Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

መታዘዝ

መታዘዝ

ዛሬ አስፈላጊ የሆነ ቀጠሮ ስለነበረኝ በጠዋት ነበር ለመሄድ የተነሳሁት። መሄድ የነበረብኝ ቦታ እኔ ከምኖርበት ሰፈር ትንሽ ራቅ ያለ ስለነበር፥ የቦታውን አድራሻ ወስጄ ስልኬን ወደዛ ቦታ እንድትመራኝ በትህትና ጠየኳት። እግዚአብሄር ይስጣት ለደቂቃ እንኳን ሳታንገራግር ነው እሺ ብላ የምፈልግበት ቦታ ያደረሰችኝ። እንዲሁ ግን አልደረስኩም። ወደምፈልገው ቦታ ለመድረስ አርጊ ያለችኝን ሁሉ ነው ያደረኩት። የእሷን ምሪት ተማምኜ ሂጂ ባለችኝ መንገዶች ሁሉ ሄድኩኝ:: ወደ ቀኝም ወደ ግራም ታጠፊ ስትለኝ አንቺ የተሻለ ታውቂያለሽ ብዬ በእሷ ላይ ያለኝን ፅኑ እምነት እየነገርኳት የምትለኝን ሁሉ አደረኩ። በዚህም ምክኒያት የምፈልግበት ቦታ ላይ መድረስ ባለብኝ ሰአት አደረሰችኝ። ዝም ብዬ ሳስበው ከእግዚአብሄር ጋር ያለን መንፈሳዊ ጉዞ በብዙ መንገድ ከዚህ ጋር ይመሳሰልብኛል። 

መቼም ከህይወታቸው ብዙ ነገር ከተማርንባቸው ሰዎች ውስጥ አንዱ መዝሙረኛው ዳዊት ነው። በእግዚአብሄር እንደ ልቤ መባሉ፥ በዘመኑ ሁሉ የእግዚአብሄርን ሀሳብ አገልግሎ ማለፉ፥ እግዚአብሄርን መፈለጉ፥ አስተዋይነቱ እንዲሁም እግዚአብሄርን ከመውደዱ ብዙ ነገሮችን ተምረንበታል። ከዚህም አልፎ የዳዊት ህይወት እግዚአብሄርን ደስ ከማሰኘቱ የተነሳ፥ በብሉይ ኪዳን የነበሩት ሌሎች ነገስታት ከእግዚአብሄር ጋር በመስማማት ሲሄዱ “በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄደ” በማለት የእግዚአብሄር ቃል ዳዊትን እንደ ሚዛን ተጠቅሞበት ነበር። ከእነዚህ ሁሉ መልካምና አስተማሪ ባህሪያቶቹ እግዚአብሄርን የበለጠ የማረከው የዳዊት ባህሪ የትኛው ነው ብላችሁ አስባችሁ አታውቁም? የዚህን መልስ ዳዊት ከሞተ በኋላ እግዚአብሄር ለልጁ ለሰለሞን ከአባቱ ህይወት እንዲማር ከነገረው ነገሮች ውስጥ ማግኘት እንችላለን። 

“ዳዊትም አባትህ በየዋህ ልብና በቅንነት እንደ ሄደ አንተ ደግሞ በፊቴ ብትሄድ፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዓቴንም ፍርዴንም ብትጠብቅ፥ እኔ ከእስራኤል ዙፋን ከዘርህ ሰው አታጣም ብዬ ለአባትህ ለዳዊት እንደ ተናገርሁ፥ የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።” (1ኛ ነገ 9፡4) 

ብዙ ጊዜ በመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ የእምነት አባቶች ወደ እግዚአብሄር ሲፀልዩ አስተውላችሁ ከሆነ አንድ የሚሉት ነገር አለ “ለሚወዱህና ትእዛዝህን ለሚጠብቁ ቃልኪዳንህንና ምህረትህን የምትጠብቅ....” ይላሉ። እግዚአብሄርንም ከዳዊት ህይወት በጣም የማረኩት ሁለት ነገሮች ዋነኞቹ እግዚአብሄርን መውደዱና መታዘዙ ናቸው። ለልጁ ለሰለሞንም ዳዊትን ምሳሌ በማድረግ የሰጠው ትእዛዞች በእነዚህ ሁለት ነገሮች ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው። 

በእግዚአብሄር ፊት ትክክለኛ ህይወትና አገልግሎት አገልግሎ ለማለፍ ከትልቁ ከእግዚአብሄር እርዳታ ቀጥሎ ከእኛም የሚጠበቅ ነገር እንዳለ የዳዊትንና የሳኦልን ህይወት ማነፃፀር በቂ ነው። ዳዊት በዘመኑ ሁሉ እግዚአብሄርን ከማገልገሉና ስኬታማ ህይወት ኖሮ ከማለፉ ጀርባ አንድ ትልቅ ሚስጥር ስለ ህይወቱ የእግዚአብሄር ቃል ይነግረናል። 

