Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ትምህርት ቤት

ትምህርት ቤት

አንድ የቅርብ ጓደኛዬ፥ በህክምና ፊልድ ውስጥ የመሆንና በዚህ የስራ ዘርፍ የማገልገል ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት ስለነበራት፥ በነርሲንግ ፕሮግራም ውስጥ ገብታ ለሁለት አመታቶች በትጋት ትምህርትዋን ትከታተል ነበር። የቅርብ ወዳጄ በመሆንዋ፥ በተገናኘንባቸው ጊዜያቶች ሁሉ የትምህርትዋን ሁኔታ ታጫውተኝ ነበር። እዚህ የትምህርት ፕሮግራም ውስጥ ከመግባቷ በፊት፥ ስለ ህክምናም ሆነ ስለ ተያያዥ ነገሮች ምንም አይነት እውቀት አልነበራትም። ይሄ የጀመረችው የህክምና ትምህርት ታዲያ ለሁለት የሚከፈል ነው። ግማሹን ጊዜ ቁጭ ብለው ከአስተማሪያቸው እንዲማሩ ከተደረጉ በኋላ፥ የቀረውን ጊዜ ደግሞ የተማሩትን በተግባር ማዋል እንዲማሩና የበለጠ ልምድ እንዲኖራቸው በየሆስቲታሎች ውስጥ በመሄድ የተማሩትን እንዲለማመዱ ይደረጋሉ። ይሄን የትምህርት አካሄድ ሳየው፥ ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን የመንፈሳዊ ህይወት ያሳስበኛል። በየቤተክስቲያኖቻችን ከምንማራቸው ትምህርቶች እንዲሁም መፅሀፍ ቅዱስን አንብበን ከተረዳናቸው ነገሮች በተጨማሪ፥ እግዚአብሄር በህይወታችን አካሄዶች ውስጥ እራሱን በመግለጥ እንድናውቀው ይፈልጋል። 

የመዳንን እውቀት ካገኘንበትና ኢየሱስን የህይወታችን አዳኝና ጌታ አድርገን ዳግም ከተወለድንበት ጊዜ ጀምሮ፥ ልክ አንድ የተወለደ ህፃን እድገቱ በጊዜ ውስጥ እንደሚታይ ሁሉ፥ ከእኛም ህይወት እግዚአብሄር የሚጠብቀው ዋነኛ ነገር እድገትን ነው። እግዚአብሄር እሱን በማወቅና በማመን እንድናድግ ይፈልጋል። እምነታችን ለዘላለም ህይወት ብቻ ከመሆን አልፎና አድጎ በሌሎች የህይወታችን ጉዳዮችም እንድናምነው ይፈልጋል። እሱን በማወቅ እንድናድግና ባህሪያቶቹን ሁሉ እንድንማር፥ እንድንማር ብቻም ሳይሆን ደግሞ፥ የራሱን ባህሪያቶች እኛ ውስጥ ማየት ይፈልጋል። ስለ እርሱ ያለን እውቀት እድጎና ለራሳችን ከማወቅ አልፈን፥ ለሌሎች ስለ እርሱ እንድንናገርና እንድናወራ ይፈልጋል። 

ታዲያ እምነታችንን ሊያሳድግና ሊያስተምረን እንዲሁም ለእርሱ ያለን እውቀት እንዲያድግ ሲፈልግ፥ የሚወስደን የህይወት መንገዶች አሉት። የምንማርበትን መንገድ መራጮቹ ደግሞ እኛ አይደለንም። መንገዱን የሚመርጥልን እግዚአብሄር እራሱ ነው። እንድንማር የወደደውን ነገር በምን መንገድ ውስጥ ብናልፍ እንደምንማረው ያውቃል። በየትኛው መንገድ ውስጥ ህይወታችንን ቢያሳልፈው ልባችንን እንደሚያገኘው ያውቃል። “እግዚአብሄርን የሚፈራ ሰው ማነው? በሚመርጠው መንገድ ያስተምረዋል” (መዝሙረ ዳዊት 25፡12)

