ሸክም
የነህምያን ታሪክ ሳጠና ከሕይወቱና ከአገልግሎቱ ከተማርኳቸው ጥቂት ነጥቦች ውስጥ፥ ምናልባት ለሰዎች የሚቀር ነገር ካለ ብዬ ለመጻፍና ለማካፈል ብእሬን አንስቻለሁ።
ታሪኩን አብዛኞቻችን እንደምናውቀው፥ ነህምያ እግዚአብሔር በዘመኑ የነበረውን ሀሳብ ያገለገለበት አስገራሚ የእግዚአብሔር ሰው ነበር። በስራው የንጉስ ጠጅ አሳላፊ ሲሆን፥ ምንም አይነት የኑሮና የኢኮኖሚ ችግር ሳይኖርበት የሚኖር ሰው ነበር። እስራኤል በባቢሎን ምርኮ ተገዝታ ወደ ባቢሎን ስትማረክ፥ እርሱ ወይንም ቤተሰቦቹ ተማርከው ወደ ባቢሎን ከፈለሱት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነበር። ከእለታት አንድ ቀን ታዲያ ከነህምያ ወንድሞች አንዱ የሆነውን አናኒን እንዲሁም ከአናኒ ጋር ከይሁዳ የመጡትን ሰዎች ነህምያ ይጠይቃል ። “ወንድሞቼ የመጣችሁት ከይሁዳ ነው። እስኪ ጥቂት ነገር ንገሩኝ፥ ይሁዳ እንዴት ናት? ከምርኮ የተረፉትስ የአይሁድ ሰዎች እንዴት ናቸው?” በማለት ወንድሞቹን ይጠይቃል። ነህምያ ይሄንን ጥያቄ የጠየቀው እንዲያው ለማወቅ ብቻ አልነበረም። የእግዚአብሔር ከተማ ስለሆነችው ስለ ኢየሩሳሌም በእርግጥም ግድ ስለሚለው ነው። አንዳንዴ እኮ እንዴት ነህ ወይንም እንዴት ነሽ ማለት ልማድ ስለሆነብን ሰዎችን እንጠይቃለን እንጂ የጠየቅነው ሰው ምንም ቢሆን ከልባችን ግድ ላይለን ይችላል። በተለይ ደግሞ ያንን ሰው ብዙም የማንቀርበው ከሆነ። ሰላም ነው? ማለት ለምዶብን እንጂ፥ የጠየቅነው ሰው ሰላም ባይሆን ሰላም የነሳውን ጉዳይ መርዳት በምንችልበት አቅም ለመርዳት ላንሄድ እንችላለን። ነህምያ ስለ ኢየሩሳሌምና ከምርኮ ስለተረፉት አይሁድ ደህንነት ከጠየቀ በኋላ፥ ከወንድሞቹ የሰማው ምላሽ በእጅጉ ስሜቱንና ልቡን የሚጎዳ ነበር። “ይኸውልህ ነህምያ ኢየሩሳሌም ደህና አይደለችም። ቅጥሮቿ በሙሉ ፈርሰዋል። በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል። ከምርኮ የተረፉት የአይሁድ ቅሬታዎች ደግሞ በታላቅ መከራና ስድብ ውስጥ አሉ ብለው ይመልሱለታል። ነህምያ ይሄንን ዜና ከሰማ በኋላ ታዲያ የሰማው ዜና በእርሱ ዘንድ ተራ ጉዳይ አልነበረም። ቁጭ ብሎ እንዳለቀሰ እንዲሁም ትንሽ ቀን ሳይሆን በጣም ብዙ ቀን በሀዘን ውስጥ እንደቆየ ክፍሉን ስታነቡ በራሱ አንደበት የሚናገረው ነው። ታዲያ ነህምያ ብዙ ቀን ካዘነና ካለቀሰ በኋላ ልቡ ውስጥ የተፈጠረው ከባድ ሀዘን ሁለት ወሳኝ ነገሮችን ወደ ማድረግ እንደመራው ከዚህም የተነሳ በዘመኑ የነበረውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽሞ ሊያልፍ እንደቻለ እንመለከታለን።
ነህምያ ስለ ኢየሩሳሌም መፍረስ የሰማው ዜና ካደረሰበት ከባድ ሀዘን በኋላ፥ በመቀጠል የወሰደው እርምጃ በጾምና በጸሎት የእግዚአብሔርን ፊት ወደ መፈለግ መሄድ እንደነበር በራሱ አንደበት እንዲህ በማለት ይናገራል።
“ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፥ አያሌ ቀንም አዝን ነበር፤ በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር፥ እንዲህም አልሁ። አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ፥ ለሚወድዱህና ትእዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ፥ እኔ ባሪያህ ዛሬ በፊትህ ስለ ባሪያዎችህ ስለ እስራኤል ልጆች ሌሊትና ቀን የምጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ጆሮህ ያድምጥ፥ ዓይኖችህም ይከፈቱ፤ በአንተ ላይም ያደረግነውን የእስራኤልን ልጆች ኃጢአት እናዘዝልሃለሁ፤ እኔና የአባቴም ቤት በድለናል። እኛም በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሠርተናል፤ ለባሪያህም ለሙሴ ያዘዝኸውን ትእዛዝና ሥርዓት ሕግም አልጠበቅንም። አሁንም ብትተላለፉ በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ወደ እኔ ብትመለሱ ግን ትእዛዜንም ብትጠብቁ ብታደርጓትም፥ ከእናንተ ሰዎች እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ምንም ቢበተኑ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፥ ስሜም ይኖርበት ዘንድ ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ ብለህ ለባሪያህ ለሙሴ ያዘዝኸውን ቃል እባክህ አስብ። እነዚህም በታላቅ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዠሃቸው ባሪያዎችህና ሕዝብህ ናቸው። ጌታ ሆይ፥ ጆሮህ የባሪያህን ጸሎት፥ ስምህንም ይፈሩ ዘንድ የሚወድዱትን፥ የባሪያዎችህን ጸሎት ያድምጥ፤ ዛሬም ለባሪያህ አከናውንለት፥ በዚህም ሰው ፊት ምሕረትን ስጠው። እኔም ለንጉሡ ጠጅ አሳላፊው ነበርሁ።” (መጽሀፈ ነህምያ ምእራፍ 1 ከቁጥር 4 ጀምሮ)
-ነህምያ ልቡ ውስጥ የተፈጠረው ከባድ ሀዘን ይዞት የሄደው ወደ ጾም ጸሎት ነው። ብዙ ጊዜ እኛ በተለያዩ ነገሮች ስናዝን ሀዘናችን ወደ ማጉረምረም ወይንም እግዚአብሔርን ወደ ማኩረፍ ይወስደን ይሆናል። ነህምያም ቢሆን እግዚአብሔር የተስፋ ምድር የሆነችውን ኢየሩሳሌምን እንዲሁም የኪዳን ህዝብ የሆነውን የአይሁድ ህዝብ እንዴት ይጥላል? እንዴትስ ለመፍረስ አሳልፎ ይሰጣል ብሎ ወደ ማጉረምረም እኮ መሄድ ይችል ነበር። ሁልጊዜ ሀዘን ሲያጋጥመን፥ ያ ልባችን ውስጥ የተፈጠረው የሀዘን ስሜት ውሳኔያችንን ወዴት እንደሚመራው በጥንቃቄ ማሰብ አለብን። ሀዘን ወደ ሁለት ተቃራኒ አቅጣጫዎች ልባችንን ሊወስደው ይችላል። ወይ መፍትሄ ፍለጋ ወደ እግዚአብሔር ልባችንን ሊያቀርበው ይችላል። ወይንም ደግሞ በማጉረምረም እየሞላ ልባችንን ከእግዚአብሔር ሊያርቀው ይችላል። በየትኛውም ሀዘን ውስጥ ስናልፍ ውስጣችን የተፈጠረውን ስሜት ችላ ሳንል ትኩረት ሰጥተን ማዘንም ካለብን ማዘናችን ስህተት ባይሆንም፥ ይሄ ልባችን ውስጥ የተፈጠረው ሀዘን ግን ልባችንን ወዴት እንደሚወስደው በጥንቃቄ መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ለዚህ ነው ከባድ ሀዘን የሰዎችን የሕይወት አቅጣጫ ሊለውጥ የሚችለው። ነህምያ የነበረበት ሀዘን የወሰደው የእግዚአብሔርን ፊት ወደመፈለግ ነበር። የእርሱን እንዲሁም የአባቶቹን ሀጢያት በመናዘዝ መጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት ካስተካከለ በኋላ፥ ጠጅ በማሳለፍ በሚያገለግለው በንጉሱ ፊት ምህረትና ሞገስ እንዲሰጠው አምላኩን ይለምናል።
ነህምያ ከጾመና ከጸለየ እንዲሁም ጉዳዩን ሁሉን ለሚችለው አምላክ ካስረከበ በኋላ በሁለተኛ ደረጃ የወሰደው እርምጃ፥ የፈረሰውን ቅጥር ወደ መስራት ማሰብ ነበር። ይሄንን የፈረሰ ነገር ለመገንባት እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ ወደሚል ጥያቄ ነበር የገባው። ከጸለየ በኋላ እርሱ ማድረግ የሚችላቸውን ነገሮች ደግሞ ማሰብ ጀመረ። አንዳንድ ጊዜ እኛ በምንችለው አቅም መርዳት የምንችላቸው ችግሮች እያሉ፥ በጸሎት ሰበብ ቸል የምንላቸው ነገሮች አሉ። እግዚአብሔር እኮ የሚያደርገው እኛ የማንችላቸውን ከእኛ አቅም በላይ የሆኑትን ነገሮች ነው። የኢየሩሳሌምን ቅጥር መስራት እኮ እንዲያውም ነህምያ ብቻውን ማከናወን የሚችለው ነገር አልነበረም። የነህምያ እምነት ግን የሰማዩ አምላክ ያከናውንልናል እኛ ባሪያዎቹ ደግሞ ተነስተን እንሰራለን። የምንችለውን እንሰራለን፥ የእኛን ሀላፊነት እንወጣለን። እግዚአብሔር ደግሞ ያከናውነዋል፥ ከእኛ አቅም በላይ የሆነውን እርሱ ያደርገዋል ነበር እምነቱ። እግዚአብሔር እኛ መሄድ የምንችለውን ርቀት እንድንሄድ ይፈልጋል። ምክኒያቱ ደግሞ ክብሩን የሚገለጠው በእኛ አለመቻል ውስጥ ስለሆነ ነው።
-ይሄ የነህምያን ታሪክ ሳነብ አንድ በጣም የገረመኝ ነገር፥ እግዚአብሔር አንድም ቀን ለነህምያ ሂድና ቅጥሩን ስራ ብሎ ትእዛዝ ሲሰጠው አንመለከትም። ብዙ ጊዜ እኮ በቃሉ ላይ የተጻፉልንን የአባቶቻችንን ታሪክ ስንመለከት፥ የአብዛኞቹ አባቶቻችን ታሪክ የሚጀምረው እግዚአብሔር ወይ በድምጽ፣ ወይንም በሕልምና በራእይ አለዚያም ደግሞ ሰዎችን በመጠቀም እነዚህ አገልጋዮች ጋር መጥቶ የልቡን ሀሳብ ለእነርሱ ከመንገር ነው። ብዙ ጊዜ ነብያቶችና የእምነት አባቶች ጉዞ የሚጀምሩት የእግዚአብሔርን ድምጽ ሰምተው ነው። አብርሀምን ብንመለከት፣ ሙሴን ብንመለከት፣ ኢያሱን ብንመለከት፣ አብዛኞቹንም ነብያቶች ብንመለከት፥ የእግዚአብሔርን ድምፅ ሰምተው ጉዞ የጀመሩ ወይንም ድምፁን እየሰሙ የጀመሩትን መንገድ የቀጠሉ ሰዎች ናቸው። የተለማመድነው እግዚአብሔር አባቶቻችንን በማዘዝ ሲልካቸው እነርሱ ደግሞ እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ነገሮች በመታዘዝ ማድረግ ያለባቸውን ነገሮች ሲያደርጉ ነው። የነህምያን ታሪክ ለየት የሚያረገው፥ መፅሀፉን ጀምራችሁ እስከምትጨርሱ ድረስ እግዚአብሔር አንድም ቀን ወደ ነህምያ መጥቶ ይሄንን አድርግ ብሎ ሲያዘው አንመለከትም። እግዚአብሔር ታላቅና የኪዳን ምድር የሆነችውን አንድ ታላቅ ሀገር ኢየሩሳሌምን እንደገና ለማደስ ሲነሳ ከተጠቀመባቸው ጥቂት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው ነህምያ። ነገር ግን አንድም ቀን እግዚአብሔር ወደ ነህምያ መጥቶ ይሄንን የልቡን ሀሳብ ሲያጫውተው አንመለከትም። ሌላው ቀርቶ ቅጥሩን በመገንባት ላይ እያለ እንኳን እግዚአብሔር መጥቶ በርታ ልጄ አይዞህ ሲለው አናነብም። እነ ጦቢያ እነ ሰንበላጥ ነህምያ የጀመረው መልካም ስራ ላይ ትልቅ ተግዳሮት ሲሆኑ እራሱ እግዚአብሔር መጥቶ አይዞህ ብሎ ድምጽ ሲልክለት አንመለከትም።
ሙሉ መጽሐፉን ስታነቡ አንድም ጊዜ እግዚአብሔር ድምጹን ወደ ነህምያ አልላከም። ነገር ግን ነህምያ የኪዳን ምድር የሆነችውን የኢየሩሳሌምን ታላቅ ቅጥር ያደሰና የገነባ የፈረሰችውን የኪዳን ምድር እንደገና ለማቆም እግዚአብሔር ካስነሳቸውና ከተጠቀመባቸው ጥቂትና ታላላቅ ሰዎች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው ነበር። እግዚአብሔር ታዲያ በነህምያ ዘመን ላይ ወደ ነበረው ታላቅ አገልግሎት እንዴት ነው የመራው ብለን ስንመለከት፥ በቃ በነህምያ ልብ ውስጥ ሸክምን ብቻ ነው ያስቀመጠው። እግዚአብሔር ጉዳዩን ሸክም አርጎ ልቡ ውስጥ አስቀመጠ። እግዚአብሔር በዘመኑ ወደነበረው ታላቅ አገልግሎት ነህምያን የመራው ልቡ ውስጥ ባስቀመጠው ሸክም ነበር።
ነህምያ እኮ አንድ የቤተክርስቲያን አገልጋይ እራሱ አልነበረም። አንድ በቃ እንደማንኛውም ሰው ስራ የሚሰራ የንጉስ ጠጅ አሳላፊ ብቻ ነው የነበረው። ያውም ሀገሩ ባልሆነ በምርኮ ሀገር ሄዶ ለአህዛብ ንጉስ ጠጅ የሚያሳልፍ አንድ ተራ የሚመስል ሰው፥ ነገር ግን የኪዳን ምድር ስለሆነችው ስለ ኢየሩሳሌም ግድ የሚለው ትልቅ ልብ የነበረው ሰው ነበር። የሚገርመው ደግሞ የኢየሩሳሌምን ቅጥር መፍረስ የሰማ የመጀመሪያው ሰው እኮ አልነበረም ነህምያ ። እንዲያውም ዜናውን ወደ ነህምያ ያመጡለት ነገሩን በገዛ አይናቸው የተመለከቱ ሰዎች ነበሩ። ነገሩ ግን ስለ ኢየሩሳሌም መፍረስ ያመጡለት ዜና በነህምያ ልብ ውስጥ መክበዱ፥ እግዚአብሔር ነገሩን ሊሰራ የወደደው በነህምያ መሆኑን ያመለክተናል። ነገሩ ወደ ነህምያ ሲመጣ፥ ሌሎቹ እንደሰሙት ተራ ዜና አልነበረም። ይልቁንም፥ ስሜቱን በእጅጉ የጎዳ፣ ልቡን ክፉኛ ያሳዘነ፣ በሚያገለግለው በንጉሱ ፊት ፊቱ እስከሚለወጥና የቀድሞ ስራውን በትክክል መስራት እስከሚያቅተው ድረስ ስሜቱ ላይ እጅግ ከባድ ተጽእኖ የፈጠረ ከባድ ዜና ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሌሎች ሰዎች የሰሙት ዜና እኛ ጋር ሲመጣ ተራ ዜና ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ሌሎች ሰዎች እንደ ቀላል ያለፉት ጉዳይ፥ እኛ ልብ ውስጥ ከባድ ተጽእኖ የሚፈጥር እና ውስጣችን ሸክም ሆኖ የሚቀመጥበት ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ምናልባት እግዚአብሔር በሰማነው ወይንም ባየነው መፍረስ ውስጥ እኛን መፍትሄ ሊያደርግ ያሰበበት ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ምናልባት እግዚአብሔር ነገሩን መልሶ መገንባት ያሰበው በእኛ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጉዳዮች ልባችን ውስጥ ከሌሎች ሰዎች ይልቅ ከከበዱ፥ ለነገሩ ጊዜ ሰጥቶ መጸለይና ነገሩን ለማስተካከል የምንችለውን ርቀት መሄዳችን የእግዚአብሔር ሀሳብ ሊሆን ይችላል። በነህምያ ሕይወት ውስጥ የነበረውን አንድ ትልቅ ከተማ የሚገነባበትን ታላቅ ፈቃዱን እግዚአብሔር የፈጸመው፥ በነህምያ ልብ ውስጥ ባስቀመጠው ሸክም ብቻ ነበር። ውስጣችን ያለው ሸክም ምንድነው? ሌሎች እንደ ቀላል ያለፉት፥ ሌሎችን ያልረበሸ እኛ ልብ ውስጥ ግን የከበደው የፈረሰ ነገር ምንድነው? ወደ እግዚአብሔር በጾምና በጸሎት ይዘነው እስክንቀርብ እግዚአብሔር እኛን እየጠበቀ ያለበት ጉዳይ እንዲሁም በጸሎታችን ውስጥ የምንገነባበትን አቅም ሊለቅልን አምላካችን እኛን የሚጠብቅበት ጉዳይ ምንድነው?
የነህምያን ታሪክ ስናነብ ከነበረው የአገልግሎት ጉዞ ከምንማራቸው መልካም ጥበቦች ውስጥ ደግሞ ሌላኛው ይሄ ነው። ነህምያ ቅጥሩን መልሶ ለመስራትና ለመገንባት የንጉሱን ፈቃድና እርዳታ ከለመነ በኋላ ቀጥታ መንገዱን ያቀናው ወደ ፈረሰችው ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ነበር። ታዲያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የፈረሰውን ቅጥር ዞሮ እየተመለከተ ለኢየሩሳሌም ያደርገው ዘንድ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ሸክም ጊዜው እስከሚደርስ ድረስ ለማንም ሰው እንዳልተናገረ ነህምያ በራሱ አንደበት ይናገራል። ጊዜው እስከሚደርስ ድረስ፥ የሚናገርበት ትክክለኛው ሰዓት እስከሚመጣ ድረስ ልቡ ውስጥ እግዚአብሔር ያስቀመጠውን ሸክም ለሌሎች ለመናገር ትክክለኛውን የእግዚአብሔርን ጊዜ ይጠብቅ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ያለጊዜው የምንገልጣቸው ራእዮች ጊዜያቸውን ሳይጠብቁ ከአንደበታችን ስለሚወጡ ጠላት ነገሮችን በአጭሩ ለማስቀረት እድል ሊያገኝ ይችላል። አያችሁ ትልቅ የእግዚአብሔር ሀሳብ ያለበትን የእግዚአብሔር ሰው ሙሴን ጠላት ለመግደል የፈለገው ገና በህጻንነቱ ነበር። ሄሮድስ ኢየሱስን ለመግደል ያሰበው ሁለት አመት እንኳን ሳይሞላው ነበር። ልባችን ውስጥ ያለውን ራእይ ጠላት ማጥፋት የሚፈልገው ገና ራእዩ ህጻን እያለ በሀሳብ ደረጃ እያለ ነው። ከነህምያ የአገልግሎት ጉዞ የምንማረው ጥበብ ግን ይሄ ነው። ምንም አይነት ነገር እግዚአብሔር ሲናገረን ወይንም ልባችን ውስጥ ሲያስቀምጥ፥ ሄዶ ለሰዎች ሁሉ ማውራት አያስፈልግም። ጊዜው እስከሚደርስ ድረስ ዝም ማለት፥ ዝም ብሎ ስለ ነገሩ መጸለይ መልካም ነው። በዝምታችን ውስጥ ውስጣችን ያለው የእግዚአብሔር ሀሳብ ይጠበቃል። በጸሎታችን ውስጥ ራእያችን ያድጋል፥ ይጠነክራል። ኢየሱስ ኢየሱስ መሆኑን ለመግለጥ 30 አመት ሙሉ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለሰዎች ሳይናገር ትክክለኛውን የእግዚአብሔርን ጊዜ ጠብቋል።
ኤልሳቤጥም ለብዙ ጊዜ ልጅ ባለመውለዷ ብዙ ጊዜ ጠብቃ የእግዚአብሔር ጊዜ ደርሶ እግዚአብሔር ጸሎቷን ሲመልስና እርጉዝ መሆኗን ስታውቅ፥ ሰዎች ሰዎች እግዚአብሔር እኮ ሰማኝ ልጅ ልወልድ ነው ብላ ወደ አደባባይ አልወጣችም። ይልቁንም ልክ ማርገዟን ስታውቅ “ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል ስትል እራሷን ለ5 ወራቶች ሸሸገች” በማለት ከህይወቷ እንማር ዘንድ በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 1 ላይ ተጽፎልናል። ኤልሳቤጥ እግዚአብሔር ጸሎቷን ሲሰማና ማርገዟን ስታውቅ ራሷን ሸሸገች። ውስጧ ያለው ጽንስ እስኪያድግና እስኪጠነክር ድረስ፥ እግዚአብሔር የእርሷን ጊዜ ሳይሆን የራሱን ጊዜ ጠብቆ በውስጧ ያስቀመጠው ጽንስ አድጎ እራሱ ለሰዎች መታየት እስኪጀምር ድረስ እሷ እራሷን ሸሽጋ ዝም አለች። ነህምያም እንዲሁ ትክክለኛው ጊዜ እስኪመጣ ድረስ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ሸክም አጠገቡ ለነበሩት ሰዎች አለማውራቱ፥ የኢየሩሳሌምን መልካም ነገር የማይፈልጉትን የእነ ጦቢያና የእነ ሰንበላጥን ተቃውሞ በጥበብ አሸንፎ የተሰጠውን የአገልግሎት ሀላፊነት ከግብ ያደርስ ዘንድ ረድቶታል።