Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ደውል

ደውል

አንዳንድ ጊዜ ቤቴ ውስጥ ቡና ሳፈላ፥ ጣሪያ ላይ ያለችው የእሳት አደጋ ደውል የቡናውን ጭስ ሰምታ ጩኸትዋን  ታቀልጠዋለች። በሩን ከፍቼ የቡናውን ጭስ ካላስወጣሁትማ፥ እልህ ይይዛታል መሰለኝ ብሶባት ነው ቁጭ የሚለው። ለነገሩ እሷ ምን ታርግ? ስራዋን እኮ በአግባቡ እየሰራች ነው። ኸረ እንደውም እሳት የተነሳ መስሏት፥ እኔኑ ከአደጋ ለማትረፍ እኮ ነው የምትጮኸው። ጭሱን ያስነሳሁት እኔው እራሴ መሆኔን አላወቀችም እንጂ የእውነት እሳት አደጋ ቢነሳ፥ በዚህ ጩኸትዋ ህይወቴን በማትረፏ እንደው ሰው ሆና ግምባሯ ላይ አንድ መቶውን ዶላር ብለጥፍላት እራሱ አይቆጨኝም። 

በክርስትና ህይወታችን ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ አንዱ ስራው ልክ እንደዚህች የማንቂያ ደውል ይመስለኛል። ህይወታችን አደጋ ላይ ሲሆን ልባችን ውስጥ የሚያሰማን የማንቂያ ደውል አለ። በተለይ በሀጢያት ጎዳናዎች መጓዝ ስንጀምር፥ ሀጢያት ከእግዚአብሄር እንደሚለየን ስለሚያውቅ ልባችን ውስጥ ጮክ ብሎ ይጮሀል። “አደጋ ላይ ናችሁ!” እያለ የአደጋ ምልክት ያሰማናል። እግዚአብሄር ህይወት ስለሆነ ከህይወት እንዳንርቅና እንዳንጎድል የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ፍቅሩ እኮ ነው! ርህራሄው እኮ ነው! ዛሬ ዝም ካልነው ነገም እኛን ለመመለስ ተስፋ አይቆርጥም። ትልቁ አደጋ ግን የሚፈጠረው ድምፁን እየሰማን በጀመርናቸው የስህተት መንገዶች የቀጠልን ጊዜ ነው። 

በሰው ልጆች ፈቃድ ውስጥ ብቻ የሚሰራ አምላክ ስለሆነ ማንንም በማስገደድ አያምንም። በፈቀድነው መንገድ ለመሄድ ልባችን ውስጥ ፈቃድን አስቀምጧል። ከመረጥናቸው የስህተት መንገዶች ጋር ግን አብሮ መጓዝ አይችልም። እኛን ለማትረፍ የሚጮኸውን የአደጋ ላይ ናችሁ ድምፅ ሰምተን ካልተመለስን፥ ለፍቃዳችን ሊተወን ይገደዳል። ይሄ አንድ ክርስቲያን የሚገባበት በጣም አደገኛ የሆነ ቦታ ነው። በስህተት ጎዳና ውስጥ ስንሄድ በውስጣችን የሚሰማን ምንም የወቀሳ ድምፅ ከሌለ፥ የእግዚአብሄርን ቃል መተላለፋችን ምንም አይነት ስሜት ካልሰጠን፥ ሰላምና ምቾት ካልነሳን እንደውም ምንም እንዳልተፈጠረ አይነት ስሜት ኖሮን በሰላም ወደሚቀጥለው ጉዳያችን ከገባን፥ አደጋ ላይ ነን! ትልቅ አደጋ ላይ ነን! ህይወታችን ላይ ያሉትን እንቅስቃሴዎች ሁሉ አቁመን መንገዶቻችንን መመርመር ያለብን በዚህ ጊዜ ነው። ቶሎ ሳይረፍድ በንሰሀ መመለስና አካሄዳችንን ከእግዚአብሄር ጋር ማስተካከል ያለብን በዚህ ጊዜ ነው። 

ክርስቲያን በሀጢያት ስህተት ውስጥ ሊወድቅ አይችልም ወይ? ኸረ በደምብ ሊሳሳት ይችላል! እንደውም መፅሀፍ ቅዱስ እኮ ሀጢያተኞችን በምህረቱ ያፀደቀበትና የእግዚአብሄርን የፀጋ ጉልበት ያየንባቸው ሰዎች ስብስብ ነው። እነ ዳዊት ቢሆኑ መቼ ፍፁምነታቸው ሆነና እንደ ልቤ ያስባላቸው! ድምፁን ሰምተው ቶሎ መመለሳቸው አይደል እንዴ የእግዚአብሄርን ምህረት በህይወታቸው ፍፁም ያደረገው! ምህረቱ እኮ ነው በተሰጣቸው ዘመን ሁሉ የእግዚአብሄርን ሀሳብ አገልግለው እንዲያልፉ አቅም የሰጣቸው። ኸረ እንኳንም ሳቱ! እንኳንም ደግሞ ስህተታቸው ከስኬትና ከድላቸው ጋር አብሮ ተፃፈልን! የስህተታቸው አስከፊነት እኮ ዛሬ ለእኛም ተስፋ እንዳለን ነገረን። እንደ እነ ጳውሎስ አይነቶቹ አሳዳጆች ላይ እግዚአብሄር ያበዛው ትእግስት አይደል እንዴ ከስህተት በመመለስ ሩጫን መጨረስ ይቻላል የሚል መልእክት ያደረሰን! ክርስቲያን ይሳሳታል። በደምብ ይሳሳታል። 