ሁላችንም ብንሆን፥ ዛሬ ላይ ከትላንትና ይልቅ ስለ እግዚአብሄር የተሻለ እውቀት አለን። ቁጭ ብለን በትምህርትና በስብከት ከምንማራቸው ትምህርቶች ጎን ለጎን፥  በህይወቶቻችን መንገዶች ደግሞ የምንማራቸው ትምህርቶች አሉ። እስኪ ህይወታችንን ዞር ብለን ያለፍንባቸውን ከባባድ ጊዜያቶች እናስባቸው። ለዛ ጊዜ በጣም ከባድና ፈታኝ ጊዜያቶች ቢሆኑም እንኳን፥ ዛሬ ላይ ግን የቆምንባቸው እውቀቶቻችን ናቸው። ዛሬ ላይ፥ እግዚአብሄርን የበለጠ እንድናምነው ያደረጉን እምነቶቻችን ናቸው። እግዚአብሄር አጠገባችን ይሁን እንጂ፥ ምንም ነገር እንደማንሆን ያወቅንባቸው ድፍረቶቻችን ናቸው። 

እኛ ክርስቲያኖች ሳንነጋገር የተስማማንበት አንድ ነገር ምንድነው? በህይወታችን ውስጥ የሚመጡ ጥሩ ጥሩ ነገሮች ሁሉ ከእግዚአብሄር፥ ከባድ ከባድ መንገዶች ሁሉ ደግሞ ከሰይጣን ነው የሚል የተሳሳተ እምነት አለን። በደምብ አስተውለን ካየነው ግን፥ ከጠላት የሚቀርቡ መልካምና ያማሩ እንዲሁም ምቾት ያለባቸው የሚመስሉ የህይወት መንገዶች እንዳሉ ሁሉ፥ ከባድና ፈታኝ የሆኑ እግዚአብሄር እንድናልፍባቸው የሚፈቅዳቸው መንገዶች ህይወታችን ላይ አሉ። እኛ አካሄዳችንን ከእግዚአብሄር ጋር እናስተካክል እንጂ፥ የትኛውም ከባድ ነገር ያለ ምክኒያት ወደ ህይወታችን አይመጣም። ሰይጣንም ቢሆን እግዚአብሄር ሳይፈቅድለት እኛ ላይ ምንም የማድረግ መብት የለውም። ታዲያ እነዚህ እግዚአብሄር እንማር ዘንድ የሚመርጥልን የህይወት መንገዶች፥ አብዛኛውን ጊዜ ለስጋችን ወይንም ለተፈጥሮ ማንነታችን አስደሳችና ምቹ አይደሉም። አንዳንዶቹ እንዲያውም ለጊዜው በጣም የሚያሙና እግዚአብሄር እንደሚያየን እስክንጠራጠር ሊያደርሱን የሚችሉ ከባባድ መንገዶች ናቸው። ታዲያ እግዚአብሄር እንድንማር የወደደውን እንድንማር ዝም የሚለው፥ ስለማያየን ወይንም ስለእኛ ግድ ስለማይለው ሳይሆን በህይወታችን ላይ ላለው ዘላለማዊ ሀሳብ፥ የግድ ልንማረው የሚያስፈልገን ነገር በመሆኑና፥ እግዚአብሄር ለአላማው ጨካኝ አምላክ ስለሆነ ነው።

