Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ችላ ያልነው ጠላታችን

ችላ ያልነው ጠላታችን

አንዳንድ ጊዜ ስፀልይ፥ ስዘምር፥ መፅሀፍ ቅዱሴን ሳነብ በጣም መንፈሳዊ እንደሆንኩ ብቻ ሳይሆን መልአክ እንደሆንኩኝም ነው የሚሰማኝ። በግራና በቀኜ ያሉትን ክንፎቼን ፈልጌ ሳላበቃ፥ መልሼ ራሴን የማልጠብቀው ቦታ ላይ አገኘዋለሁ። እንዴ ቆይ እኔ መንፈሳዊ ሰው አይደለሁ እንዴ? እንዴት ነው እንዲህ አይነት እግዚአብሄር የማይከብርበት ሀሳብ አይምሮዬ ውስጥ ሊመጣ የሚችለው? እንዴትስ ነው በገዛ ስጋዬ ምኞት ልሳብ የምችለው? እያልኩ አንዴ ሳወጣ አንዴ ሳወርድ አስቤ አስቤ ቆይቼ ቆይቼ፥ ከተማርኩ በኋላ፥ ምንም አይነት የመልአክ ዘር ውስጤ አለመኖሩን፥ ይልቁንም የሰው ልጅ በእርግማን ከወደቀ በኋላ፥ በስጋው ተሸክሞ ከሚዞረው የስጋ ምኞት ጋር በመጋደል ለመኖር እንደተጠራሁ ገባኝ።

ዛሬ በውስጤ የሞላውን ሀሳብ ሳካፍላችሁ፣ ይሄ ነው የማልለው ደስታ ይሰማኛል። ለምን መሰላችሁ? በህይወቴ፣ በመውጣትና በመውረድ፥ በመሳትና በመመለስ፥ በእግዚአብሄር የፀጋው ብርታት ተደግፌ፥ ባለማስተዋሌ ውስጥ ባሳለፈው እውቀቱ ተደንቄ የተማርኩት፣ አሁንም እየተማርኩ ያለሁትና እያንዳንዱን የትግል ቀናቶቼን ለማሸነፍ ብርታት የሆነኝን ነገር ስለማካፍላችሁ ነው። 

በዚች በተሰጠን አጭር እድሜ ውስጥ ስንኖር፥ ከተጠራንባቸው ዋና አላማዎች ውስጥ አንዱ ከሀጢያት ጋር እየታገልን በመኖር፣ በክርስቶስ የተሰጠንን የአሸናፊነት ህይወት ለመጠበቅ ነው። ሁላችንም መጀመሪያ ስጋውያን ነበርን:: ቀጥሎ ነው መንፈሳውያን የሆነው። በፊት፥ የገዛ ምኞታችን  የሚመራን፥ በስጋችን ፈቃድና ምኞት እንኖር የነበርን የገዛ ስጋችን ባሪያዎች ነበርን። አሁን ግን የሚመራን የስጋችን ምኞት አይደለም:: በውስጣችን የሚኖረው የእግዚአብሄር መንፈስ ነው። 

መፅሀፍ ቅዱስ ሲናገር፣ በምድር ላይ እግዚአብሄርን አስከብረው ያለፉ፥ የዚህን ምድር ቆይታቸውን በአላማ  የኖሩ፥ ከህይወታቸው ብዙ የተማርንባቸው ሰዎች አሉ። እነ ጳውሎስን፥ እነ ሙሴን፥ እነ ዳዊትን፥ እነ አብርሀምንና ብዙዎችን በምሳሌነት መጥቀስ እንችላለን። በአንፃሩ ደግሞ ከእግዚአብሄር ጋር የጀመሩ ነገር ግን አላማቸው መንገድ ላይ የተሰናከለባቸውና ሩጫቸውን ያልጨረሱ ሰዎችን እነ ሳኦልን፥ ሳምሶንን፥ አብዛኛውን የእስራኤልን ህዝብ የምድረበዳ ጉዞ ጨምሮ ብዙዎችን በምሳሌነት ማንሳን እንችላለን። በጣም የሚገርመው ነገር፥ የተፈጠሩበትን ትልቅ አላማና እግዚአብሄር በህይወታቸው ላይ ያለውን ዘላለማዊ ሀሳብ በሚጨርሱና በማይጨርሱ ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት ለስጋቸው ምኞት የሰጡት ምላሽ ነው። አላማቸውን በትክክል ያልጨረሱትን ሰዎች ህይወት ስታጠኑ ያሰናከላቸውና መንገድ ላይ ያስቀራቸው ለገዛ ስጋቸው ምኞት የሰጡት ምላሽ ነበር።

