Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ልቤ

ልቤ

ዛሬ ቀኑ ፀሀያማና ደስ የሚል ነው። እኔም ከሰዎች ጋር አንድ አስፈላጊ ቀጠሮ ስላለኝ ወደዛ ለመሄድ እየተዘጋጀሁ ነው። መዘነጥ አይበላችሁ! ፏ ብያለሁ! የክት ልብሴን ለባብሼ፥ ፀጉሬን አስተካክዬ፥ ሽቶዬን ተቀባብቼ ከጨረስኩ በኋላ፥ ከመውጣቴ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ራሴን በመስታወት ማየት ስለነበረብኝ ወደ መስታወቱ ጋር ጠጋ ብዬ ራሴን ማየት ጀመርኩ። እዛው እንደቆምኩ ጥቂትም ሳይቆይ ነው ሀሳቦች በልቤ መምጣት የጀመሩት። እነዚህ የምሄድባቸው ሰዎች እኮ መልኬን ብቻ ነው ማየት የሚችሉት። እንዲህ መልኬን የሚያሳይ መስታወት እንዳለ ልቤንም የሚያሳያቸው መስታወት ይኖር ይሆን? እያልኩ መልኬንም ልቤንም በአንድ ጊዜ ማየት ስለሚችለው አምላክ ማሰብ ጀመርኩ። ነፍሴን ከመንፈሴ መለየት እስኪችል ድረስ ዘልቆ የሚገባው ቃሉ፥ ልቤ ውስጥ ያሉትን ሀሳቦች በሀሳብ ደረጃ ገና ወደ ልቤ ከመምጣታቸው በፊት ያውቃቸዋል። ምኞቶቼን ከነ ምክኒያታቸው መርምሮ እኔ እንኳን ስለ ራሴ የማላውቃቸውን ማንነቶቼን በዝርዝር ያውቃቸዋል። የእኔን ትክክለኛ ማንነት ለማወቅ የትኛውንም የቅርቤን ሰው መጠየቅ አያስፈልገውም። ገና ከእናቴ ማህፀን ሳይፈጥረኝ በፊት፥ የህይወቴን አካሄድ አይቶታል። ያልተፈጠሩትን ቀናቶቼን ደግሞ አንድም ሳይቀሩ በራሱ መፅሀፍ ላይ ፅፏቸዋል። ሰዎች እንዳያውቁብኝ ብዬ በልቤ የሚስጥር ክፍል ውስጥ ያስቀመጥኳቸውን ሚስጥራቶች በሙሉ ፊት ለፊት ያያቸዋል። የሆንኩትን ካልሆንኩት ለይቶ ትክክለኛ ማንነቴን በሚያውቀው አምላክ ፊት እንደምወጣና እንደምገባ ሳስበው ፈራሁምም ተገረምኩምም። 

ታዲያ ግን ቆይ ሰዎች ስለሚያዩት ውጫዊው ማንነታችን ይሄንን ያህል ከተጨነቅን፥ 24 ሰዓት በእግዚአብሄር ፊት እየታየ ስላለው ልባችን የማንጨነቀው ለምንድነው? ጠዋት ከቤታችን ስንወጣ፥ ስለ አለባበሳችን ተጨንቀን አለባበሳችንን አሳምረን ከወጣን፥ ለምንድነው የህይወታችንን ትርጉም በያዘው አምላክ ፊት የሚታየው ልባችንን አስተካክለን የማንወጣው? በህይወታችን ላይ እኮ ትክክለኛውን ፍርድ ሰጪ ሰው አይደለም፥ እግዚአብሄር ነው። የሚመዝነን ደግሞ በአለባበሳችንም አይደለም። ባንካችን ውስጥ በሰበሰብነው የገንዘብ መጠንም አይደለም። በምንነዳው የመኪና ዘመናዊነትም አይደለም። በትምህርት ደረጃችንም አይደለም። በእኛ ምድራዊ መለኪያዎች አይደነቅም። አይምሮአችንን ፈጥሮ፥ በአይምሮአችን የግምት መጠን ውስጥ ሊገባ የማይችለው ይሄ ትልቁ እግዚአብሄር ከእነዚህ እድሜ የጠገቡ ተራሮች አንስታችሁ፥ ሰው በእውቀቱ ልክ ተመራምሮ ያልደረሰባቸው ሰማይ በሉት ምድር፥ ህዋ በሉት ጠፈር፥ የብስ በሉት ደረቅ ምድር እነዚህ ሁሉ እግዚአብሄር ከአንደበቱ ያወጣው የአንድ ቃል ውጤቶች ናቸው። እኛ በአውሮፕላን ከፍታ ላይ ወጥተን በመደነቅ ፎቶ የምናነሳቸው ደመናዎች ደግሞ፥ ለእርሱ የእግሩ ትቢያዎች ናቸው።  

