Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ከትዳር በፊት ማወቅ ያሉብኝ ነገሮች

ከትዳር በፊት ማወቅ ያሉብኝ ነገሮች

ዛሬ በጣም ደክሞኛል። ምን የመሰለ ሰርግ ላይ ውዬ አሁን ቅርብ ጊዜ ነው ወደ ቤቴ የገባሁት። አቤት ሙሽሮቹ እንዴት እንደሚያምሩ! ሚዜዎቹስ ብትሉ፥ የቃልኪዳን ስነስርዓቱ፣ የሰርጉ አዳራሽ ደግሞ ማማሩ! አምልኮውንማ አጠይቁኝ፥ በጣም ቀውጢ ነበር። እስኪያልበን ድረስ መዝለላችን፥ አምልኮ የሚለውን ቃል ባይተካውም፥ ያው እየዘለልን ዘምረናል። ምናለበት ግን የእሁድ እሁድ የቤተክርስቲያን አምልኮአችንም እንዲህ ቢመስል! ማለት፥ ተፈቶ ሲያመልክ አይተነው የማናውቀው ሰው ሁሉ ሰርግ ላይ ሲፈታ እናየዋለን። ይሄን ባህል ግን ከአህዛብ ሰርግ ይሆን እንዴ የወረስነው? ሰርጌ ላይ በደምብ አልጨፈሩም እንዳንባል ይሆን የምንጨፍረው? እኛ ክርስቲያኖች ግን ከዚህ ፍርሀት ነፃ ሆነን ነው ማምለክ ያለብን። መዝለልና መጨፈራችን ምንም ክፋት ባይኖረውም፥ እግዚአብሄር ስላደረገልን ነገር ወይንም በውስጣችን ስለ ፈሰሰው የመንፈስ ቅዱስ ደስታ እንጂ፥ ሰውን የሚለንን ፈርተን መሆን የለበትም። ብቻ ግን በአጠቃላይ ሰርጉን ወድጄዋለሁ። ሁኔታው ሁሉ ደስ ይል ነበር። 

የሰርጉን ስርዓት ካጠናቀኩኝ በሁዋላ፥ ወደ ቤቴ እየተመለስኩ፥ ልዩ በሆነ ፀጥታና፥ በሚገርም ተመስጦ ውስጥ ነበርኩ። ስለ ሰርጉ ሁኔታ እያሰብኩ፥ አንድ ጥያቄ እየደጋገመ ወደ ሀሳቤ ይመጣ ነበር። እነዚህ የሚያምሩ ወንድና ሴት ሙሽሮች ግን በአላማ ይሆን የተገናኙት? እኛማ እግዚአብሄር ይስጣቸው በእነሱ ወጪ በልተን ጠጥተን፥ ጨፍረን ወደየቤቶቻችን ሄደናል። ሰርግ ግን ዋናው የአብሮነት ህይወት አንድ ተብሎ የሚጀመርበት  የመጀመሪያ ቀን እንጂ ትዳር ማለት አይደለም። በተለይ እኛ ሴቶችማ በጣም የሚከብደን ነገር ቢኖር፥ ሰርግና ትዳርን ለያይቶ ማየት ነው። በህይወት የምንኖርበት የመጨረሻው ቀን ይመስል፥ ጭንቀታችን ሁሉ እኮ ስለ ሰርጋችን ቀን ነው። የኔንማ ተውት፥ ገና በ11 አመቴ ነበር እኮ ሚዜዎቼን የመረጥኩት።