ልማድ ሆኖብን ሰይጣን ላይ እናሳብባለን እንጂ፣ እኛ ከእግዚአብሄር ጋር በትክክል የምንሄድ ከሆንን በእግዚአብሄር መለኮታዊ ጥበቃ ስር ከመሆናችን የተነሳ ያለ እግዚአብሄር ፈቃድ ሰይጣን በህይወታችን ላይ ምንም የማድረግ መብት የለውም። ይልቁንም፣ ሰይጣን እራሱ እኛን ከእግዚአብርሄ ሀሳብ ለማጉደል እንደ መሳሪያ አድርጎ የሚጠቀመው የገዛ ስጋችንን ምኞት ነው። የእስራኤልን ህዝብ ታሪክ በጥልቀት ስታጠኑ፥ ጠላቶቻቸው ምንም ቢበዙና ሀይለኞች ቢሆኑ እንኳን፥ እንድም ጊዜ ያለ እግዚአብሄር ፈቃድ መጥተው ምንም ጉዳት አድርሰውባቸው አያውቁም። ህዝቡ እራሳቸው ግን በስጋቸው ምኞት ሲሰናከሉና በልዩ ልዩ ሀጢያት እግዚአብሄርን ሲፈታተኑት፥ መለኮታዊ ጥበቃውን ከላያቸው በማንሳት፣ ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር። አንድ ጊዜ የሞአብ ንጉስ የሆነው ባላቅ ከአምላካቸው ጥበቃና አብሮነት የተነሳ የእስራኤልን ህዝብ ቢፈራቸው፣ በልአምን በመጥራት ህዝቡን እንዲረግምለት ጠየቀው። በልአምም፣ እግዚአብሄር የባረከውን ህዝብ በፍፁም አልረግምም በማለት የእስራኤልን ህዝብ ሲባርክ፣ ባላቅ እስራኤልን ለመጉዳት የሞከረው ሙከራ አልሳካ ቢለው፣ አንድ ዘዴ አገኘ። የሀገሩ ሴቶች ከእስራኤል ወንዶች ጋር በሀጢያት እግዚአብሄርን እንዲበድሉ የተንኮል ሁኔታን በማመቻቸት ከአምላካቸው ጋር አጣላቸው። እግዚአብሄርም በእስራኤል ልጆች ላይ በመቆጣት፣ በፅኑ ቅጣት ቀጣቸው። በጣም መፍራት ያለብን በሀጢያት እግዚአብሄርን መበደል እንጂ ሰይጣን የሚያመጣብንን ክፉ ነገር አይደለም።  

 ሀጢያት ማለት የሰው ልጅ ከእግዚአብሄር ቃል ውጪ የሚያደርገውና እግዚአብሄር የሚፀየፈው ነገር ማለት ነው። ሀጢያት ምንጊዜም ከሀጢያት አይጀምርም። የሚጀምረው ከሀሳብ ነው። ሰይጣንም ይሄንን በደምብ ስለሚያውቅ ያለመታከት ለመቆጣጠር የሚፈልገው ማንነታችን ቢኖር አይምሮአችንን ነው። የሰይጣን ዋነኛ የጦር መሳሪያው ሀሳብ ነው። ሀሳብን በሰዎች አይምሮ ውስጥ አስቀምጦ ይሄዳል። ምንም አይነት የሀጢያት ሀሳብ አይምሮአችን ውስጥ መጣ ማለት ግን ሀጢያተኞች ነን ማለት አይደለም። የክፋት ሀሳብ ውስጣችን ስለመጣ ክፉዎች ነን ማለት አይደለም። ሰይጣን እንኳን እኛ ጋር፣ ኢየሱስም ጋር ሀሳብን ይዞ ሄዷል። ምንም መንፈሳዊ ሰዎች ብንሆን፥ እንዴት እንዲህ አይነት የሀጢያት ሀሳብ ልባችሁ  ውስጥ ይመጣል ብሎ እግዚአብሄር  አያዝንም። ማየት የሚፈልገው ግን አይምሮአችን ውስጥ ለሚመጡት የሀጢያት ሀሳቦች የምንሰጣቸውን ምላሾች ነው። በእነዚህ ምላሾቻችን ሊደሰትም ሊያዝንም ይችላል።

