Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ሩጫ

ሩጫ

በልጅነቴ በጣም ከምወዳቸው ነገሮች አንዱ ሩጫ ነበር። በአጭሩ፥ ቆመን እናውራ ከምትሉኝ እየሮጥን እናውራ ብትሉኝ ይቀለኝ ነበር። አንዳንዴማ ማዘር ሱቅ ስትልከኝ፥ ለመሮጥ ከመቸኮሌ የተነሳ የምገዛውን ነገር በሙሉ ተናግራ እስክትጨርስ ለመስማት የሚሆን ትእግስት አልነበረኝም። እሷ ተናግራ ሳትጨርስ እኔ ሮጬ ሱቁ ጋር ደርሻለሁ። ግዢ ያለችኝን ነገሮች በትክክል ስላልሰማሁ ተመልሼ ስመጣ፥ ማዘር እዛው ቦታ ጋር ቆማ እየጠበቀችኝ ነው። ያው ወይ እገረፋለሁ ወይንም ደግሞ ከቻልኩ ለጊዜው ሮጬ በማምለጥ ቅጣቱን ወደ ማታ አራዝመዋለሁ። እነ ቀነኒሳ ሲሮጡ ማየትማ ነፍሴ ነበር። ሲሮጡ ፊታቸው ላይ የነበረው የድካም ስሜት እስካሁን ድረስ ትዝ ይለኛል። መቼም ያንን ሁሉ ኪሎ ሜትር ያለ ምንም እረፍት መሮጥ እጅግ አድካሚና ብዙ ትእግስት የሚጠይቅ እንደሆነ ግልፅ ነው። ትልቁ ደስታና ያቺ ትንሿ ሰፈራችን በጩኸት የምትሞላው ግን ልክ የተመደበላቸውን ኪሎ ሜትር ጨርሰው ሲገቡና ሲያሸንፉ ነው። በደስታ የሚያለቅሱ ሰዎች እራሱ ነበሩ። ግማሹ ይዘላል፥ ግማሹ ይጮሀል፥ ሰው ሁሉ ልቡ ውስጥ ያለው ደስታ ሁን እንደሚለው ስለሚሆን፥ ቤቱ ልዩ በሆነ የደስታ ስሜት ይሞላ ነበር።  ምድራዊውን የጨዋታ ሩጫ መጨረስ እንዲህ የሚያስደስት ከሆነ፥ የዘላለም አክሊል የሚያስገኝልንን መንፈሳዊ ሩጫ ጨርሶ መግባት እንዴት የሚያስደስት ይሆን? ጳውሎስ ልክ እንደ ቀነኒሳ የራሱን ሩጫ ከጨረሰ በሗላ የተናገረው ነገር ትዝ አለኝ። 

“መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሀይማኖትን ጠብቄያለሁ ወደፊት የፅድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል። ይህንም ፃድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል። ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም” (2ኛ ጤሞ 4፡7) 

ብዙ ጊዜ የእግዚአብሄርን ቃል ስታዩት፥ በምድር ላይ ያለንን የክርስትና ህይወት ከሩጫ ጋር እያወዳደረ ያስተምረናል። በዚህ ምድር ስንኖር የተመደበልን መንፈሳዊ ሩጫ አለ። ይሄ ሩጫ አንዳንድ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሁላችንን በክርስቶስ አምነን የዳነውን ሁሉ የሚመለከት ነው። አላማው ደግሞ በትእግስት፥ በፅናት፥ በሙሉ ትኩረት፥ ኢየሱስን በማየት ሮጦ መጨረስ ነው። ስለዚህ ስኬታማ ነን የሚባለው ይሄንን የተመደበልንን ሩጫ ሮጠን ጨርሰን ስንገባ ነው። ክርስቶስን በማመን የጀመርነው ህይወት፣ ልክ እንደ ሩጫ መነሻም መድረሻም አለው። ለዘላለም አንሮጥም። ትንሽ ብቻ ሮጠን፣ ዘላለም እናርፋለን። ሯጭ፣ መድረሻው ላይ የሚጠብቀውን ሽልማት እያሰበ ድካሙንና የሚከፍለውን ዋጋ ሁሉ እንደሚታገስ፣ ሩጫቸውን በትእግስትና በጽናት ለሚጨርሱ ሰዎች፥ እግዚአብሄር ያዘጋጀው ዘላለማዊ አክሊል አለ። ይሄ ሩጫ በዚህ ምድር ላይ በምንኖረው ኑሮ፣ እግዚአብሄርን ለመታዘዝና ደስ የሚያሰኘውን ህይወት ለመኖር በምንከፍለው መስዋእትነት ይመሰላል። አሁን ያለነው ሩጫ ላይ ነው። መንገድ ላይ ነን። ወደ ዘላለማዊ አክሊላችን የሚያደርሰን መንገድ ላይ ነን። 