መቼም ሰርግና ትዳርን ሲያስብ ደስታ የማይሰማው ያላገባ ሰው ያለ አይመስለኝም። ታዲያ፣ እንኳን ትዳርን የሚያክል ትልቅና ህይወታችንን በሙሉ የሚይዝ ነገር ይቅርና፣ በህይወታችን ላይ የምናረጋቸውን ትንንሽ ነገሮች እንኳን ሳናስብና ሳንዘጋጅ አናደርጋቸውም። እስኪ ዛሬ ስለ ዝግጅት እናውራ። ስለ ዝግጅት ስናስብ፥ ብዙ ጊዜ ወደ አይምሮአችን ውስጥ የሚመጡብን ገንዘብን ለሰርጋችን ማጠራቀም፥ ትምህርታችንን መጨረስና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮችን ናቸው። እነዚህ ሁሉ መልካምና የሚጠቅሙ ዝግጅቶች ቢሆኑም ግን፥ ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በላይ ራሳችንን መጠየቅ ያሉብን ሌሎች በጣም አስፈላጊ ጥያቄዎች አሉ። እነዚህን ጥያቄዎች ከማየታችን በፊት፥ እስኪ የመጀመሪያውን የአዳምና የሄዋንን ትዳር አጀማመር በጣም በአጭሩ ከመፅሀፍ ቅዱስ ለማየት እንሞክር። አዳም በኤደን ገነት ውስጥ የሚኖርና እግዚአብሄር የሰጠውን ስራ የሚሰራ የመጀመሪያው ሰው ነበር። እግዚአብሄርም አለ፥ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፥ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት” (ዘፍጥረት 2:18) ከዚህ የእግዚአብሄር ንግግር እንግዲህ፥ ሁለት ነገሮችን መረዳት እንችላለን። 1ኛ ሰው ብቻውን መሆኑን አልወደደውም። 2ተኛ ደግሞ ሰው ረዳት ማጣቱን አልወደደውም። ስለዚህ ትዳር የሚለውን ሀሳብ ሲያመጣው፣ ለእነዚህ ሁለት ችግሮች መፍትሄ እንዲሆን ነው። የመጀመሪያው፥ ሰው ብቻውን መሆኑ መልስ እንዲያገኝ። ቀጥሎ ደግሞ፥ ሰው ሊረዳው የሚችልን ሰው እንዲያገኝ ነው። ረዳት በሚለው ቃል ውስጥ ታዲያ፥ ስራ የሚል ሚስጥራዊ ቃልን እናገኛለን። ምክኒያቱም እየሰራ ያለ ሰው እንጂ፥ አንድ ቁጭ ያለ ሰው ለመቀመጥ ምንም እርዳታ አያስፈልገውም። ስራ እያልን ስናወራ ግን ደሞዝ ስለምናገኝበት ስራ እያወራን አይደለም። ምክኒያቱም እግዚአብሄር ለአዳም ረዳት ትሆነው ዘንድ ሄዋንን የሰጠው፥ በሀጢያት ምክኒያት ሰርቶ ደሞዝ እንዲያገኝ ሳይረገም በፊት ነው። ይልቁንም አዳም ረዳት ያስፈለገው፥ በጊዜው እግዚአብሄር በኤደን ገነት ላይ የሰጠውን ሀላፊነት ወይንም ስራ በተሻለ ሁኔታ ለመስራት እርዳታ እንዲያገኝ ነው። እግዚአብሄር በመጀመሪያ ለአዳም የሰጠው ስራን ነው። ትዳርን የሰጠው ደግሞ፣ ይሄን የተሰጠውን ስራ ለመስራት የሚያስፈልገውን እርዳታ እንዲያገኝ ነው። እግዚአብሄር በመጀመሪያ ትዳር የሚለውን ሀሳብ ያመጣው፥ ሰው ከእግዚአብሄር ዘንድ ለተሰጠው ስራ፥ እርዳታ የሚያገኝበት ቦታ እንዲሆን ነው። ስለዚህ ትዳር ተፋቅሮ ከመጋባት ያለፈና፥ ከእግዚአብሄር የተሰጠንን ስራ በተሻለ ሁኔታ ለመስራት፥ እርዳታ የምናገኝበት ቦታ እንደሆነ እንረዳለን ማለት ነው።