 “በመንፈስ ተመላለሱ የስጋንም ምኞት ከቶ አትፈፅሙ” (ገላትያ 5፡16)

 በፊት በስጋችን ፈቃድ ብቻ የምንመራ የስጋችን ባሪያዎች ነበርን። አሁን ግን ክርስቶስ ከሰጠን ስልጣኖች አንዱ፣ የገዛ ስጋችንን ውስጣችን ላለው ለእግአብሄር መንፈስ በማስገዛት በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ እንድንመላለስ ነው። ይሄ ነው የተሰጠን የአሸናፊነት ህይወት። ይሄንን የአሸናፊነት ህይወት ለመለማመድ የሚረዱንን ሶስት ዋና ዋና ተግባራዊ መንገዶች እስኪ እንመልከት።

 1. መሸሽ፡ “መሸሽ ልክ እንደ አሸናፊነት ይቆጠራል” የሚለው የሀገሬ ምሳሌያዊ አነጋገር ትዝ አለኝ። አያችሁ፣ በዚህ አለም ሂሳብ ሰው እሸነፈ ተብሎ የሚቆጠረው ፊት ለፊት ተጋጥሞ የእሱን ብርታት የበላይነት ሲያሳይ ነው። በእግዚአብሄር አለም ውስጥ ግን ሰው አሸነፈ የሚባለው የእግዚአብሄርን ሀሳብና ፈቃድ በህይወቱ ሲፈፅም ነው። ለምሳሌ የክርስቶስን የመስቀል ሞት ብታስቡት፥ ያሰቃዩትና የሰቀሉት ሰዎች በሙሉ እንደተሸነፈ ነበር የቆጠሩት። የክርስቶስ የማሸነፍ ሂሳብ ግን፥ ከመስቀል ወርዶ ራሱን ማዳንና ያሰቃዩትን ሰዎች ልካቸውን ማስገባት አልነበረም። እንደዛ ያላደረገው ስለማይችል ሳይሆን ለእርሱ አሸናፊነት ማለት ወደ ምድር የመጣበትን ዋና አላማ በመፈፀም ዓለምን ሁሉ በመስቀል ሞቱ ውስጥ ህይወትንና ትንሳኤን መስጠት ነበር። ስለዚህ ስለ ሀጢያት ስናወራ የአሸናፊነታችን የመጀመሪያው ተግባር በምኞት ፈተና ውስጥ ሊጥሉን ከሚችሉት ነገሮች በሙሉ ራሳችንን ማራቅ ነው። ለራሳችን እውነተኞች መሆን ከቻልን ወደ ሀጢያት ጎዳና የሞወስዱንን መንገዶች እናውቃቸዋለን። መንቃት ያለብን ተጠላልፈን ከወደቅን በኋላ አይደለም። አያችሁ እኛ ክርስቲያኖች እኮ በማስተዋል ለመኖር የተጠራን፥ የጥብና የማስተዋል መንፈስ የተሰጠን ህዝቦች ነን። በውስጣችን ያለው መንፈስ፣ አስተዋይ የሚያደርግ የማስተዋል መንፈስ ነው። ይሄ ማስተዋል ደግሞ፣ መጀመፊያ ላይ ቆሞ መጨረሻውን ማየት ይችላል። አንድ ሰው በሚያዳልጥ ጉድጓድ አጠገብ ቆሞ “እግዚአብሄር አምላኬ ሆይ፣ እባክህ እዚህ ጉድጐድ ውስጥ እንዳልወድቅ ጠብቀኝ” ብሎ አይፀልይም። ይልቁንም እንደሚያዳልጠው ስለሚያውቅና የራሱን ደህንነት ለመጠበቅ፣ ከጉድጐዱ ለመራቅና ለመሸሽ የተቻለውን ያደርጋል እንጂ። በእግዚአብሄር አለም ውስጥ ከሀጢያትና ወደዛ ከሚመሩን ጎዳናዎች መራቅ፣ የመጀመፊያው የአሸናፊነት መንገድ ነው። ይሄ የድላችን በር ነው። የተፈጠርንበትን ዓላማ ለማሳካት የጀመርነው ፅኑ የሆነ ውሳኔ ነው። በፍፁም አንፀፀትበትም። የህይወትና የሰላም መንገድ ነው። መጨረሻው ደግሞ ክብር ነው። ታዲያ ከምን ከምን እንሸሻለን ካልን፥ ለራሳችን እውነተኞች በመሆን ደጋግመን በሀጢያት የምንጠላለፍባቸውን መንገዶች እናስብ። የእነሱን ነገሮች መጀመፊያ አስተውለን በመመልከት፣ ከእነዚህ ነገሮች ለመራቅ እንሞክር። ጏደኞች ሊሆኑ ይችላሉ። የምናያቸው የቴሌሽን ቻናሎች ወይንም የማህበራዊ ገፆቻችን ሊሆኑ ይችላሉ።

