Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ሰላምና ደስታ

ሰላምና ደስታ

ዛሬ ገና ከእንቅልፌ ስነቃ ነው ውስጤ በደስታ የተሞላው። ፈገግ እያልኩኝ ነበር ቀኔን የጀመርኩት። እኔ መሳቅና መደሰትን ከእግዚአብሄር እንደ ተሰጡኝ በረከቶች ነው የምቆጥራቸው። እውነተኛ የልብ ደስታ የሚመጣው ከእግዚአብሄር ዘንድ ብቻ እንደሆነ ልቤ በብዙ ሁኔታዎች ውስጥ ተምሯል። አሁን ላይ አንድ የሰማሁት ቀልድ ካሳቀኝ፥ መሳቅ የቻልኩት ቀልዱ ስለሚያስቅ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሄር የውስጥ ደስታን ስለሰጠኝ እንደሆነ ስለሚገባኝ፥ እግዚአብሄርን “አንተ እኮ ደስታ እና ሳቄ ነህ”  እለዋለሁ።

ሰው እውነተኛ የሆነውን ደስታ ከብዙ ነገሮች ውስጥ ይፈልጋል። በህይወቱ ስኬቶች ብሎ ያስቀመጣቸውን ነገሮችም ቢያገኝ ዘለቄታዊ የሆነ ደስታ የሚያገኝ ይመስለዋል። የእነዚህ ነገሮች መሳካት ግን ጊዜያዊ እንጂ ዘለቄታዊ ደስታና እርካታን ህይወታችን ላይ ሊያመጡ አይችሉም። ምድራዊ ደስታ በጣም አጭር ከመሆኑም በላይ፥ በምክኒያት ውስጥ ብቻ የሚሰራ ነው። አሁን እያወራን ያለነው ደስታ ግን በስኬቶቻችን ውስጥ የምናገኘው አይነት ደስታ አይደለም። እኛ ከምናረጋቸውና ከማናረጋቸው ነገሮች ጋርም ምንም አይነት ተያያዥነት የለውም። ይሄ አይነቱ ሰላምና ደስታ እኛ ምድር ላይ ስኬት ብለን ባስቀመጥናቸው ነገሮች ውስጥ የሚገኝ ቢሆን ኖሮ፥ ስንት ተሳካላቸው የምንላቸው ሚሊየነሮችና ቢሊየነሮች ሰላም ማጣት ውስጥ እየገቡ ራሳቸውን አያጠፉም ነበር። ስንት ታዋቂና ዝነኛ ሰዎች የአይምሮ ውጥረት ውስጥ እየገቡ ራሳቸውን ላይ ከባባድ ነገሮችን አይፈጽሙም ነበር። ይሄ የምንነጋገረው ደስታ ግን፥ ለመደሰት የትኛውንም አይነት ነገር ሳናደርግ፥ እንዲሁ በልባችን ውስጥ የሚፈስና ከእግዚአብሄር ብቻ የሚሰጥ የእግዚአብሄር በረከት ነው። ይሄ አይነቱ የመንፈስ ቅዱስ ደስታ መሳካትና አለመሳካት፣ መሆንና አለመሆን፣ ማግኘትና አለማግኘት የሚባሉት ነገሮች አያስቆሙትም። ከምክኒያቶቻችን ውጪ የሚሰራ አስደናቂ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው። እንደ ምድራዊው ደስታ ከውጪ የሚመጣ ሳይሆን፥ ከውስጣችን ልክ እንደ ውሀ ምንጭ የሚፈልቅ ስለሆነ፥ በህይወታችን ውስጥ የሚያልፉት የትኞቹም ከባባድ ፈተናዎች ሊያስቆሙት አይችሉም። ለዚህ ነው መፅሀፍ ቅዱሳችንን ስናነብ የእግዚአብሄር ሰዎች በእስር ቤት ውስጥ ሆነው በምስጋናና በሀሴት እየተሞሉ የዘመሩት። ለዛ ነው በጣም ከባድ በሆኑ ችግሮች ውስጥ እያለፉ ስለ መንፈስ ቅዱስ ደስታ የጻፉልን። አንድ ሰው ህይወቱ በብዙ ውጫዊ ፈተናና መከራ ውስጥ እያለፈ፥ ይሄንን መከራ ከብዙ የመንፈስ ቅዱስ ሰላምና ደስታ ጋር ሊያልፈው ይችላል። ሌላ ሰው ደግሞ ከውጪ ያለውን ህይወቱን ስትመለከቱት በብዙ ስኬት ውስጥ ያለ የሚመስል፥ እናንተ የምትፈልጉት ነገሮች በሙሉ ስላለው ደስተኛ የሚመስላችሁ፥ ውስጡ ግን ሰላም በማጣት፣ በፍርሀትና በጭንቀት ማእበል ውስጥ የሚናወጥ ሰው ሆኖ ሊገኝ ይችላል። 