ይሄንን ትልቅ የሆነውን የትዳር አላማ ስንረዳ ታዲያ፣ አመለካከቶቻችንና ቅድሚያ የምንሰጣቸው ነገሮች መለወጥ ይጀምራሉ። ለትዳር የምንፈልገውን ሰው የምንመርጥበት መስፈርት ከመልክ፥ ከገንዘብና ከመሳሰሉት ነገሮች ያልፍና፥ ይሄ ሰው ውስጤ የተቀመጠውን የእግዚአብሄርን ሀሳብ ወይንም ከእግዚአብሄር የተሰጠኝን ስራ በትክክል ለመስራት ይረዳኛል? ወደሚለው ዋና ጥያቄ ውስጥ እንገባለን። ይሄንን ለማለት ታዲያ ከማግባታችን በፊት ማወቅ ያለብን ዋናው ነገር ከእግዚአብሄር የተሰጠንን ስራ ነው። አላማችንን ነው መጀመሪያ ማወቅ ያለብን። እግዚአብሄር በክርስቶስ ኢየሱስ የፈጠረንና አዲስ ፍጥረት የሆነው እግዚአብሄር አስቀድሞ ያዘጋጀልንን ስራ ለመስራት እንደሆነና ይሄ ለእያንዳንዳችን የተሰጠንን የግል ሀላፊነት ነው መጀመሪያ ማወቅ ያለብን። ከዘላለም አንፃር ስናያት ነጥብ የምታክለው ይህቺ በጣም አጭር የምድር ቆይታ የተሰጠችን፥ እንድንሰራባት ነው። ለማረፍማ ዘላለም አለልን። ታዲያ፥ ሰው የሆነ ነገር ለማድረግና ለመስራት ተፈጥሮ፥ የተፈጠረበትን አላማ እንዲሰራ ሊረዳው ከማይችል ሰው ጋር፥ በትዳር ቃልኪዳን ተሳስሮ መቀመጡ ትርጉሙ ምንድነው? እኛ እኮ፥ ለራሳችን ብቻ ኖረን ለመሞት የተጠራን ሰዎች አይደለንም። ሁሉም ሰው የሚኖረውን ህይወት ለመኖርማ ክርስቲያኖች መሆንም አይጠበቅብንም። እኛ የተፈጠርነው ለአገልግሎት ነው። በእያንዳንዳችን ህይወት ውስጥ እግዚአብሄር የተለየ ስራ አለው። ለእኛ ብቻ የተዘጋጀ ልዩ ስራ አለ። መፅሀፍ ቅዱሳችንን እኮ ስናነብ፥ በሙሴ ብቻ የተሰራ ስራ ነበረ። ለዳዊት ብቻ የተጠበቀ፥ ብዙዎች ለመውሰድ ጦርነት የከፈቱበት፥ እግዚአብሄር ግን ለሱ ብቻ የጠበቀው የንግስና አገልግሎት ነበረ። ኤርምያስ በሆድ ሳይሰራ በእግዚአብሄር የታወቀበትና የተፈጠረበት ልዪ የሆነ አገልግሎት ነበረው። አስቴርን፥ ከብዙ ቆንጆዎች መካከል ያስመረጣት፥ ህዝቡዋን የመታደግ አገልግሎት ነበራት። በጳውሎስ ብቻ የተፃፉ 13 የመፅሀፍ ቅዱስ መፅሀፎች አሉ። ሀረ ስንቶቹን እንጥቀስ? ዛሬ ላይ እያነበብን የምንደነቅባቸውና ምሳሌ የሆኑልን ሰዎች ሁሉ፥ የተሰጣቸውን ስራ ስላወቁና ያንን ስራ የሚያስከፍለውን ዋጋ በመክፈል ስላገለገሉ ነው። ስለዚህ ለእያንዳንዳችንም እንዲሁ የተቀመጠ ስራ አለ። ይሄ ነው የመፈጠራችን ትርጉሙ። አይን የአፍንጫን፣ ጆሮ የእጅን ስራ እንደማይሰራ ሁሉ በክርስቶስ አካል ውስጥ ልዩ ልዩ ስራ እንድንሰራ፥ አካል ተደርገን ነው የተፈጠርነው። አላማን ማወቅ ማለት የትኛውን የአካል ክፍል ሆነን ለማገልገል እንደተጠራን ከእግዚአብሄር ከራሱ መስማት ማለት ነው። ከዚያ በሀዋላ፣ በቃ የህይወታችንን ትኩረት እዚህ የተሰጠን ስራ ላይ እናረጋለን። ህይወታችንንም ሆነ የወደፊት ትዳራችንን በዚህ አላማ ውስጥ ማቀድ እንጀምራለን።