“ወዳጆች ሆይ ነፍስን ከሚዋጋ ስጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መፃተኞች እንደመሆናችሁ እለምናችህለሁ” (1ኛ ጴጥሮስ 2፡11)

2. በቃሉ መሞላት፡  በክፉዎች ምክር አልሄድም፥ በዋዘኞች ወንበር አልቀመጥም፥ በሀጢያተኞች መንገድ ደግሞ አልቆምም፥ ብለን የሀጢያት መንገዶችን ሁሉ ከህይወታችን ካስወገድን በኋላ፣ በእግዚአብሄር ህግ መደሰት፥ ህጉን ደግሞ በቀንና በሌሊት ማሰላሰል ያስፈልገናል። እስኪ ቃሉን ስለማሰብና ስለማሰላሰል ጥቂት እንነጋገር። የጦርነቱ ዋነኛ ስፍራ እንግዲህ አይምሮአችን እንደሆነ ቀደም ብለን ተነጋግረናል። ጨዋታው አይምሮአችንን በሙሉ በመቆጣጠር፣ በፍቃዱ ስር ማስገዛት ነው። አይምሮአችን በእግዚአብሄር ቃል እውነት ሙሉ ከሆነ ግን፥ ሰይጣን የሚያመጣው ሀሳብ ቦታ ሊያገኝ አይችልም። የምናሰላስለው የእግአዚብሄርን ቃል ከሆነ፥ ፈቃዳችን በሙሉ የሚገዛው ለምናሰላስለው ቃል ነው። ብዙ ጊዜ መፅሀፍ ቅዱስን ስለማንበብ እንጂ ስለማሰላሰል ትኩረት ስንሰጠው አይታይም። ጠዋት ላይ ተነስተን አንድ ቃል አነበብን ከዚያም ወደ ጉዳያችን እንገባና ሀሳቦቻችን በተለያዩ ነገሮች ሲበታተኑ፣ ያነበብነው ቃል ምንም  ትዝ ሳይለን ይውላል። እስኪ ማታ ማታ ብቻችሁን ሁኑና፣ 5 ደቂቃ ውሰዳችሁ ቀናችሁ እንዴት እንደነበረ በማስተዋል ለማሰብ ሞክሩ። ከመደበኛ ስራችሁና እንቅስቃሴያችሁ በላይ፣ አይምሮአችሁን ቢዚ በማድረግ፣ የእግዚአብሄርን ቃል እንዳታስቡና እንዳታሰላስሉ ያደረጋችሁ ነገር ብዙ ነው። እነ ሶሻል ሚዲያ፥ ዩ ቱብ፥ በጣም አስፈላጊ ያልሆኑ የስልክ ጥሪዎች እና ብዙዎችን መጥቀስ እንችላለን። እነዚህ ነገሮች በህይወታችን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ቢሆኑም እንኳን፣ ጊዜ በመመደብና በማስተዋል ካልተጠቀምንባቸው፣ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ሊያመዝን ይችላል።

