞላ ፀሎት ወይንም በቤተክርስቲያን ውስጥ የምናያቸው ለየት ያሉ እንቅስቃሴዎች ናቸው። የእግዚአብሔር መንፈስ ግን ከፀሎት እና በልሳን ከመናገር ያለፈ በርካታ ስራዎችን በሕይወታችን ውስጥ ይሰራል።
ሐዋርያቱ በመንፈስ ቅዱስ ከተሞሉ በኋላ፥ በሕይወታቸው ውስጥ ልዩ ልዩ ለውጦች ሆነው እንደነበር ከእግዚአብሔር ቃል እንረዳለን። ኢየሱስን ሶስት ጊዜ የካደው ጴጥሮስ፥ ከሶስት ሺህ በሚበልጡ ሰዎች መሀከል ስለ ኢየሱስ የሚመሰክርበትን ድፍረት አግኝቶ ነበር። የእግዚአብሔር መንፈስ በተጠራንበት የአገልግሎት ስፍራ የምንቆምበት ድፍረታችን ነው። ይሄ በሐዋሪያቱ መካከላቸው የመጣው የእግዚአብሔር መንፈስ፥ በብዙ አይነት መንገድ የደቀ መዛሙርቱን ሕይወትና አገልግሎት እየለወጠ፥ ብዙ ድንቆችንና ተአምራቶችን ያደርግ ነበር፥ ብዙ አዳዲስ ሰዎችም ኢየሱስን በማመን በእነርሱ ላይ ይጨመሩ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ፥ ደቀ መዛሙርቱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲኖሩ መንፈስ ቅዱስ ሕይወታቸውን በተለያየ አቅጣጫ እየቀደሰ፥ በአገልግሎታቸው ውስጥ ይሰራ ነበር። የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንደመሆኑ እኛን ለመቀደስ የሚረዳን ቅድስናችን ነው። ከዚህም በተጨማሪ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራን መሪያችን ነው።
መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ሁለት ትልልቅ አላማዎች አሉት። አንዱ አላማው፥ እኛ ክርስቶስን በመከተል ስንኖር በሚያስፈልገን ነገሮች ሁሉ እኛን መርዳት ሲሆን፥ ሌላኛው አላማው ደግሞ በእኛ ውስጥ ሆኖ ሌሎች ሰዎችን መርዳት ወይንም ማገልገል ነው። የመጀመሪያው የመንፈስ ቅዱስ አላማ እኛን እራሳችንን መርዳት ነው። መቼም መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ያለውን ስራና አገልግሎት አንድና ሁለት ብለን መቁጠር ባንችልም ጥቂቶቹን እንዘርዝር ካልን፥ እኛን በማጽናናት፣ በመምከር፣ በመውቀስ፣ ወደ እውነትና ወደ እግዚአብሔር ሀሳብ በመምራት፣ በመቀደስ፣ ድካማችንን በማገዝ፣ የእግዚአብሔርን ማንነቶች ለእኛ በማስረዳት፣ የእግዚአብሔርን ቃል ፍቺ በማብራት፣ በእኛ ውስጥ ሆኖ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመጸለይ እንዲሁም በሌሎች በርካታ ነገሮች ይረዳናል፣ ያንጸናል፣ እግዚአብሔርን የሚመስል ሕይወት እንድንኖር በተለያየ አቅጣጫዎች ያግዘናል። በሮሜ 8፡26 ላይ ሲናገር፥ መንፈስ ቅዱስ ድካማችንን እንደሚያግዝ እና እኛ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ስለማናውቅ በማይነገር መቃተት በውስጣችን እንደሚቃትት እንዲሁም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን እንደሚማልድ ይናገራል። እኛ በስጋችን ስንጸልይ የራሳችንን ፍላጎቶች ብቻ ነው የምንጸልየው፥ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ የሚጸልየው ግን የአብን ፈቃድ ነው።
እንግዲህ ከላይ እንዳልነው የመንፈስ ቅዱስ አንዱ ስራው እኛን መርዳት ሲሆን፥ ሌላኛው በሕይወታችን የሚሰራው ትልቁ ስራ ደግሞ በተፈጠርንበት አላማ ውስጥ ሌሎችን ማገልገል ነው። መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ ሆኖ ሌሎችን ያገለግላል፥ ይመክራል፣ ያስተምራል፣ ያጽናናል፣ ይፈውሳል፣ መንገድ ያሳያል፣ የእግዚአብሔርን ቃል ይገልጣል፣ በወደደው መንገድ እኛን ለራሱ አላማና ስራ ይጠቀማል።
በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ልክ ድንገት እንደሚነጥቅ አውሎ ነፋስ በመካከላቸው እንደመጣና ቤቱን እንደሞላው፥ እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች እንደታይዋቸው፥ በሁሉም ላይ መንፈስ ቅዱስ እንደሞላባቸውና መንፈስ ቅዱስ በሰጣቸው ልሳኖች መናገር እንደጀመሩ ይናገራል።