“ዳዊት በዘመኑ ሁሉ በእግዚአብሄር ፊት ቅን ነገርን አድርጎ ነበርና ካዘዘውም ነገር ሁሉ ፈቀቅ አላለም ነበረና” (1ኛ ነገ 15፡5) 

እግዚአብሄር እያንዳንዳችንን የፈጠረበት ልዩ አላማ አለው። ይሄ አላማ የሚፈፀምበት ዋነኛ መንገድ ደግሞ የእኛ መታዘዝ ነው። በመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ አካሄዳቸውን ከእግዚአብሄር ጋር ያደረጉና አላማቸውን በትክክል ያገለገሉ ሰዎችን ህይወት በጥልቀት ብናይ፥ የእግዚአብሄርን ድምፅ በመታዘዝ የተሰጣቸውን የህይወትና የአገልግሎት አደራ ከግብ ያደረሱ እንዲሁም በኖሩበት ዘመንና ትውልድ ላይ ይሄ ነው የማይባል ተፅእኖ የፈጠሩ ሰዎች ናቸው። በተቃራኒው ደግሞ ባለመታዘዝ መንገድ ላይ የቀሩ ሰዎች ታሪክም እንዲሁ ለትምህርታችን ተፅፎልናል። 

እግዚአብሄር በህይወታችን ላይ የሚሰጠን ትእዛዞች በጠቅላላ ከዘላለማዊ ሀሳቦቹ ጋር በቀጥታ የተገናኙ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ትእዛዞቹ ለእኛ ተፈጥሮአዊ ማንነት ስሜት ባይሰጡንም፥ መታዘዝ እግዚአብሄር ከእኔ የተሻለ ያውቃል የሚል እምነት ውስጡ ስለያዘ እግዚአብሄርን ደስ ያሰኘዋል። መታዘዝና እምነት በጣም የተያያዙ ነገሮች ናቸው። ዶክተሮች አርጉ ያሉንን ሁሉ የምናረገው ጤናችንን ወደ ትክክለኛው ቦታ የመመለስ እውቀት አላቸው የሚል እምነት ስላለን ነው:: እግዚአብሄር የሚሰጠንን ትእዛዞች በመታዘዝ ውስጥ እግዚአብሄር ከእኔ በላይ ህይወቴ በየት አቅጣጫ መሄድ እንዳለበት ያውቃል የሚል እምነትን ውስጡ ይዟል። 

አንድ ጊዜ እግዚአብሄር አብርሀም ጋር መጣና 75 አመት ሙሉ ከኖረበት ሀገር ዘመዶችና ቤተሰቦች ተለይተህ ውጣ አለው። ታሪኩን በተደጋጋሚ ስለሰማነውና ስለለመድነው እንጂ ራሳችንን በአብርሀም ቦታ አስቀምጠን ከተለያየ አቅጣጫ ብናየው ወደማያውቀው ሀገር ቤተሰቡን ይዞ መውጣት ቀላል ውሳኔ አልነበረም። 

አብርሀም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ። (ዕብ 11፡8)

“እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ” ብሎ እግዚአብሄር ለአብርሀም ትእዛዝን ሲሰጠው፥ በህይወቱ ላይ ካለው ዘላለማዊ ሀሳቡ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ስለሆነ ነው። እግዚአብሄር ከአብርሀም ውስጥ ለራሱ የተለየ ህዝብ የማውጣት አላማ ነው የነበረው። አብርሀምን ሲያየው በእርሱ ውስጥ የእስራኤልን ህዝብ ነበር ያይ የነበረው። ታዲያ ይሄ እግዚአብሄር በዘላለማዊ ሀሳቡ ውስጥ ያየውን ህዝብ ከአብርሀም ውስጥ ለማውጣት፣ አብርሀም ከነበረበትና ከለመደው ምቹ ስፍራው መውጣት አስፈልጎት ነበር። ወዴት እንደሚሄድ ሳያውቅ የእግዚአብሄርን ድምፅ በእምነት ታዘዘ። አብርሀም አልታዘዝም ቢል የእግዚአብሄር ሀሳብ በህይወቱ አይፈፀምም ነበር።  ያ ደግሞ አብርሀም የተፈጠረበትን አላማ እንዲስት ያደርገዋል። በመታዘዙ ግን እግዚአብሄር እንደተናገረው ታላቅ ህዝብ አደረገውና የእስራኤልን ህዝብ እንዲሁም ትልልቅ ነገስታትን ከእርሱ ውስጥ አወጣ። ኢየሱስም በዚህ የዘር ሀረግ ውስጥ መጣ። 