እንግዲህ ስለ መንፈሳዊ ሩጫ ስናስብ አላማው ሮጦ መጨረስ ይሁን እንጂ፥ የጀመረ ሁሉ ግን ይጨርሳል ማለት አይደለም። ብዙ ጊዜ ሩጫን ስታዩት የሚጀምሩት በጣም ብዙዎች ቢሆኑም የሚጨርሱት ግን ጥቂቶች ናቸው። የእስራኤልን ልጆች ታሪክ እንደ ምሳሌ ብናነሳ፥ መንፈሳዊውን ጉዞ የጀመሩት ከ600 ሺህ የበለጡ ሰዎች ቢሆኑም ከጀመሩት ውስጥ የጨረሱት ግን 2 ሰዎች ብቻ ነበሩ። ታዲያ የጀመርነውን ይሄ የከበረና የዘላለም አክሊል የሚያስገኝልንን ሩጫ ለመጨረስ፥ የራሱን ሩጫ የጨረሰው ጳውሎስ ከመከረን ጠቃሚ ምክሮች ውስጥ ሁለቱን እንመልከት።

“እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” (ዕብ 12፡1-2) 

1፥ ሸክምን ማስወገድ፦

እንግዲህ ሯጮችን ስናይ፥ ሲሮጡ ምንም የሚሸከሙት ሸክም የለም። ባዶ እጃቸውን ናቸው። አለባበሳቸውንም ስናይ፥ ጋቢ ለብሶ ወይንም ደግሞ ሙሉ ሱፍ ልብስ በቆዳ ጫማ አርጎ የሚሮጥ ሯጭ አይተን አናውቅም። በተቻላቸው መጠን ለሩጫው ይረዳቸው ዘንድ ሰውነታቸው ላይ ያለውን ሸክም ያቀሉታል። ሀጢያት ሩጫን የማዘግየት አልፎም ደግሞ አቋርጠን እንድንወጣ የማድረግ አቅም አለው። አቋርጠን መውጣት ስል፥ ከቤተክርስቲያን መቅረትንና ከክርስትና ህይወት መውጣትን ብቻ ሳይሆን፥ እዚሁ እግዚአብሄር ቤት ውስጥ እየተመላለስን ነገር ግን በትክክለኛው መንፈሳዊ ሩጫ ላይ ላንኖር እንደምንችል ማሰብም ጥሩ ነው። ምክኒያቱም ቤተክርስቲያን ውስጥ የምንሰባሰበው እንደ እኛ ከሚሮጡ ጋር እርስ በእርስ ለመበረታታት፥ ለሩጫችን የሚያስፈልገንን ፀጋ ለመካፈል፥ እንዲሁም የህብረት አምልኮን ለማድረግ እንጂ እግዚአብሄር የእያንዳንዳችንን የህይወት አካሄድ ወይንም ሩጫ የሚመዝነው በግል ነው። ስለዚህ ሩጫችንን የማስቆም ሀይል ስላለው፥ ከሀጢያትና ወደዛ ከሚወስዱን መንገዶች መራቅ የጀመርነውን ሩጫ ለመጨረስ በጣም ወሳኝ ነገር ነው ይለናል ጳውሎስ። 