ታዲያ እዚያው የሐዋሪያት ሥራ መጽሐፍን ማንበባችሁን ስትቀጥሉ፥ ሐዋሪያቱና ደቀ መዛሙርቱ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ከተቀበሉ በኋላ፥ ወዲያው የገቡት ወደ አገልግሎት ነበር። ወዲያውኑ ነበር ስለ ክርስቶስ መመስከር የጀመሩት። ኢየሱስም ወደ አባቱ ሳያርግ በፊት በሐዋሪያት ሥራ ምእራፍ 1 ላይ እንዳላቸው፥ “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” በማለት የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ሳይቀበሉ ወዴትም እንዳይሄዱ እና አገልግሎት እንዳይጀምሩ ኢየሱስ አዛቸው ነበር። መንፈስ ቅዱስን ከተሞሉ በኋላ ወዲያውኑ ነው የክርስቶስ ምስክሮች በመሆን ወደ አገልግሎት የገቡት። መንፈስ ቅዱስን እስከሚቀበሉበት ሰአት ግን ምንም አይነት አገልግሎት አልነበረም። አገልግሎት የጀመረው፥ ከመንፈስ ቅዱስ ሙላት በኋላ ነበር፥ መንፈስ ቅዱስ ከመጣና በእነርሱ ላይ ከሞላባቸው በኋላ ነበር። ይሄ የእግዚአብሔር ቃል ክፍል የሚያስተምረን፥ በእኛ ውስጥ የእግዚአብሔርን ሀሳብ የሚያገለግለው መንፈስ ቅዱስ እንደመሆኑ መጠን ከአገልግሎቶቻችን በፊት እጅግ በጣም የሚያስፈልገን ዋና ነገር የመንፈስ ቅዱስ ሙላት እንደሆነ ነው።
ሐዋርያትና ደቀ መዛሙርት ታዲያ የእግዚአብሔርን መንፈስ ከተሞሉ በኋላ የነበረው አገልግሎታቸው እጅግ በጣም ውጤታማ እና የሚያረካ ነበር። ፈሪ ተብሎ እናውቀው የነበረው ጴጥሮስ ወዲያው በመንፈስ ቅዱስ ድፍረት ሲሞላና ወደ አገልግሎት ሲገባ እንመለከታለን። በዚያው ጴጥሮስ ባገለገለበት ቀን 3000 ሰዎች ናቸው በክርስቶስ አምነው የዳኑት። ይሄንን ያደረገው የጴጥሮስ ችሎታ አይደለም፥ ጴጥሮስ የተሞላው የእግዚአብሔር መንፈስ ነው። የሰዎችን ልብ መማረክ የሚችለው፣ ሰዎችን ከጨለማ መንግሥት አውጥቶ ወደሚደነቅ ብርሀን ሊያመጣ የሚችለው የእኛ የስጋ አገልግሎት አይደለም፥ በእኛ ውስጥ የሚሰራው የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ብቻ ነው። ስለዚህ ውጤታማ የሆነ አገልግሎት ለማገልገል አስቀድመን በእግዚአብሔር መንፈስ መሞላት ይኖርብናል።
በጴጥሮስ ውስጥ በተገለጠው በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት፥ በአንድ ቀን ሶስት ሺህ ሰዎች በክርስቶስ አዳኝነት አምነው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ተጨምረዋል። ጌታም የሚድኑትን እለት እለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር። ብዙ በሽተኞች ይፈወሱ ነበር፣ ርኩሳን መናፍስት በታላቅ ድምጽ እየጮሁ ከብዙ ሰዎች ውስጥ ይወጡ ነበር፣ የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ በመካከላቸው በኃይልና በሥልጣን ይሰራ ነበር፣ በብዙ የመንፈስ ቅዱስ ድፍረት ተሞልተው ያገለግሉ ነበር፥ በወንጌል ምክንያት የሚመጣባቸውን ተግዳሮቶች አይፈሩም ነበር፥ ስደት እንኳን ሲመጣባቸው፥ በተሰደዱበት ቦታ ሁሉ እየዞሩ ወንጌልን ይሰብኩ ነበር። አገልግሎታቸውን ፍሬያማ በማድረግና ውጤት በመስጠት የተገለጠው በእነርሱ ውስጥ ይሰራ የነበረው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ብቻ ነበር።
መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ኃይልና አሰራር ነው። ይሄ መለኮታዊ የሆነ ኃይል ነው ትልቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሀሳብ በእኛ ተጠቅሞ ማከናወን የሚችለው። እግዚአብሔር የራሱን ሀሳብ የሚያገለግለው በሰው አቅም አይደለም፥ የሰው አቅም ትልቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሀሳብ ማገልገል አይችልም። እግዚአብሔር ትልቅ የሆነውን፣ ዘለዓለማዊ የሆነውን ሀሳቡን በእኛ ውስጥ የሚያገለግለው፥ በመንፈሱ ውስጥ በሚገለጠው በራሱ ኃይልና አቅም እንዲሁም ችሎታ ነው። የእኛን አቅምና ኃይል አይፈልግም፥ የሚፈልገው የእኛን ፈቃድ ብቻ ነው። በፈቃዳችን ውስጥ የራሱን ኃይል በመንፈሱ እየገለጠ፥ ሀሳቡን በዘመናችን የሚያገለግለው እግዚአብሔር እራሱ ነው። ለዚያ ነው በትንቢተ ዘካርያስ ምእራፍ 4፥6 ላይ ለዘሩባቤል ሲናገር፥ “በመንፈሴ እንጂ በሀይልና በብርታት አይደለም ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር” በማለት የተናገረው።
ለማገልገል ከመነሳታችን በፊት የምናገለግለው አገልግሎት ውጤት ይኖረው ዘንድ፥ የእግዚአብሔርን መንፈስ አጥብቀን መፈለግ ይኖርብናል፥ አለበለዚያ ትርፉ ድካም ብቻ ነው። ከመንፈስ ቅዱስ ውጪ በስጋችን የምናገለግለው አገልግሎት ለጊዜው ሰዎችን ስሜታዊ ሊያደርግ ይችል ይሆናል እንጂ፥ ውጤትና ፍሬ ግን አይኖረውም። ዛሬም በእኛ ውስጥ ባለው በየትኛውም የፀጋ ስጦታ ውስጥ እግዚአብሔር ይሰራ ዘንድ፥ አብዝተን መጠማት ያለብን የመንፈስ ቅዱስን ሙላት ነው። ዘማሪዎች ብንሆን ሰባኪዎች፥ አስተማሪዎች ብንሆን በምክር የምናገለግል፥ ወንጌላዊያን ብንሆን ዲያቆናት፥ ነቢያቶች ብንሆን ቤተክርስቲያንን በልዩ ልዩ ነገሮች የምንረዳ፥ በየትኛውም የአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራን እንዲሁም ገና ወደ አገልግሎት ለመግባት እያሰብንና እየተዘጋጀን ያለን ሰዎች ብንሆን፥ አስቀድመን መፈለግ ያለብን የመንፈስ ቅዱስን ሙላት ነው።
እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ሀሳብ በእኛ ውስጥ ሆኖ የሚያገለግለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከሆነ፥ እኛ የእርሱ መጠቀሚያ መሳሪያዎች ወይንም በእኛ ውስጥ አድሮ የሚሰራብን ማደሪያ እቃዎች ብቻ ነን ማለት ነው። የቅባቱ መቀመጫዎች፣ የቅባቱ ማረፊያዎች፣ ሁሉን የሚሰራው የመንፈስ ቅዱስ እቃዎች ብቻ ነን። በእኛ ውስጥ አድሮ የወደደውን ይሰራብናል፥ ሰማያዊ ሀሳቡን በምድር ላይ ይፈፅምብናል፥ ዘለዓለማዊ ሀሳቦቹን ያገለግልብናል።
“ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን፥ ስለዚህ በስጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። (1ኛ ቆሮ 6:19)
ለምንኖረው ሕይወትም ሆነ ለምናገለግለው አገልግሎት የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ይሄንን ያህል እጅግ በጣም አስፈላጊ ከሆነ፥ ይሄ ሙላት ሁልጊዜ በእኛ ውስጥ እንዲኖር ከእኛ የሚጠበቀው አንድ ነገር ብቻ ነው። እርሱን አጥብቆ መፈለግ፣ እርሱን መራብ እንዲሁም አብዝቶ መጠማት ነው። ኢየሱስ የመንፈስ ቅዱስን ውሀ መጥተው እንዲወስዱ የጋበዘው፥ የተጠሙትን ሰዎች ብቻ ነው። በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት የሚያስፈልገን፥ በእውነተኛ ልብ እርሱን መጠማትና አብዝቶ መፈለግ ብቻ ነው።
“ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ” (የዮሐንስ ወንጌል 7፥37)
መጠማት በመንፈሳዊ አለም ላይ ልክ እንደ ገንዘብ ነው። ብዙ ገንዘብ ያለው ሰው ብዙ ነገሮችን መግዛት እንደሚችል ሁሉ፥ ብዙ መንፈሳዊ ጥማት ያለው ሰውም እንዲሁ ብዙ የመንፈስ ቅዱስን ውሀ መውሰድ ይችላል። እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ እንደማይሰጥ በዮሐንስ 3፡34 ላይ ይናገራል፥ ይሄ ይበቃሀል/ይበቃሻል አይልም። የምንወስደው በተጠማነው ልክ ነው፥ የምንወስደው መጠኑ የሚለካው፥ በእኛ ጥማት መጠን ነው። ምን ያህል ጥማት ውስጣችን አለ? መንፈስ ቅዱስን የምንፈልግበት ፍላጎት መጠኑ ምን ያህል ነው?