ምንም ከባድ ነገሮች ውስጥ ሊያሳልፈን ቢወድም ግን፥ ከማለፋችን በፊት በዚህ መንገድ ውስጥ ለማለፍ ያለንን አቅም ሳይመዝን፥ በየትኛውም መንገድ ውስጥ እናልፍ ዘንድ አይፈቅድም። ምክኒያቱ ደግሞ፥ የመንገዱ አላማ እኛን ማሰቃየት ሳይሆን ማስተማር ስለሆነ ነው። እግዚአብሄር አዋቂ፥ ስራውንም ደግሞ የሚመዝን አምላክ በመሆኑ፥ ህይወታችን ላይ የሚያደርገውን ምንም አይነት ነገር ሳይመዝን አያደርገውም። “ካለፉ ይለፉበት፥ ካላለፉ ደግሞ እንደሚሆኑ ይሁኑ” ብሎ ለራሳችን በፍፁም አይተወንም። ይልቁንም፥ በድካማችን ውስጥ የራሱን ሀይልና ብርታት እያሳለፈ፥ መሄድ ሲያቅተንና ሲደክመን ደግሞ በጀርባው እየተሸከመ፥ በምናልፍበት ሁሉ ውስጥ አብሮ በእኛ ፍጥነት ከጎናችን ይጉዋዛል። በጣም ፈጣንና ሀያል ስለሆነ፥ ቀድሞንና ጥሎን አይሄድም። ህመማችን ሁሉ እሱንም ያመዋል። የነገሩ ክብደት እሱንም ልክ እንደ እኛ ይሰማዋል፥ ይገባዋል። በሚያሳልፈን መንገዶች ሁሉ ውስጥ ደግሞ ፀጋ የሚባል መሸፈኛ አለው። አንዳንድ ነገሮች ካለፋችሁበት በሁዋላ “እንዴት ግን በዚህ ነገር ውስጥ የማልፍበትን አቅም አገኘሁ?” ብላችሁ የምትደነቁባቸው ነገሮች የሉም? አንዳንዶቹ መንገዶች እንዲያውም ምንም ትላንት አልፋችሁ የወጣችሁባቸው መንገዶች ቢሆኑም እንክዋን “ትላትና በዚህ መንገድ ውስጥ የማለፍ ልምድ ስላገኘሁ፥ እንደገና አልፌ መውጣት እችላለሁ” ለማለት የማትደፍሩባቸው ከባባድ መንገዶች ናቸው። በእነዚያ ፈታኝ መንገዶች ውስጥ ያሳለፈን የፀጋው ብርታት ብቻ ነው። እግዚአብሄር ከባባድ በሚባሉ መንገዶች ውስጥ ሊያሳልፈን የሚወድበትን 3 ዋና ዋና ምክኒያቶች እስኪ እንመልከት።  

1፥ የልጁን መልክ እንድንመስል፡ ዳግም ከተወለድን በሁዋላ፥ ህይወታችን የክርስቶስን መልክ ወደመምሰል ይለወጥ ዘንድ፥ እግዚአብሄር እንድናልፍባቸው የሚፈቅዳቸው መንገዶች አሉ። በነገራችን ላይ መፅሀፍ ቅዱስ “የልጁን መልክ” በማለት ስለ መልክ የሚያናገራቸው ነገሮች፥ በስጋችን ስላለው ስለ ፊታችን ወይንም ስለ ተፈጥሮ መልካችን የሚናገሩ አይደሉም። ስለ ባህሪ የሚናገሩ ናቸው። በመጀመሪያም እግዚአብሄር ሰውን በመልካችን እንፍጠር በማለት ሲናገር፥ ስለ ተፈጥሮ የፊት መልክ እየተናገረ አልነበረም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ሁላችንም አንድ አይነት ፊትና መልክ ነበር የሚኖረን። እግዚአብሄር መንፈስ በመሆኑ፥ በመልካችን እንፍጠር ሲል፥ በመንፈስ ውስጥ ስለምንካፈለው ባህሪ እንጂ ስለ ስጋችን መልክ እየተናገረ አልነበረም። 

“እግዚአብሄርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ። በእግዚአብሄር መልክ ፈጠረ። ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍ 1፡27) እግዚአብሄር ወንድንም ሴትንም ሲፈጥራቸው፥ የራሱን ባህሪይ በውስጣቸው አድርጎ ነበር የፈጠራቸው። ሰይጣን በተንኮሉ ሄዋንን በማሳት፥ የሰው ልጆችን ከህይወት ብቻ ሳይሆን፥ ያጎደለው መጀመሪያ ከተፈጠርንበት ከእግዚአብሄር መልክም ጭምር ነበር። ታዲያ ክርስቶስ እኛን የሰው ልጆችን ከአባቱ ጋር ለማስታረቅ ወደ ምድር ሲመጣ፥ አላማው ህይወትን መስጠት ብቻ ሳይሆን፥ በሀጢያት ምክኒያት ወዳጣነው ወደ ራሱ መልክ መመለስም ነበር። የክርስቶስን መልክ ወደ መምሰል መለወጣችን ታዲያ፥ ልክ እንደ መዳናችን በአንድ ቀን የሚከሰት ነገር አይደለም። በሂደት ውስጥ የሚከናወን ስርአት ነው። እግዚአብሄር እኛን ወደራሱ መልክ ለመለወጥ የሚጠቀምባቸው የህይወት መንገዶች አሉት። ለምሳሌ፥ ለመውደድ ከሚያስቸግር ሰው ጋር ካልኖርን፥ የሚወዱንን ብቻ እየወደድን እንኖራለን እንጂ፥ እውነተኛውን የክርስቶስን ፍቅር ልንማረው አንችልም። ሰው ካልበደለን፥ ይቅር ማለትን መለማመድ አንችልም። እግዚአብሄርን ማመን በሚያስፈልጉን ነገሮች ውስጥ ህይወታችን ካላለፈ፥ እምነትን መማር አንችልም። ትእግስትን በሚጠይቁ የህይወት መንገዶች ውስጥ ካላለፍን፥ ትእግስትን መለማመድ አንችልም። 