ሌሎች ነገሮች ደግሞ አሉ ሀጢያት ያልሆኑ ነገር ግን ከተመደበልን ሩጫ አንፃር ስናያቸው ሸክም የሆኑና ምንም ጥቅም የሌላቸው። ፀሀፊውም ሲፅፍ “ሸክምን ሁሉ፥ ቶሎም የሚከበንን ሀጢያት”  ብሎ የከፋፈለበት ምክኒያት አለው። በመንፈሳዊ ህይወታችን እያደግን ስንመጣ “ይሄ ነገር ሀጢያት ነው ወይንስ ሀጢያት አይደለም” ከሚል አስተሳሰብ አልፈን “ለጀመርኩት ሩጫ ይጠቅማል ወይንስ አይጠቅምም” ወደሚለው አስተሳሰብ ውስጥ እናድጋለን። ጳውሎስ አንድ ቦታ ላይ ሲናገር “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም” እንዳለ፥ የተፈቀደልን ነገር ሁሉ የሚጠቅም ላይሆን ይችላል። ያንን የምንወስነው ከተመደበልን የመንፈሳዊ ሩጫ አንፃር ነው። አንዳንድ ነገሮች ሀጢያት አይደሉም ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ማስተዋል ውስጥ ስናያቸው ሸክሞች ናቸው። ሩጫችንን የማዘግየት አልፎም የማስቆም አቅም ሊኖራቸው ይችላል። 

2፥ እይታን ማስተካከል፡-

የሯጭ ሌላኛው ባህሪው፥ ለሚያጨበጭቡለት ሰዎች በየመንገዱ እየቆመ ምስጋና አያቀርብም። ለሚተቹትና ለሚነቅፉትም ሰዎች ቆሞ ራሱን አያብራራም። መሀል መሀል ላይ እየቆመ ድካሙንና ስሜቱን ለሰዎች ለማስረዳት አይሞክርም። ወደ ግራና ወደ ቀኝ ዞር ዞር እያለም የከተማውንና የተፈጥሮውን ውበት አያደንቅም። የእሱ አላማ እና ሙሉ ትኩረት ወደ ፊት ብቻ ነው። ሙሉ ልቡ ያለው መጨረሻ ላይ የሚጠብቀው ሽልማት ላይ ነው። በዚህ የመንፈሳዊ ሩጫ ውስጥ ጳውሎስ ከሚመክረን በጣም ጠቃሚ ምክሮች ውስጥ አንዱ እይታችንን በዙሪያችን ካሉት ሰዎችና ነገሮች ላይ አንስተን የእምነታችን ራስና ፈፃሚ የሆነው ክርስቶስ ላይ እንድናደርግ ነው። የምናየው ነገር ሩጫችንን የማበርታትም የማድከምም አቅም አለው። በሚገጥሙን ከባባድ የህይወት ፈተናዎች ላይ በፈተና የፀናውን ክርስቶስን ማየትና ማሰብ የፅናትን አቅም ይሰጠናል። አይኖቻችንን በዙሪያችን ካሉት ነገሮች ላይ አንስተን በክርስቶስ ውስጥ የምናገኘውን ዘላለማዊ ደስታና አክሊል ማየት፥ የምናልፍበትን ጊዜያዊ መከራ እንድንታገስ ይረዳናል። የክርስቶስን ህይወትና አገልግሎቶች ማጥናት አላማ ተኮሮች ያደርገናል። በዙሪያችን በሚሆኑት ነገሮች ተፅእኖ ስር ወድቀንም ሩጫችንን እንዳናቆም ይረዳናል። 

zach-lucero-x_x3RPpDbII-unsplash.jpg
ደውል

ደውል

መታዘዝ

መታዘዝ