እግዚአብሄር በደስታ ውስጥ እንድንኖር ይፈልጋል። ሲፈጥረን እራሱ እኮ የፈጠረን፥ ደስተኞች ሆነን እንኖር ዘንድ ነው። እግዚአብሄር አዳምና ሄዋንን የፈጠራቸው፥ በኤደን ገነት ውስጥ ያለውን ደስታ እያጣጣሙ በእርካታ እንዲኖሩ ነበር። ይሄንን ሀሴትና ደስታ የሞላበት ሕይወት የቀማቸው አለመታዘዝ ነው። ይሄንን ደስታ የቀማቸው ሀጢያት ነው። እኛ ታዲያ በክርስቶስ ኢየሱስ የምናምን ሰዎች ሁሉ፥ እግዚአብሄር በልጁ ውስጥ መልሶ ከሰጠን ስጦታዎች ውስጥ አንዱ የራሱን ሰላም ነው። እግዚአብሄር እውነተኛ ደስታን ያስቀመጠው ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተልና የእርሱን ሀሳብ በመታዘዝ በምንሄድባቸው መንገዶች ውስጥ ነው፡፡ በኢሳይያስ መጽሀፍ ምእራፍ 9 ላይም ሲናገር፥ “በጨለማ የሄደ ህዝብ ብርሀን አየ። በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሀን ወጣላቸው” ካለ በኋላ፥ “ህዝብን አብዝተሀል። ደስታንም ጨምረህላቸዋል። በመከር ደስ እንደሚላቸው፣ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል።” በማለት እግዚአብሄር ልጁን ኢየሱስን የሰጠን፥ ከጨለማ ወደ ብርሀን ሊያሻግረን እንዲሁም በህይወታችን ላይ ደስታን ሊጨምርልን እንደሆነ ይናገራል። ኢየሱስም በአንድ ቦታ ላይ ሲናገር እንዲህ አለ። “ሰላሜን እሰጣችኋለሁ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ደግሞ አለም እንደሚሰጠው አይነት አይደለም” አለ። ኢየሱስ የሰጠን የራሱን ሰላም ነው። ኢየሱስ ጋር ያለው ሰላም ሌላ፥ ለእኛ የሰጠን ሰላም ደግሞ ሌላ አይደለም። ሰላሜን እሰጣችኋለሁ ብሎ የሰጠን ራሱጋ ያለውን ሰላም ነው። መንፈሳዊነትን ልክ እንደ ሀዘን ቤት የሚቆጥሩ፥ አርግና አታርግ ከሚለው ህግ ጋር በማያያዝ፥ ልክ እንደ ህግ መፈጸሚያ ቦታ ብቻ የሚቆጥሩ ሰዎች አሉ። ይሄ ግን ፈፅሞ ከእውነት የራቀ ነው። እኛ እግዚአብሄርን ደስ ለማሰኘት የምንኖር ሰዎች ስንሆን፥ እግዚአብሄር በእኛ ደስ በተሰኘ ቁጥር፥ ደስታውን በመንፈስ ቅዱስ መልሶ በልባችን ውስጥ እንደሚያፈሰው መረዳት አለብን። እግዚአብሄር ተደሰተ ማለት እኛ ተደሰትን ማለት ነው። ምክኒያቱ ደግሞ እግዚአብሄር እራሱ በመንፈሱ በልባችን ውስጥ ስለሚኖር ነው። አንድ ክርስቲያን እኮ በሀጢያት ጎዳና ውስጥ ሲጓዝ ደስተኛ መሆን የሚያቅተው፥ ልቡ ከእግዚአብሄር ልብ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ነው። የእግዚአብሔር መቅደስ ፥ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ስለሆነ ነው። እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኘው ነገር ሁሉ ደስ ያሰኘዋል። የሚያሳዝነው ነገር ሁሉ ያሳዝነዋል። የሚያስቆጣው ነገር ሁሉ ያስቆጣዋል። ስሜቶቹ በልቡ ከሚኖረው ከእግዚአብሄር መንፈስ ጋር የተያያዙ ናቸው። አንድ ሰው ግን ከእግዚአብሄር መንፈስ እንዲሁ በነጻ የሚሰጠውን የደስታ መንፈስ ካላወቀ፥ ደስታ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዴት ያውቃል? ሰው የመንፈስ ቅዱስን ደስታ ካልተለማመደ፥ በህይወቴ ተደስቼ አውቃለሁ ብሎ ቢያስብም፥ እውነተኛ ደስታ ምን አይነት ስሜት እንዳለው እንዴት ያውቃል? ይሄ እውነተኛ ደስታ፥ ከእግዚአብሄር ብቻ የሚመጣ ነገር እንደሆነ ሳይረዱ “እስኪ ፈታ ልበል” ብለው ሰዎች ፈታ ማለትን ከዚህች ክፉ አለም ሲፈልጉ ያሳዝኑኛል። ይቺ አለም እኮ በአንድ በኩል ብትፈታም በሌላ በኩል ደግሞ እያሰረች ነው። ሙሉ ለሙሉ የፈታን እግዚአብሄር ብቻ ነው።