2, እግዚአብሄርን የበለጠ እንድናውቀውና የእርሱን ባህሪያቶች እንድንማር—-እግዚአብሄር ይሄ ነው ተብለን ከምንማራቸው ትምህርቶች በተጨማሪ፥ እግዚአብሄር በህይወታችን አካሄዶች እንድናውቀው ይፈልጋል። አባቶቻችንን በመምራት፥ በእያንዳንዱ የህይወታቸው ምእራፎች እራሱን ይገልጥላቸው የነበረውም ለዚሁ ነበር። “ለሙሴ መንገዱን አስታወቀ፥ ለእስራኤል ልጆችም አደራረጉን” (መዝሙረ ዳዊት 103፡7) የእስራኤል ልጆች እግዚአብሄርን ያወቁት በአደራረጉና በሰራላቸው ተአምራቶች ብቻ ነበር። ሙሴ ግን ከእግዚአብሄር ጋር በነበረው ጉዞ፥ የእግዚአብሄርን አካሄድ፥ መንገዱንና ባህሪያቶቹን የተማረና ያወቀ ሰው ነበረ። እግዚአብሄርን በአደራረጉና በሰራላቸው ተአምራቶች ብቻ የሚያውቁት ሰዎች አሉ። በአንፃሩ ደግሞ፥ መንገዱንና አካሄዱን እንዲሁም ማንነቱንና ባህሪያቶቹን የተማሩ ሰዎች ደግሞ አሉ። ለምሳሌ አንድን ሰው እግዚአብሄር ከአንድ በሽታ ቢፈውሰው፥ ሊማር የሚችለው የእግዚአብሄርን ፈዋሽነት ብቻ ነው። እግዚአብሄር ግን ያንን ሰው ለጥቂት ጊዜ በዛ ህመም ውስጥ እንዲቆይ በማድረግ እምነትን፥ ትእግስትን፥ ፅናትን፥ ከመሆንና ካለመሆን ጋር ያልተያያዘ እውነተኛ ምስጋናን ሊያስተምረው  ይችላል። እግዚአብሄርን በጣም ያወቅነው በምቾቶቻችን ውስጥ አይደለም። ከባድ ብለን በምንላቸው ጊዜያቶቻችን ውስጥ ነው። ከእግዚአብሄር ጋር የበለጠ የተጠጋጋነው፥ የሚገርሙ የፍቅር ጊዜያቶችን ከእርሱ ጋር ያሳለፍነውና ወደ ልቡ ሀሳብ የተጠጋነውም በእነዚህ ፈታኝ የህይወታችን ጊዜያቶች ነው። 

 3፥ ከፊት ለፊታችን ላዘጋጀልን ስራ ወይንም አገልግሎት እኛን ለማዘጋጀት—-ሁላችንም በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ሆነን የተፈጠርነው፥ እግዚአብሄር አስቀድሞ  ያዘጋጀልንን አገልግሎት እንድናገለግል እንደሆነ የእግዚአብሄር ቃል ይነግረናል። ታዲያ ይሄ አገልግሎት የእኛን እግዚአብሄርን ማወቅና ማንነቶቹን መረዳትን የሚጠይቅ ነው። እግዚአብሄርን ሳያውቁት ማገልገል ከባድ አደጋ እንዳለው ከምንማርባቸው ሰዎች ውስጥ ዋነኞቹ የኤሊ ልጆች ናቸው። የኤሊ ልጆች፥ በቤተ መቅደስ ውስጥ የማገልገል ልምድ ያላቸው፥ እግዚአብሄርን በክህነት አገልግሎት የሚያገለግሉ ልጆች ነበሩ። ሆኖም ግን በ1ኛ ሳሙኤል ምእራፍ ሁለት ላይ “የኤሊም ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፥ እግዚአብሄርንም አያውቁም ነበረ” በማለት እግዚአብሄርን አለማወቃቸው አገልግሎታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደጎዳና፥ እግዚአብሄር ከባድ እርምጃ እንዲወስድባቸው እንዳደረገ ይነግረናል። “እግዚአብሄርን ማወቅ ጠልተሀልና እኔ ደግሞ ካህን እንዳትሆን እጠላሃለሁ” (ሆሴእ 4፡6)