ከእግዚአብሄር የሚመጡ ትእዛዞች በውስጣቸው ትልልቅ ትርጉሞችንና አላማዎችን የያዙ ከመሆናቸውም በላይ በህይወታችን ፐዝል ውስጥ የሚገጣጠሙ ናቸው። ተገጣጥመው እስኪያልቁ ሙሉ ስእሉን ማየት ቢከብድም መታዘዝ እግዚአብሄርን ከማመን ጋር በቀጥታ የሚያያዘው ለዚህ ነው። በክርስቶስ ዳግም የተፈጠርነው መልካሙን ስራ ለመስራትና ሌሎችን ለማገልገል ነው። እኛን የፈጠረበትን አላማ የሚያውቀው እግዚአብሄር ስለሆነ ወደዛ አላማ የሚመራን በእኛ መታዘዝ ውስጥ ነው:: እያንዳንዱን ትንንሽም ሆነ ትልልቅ ትእዛዞች ከመታዘዛችን ጀርባ እግዚአብሄር በእኛ ውስጥ ሊያገለግል ያሰባቸው ሰዎች አሉ። እሺ ብለን እግዚአብሄር የሚመራንን አቅጣጫዎች ተከትለን በመሄዳችን ውስጥ እግዚአብሄር ያያቸው ሰዎች አሉ። ቢገባንም ባይገባንም መታዘዛችን የእኛ ህይወት ላይ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ህይወት ላይ ተፅእኖ ያመጣል። ዛሬ የእኛ መዳን ከዛሬ 2000 አመታቶች በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ መስቀል ሞት ለመታዘዝ በመወሰኑ ላይ የተመሰረተ ነው። እሱ ባይታዘዝ እኛ እስካሁን የዘላለም ጨለማ ውስጥ በሆንን ነበር። የእርሱ መታዘዝ ግን ነፍሳችንን ከዘላለም ሞት አዳነ፥ የህይወታችንንም አቅጣጫ በሙሉ ቀየረው። የእኛ መዳን በክርስቶስ መታዘዝ ላይ እንደተመሰረተ ሁሉ፥ ዛሬ በእኛ መታዘዝ ላይ ህይወታቸው የተመሰረተ ሰዎች አሉ። ከመታዘዛችን ጀርባ እግዚአብሄር ሊያድንና ሊያገለግል ያሰባቸው ሰዎች አሉ። የእኛን መታዘዝ የሚጠብቅ ህዝብና ትውልድ አለ። 

አካሄዱን ከእግዚአብሄር ጋር ያደረገው ኖህ፥ አንድም ቀን በአደባባዮች ላይ ወጥቶ ሳይሰብክና ሳያስተምር፥ መርከብ እንዲሰራ የተሰጠውን መመሪያ ምንም አይነት ዝናብ ሳያይ ፀጥ ብሎ በእምነት በመታዘዙ ዓለምን ኮነነ ይለናል የእግዚአብሄር ቃል። በእምነት የሚገኘውንም ፅድቅ ወራሽ ሆነ። መታዘዛችን ከእኛ ያልፋል፥ ከእኛ ህይወት ያለፈ ተፅእኖን ያመጣል። ዓለምን ይኮንናል፥ ትውልድን ያድናል፥ የእግዚአብሄርን ፈቃድ በምድር ላይ ያስፈፅማል። መታዘዛችን በጣም ሰፊ ነው። እኛ ካለን ጠባብ አስተሳሰብ ያለፈ ነው! 

ታዲያ መታዘዝ ከመፈጠራችን አላማ እና እግዚአብሄር በህይወታችን ውስጥ ካለው ዘላለማዊ ሀሳብ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነገር ከሆነ፥ በቃሉ ውስጥ የተፃፉልንን የእግዚአብሄርን መመሪያና ትእዛዞች ምን ያህል ለመታዘዝ እየሞከርን ነው? በግል ህይወታችንስ እግዚአብሄር የሰጠንን ትእዛዞች ምን ያህል ተግባራዊ እያደረግን ነው? ህይወታችን ፍፁም ባይሆንም፥ እንዳንድ ጊዜ ግን ቆም ብሎ እግዚአብሄር እንድናደርገው እየጠበቀብን ያሉትን ነገሮች ማሰብ፥ ለመታዘዝ መወሰን፣ እንዲሁም በሚያቅተን ነገሮች ሁሉ ላይ የእግዚአብሄርን እርዳታ መጠየቅ ትልቅ ማስተዋል ነው።

ሩጫ

ሩጫ

How do I know the will of God in my romantic relationship?

How do I know the will of God in my romantic relationship?