“የእግዚአብሔር መንግስት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና።” (ሮሜ 14:17)

ይሄ የእግዚአብሄር ደስታ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ አምነው የእግዚአብሄር ልጆች ለሆኑ ሁሉ እንዲያው በነጻ የተሰጠ ስጦታ ቢሆንም፥ በክርስቶስ አምነው የዳኑ ሁሉ ግን እግዚአብሄር በሰጠው የደስታ ሙላት ልክ ይኖራሉ ማለት አይደለም። ይሄንን የእግዚአብሄርን ነጻ ስጦታ ለመስረቅ በየእለቱ የሚሰማራ ጠላት ቢኖረንም፥ አብዛኞቻችን ግን ይሄንን የደስታ መንፈስ የምናገኝበትን ዋና የሆነ መንገድ ቸል ስንለው ይታያል። የዚህን እውነተኛ ደስታ ሚስጥር ግን መጽሀፍ ቅዱስ በመዝሙረ ዳዊት ምእራፍ 45 ቁጥር 7 ላይ እንዲህ በማለት በግልጽ ጽፎልናል። “ፅድቅን ወደድህ፥ አመፃንም ጠላህ ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሄር አምላክህ በደስታ ዘይት ቀባህ” በማለት በእውነተኛ ደስታ የመቀባት ሚስጥሮች ሁለት መሆናቸውን ይነግረናል። የመጀመሪያው ፅድቅን መውደድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አመጻን መጥላት ነው። ይሄ የደስታ ዘይት ብዙ ጊዜ ሰው እጁን ጭኖብን የምናገኘው ነገር አይደለም። ይልቁንም በእግዚአብሄር ፊት ትክክል በሆነ ሕይወት በመመላለስ ውስጥ ብቻ እግዚአብሔር በመንፈሱ በልባችን የሚያፈሰው አስደናቂ የሆነ የእግዚአብሔር ሀሳብ ነው። ጽድቅን መውደድ ማለት፥ የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዛት መውደድ ማለት ነው። በህይወታችን ውስጥ የምንወስናቸውን ትንንሽም ሆነ ትልልቅ ውሳኔዎች በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ለማየት መሞከር፣ እንደ እግዚአብሄር ቃል የሆኑትን መንገዶች መከተል፣ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ጊዜ በማሳለፍና ያወቅነውን ቃል ተግባራዊ በማድረግ መኖር ማለት ነው። አመጽን መጥላት ማለት ደግሞ፥ እግዚአብሔር ከሚጠላቸው ነገሮች መራቅ ማለት ነው። በእግዚአብሄር ሕግና ትእዛዛት ውስጥ በመሄድ፣ አለም ልትሰጠው የማትችለው ሰላምና ደስታ አለ። በምሳሌ መጽሀፍ ምእራፍ ሶስት ላይ ሲናገር፥ “ልጄ ሆይ ህጌን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። ብዙ ዘመናትና ረጅም እድሜ፣ ሰላምም ይጨምሩልሀል።” በማለት፥ የመታዘዝ ህይወታችን ሰላም በህይወታችን የሚጨመርበት መንገድ እንደሆነ የእግዚአብሄር ቃል በግልጽ ይናገራል። የእግዚአብሔርን ቃል እንዲሁም በሕይወታችን ያለውን ሀሳቡን በመከተል መኖር፥ በ1ኛ ጢሞቴዎስ ምእራፍ 4 ላይ “እግዚአብሄርን ለመምሰል ራስህን አስለምድ” በማለት እንደሚናገረው፥ በቀን ለቀን በምናደርጋቸው ትንንሽ ጉዳዮች ጀምረን እራሳችንን እያስለመድን የምንመጣው ነገር ነው። ይሄንን በመለማመድ ስንኖር፥ ጽድቅን በመውደድ ውስጥ ያለው የደስታ ዘይት ሳያቋርጥ በህይወታችን መስራት ይጀምራል። የብሉይ ኪዳን መጻህፍቶችን ስናነብ፥ እግዚአብሄር ለእስራኤል ህዝቦች ህጎቹንና ትእዛዞቹን በማክበርና እርሱን በመታዘዝ በሚሄዱባቸው መንገዶች ውስጥ ብዙ ሰላም መኖሩን፥ ባለመታዘዝ በሚሄዱባቸው መንገዶች ውስጥ ግን ድንጋጤ፣ ፍርሀትና ጭንቀት እንደሚያጋጥማቸው ይናገራል።

“ሕግህን ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው፥ እንቅፋትም የለባቸውም” (መዝሙረ ዳዊት 119:165)

እኔም አንድ የክርስቶስ ተከታይና የእግዚአብሔርን መንገድ ለመከተል ከሚሞክሩ ክርስቲያን ሰዎች ውስጥ አንዷ እንደመሆኔ፥ ባለፉት ጥቂት አመታቶች ውስጥ እየተለማመድኩ የመጣሁትና በክርስትና ጉዞዬ ላይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመከተል ለመሄድ የረዳኝን አንድ ነገር ባካፍላችሁ ምናልባት ሰው የሆነ ነገር ሊያገኝበት ይችላል ብዬ አሰብኩ።

ሰላም መጠን ወይንም ደረጃ አለው። ጥቂት ሰላም አለ። የበዛ ሰላም ደግሞ አለ። ትንሽ ሰላም አለ፥ ብዙ ሰላም ደግም አለ። ከላይ ስንነጋገር እንደመጣነው፥ ሰላምና ደስታ ጽድቅን በመውደድ ወይንም የእግዚአብሔርን ሀሳብ በመከተል ውስጥ በሕይወታችን የሚበዛ ነገር እንደሆነ ስለገባኝ፥ የጸጥታ ጊዜዬን በማሳልፍባቸው ወይንም ለመጸለይ በእግዚአብሔር ፊት በምሆንባቸው ጊዜያቶች ውስጥ፥ ከአምላኬ ጋር ለመነጋገር ቃል ከአንደበቴ ሳላወጣ በፊት ዝም ብዬ መንፈሴ ውስጥ ያለውን ሰላም መጠኑን በብዙ ጸጥታ ውስጥ ሆኜ አዳምጠዋለሁ። የሰላሜን መጠን መመዘን ወይንም መገምገም ተለማምጃለሁ።