ለማግባት ከማሰባችን በፊት እግዚአብሄር በህይወታችን ላይ ያለውን ሀሳብ ማወቃችን፥ ህይወታችን ላይ ምን አይነት ሰው እንደምንፈልግ እንድናውቅ ይረዳናል። ለምሳሌ፣ አንድ ሰው ቤት ለመስራት ካሰበ፥ የሚፈልጋቸው ሰዎች ይሄን ፍላጎቱን ለማሳካት የሚረዱትን ሰዎች ነው። የቤት ዲዛይነሮችን፥ አርክቴክተሮችን፥ በቤት ግንባታ ላይ እውቀትና ሙያ ያላቸውን ሰዎች ነው እንጂ የሱቅ ነጋዴዎችን አይደለም። የሱቅ ነጋዴዎች ጋር ቢሄድ፣ ለመስራት ላሰበው ነገር ምንም አይነት እርዳታ ሊያገኝ አይችልም። መገናኘት ያለበት ግን ከትክክለኛና ውስጡ ያለውን መሻት ለመፈፀም  ከሚረዱት ሰዎች ጋር ነው። ለማግባት ከመዘጋጀታችን በፊት ማወቅ ያለብን፥ ህይወታችን ላይ ምን መስራት እንደምንፈልግ ነው። አላማችንን ነው መጀመሪያ ማወቅ ያለብን። በውስጣችን ያለው ጠንካራ መሻት ምንድነው? ወደፊት ራሳችንን ስንሰራ የምናየው ህልማችን ምንድነው? አያችሁ፣ እነዚህን ጥያቄዎች መመለሳችን አላማ ያለን ሰዎች ያደርገናል። አላማ ያለው ሰው ደግሞ ህይወቱ ላይ ምን እንደሚፈልግ ያውቃል። ማንን ማግባት እንዳለበት ያውቃል። ማንን ማግባት እንደሌለበትም ያውቃል። ማን ከሱ አላማ ጋር እንደሚሄድ ለማወቅ ብዙ ጊዜያቶች አይፈጁበትም። እግዚአብሄርንም በትዳር አቅጣጫ ለህይወቴ የሚሆንና ፍቃድህ ያለበት ሰው ጋር ምራኝ ብለን ከጠየቅነው የሚመራን፣ እንድናገለግል የወደደውን ሀሳቡን ለማገልገል ሊረዳን ወደሚችለው ሰው ነው።

በእግዚአብሄር ፈቃድ አግብተው፣ በብዙ የአገልግሎት ፍሬ የተባረኩ፣ ትክክለኛ ጥሪያቸውን ያወቁና በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል እርዳታ ያገኙ ሰዎችንና የትዳር ምሳሌዎችን አውቃለሁ። በአንፃሩ ደግሞ፣ ለትውልድ ሊተርፍ የሚችል የከበረ ሀብታቸውን በትዳር ምክኒያት የጣሉ ሰዎችንም እንዲሁ አውቃለሁ። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ፥ ከማግባታቸው በፊት፥ አላማ ስለሚባለው ነገር ምንም መረዳት ባይኖራቸውም፥ የእግዚአብሄርን ፈቃድ በመጠየቅና በእርሱ ፈቃድ በመመራት ካገቡ በሁዋላ “ይሄ ሰው ነበር ህይወቴ ላይ የሚያስፈልገኝ” ሲሉ እንሰማቸዋለን። ዋናው ወገኖቼ፥ ማግባት አይደለም። የእግዚአብሄር ሀሳብ ያለበት ህይወት ውስጥ መግባት ነው። ዋናው፥ ሊያገባን የሚችልን አንድ የሆነን ሰው ማግኘት አይደለም። እግዚአብሄር ለህይወታችን ትክክለኛ ረዳት ካለው ሰው ጋር መገናኘት ነው። 