ነገር ግን ክርስቲያን በሀጢያት ውስጥ መኖር አይችልም። ሀጢያትን መኖሪያ ቦታው ማድረግ ግን አይችልም። እንደ ማንኛውም በክርስቶስ መዳንን እንደማያውቅ ሰው በሀጢያት ውስጥ ሊዝናና ግን አይችልም። ከሀጢያት አርነት ያወጣውና ውስጡ ያለው የህይወት መንፈስ ህግ አይፈቅድለትም። ከእግዚአብሄር በመወለዱ ሀጢያትን የሚቃወም መንፈስ በውስጡ አለ። የእግዚአብሄርን ዘር ስለተሸከመ ሀጢያትንና ውስጡ ያለውን የእግዚአብሄር ዘር ጎን ለጎን ማስኬድ አይችልም። አንዱን ይመርጣል። ወይ ከዚህኛው ወይንም ከዚያኛው ይሆናል። አንድ ሰው ማገልገሉ፥ ክርስቲያን የሚያደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ ማድረጉ ከእግዚአብሄር ዘር ነው ሊያስብለው አይችልም። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ እንደተባለው ማስታወቂያው ፍሬው ነው እንጂ የመድረክ ላይ አገልግሎቱም አይደለም። በከፍተኛ መሰጠትና ሀይል አገልግሎ ብዙዎችን ወደ እግዚአብሄር መንግስት ያመጣው ሀዋሪያው ጳውሎስ “እኔ ከሰበኩ በሗላ የተጣልኩ እንዳልሆን ስጋዬን እየጎሰምኩ አስገዛዋለሁ” ብሎ የግል ህይወቱንና አገልግሎቱን ነጣጥሎ ያየው፥ እግዚአብሄር አገልግሎታችንንና የግል ህይወታችንን ለያይቶ እንደሚመዝናቸው ስለገባው ነው። ለካ ክርስቲያን ነኝ እያሉ ኖር ኖሮ፥ አገልጋይ ነኝ ብሎ አገልግሎ አገልግሎ ህይወትን በትክክል ካልኖሩ፥ መጨረሻ ላይ መጣል የሚባል አደጋም አለ። 

መዳናችን፥ በፀጋ ድነናል ብሎ ብቻ አያበቃም። ይሄው እራሱ ያዳነን ፀጋ፥ መጀመሪያ አለማዊ ምኞትንና ሀጢያትን ካስካደን በሗላ የሚያስተምረን ከሀጢያት ጋር መጋደልን ነው። በፅድቅና በቅድስና መኖርን ነው። እግዚአብሄርን በመምሰል እየኖርን የክርስቶስን መምጣት መጠበቅን ነው። ክርስቲያን ታጋይ ነው!  በእግዚአብሄር መንፈስና ፀጋ እየታገዘ፥ በስጋው ውስጥ ከሚኖረው ሀጢያት ጋር እየተጋደለ የሚኖር ተዋጊ እንጂ፥ ፀጋውን እየሄደበት ላለው የስህተት መንገድ እንደ ፈቃድ ተጠቃሚ  አይደለም። 

አንድ ሴት ለመፀነስና ልጅ ለመውለድ ቢያንስ 9 ወር እንደሚያስፈልጋት፥ ፀንሳ መውለድዋ በጊዜ ሂደት ውስጥ የሚከናወን እንደሆነ ሁሉ፥ የስጋ ምኞትና የድፍረት ሀጢያት በጊዜ ሂደት ውስጥ ፀንሰው የሚወልዱት አንድ ነገር አለ። ሞት። ቤተክርስቲያን ውስጥ እየተመላለስን፥ የሞተ ወይንም ከእግዚአብሄር የተለየ ህይወት ሊኖረን ይችላል። ይሄ ደግሞ በክርስቶስ ያገኘነውን የዘላለም መዳን ሊያሳጣን የሚችል ነገር ስለሆነ፥ የተሰጠንን አንድና ድጋሚ እድል የሌለበት ህይወት በጥንቃቄ መኖር ማስተዋል ነው። 

ልቤ

ልቤ

ሩጫ

ሩጫ