ይሄ ሰማይ ዙፋኑ ሆኖ ምድርን የእግሩ መረገጫ ያደረገው ትልቁ አምላክ፥ እነዚህን ሁሉ እጁ ሰርታ ከጨረሰች በኋላ ልክ እንደ እኔና እንደ እናንተ በሰማይ ትልቅነትም ሆነ በምድር ስፋት አልደነቅም አለ! መንፈሱ ወደተሰበረና በቃሉ ወደሚንቀጠቀጥ ልቡ ውስጥ ትህትናን ባገኘበት ሰው ግን ተደነቀ! በሰው ልጆች የልብ ሁኔታ ግን ተደነቀ! ምን አይነት ነገር ነው ቆይ?! ይሄ ከአይምሮአችን በላይ የሆነው አምላክ የእኛን ልብ ለማየት ጊዜ እራሱ አለው እንዴ? ልባችንን ለማየት ጊዜ አለኝ ማለቱ ሳያንስ፥ ልባችንን ቤቱ ለማድረግ መፈለጉ ምን አይነት ተአምር ነው?! ቆይ እኛ ማነን? እኛ ምንድነን? 

እኛ ደግሞ እንዲያው ጥሎብን የሚያስጨንቀን በሰዎች ፊት ትክክል እና ፍፁም ሆኖ መታየት ነው። “ሰው ምን ይለኛል?” የሚለው ሀሳብ ህይወታችንን በይሉኝታ መኪና ወደ ወደደው ይነዳዋል። ከአለባበሳችን ጀምሮ፥ አነጋገራችን፥ ድርጊቶቻችንና ውሳኔዎቻችን በሙሉ “ሰው ምን ይለኛል?” በሚለው ተፅእኖ ስር ያደሩ ናቸው። ሰዎችን መፍራት ወጥመድ ሆኖብን፥ እግዚአብሄር እንድንኖር ከፈለገው የነፃነትና የአላማ ህይወት እየጎደልን ያለነው ጥቂቶች አይደለንም። አንዳንድ ጊዜ ትክክለኛ ያልሆኑ ነገሮችን ስናደርግ፥ የመጀመሪያው ጭንቀታችን ሰው እንዳያየንና እንደያውቅብን ነው። አይቻልም እንጂ ቢቻል፥ ከእግዚአብሄር ተደብቀን በሰው ፊት ብናደርገው ነበር የሚሻለው። በጣም መፈራት ያለበት ሰው የሚያየው ነገራችን አይደለም። እግዚአብሄር የሚያየው ነገራችን ነው። ያ ሰው ሊያየው የማይችለው በእግዚአብሄር ዘንድ ግን 24 ሰአት እየታየ ያለው ነገራችን ደግሞ ልባችን ነው። ይሄ ልብ የሚባለው ነገር በእኛ ውስጥ ይኑር እንጂ፥ እግዚአብሄር መላው ህይወታችንን ለመመዘን የሚጠቀምበት ዋና ነገሩ ነው። ልባችንን መዝኖ ሊያከብረንም  ሊንቀንም ይችላል። በሰዎች ዘንድ ይሄ ነው የማይባል ክብር የተሰጣቸው፥ በእግዚአብሄር ፊት ግን የተናቁ ብዙ ሰዎች አሉ። በአንፃሩ ደግሞ፥ በሰዎች ዘንድ ቦታ ያልተሰጣቸው፥ በእግዚአብሄር ፊት ግን ሞገስ ያገኙ ሰዎች አሉ። 

በመልክና በውጫዊ ነገር፥ በቁመትና በዘለግታ ቢሆን ኖሮ የእስራኤል ንጉስ የሚሆነው ዳዊት ሳይሆን ወንድሙ ኤልያብ ነበር። ደግነቱ ከእግዚአብሄር የሚመጣ ቅባት አድራሻ አይስትም እንጂ፥ የኤልያብ ሁኔታ እኮ እንኳን ሌላ ሰውን፥ ከዳን እስከ ቤርሳቤ ቃሉ ጠብ የማይለውን አንጋፋውን ነብይ እንኳን አሳስቷል። እግዚአብሄር ግን ፊትን አላይም አለ! ስለ ውጫዊውና ሰው ስለሚያየው ነገራችሁ ብዙም አይገደኝም አለ። ልባችሁን ግን ሁልጊዜ እየመረመርኩ እመዝናችኋለሁ አለ። የእግዚአብሄርን ቅባት ከሰማይ ጎትቶ ያመጣው የዳዊት ልብ፥ ለንግስና ተፈልጎ ከጫካ ተጠራ። ሲመሰክርለትም እንደ ልቤ አለው! ልቡ ከልቤ ጋር ይሄዳል አለ። ኤልያብ በእግዚአብሄር ፊት የተናቀው፥ ዳዊትም በእግዚአብሄር ፊት የተወደደው ሁለቱም በልባቸው ሁኔታ ነው። እውነትም መፅሀፍ ቅዱስን ስታጠኑ፥ ዳዊት ከምንም ነገር በላይ ቀንና ሌሊት የሚያስጨንቀው ሰው ስለሱ የሚለው ነገር ሳይሆን፥ በእግዚአብሄር ፊት የሚታየው የልቡ ሁኔታ ነው። ብልህ ነው። ልብ በእግዚአብሄር ፊት ያለው ቦታ በደምብ የገባው ይመስላል። ልቤን መርምረው ይላል። ፈትነኝ ይላል። ልቡን በንፅህና መጠበቅ ሲሳነው ደግሞ፥ ንፁህ ልብን ፍጠርልኝ እያለ ይለምናል።  

በመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ በዘመናቸው ትልልቅ ተፅእኖዎችን ያመጡ ሰዎችን ህይወት ስታጠኑ፥ በእግዚአብሄር ፊት በትክክለኛ ልብ የሄዱ ሰዎች ናቸው። እግዚአብሄር ልባቸውን የወደደላቸው ሰዎች ናቸው። አንድ ትልቅና የምናከብረው ሰው አጠገባችን ቢኖር፥ ለዛ ሰው ክብር ስንል የምንናገረውን ሁሉ አስበንና ተጠንቅቀን እናደርጋለን።  ያ ትልቅ ሰው እያየን እንደሆነ ስለምናውቅ፥ አብሮነቱንና በፊቱ መሆናችንን ዋጋ እንሰጠዋለን። እንደፈለግን ከሆንን፥ አጠገባችን መሆኑና አለመሆኑ ትርጉም ካልሰጠን፥ በአጭሩ ያንን ሰው ንቀነዋል ማለት ነው። ህይወታችን መለወጥና መቀየር የሚጀምረው፥ 24 ሰአት በእግዚአብሄር ፊት እየታየን እንደሆነ በማስተዋል ስንኖር ነው። 24 ሰአት ስንል፥  እኛ በሀይለኛ እንቅልፍ ውስጥ ሆነን ራሳችንን በማናውቅበት ሰአት እንኳን፥ እግዚአብሄር ልባችንን እየመረመረ ነው። ዳዊት ሲፀልይ እንዲህ ይላል “ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጎበኘኸኝ፥ ፈተንኸኝ፥ ምንም አላገኘህብኝም” (መዝ 17፡3) “ክብር እሰጥሀለሁ ጌታዬ” ብለን ብንዘምር ህይወታችን ክብርን ካልሰጠው ምን ትርጉም ይኖረዋል? በመዝሙሩ ዜማና ሙዚቃ እንደሆነ አይደነቅም። እግዚአብሄር እኮ በመላእክት ዜማ ቀንና ሌሊት ይመለካል! ትርጉም የሚሰጠው በቀናቶቻችን ውስጥ እኛን ማየቱን እውቅና መስጠታችን ነው። ሁሉን በሚያዩ አይኖቹ ፊት እንደምንወጣና እንደምንገባ በመረዳት የምንኖረው ኑሮ ነው። ይሄ ኑሮ ከመዝሙሩ ጋር ሲደመር የዝማሬ አምልኮአችንን ይቀበለዋል። 

እግዚአብሄር ልብ ላይ ትኩረት የሚሰጥ አምላክ ከመሆኑ የተነሳ፥ እንማር ዘንድ መፅሀፍ ቅዱስ ስለ ተለያዩ የልብ አይነቶች ፅፎልናል። ትእቢተኛ ልብ አለ፥ አመፀኛ ልብ አለ፥ ሰነፍ፥ ሀጢያትን የሚመኝ፥ ክፉና፥ አሳች እንዲሁም ግብዝ የሆነ ልብ አለ። በአንፃሩ ደግሞ እግዚአብሄርን የሚፈራ፥ ትሁት የሆነ፥ ንፁህ፥ ትጉህ፥ ጥበበኛና መልካም ልብ አለ። የእኛ ልብ በእግዚአብሄር ፊት ሲታይ ምን ይመስላል? ዛሬ እስኪ ትኩረታችንን ከሌሎች ከማይጠቅሙን ነገሮች ላይ አንስተን እግዚአብሄር ዋጋ በሚሰጠው ነገሮች ላይ እናድርግ። ልባችንን ለመመርመር ጥቂት ጊዜ እንውሰድ። አንዳንድ ጊዜ እኮ በህይወታችን ላይ ያን ያህል ቦታ ለማንሰጣቸው ነገሮች የምንጨነቀቅን ያህል እንኳን፥ ስለ ልባችን ግድ አይለንም። ልባችንን ሰው ሊያይብን ስለማይችል ውጪያችንን ብቻ አሳምረን ስንሄድ፥ ኢየሱስ “የተለሰናችሁ መቃብሮች” ያላቸው ፈሪሳውያን እንደዚህ አይነት ሰዎች ነበሩ። የምድር ሰው ሁሉ ተሰብስቦ ቢቀበለንና ቢወደን፥ እግዚአብሄር ግን ከናቀን ምን ይጠቅመናል? ትርጉሙስ ምንድነው?

ችላ ያልነው ጠላታችን

ችላ ያልነው ጠላታችን

ደውል

ደውል