አብዛኛውን ጊዜ የሰላሜ መጠን ብዙ ሆኖ የማገኘው፥ ከእግዚአብሔር ሀሳብ ጋር ተስማምቼ ለመሄድ ዋጋ በምከፍልባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ነው። በመታዘዝ በምሄድባቸው ጊዜያቶች ውስጥ ነው። ይሄ ነገር ከገባኝ ጊዜ ጀምሮ ውስጤ ያለው የሰላም መጠን ሲቀንስ፥ ልታዘዝ ወይንም ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ልስማማ የሚገቡኝን ጉዳዮች ያሳየኝ ዘንድ በፊቱ ራሴን አቀርባለሁ። ይሄ እንግዲህ እግዚአብሔር ህይወቴን ወደራሱ ሀሳብ የመራበትና እግሮቼን በፈቃዱ መንገድ ያቀናበት አስደናቂ መንገድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ከእግዚአብሔር ሀሳብ ጋር ለመስማማት ዋጋ እየከፈልኩ ስመላለስ ደግሞ፥ የሰላሜና የደስታዬ መጠን ከፍ ሲል መንፈስ ቅዱስ በውስጤ እየተደሰተ ሲያስደስተኝ እሰማዋለሁ። ሰላም ልቤ ውስጥ ብዙ ይሆናል፣ ለመሳቅ የምፈልገው ምክኒያቶችን ይሆናል። ምክኒያቶች ካጣሁ ደግሞ ምክኒያት እስኪፈጠር ሳልጠብቅ ያለ ምክኒያት ዝም ብዬ እስቃለሁ። ሰው አደጋ ላይ ሕይወቱ ሲወድቅ ሰላም ሊሰማው እንደማይችል ሁሉ፥ የእግዚአብሔር ሀሳብ በሌለበት ጎዳና እየሄድን እንደሆነ ከምናውቅባቸው ዋና ዋና መንገዶች ውስጥ አንዱ ውስጣችን ያለው የሰላም መጠን ነው። የእግዚአብሔር ቃል በኢሳይያስ ምእራፍ 55፥12 ላይ ሲናገር “እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ” ይላል:: የእንግሊዘኛው መጽሀፍ ቅዱስ ይሄንኑ ቃል ሲጽፈው “በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትመራላችሁ።” በማለት ያስቀምጠዋል። እግዚአብሔር ምንጊዜም እኛን የሚመራን በሰላም ውስጥ ነው። በሌላ አማርኛ የመንፈስ ቅዱስን ሰላም እየተከተልን ሄድን ማለት፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እየተከተልን ሄድን ማለት ነው ብለን በድፍረት መናገር እንችላለን። መጽሀፍ ቅዱስ በገላትያ መጽሀፍ ምእራፍ 5 ላይ የመንፈስ ፍሬ ብሎ ከዘረዘራቸው ዋና ዋና ፍሬዎች ውስጥ ሰላም እና ደስታ ይገኙበታል:: ሰላም እኛ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በተግባባንና በተስማማን መጠን በሕይወታችን እየበዛና እየጨመረ የሚሄድ ነገር ነው።

ጊዜው ቆየት ቢልም አንድ አገልጋይ ሰላምን የገለጸበት መንገድ ልቤ ውስጥ ቀርቷል። ባልና ሚስት ሲጣሉና ሲጨቃጨቁ ቤቱ በሙሉ ይደብራል አለ። ቤቱ ያስጠላል። ሲታረቁና ሲዋደዱ ደግሞ ሙሉ ቤቱ ሳቅና ጨዋታ ሰላምና ደስታ ይሆናል። የቤቱ ሰላም መጨመርና መቀነስ የሚወሰነው በእነርሱ መግባባትና መስማማት ነው:: የአንድ አማኝ ሰላም መጠኑ የሚወሰነው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ባለው መግባባት እና መስማማት ነው። የእግዚአብሔርን ሀሳብ እየተከተልንና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እየተስማማን በሄድን ቁጥር የሰላም መንፈስ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በእኛ ውስጥ በሙላት ይኖራል፥ ሰላማችንም ብዙ ይሆናል።

ምርጫ 

ምርጫ