 ዋናው መፅሀፍ ቅዱስን ማንበብ ብቻ አይደለም። ማሰላሰልም ነው። ለዛ እኮ ነው ህጉንም በቀንና በሌሊት ያነባል ሳይሆን በቀንና በሌሊት ያስባል ያለው። ቀኑን ሙሉ ትዝታው ቃሉ ነው። በሌሊትም የሚያሰላስለው ያነበበውን ቃል ነው። በማሰላሰል ውስጥ ሀይል አለ። መፅሀፍ ቅዱስ ነቢያቶች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የፃፉት መፅሀፍ ስለሆነ፣ ከዚህ መፅሀፍ ጋር ያለንን ህብረት የምናሳድገው፣ ስናነበው ብቻ ሳይሆን ያነበብነውን በማሰላሰል ነቢያቶቹ የፃፉበትን መንፈስ ስናገኘው ነው። ህይወታችንን የሚቀይረው ቃሉን ማወቃችን ብቻ አይደለም። በቃሉ ውስጥ ያለውን መንፈስ ማግኘታችን ነው። ኢየሱስ እኔ የምነግራችሁ ቃል ህይወትም መንፈስም ነው እንዳለ፣ ከቃሉ ውስጥ ህይወታችን የሚለወጥበትን መንፈስና ህይወት የምናገኝበት ትልቁ መንገድ፣ ጊዜና ሁኔታ በማመቻቸት ማሰላሰላችን ነው። አንድ ጊዜ የእግዚአብሄር ሰው ሙሴ ከሞተ በኋላ ፣ እግዚአብሄር ኢያሱ ጋር መጥቶ፣ አይዞህ ፅና በርታ ከሙሴ ጋር እንደነበርኩ እንዲሁ ከአንተም ጋር እሆናለሁ ብሎ ካበረታታው በኋላ እንዲህ አለው። “የዚህ ህግ መፅሀፍ ከአፍህ አይለይ፥ በውስጡ የተፃፈውን ሁሉ ትጠብቅና ታደርገው ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው” አለው። ቃሉን እንድትፈፅመው የሚረዳህ በቀንና በሌሊት ማሰብህና ማሰላሰልህ ነው ይለዋል። መፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ቃሎች ማሰላሰላችን፣ ተራና አሮጌ የሆኑ አስተሳሰቦችን ከውስጣችን አውጥቶ አይምሮአችን በማደስ፣ እግዚአብሄር ነገሮችን እንደሚያያቸው እንድናይ ይረዳናል። በክርስቶስ የተሰጠንን ሀጢያትን የማሸነፍ ህይወት እንድንለማመድ ከሚረዳንና በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ውስጥም ዋነኛው ነው።

 “አለቆች ደግሞ ተቀምጠው እኔን አሙኝ፥ ባሪያህ ግን ህግህን ያሰላስል ነበር” (መዝሙረ ዳዊት 119፡23)

 3. በመንፈስ መፀለይ፡  

“በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በሀይል እንድትጠነክሩ፥ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር፥ እንደ ክብሩ ባለጠግነት መጠን ይስጣችሁ” (ኤፌሶን 3፡16)

የፀሎትን አስፈላጊነት ሁላችንም እንደምናውቀው ሆኖ፥ ከሀጢያት ጋር ላለን ጦርነት ይሄ ነው የማይባል አስተዋፆ ያደርጋል። በፀሎት ውስጥ፥ ከመንፈስ ቅዱስ የምንቀበለው ሀይል አለ። ይሄ ሀይል ደግሞ ባለንበት መንፈሳዊ ጦርነት እንዳንሸነፍ የሚያበረታንና፣ ውስጣዊ ሰውነታችንን ወይንም መንፈሳችንን የሚያጠነክርልን ነው። አንዳንድ ጊዜ በመንፈሳችሁ በጣም ደክማችሁ፥ ብቻችሁን ወይንም በህብረት ፀሎት ውስጥ ስትፀልዩ ውስጣችሁ ጠንክሮ ሀይል ተሰምትዋችሁ አያውቅም? ያ፣ በፀሎት ውስጥ ያገኛችሁ የመንፈስ ቅዱስ ሀይል ነው። ይሄ ሀይል መንፈሳዊ አካላችንን በማጠንከር፥ ሀጢያትን እምቢ የምንልበትን አቅም የሚሰጠን ነው። በፀሎት ውስጥ የምናገኘው የእግዚአብሄር መንፈስ፥ የተጠራንበትን ህይወት እንድንኖር የሚሰጠን አቅም አለ። በመንፈስ ስንፀልይ፥ ክርስቶስ ሀጢያትን ድል ያረገበትን መንፈስ ነው የምንሞላው።