በሐዋሪያት ስራ ምእራፍ 2 ላይ የተገለጠው አስደናቂ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል፥ በምእራፍ 1 ላይ የነበረው ጸሎት፣ መንፈሳዊ ረሀብና ጥማት መልስ ነው። ምእራፍ 1 ላይ ስትመለከቱ፥ ኢየሱስ ወደ አባቱ ካረገ በኃላ፣ የኢየሱስ እናት ማሪያም ከሐዋሪያቱ፥ ከወንድሞቹ እና ለሌሎች እህቶች ጋር ሆነው በአንድ ልብ በእግዚአብሔር ፊት በመሆን ለጸሎት ይተጉ ነበር። ምእራፍ 1 ላይ የትጋት ጸሎት ነበረ፥ ምእራፍ 2 ላይ ደግሞ የእግዚአብሔር መልስ መጥቷል። ምእራፍ አንድ ላይ መጠማት ነበረ፥ ምእራፍ ሁለት ላይ ደግሞ መጠጣትና መርካት ሆኗል።
አንዳንድ ጊዜ የሆኑ የጾም ጸሎት ቀናቶችን ወስደን እግዚአብሔርን ምንም ነገር ልንጠይቀው ሳይሆን ልንፈልገው ብቻ፥ እንደምንፈልገው ልንነግረው ብቻ፥ በሕይወታችን ውስጥ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ልንነግረው ብቻ በፊቱ መሆንን ራሳችንን ማስለመድ አለብን። እግዚአብሔርን መፈለግን ነፍሳችንን ማስተማር አለብን። ለምሳሌ ይሄ ምድራዊ ስጋችንን ምሳሌ አድርገን ብንመለከት፥ በየቀኑ እንዲራብ ተደርጎ የተፈጠረ ነው። ትላንት በልቻለሁ ትላንት ጠግቤያለሁ ብሎ ዛሬ ምግብን ከመፈለግ ወደኃላ አይልም። ትላንት ምግብ ብንበላም የበላነው ለትላንትና ነው። ዛሬ እንደገና ይርበናል። ትላንት ውሀ ብንጠጣም፥ የጠጣነው ለትላንትና ነው። ዛሬ እንደገና ይጠማናል። መንፈሳችንም የተሰራው በትላንትና ሙላት ሊቀጥል አይደለም። በቃ የተሰራነው እድሜ ልካችንን የእግዚአብሔር ረሀብተኞች ለመሆን ነው። ማብቂያ በሌለበት ረሀብ ውስጥ ልንኖር። በረሀባችን ልክ እየበላን፥ በጥማታችን ልክ እየጠጣን እንድንረካ፥ ዛሬ ደግሞ ትላንት ምንም እንዳልበላ ሰው ልንራብ ነው የተሰራነው። እየበላን ስንቀጥል እስትንፋሳችን ይቀጥላል። መብላታችን በሕይወት መቀጠላችንን ይወስናል። በሕይወት መቆየታችን ከመብላታችን ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው። የእግዚአብሔር ቃል በትንቢተ አሞጽ 5፡4 ላይ ሲናገር “እግዚአብሔርም ለእስራኤል ቤት እንዲህ ይላልና፡ እኔን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁና።” ይላል። ሰው ምግብ በመብላት እየጠነከረና እየበረታ እስትንፋሱን እንደሚያስቀጥል ሁሉ፥ እግዚአብሔርን መፈለጋችን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ሕብረት ወይንም መንፈሳችንን ህያው እያረገ የሚያስቀጥልልን ዋና ነገር ነው። ሰው ምግብ መፈለግን ባቆመ መጠን ቀስ እያለ ወደ ሞት እንደሚሄድ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባልፈልግነው መጠን የምንሄደው ወደ ሞት እንደሆነ ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው።