Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ፍለጋ

ፍለጋ

የዘጸአትን መጽሀፍ ሳነብ፥ አንድ እስከዛሬ ያላስተዋልኩትን ነገር አነበብኩ። በመጽሀፉ 33ተኛ ምእራፍ ላይ እንደሚናገረው፥ ሙሴ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር የሚገናኝበትን የመገናኛ ድንኳን የተከለው፥ ሰፈር ውስጥ አልነበረም። የተከለው ከሰፈር ውጪ፣ ከመንደር ውጪ፣ አብዛኛው ሰው ከሚኖርበት ሰፈር ውጪ ነበር። ታዲያ እዚያው ምእራፉ ላይ እንደሚናገረው፥ እግዚአብሄርን እፈልገዋለሁ የሚል ሰው ሁሉ ከሰፈሩና ከመንደሩ እየወጣ፥ የመገናኛው ድንኳን ወዳለበት ቦታ በመሄድ እግዚአብሄርን ያገኝ ነበር። ቃሉ ለትምህርታችን እንደመጻፉ፥ ለህይወቴ የምማረውን ነገር ለማስተዋል ጥቂት ዝም አልኩ። ህዝቡ ከእግዚአብሄር ጋር ሊገናኝ የሚችልበትን የመገናኛ ድንኳን ለምንድነው ሙሴ ከሰፈር ራቅ አርጎ የተከለው? ለምንድነው እዚያው ለህዝቡ ቅርብ የሆነ ሰፈር ያልተከለው? እግዚአብሄር እርሱን ፍለጋ የምንሄደውን ርቀት ማየት ስለሚፈልግ ነው። መፈለግ ማለት ያንን የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት የምናደርገው ብርቱ ጥረት ማለት ነው። እግዚአብሄርን ለማግኘት የምናደርገው ብርቱ ጥረት እግዚአብሄርን ያስደስተዋል። ብዙ ጊዜ ፍለጋ ውስጥ የምንገባው፥ ማግኘት ያቃተን ነገር ሲሆን ነው። እግዚአብሄር እኔን ፈልጉ ፊቴን ፈልጉ ብሎ ሲያዘን ግን ፊቱ ተፈልጎ ስለማይገኝ አይደለም። የፍላጎታችንን ብርቱ ጥረት ካሳ በመስጠት የሚደሰት አምላክ ስለሆነ ነው። እንኳንና እግዚአብሄርን ለማግኘት ቀርቶ፥ ሌሎችንም ነገሮች እኮ በህይወታችን ለማግኘት ኢየሱስ እንደነገረን “ለምኑ ይሰጣችሁዋል። ፈልጉ ታገኙማላችሁ” በማለት፥ መፈለግ ነገሮችን የምናገኝበት ዋና መንገድ መሆኑን ተናግሯል። እግዚአብሄርም በህይወታችን አንድን ነገር ሊያደርግ ሲፈልግ፥ መጀመሪያ በልባችን የሚያስቀምጠው ፍላጎትን ነው። መጀመሪያ በልባችን የሚያስቀምጠው መፈለግን ነው። የእስራኤል ህዝብ እግዚአብሄርን ለማግኘት፥ ከሰፈራቸው ውጪ ወደተተከለው የመገናኛ ድንኳን መሄድ ነበረባቸው። እግዚአብሄርን ለማግኘት ካሉበት ሰፈር መውጣት ነበረባቸው። ካሉበት መንደር፣ ከሚኖሩበት፣ ሰዎች ከበዙበት፣ ግርግርና ጫጫታ ከሞላበት ሰፈር ወጥተው፥ ከሰፈርና ከመንደራቸው ውጪ ወደተተከለው ወደ እግዚአብሄር ድንኳን መሄድ ነበረባቸው። የእግዚአብሄርን ህልውና በሙላት የምናገኘው፥ ከጫጫታና ከግርግር ተለይተን ለብቻችን በምሆንበት የጸጥታ ቦታችን ነው። ከብዙሀኑ ድምጽና ካለንበት ሰፈር ወጥተን ወደ መገናኛው ድንኳን መሄድን እራሳችንን ማስለመድ አለብን። መውጣት፣ ብቻችንን መሆን መልመድ። ዝም ባለ ቦታ ሆነን ልባችንን ወደ እግዚአብሄር ማንሳት። የምንወደውን ሰው ለማግኘት ህይወታችን ላይ ያሉትን ነገሮች እንደምናመቻች ሁሉ፥ እስትንፋሳችንን በእጁ ይዞ ከምንም ነገር በላይ ለእኛ አስፈላጊ የሆነውን እግዚአብሄርን ለማግኘት ካለንበት ሰፈርና መንደር መውጣት። ወደ መገናኛው ድንኳን መሄድ። እግዚአብሄርን ፍለጋ። ህልውናውን ፍለጋ። ድምጹን ፍለጋ። መገኘቱን ፍለጋ። ከእርሱ ጋር መሆንን ፍለጋ። አንድ በፍቅር የተያዘች ነፍስ፥ ያፈቀረችውን ሰው ለማግኘት መሄድ ያለባትን ርቀት ሁሉ እንደምትሄድ፥ ልክ እንደዚያ እግዚአብሄርን ፍለጋ መሄድ። 

የእስራኤል ህዝብ እግዚአብሄርን ለማግኘት ከሚኖሩበት ሰፈር ወጥተው የመገናኛው ድንኳን ወደ ተተከለበት ቦታ መሄድ ነበረባቸው። ሙሴ ደግሞ ከእግዚአብሄር ጋር ጊዜ ለማሳለፍና ለመነጋገር ወደ ሲና ተራራ መውጣት ነበር። ተራራ መውጣት አድካሚ ነው። ቀጥ ያለ መንገድ እንደመሄድ ወይንም ቁልቁለት እንደመውረድ ቀላል አይደለም። ምናልባት አንዳንድ ጊዜ ለመዝናናት hiking ስንሄድ ድካሙን እናውቀዋለን። እኛ ለመዝናናትና ተራራው ጫፍ ላይ ወጥተን ፎቶ ለመነሳት ነው የምንሄደው። ሙሴ ግን የሲናን ተራራ ብቻውን የሚወጣው፥ 40 ቀንና 40 ሌሊት እዚያው ተራራው ላይ ምንም ምግብ ሳይበላ ለመቆየት ነው። መንገዱ ታዲያ ምንም አድካሚ ቢሆንም፥ ተራራው ጫፍ ላይ በእግዚአብሄር ህልውና ውስጥ የሚያሳልፈው ጊዜ አለመብላትና አለመጠጣቱን ሁሉ እንደሚያስረሳው እርግጠኛ ነኝ። ተራራው ጫፍ ላይ ከወጣ በኋላ የሚጠብቀው የእግዚአብሄር ክብር ያለበትን ዓለም እንደሚያስረሳው ምንም አልጠራጠርም። እኛ እንኳን አብረን ስናመልክ ወይንም በቤታችን ለጥቂት ሰአታቶች ስንጸልይ፥ በሩቅ የሚሰማን የእግዚአብሄር ህልውናና ክብር ሁሉን ነገር አይደል እንዴ የሚያስረሳን! ሙሴ እኮ ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር እግዚአብሄር ፊት ለፊት በግርማ ሞገሱ እየወረደ የሚያናግረው ሰው ነበር። ሙሴ ወደ ተራራው ሲወጣ እኮ፥ የእግዚአብሄር ደመና ተራራውን ይሸፍነው ነበር። የእግዚአብሄር ክብር በተራራው ላይ ይቀመጥ ነበር። በዘጸአት 24 ላይ እንደሚናገረው፥ የእግዚአብሄር ደመና ስድስት ቀን ተራራውን ከሸፈነው በኋላ፥ በሰባተኛው ቀን ሙሴ ወደ ደመናው ውስጥ እንዲገባ ተጠርቶ ነበር። በተራራው ራስ ላይ የሚወርደው የእግዚአብሄር ክብር፥ ልክ እንደሚያቃጥል እሳት እንደነበር የእግዚአብሄር ቃል ይናገራል። ምን አይነት ነገር ነው? ሙሴ እኮ በእግዚአብሄር ፊት ሆኖ ጊዜ ሲያሳልፍ፥ ልክ እንደ እኛ ለአንድ ወይንም ለሁለት ሰአት ጸልዮ መነሳት ሳይሆን፥ ለ6 ቀናቶች በተራራው ላይ ቆሞ መጠበቅ፥ ከዚያ ወደ  ደመናው ውስጥ ሲጠራ በመግባት፥ በእግዚአብሄር ክብርና ህልውና ውስጥ ሆኖ 40 ቀንና 40 ሌሊት ሙሉ እዚያው መሆን። እዚያው ቦታ መቆየት። የጸሎት ስነ ስርአት አከናውኖ ጨርሶ ወደ ሌላ ጉዳይ ውስጥ መግባት ሳይሆን፥ በቃ እዚያው መሆን። እዚያው መቆየት እዚያው መዋልና ማደር።  

ታዲያ ግን የእግዚአብሄር መገኘትና ህልውና እንደማይጠገብ የምታውቁት፥ ሙሴ እግዚአብሄር ፊት ለፊት ወርዶ የሚያናግረው ሰው ቢሆንም፥ “ክብርህን አሳየኝ” እያለ መጠየቁ ነው። በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ ከተጻፉት ትልልቅ የእግዚአብሄር ሰዎች መካከል፥ እንደ ሙሴ የእግዚአብሄርን ክብር ያየ ሰው ያለ አይመስለኝም። የእግዚአብሄር መገኘትና ህልውና እንደማይጠገብ የሚያስተምረኝ ደግሞ የሙሴ “ክብርህን አሳየኝ” ጥያቄ ነው። እግዚአብሄር ክብሩን ያሳያችሁ። እግዚአብሄር በህልውናው ያረስርሳችሁ። ሙሴ ታዲያ ወደ ሲና ተራራ ላይ እየወጣ ከእግዚአብሄር ጋር ካሳለፋቸው ጊዜያቶች በኋላ ሁልጊዜ ከእግዚአብሄር ዘንድ ወደ ህዝቡ ይዞ የሚመጣው መልእክት ነበረው። አንድም ጊዜ ወደ ተራራ ላይ ወጥቶ ከእግዚአብሄር ጋር ቆይቶ ሲመጣ ያለ መልእክት ወደ ህዝቡ ተመልሶ አያውቅም። በእግዚአብሄር ህልውና ውስጥ የሚቆይ ሰው፥ ሁልጊዜ መልእክት አለው። የሚለው ነገር አለው። ሙሴ ከተራራው ሲወርድ ይዞ የመጣው፥ የእግዚአብሄር ህጎች የተጻፉበትን ጽላቶች ነበር። እግዚአብሄር ለህዝቡ እንዲሰጥ የሰጠው ትእዛዝ ነበር። መልእክት ነበረው። አሁንም በዘመናችን ላይ ትክክለኛ የሆነውን የእግዚአብሄርን ሀሳብ ወደ ህዝቡ የሚያመጡት፥ ከእግዚአብሄር ጋር ትክክለኛ ጊዜ የሚያሳልፉ ሰዎች ናቸው። ከእግዚአብሄር ጋር ጊዜ ስታሳልፉ፥ ለሰዎች የምትሉት ነገር ይኖራችኋል። መልእክት ይኖራችኋል። ለዚህ ትውልድ የምታስተላልፉት መልእክት ይኖራችኋል። ላገኛችሁት ሰው ሁሉ የምትሉት ነገር አላችሁ። መንገድ ለጠፋበት ሰው መንገድ ታሳያላችሁ። ግራ ለገባው ሰው መፍትሄ ትሆናላችሁ። ጥያቄ ላለው ሰው መልስ ትሆናላችሁ። እንዲያውም ትዝ አይላችሁም ሳኦል የአባቱ አህዮች ሲጠፉበትና ግራ ሲገባው ወዴት ነበር የሄደው? ትልቅ የእግዚአብሄር ሰው ወደሆነውና ከልጅነቱ ጀምሮ በመቅደስ በእግዚአብሄር ማደሪያ እየዋለና እያደረ የእግዚአብሄርን ድምጽ ወደተለማመደው ወደ ሳሙኤል ነበር የሄደው። እንደገና ደግሞ በ2ኛ ነገስት ምእራፍ 3 ላይ፥ የእስራኤል፣ የይሁዳና የኤዶም ያስ ንጉስ ተጋግዘው ለሰልፍ ወደ ምድረበዳ ሲወጡና በውሀ ጥም ሲጨነቁ ወደ ማን ነበር የሄዱት? ተቀብቶ የእግዚአብሄር መንፈስ ወዳረፈበት ወደ ነቢዩ ወደ ኤልሳእ ነበር። ያቺ ደግሞ በ2ኛ ነገስት ላይ ያለችውና ልጇ የሞተባትን ሱናማዊት ሴት ስትመለከቱ፥ የልጇን መሞት እጅግ በጣም በቅርቧ ላለው ለባሏ እንኳን ሳትናገር፥ መፍትሄ ፍለጋ ሩቅ መንገድ የሄደችው ወደ ነቢዩ ኤልሳእ ነበር። እነዚህ ሰዎች የሰዎች ጥያቄ መልስ ሊሆኑ የቻሉት፣ ለሰዎች ጭንቀትና ሀዘን መፍትሄ ሊሆኑ የቻሉት፣ በእግዚአብሄር ስለተመረጡና በእግዚአብሄር ህልውና ውስጥ ስለሚቆዩ ነው። 

መቼም እያንዳንዳችን ብንጠየቅ፥ ሳናደርግ መሞት የማንፈልጋቸው ህልሞች በልባችን ውስጥ ይኖራሉ። እነዚህ ህልሞች ታዲያ፥ ለራሳችን የሚጠቅመንን ነገሮች ከማግኘት ባለፈ፥ የእግዚአብሄርን ሀሳብ በዘመናችን ከማገልገልና ውስጣችን በተቀመጠው ሸክም አቅጣጫ ሌሎችን ማገልገል፣ ለሆነ ሰው መፍትሄ መሆን፣ የሆነን ሰው መርዳት፣ ለሆነ ሰው መልስ መሆን እንደሚሆን እገምታለሁ። እነዚህ ህልሞቻችን እውን የሚሆኑት ታዲያ፥ ከእግዚአብሄር ጋር ባሳለፍነው ጊዜ ልክ ነው። በእኛ ውስጥ ለሰዎች መልስ የሚሆነው እግዚአብሄር እራሱ ነው። በእኛ ውስጥ ለሰዎች መፍትሄና የልብ እረፍት የሚሆነው እግዚአብሄር እራሱ ነው። የጥያቄዎች ሁሉ መልስ ከሆነው ከእርሱ ጋር ጊዜን ባሳለፍንና በህልውናው በተሞላን መጠን፥ አካባቢያችን ላይ ላሉት ሰዎች አልፎም ለዚህ ትውልድ እረፍትና መፍትሄ አለመሆን አንችልም። የምንሞላው መልስ የሆነውን የእግዚአብሄርን ህልውና ነው። የምንሞላው መንገድ የሆነውን እግዚአብሄርን ነው። የእግዚአብሄርን ቃል ስናነብ፥ በቃሉ ውስጥ ትልልቅ ተጽእኖን በማምጣት የእግዚአብሄርን ሀሳብ ያገለገሉ ሰዎች በሙሉ እግዚአብሄርን በብርቱ የሚፈልጉ ሰዎች ነበሩ። ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ መቼም ሳናነሳ የማናልፈው ንጉስ ዳዊትን ነው። ዳዊት ዘማሪ ነው ደግሞም ንጉስ ነው። መቼም በምድራዊ አስተሳሰብ ካሰብነው፥ የሀገር መሪ ወይንም ንጉስ ከመሆን በላይ የስኬት ደረጃ የለም። ብዙ ሰው ቢችልና ቢሳካለት፥ የንግስና ወንበር ላይ ቢቀመጥ ደስ ይለዋል። መሪ መሆን፣ ንጉስ መሆን፣ ስልጣን ላይ መቀመጥ፣ የስልጣኑን አቅም መጠቀምና ከዚያ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ክብርና ዝና ይፈልጋል። ዳዊት ምንም ይህቺ ምድር ስኬት ብላ ያስቀመጠችው የስኬት ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ቢሆንም እንኳን፥ በዚህ ስኬቱ የረካ ሰው አልነበረም። ብዙ ሰው የሚፈልገው ወንበር ላይ ተቀምጦ፥ ነፍሱ ከፍተኛ የሆነ ጥማት ውስጥ ነበረች። ነፍሱ ባገኘው ስልጣንና ምድራዊ ክብር አልረካችም። ዋላ ውሀ ፍለጋ ውሀ ወዳለበት ስፍራ ሁሉ እንደምትሄድ፥ ነፍሱ እየተነሳች ትሄድበታለች። እግዚአብሄርን ፍለጋ። መገኘቱን ፍለጋ። ህልውናውን ፍለጋ። ዳዊት ታዲያ ሁሉም ሰው የሚመኘው የንግስናና የስኬት ጫፍ  ላይ ቁጭ ካለ በኋላ ስለ መርካት አላወራም። ነፍሱ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡት የጠገበችው፥ እንጨትና ውሀ በሌለበት ምድረበዳ ነፍሱ የተጠማችውን የእግዚአብሄርን ህልውና ሲያገኝ ነው። 

የትኛውም ስልጣን፣ የትኛውም የትምህርት ደረጃ፣ የትኛውም የገንዘብ ክምችት ሊሞላ የማይችለውን የነፍሳችንን ክፍተት የሚሞላው፥ የእግዚአብሄር ህልውና ብቻ ነው። ያልረካነው፥ የፈልግነው የትምህርት ደረጃ ጋር ስላልደረስን፣ ስላላገባንና ስላልወለድን ወይንም ገንዘባችን የምንፈልገው ደረጃ ስላልደረሰ አይደለም። እርካታ የሚባለው የእርካታ ደረጃ መድረስ ያቃተን፥ ቢሞላልን ብለን ያሰብናቸውና የተመኘናቸው ነገሮች ስላልሞሉልን አይደለም። የነፍሳችን ክፍተት በእግዚአብሄር መገኘት ስላልተሞላ ነው። በብርቱ መፈለግ ያለብንን ትተን፥ በብርቱ መፈልግ የሌለብንን እየፈለግን ስለሆነ ነው። ያልረካነው፥ ሊያረካን ለሚችለው አምላክ የሚገባውን ጊዜ ሳላልሰጠነው ነው። መልሱ እኛ መልስ ይሆናል ያልነው ነገር አይደለም። መልሱ የእግዚአብሄር በህይወታችን በሙላት መገኘት ነው። ምድራዊውን ህይወት እየኖርን፥ ልባችንን ግን እርሱን ወደ መፈልግ ማንሳት አንችላለን። ጠዋት ስንነሳ ከሁሉ ነገር አስቀድመን እግዚአብሄርን እንፈልገው። ቀን በስራችን ቦታ ስንውል፥ በምናገኛቸው የስራ ክፍተቶች እግዚአብሄርን እንፈልገው። ወደ ቤታችን እየመጣን ወይንም መሄድ ወዳለብን ቦታ እየሄድን እግዚአብሄርን እንፈልገው። በቅዱሳን ጉባኤ የእግዚአብሄር ስም ወደሚጠራበት ቦታ ከመሄድ አንዘግይ። በሰጠን እስትንፋስ መልሰን እርሱን እናክብረው። መልሰን እርሱን እንፈልገው። ይሄ የህይወት ልምምዳችን ሲሆን፥ አለመርካት አንችልም፡፡ አካባቢያችን ላሉት ሰዎች መፍትሄና መልስ አለመሆን አንችልም። የተፈጠርንበትን ዋና አላማ ሳናሳካ ማለፍ አንችልም። በቅርቡ በዙፋኑ ፊት ስንቆም፥ የማንቆጭበትን ህይወት አለመኖር አንችልም። 

 መወደድ 

መወደድ 

 ዝግጅት

 ዝግጅት