እግዚአብሄር እኛን በጣም ከመውደዱ የተነሳ ካደረገልን ትልልቅ ነገሮች ውስጥ አንዱ፥ 24 ሰአት ራሱን ለእኛ ማስገኘቱ ነው። በጣም ውድ ሆኖ እያለ፥ እሱን ለማግኘት ግን ቀጠሮ እንድንይዝ  አልጠየቀንም። በየትኛውም ሰአትና ቦታ፥ ያለ ገደብ ራሱን ያስገኘልን አምላክ ይባረክ! እየሰራን፥ መንገድ ላይ እየሄድን፥ ምግብ እያበሰልን፥ ሰዎች መሀል ቁጭ ብለን እንኳን፥ በልባችን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መነጋገርና ህብረት ማድረግ እንችላለን። ይሄ ከእግዚአብሄር መንፈስ ጋር ያለን ህብረታችን፣ ሀጢያትን በማሸነፍ፣ እንድንኖር ለተጠራንበት ህይወት ይሄ ነው የማይባል ሚና ይጫወታል።

በመጨረሻ አንድ ነገር ብለን እንጨርስ። እግዚአብሄር የጠራንን የክብርና ድል የሞላበት ህይወት ለመኖር፣ የሚያስፈልገንን ሁሉ በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥ ሰጥቶናል። የተሰጠንን የአሸናፊነት ህይወት ጠብቆ ለመኖር በምናደርገው ትግል ውስጥ፣ በፍፁም ብቻችንን አይደለንም። የእግዚአብሄር እርዳታ ከሙሉ የፀጋው ብርታትና መንፈስ ጋር እኛን ለመርዳት ከጎናችን ነው። ሲደክመን እንኳን ድካማችንን አይቶ የሚራራልንና የሚረዳን አምላክ ነው ያለን። ምንም በሀይሉ የበረታ አምላክ ቢሆንም እንኳን፣ ድካም ምን ማለት እንደሆነ ይገባዋል። በድካማችን ውስጥ ሀይሉን በማሳለፍ ለራሱ ክብርን ይወስዳል።  ወደዚህ ህይወት ሲጠራን ደግሞ፣ የእኛን አቅምና ችሎታ ተማምኖ አይደለም። የፀጋውን ጉልበት፣ ራሱን ተማምኖ ነው። እግዚአብሄር ከእኛ የሚፈልገው፥ ፈቃደኝነትና ውሳኔያችንን ብቻ ነው። በፍቃድና በውሳኔያችን እንዲሁም እርሱን በመፍራት ለመኖር  በምንሞክረው ጥቂት ሙከራ፣ የራሱን አቅም በህይወታችን በማሳለፍ በፍፁም በራሳችን አቅም ለመኖር የማንችለውን ህይወት የሚያኖረን እግዚአብሄር እራሱ ነው። በዚህ ከሀጢያት ጋር ለመታገል በተጠራንበት ህይወት ውስጥ ደግሞ መውደቅም መሳትም አለ። ፃድቅ 7 ጊዜ ቢወድቅም እንኳን 7ቱንም ጊዜ ከወደቀበት ተነስቶ የጀመረውን ሩጫ ለመጨረስ በትእግስት እንደሚሮጥ ሁሉ፣ ዛሬ ላይ የመታን እንቅፋት ድጋሚ እንዳይመታን መንገዳችንን አስተካክለን፣ የጀመርነውን የክብር ፍፃሜ ያለው መንገድ መቀጠል እንችላለን። 

kelly-sikkema-ERk-ufpaV0Y-unsplash.jpg
ትምህርት ቤት

ትምህርት ቤት

ልቤ

ልቤ