የሁለቱን የእስራኤል ነገስታት የሳኦልንና የዳዊትን የንግስና አገልግሎትም እንዲሁ በንፅፅር ብናይ፥ ሳኦል የእግዚአብሄርን ሀሳብ እንዲሁም ባህሪውን አለመረዳቱ አገልግሎቱን በአጭር እንዳስቀረው እናነባለን። ዳዊት ግን በምድረበዳ ያለፈባቸው የህይወት መንገዶቹ፥ ምንም ብቸኛ የነበረባቸውና፥ ከአንበሳና ከድብ ጋር ያታገሉት ፈታኝ ጊዜያቶች ቢሆኑም እንኳን፥ እግዚአብሄርን ለማወቅ ግን እድል እንደሰጡትና፥ ይሄ ስለ እግዚአብሄር ያገኘው እውቀቱ፥ ለንግስና አገልግሎቱ ይሄ ነው የማይባል አስተዋፆ እንዳደረገ እናያለን። እግዚአብሄር እሱን ለማገልገል ስንነሳ፥ ከምንም ነገር በላይ የሚፈልገው እንድናውቀው ነው። ምክኒያቱም ትክክለኛ የሆነውን ሀሳቡን በዘመናችን ውስጥ ማገልገል የምንችለው፥ መጀመሪያ እሱንና የሚፈልጋቸውን ነገሮች ስናውቅ ነው። ከዘፍጥረት እስከ ዮሀንስ ራእይ ድረስ በተፃፉት በእያንዳንዱ መፅሀፎች እግዚአብሄር ማንነቱን በተለያዩ መንገዶች ገልጧል። እነዚህን ማንነቶቹን በጥልቀት እንረዳ ዘንድ ደግሞ፥ የሚወስደን የህይወት መንገዶች አሉት።

እኛ ከእግዚአብሄር ጋር በትክክል እንሂድ እንጂ፥ እያለፍንባቸው ያሉት ፈታኝና ከባድ መንገዶች ሁሉ አላማ አላቸው። እግዚአብሄር አላማ የሌለበት መንገድ ህይወታችን ላይ የለውም። የህይወታችንን አካሄድና መንገድ የሚቀይሰው ከዘላለም ሀሳቡ ተነስቶ ነው። በእነዚህ መንገዶች ውስጥ ደግሞ ከትላንትና ዛሬ ጠንካሮች፥ አማኞች፥ ትእግስተኞች፥ ፅኑዎች፥ በመንፈስ አለም ውስጥ ስንታይ ደግሞ በእሳት ውስጥ አልፎ እንደወጣና እንደሚያንፀባርቅ እንቁዎች ሆነናል። ይሄ መንገድ ዛሬ ላይ ያስለቅሰን እንጂ፥ ነገ ላይ ግን ደስታና ሳቅን ይዞልን የሚመጣ የተስፋ መንገድ ነው። መጨረሻው ደግሞ ክብር ብቻ ነው።

“ለእናንተ የማስባትን ሀሳብ እኔ አውቃለሁ። ፍፃሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም ሀሳብ ነው እንጂ የክፉ አይደለም” (ትንቢተ ኤርምያስ 29፡11)

green-chameleon-s9CC2SKySJM-unsplash.jpg
ከትዳር በፊት ማወቅ ያሉብኝ ነገሮች

ከትዳር በፊት ማወቅ ያሉብኝ ነገሮች

ችላ ያልነው ጠላታችን

ችላ ያልነው ጠላታችን