አንዳንዶቻችን ደግሞ አላማዬን አላውቀውም። ህይወቴ ላይ ምን ማድረግ እንደምፈልግ አላውቅም የምንል ካለን፥ ጊዜው በፍፁም አልረፈደም። ወደ ጉዋዳችን ገባ ብለን፥ ወደ እግዚአብሄር ወደ አባታችን ልብ በመጠጋት፥ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ህይወት እየተናገረ ያለውን ድምፅ መስማት እንችላለን። እግዚአብሄር ሆይ እኔን ለመፍጠር ያነሳሳህ ምክኒያት ምንድነው? በህይወቴ ላይ ያለው ሀሳብህ ምንድነው? ወዳንተ ሳልመጣ በፊት እንድሰራልህ የምትፈልገውን ነገር አስታውቀኝ ብለን እግዚአብሄርን ከጠየቅነው፥ በህይወታችን ላይ ያለውን ዋና ሀሳቡን ይነግረናል። ከዚያ ደግሞ እንደ ፈቃዱ የሆነና ይሄንን የሰጠንን ስራ ለመስራት የሚረዳንን ትዳር ይሰጠናል። የፍቅር ጉዋደኝነት ውስጥም ከገባን በሁዋላ፥ በጨዋቶቻችንና በምናሳልፋቸው ጥሩ ጥሩ ጊዜያቶች መካከል፥ ቀስ ብለን ትኩረት ሰጥተን መጠየቅና ማወቅ ያለብን፥ የህይወት ግቦቻችንን፥ ህልሞቻችንን፥ እቅዶቻችንንና ለወደፊት ትዳራችን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ነው። አያችሁ ይሄ የግምገማ ጊዜ ነው። በንቃት ነገሮችን የምናይበት ጊዜ ነው። መንቃት ያለብን፥ ከተጋባንና ከተፈራረምን በሁዋላ አይደለም። አሁን ነው ጊዜው። ምክኒያቱም ገና ባልና ሚስት አልሆንም። ባልና ሚስት እንደሆንንም ሊሰማን አይገባም። ለሁሉም ጊዜ አለው። እነዚህን ጥያቄዎች ለመጠየቅ ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው። ምክኒያቱም ጥያቄዎቹን መጠየቅ የማንችልበት፥ ብንጠይቅም ትርጉም የሌለበት ጊዜ ይመጣል። ከዚያ፥ እነዚህን መልሶች በልባችን ይዘን ከእግዚአብሄር ሀሳብና ከአላማችን አንፃር ልናያቸው እንሞክራለን። በመረጋጋትና በጥልቀት እናስብበታለን። እንፀልይበታለን። የእግዚአብሄርን ፈቃድ፥ እንጠይቅበታለን።

ሌላው ከማግባታችን በፊት ማወቅ ያለብን አስፈላጊ ነገር፥ የእውነተኛ ፍቅርን ምንነት ነው። ካልተጠነቀቅን፥ ፍቅር ተብሎ በሚጠራው ጠንካራ የሆነ ስሜት ተገፋፍተን፥ ህይወታችንንና የተፈጠርንበትን አላማ ሊጎዳ የሚችል ትዳር ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን። ፍቅር፥ ለትዳር አስፈላጊ  የሆነ ነገር ቢሆንም እንኳን፥ ትዳር የሚመሰረተው ግን በፍቅር ብቻ አይደለም። ለትዳር የሚያስፈልገው ፍቅር ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ይሄ ሁሉ ተፋቅሮ የተጋባ ሰው፥ መሀል ላይ እየደረሰ ለምን ይፋታል? እግዚአብሄርን ፈርተው ያልተፋቱና፥ ህይወት የሌለበት ትዳር ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉም ልባችሁ ውስጥ ያዙልኝ። ዛሬ ላይ እኮ የተለያዩ ጥናቶች ፍቺ 50% ደርስዋል እያሉን ነው። ይሄ ማለን ምን ማለት መሰላችሁ? 10 ሰዎች ቢጋቡ፥ 5ቱ ብቻ ናቸው በትዳር የሚቆዩት ማለት ነው። ሌሎቹ 5ቶቹ ደግሞ ተዋደው የተጋቡ ቢሆንም፥ መሀል ላይ ግን ይፋታሉ። ይሄንን የምንነጋገረው ትዳርን እንድንፈራው አይደለም። አይደለም፥ ትዳር ከእግዚአብሄር የተሰጠ ትልቅ በረከት ነው። በረከት የሚሆንልን ግን፥ በራሱ በእግዚአብሄር ሀሳብ ተመርተንና አስተውለን ስንገባበት ነው። ሰጪው እግዚአብሄር ሆኖ፥ ስርዐቱና አካሄዱ ከኛ ሊሆን አይችልም። ከተለያዩ የመፅሀፍ ቅዱስ መፅሀፎችና ከእምነት አባቶቻችን እንደተማርነው ከሆነ፥ የትኛውም የእግዚአብሄር በረከቶች ጋር የምንደርሰው፥ እግዚአብሄር ባሰመረልን መስመሮች የሄድን እንደሆነ ብቻ ነው።

ዛሬ ላይ አብዛኞቻችን ፍቅር እያልን የምንጠራው፣ የሆነ ሰው ያሳየንን ወይንም ለሆነ ሰው የሚሰማንን ጠንካራ የሆነ ስሜት ነው። እውነተኛ ፍቅር ግን ስሜት አይደለም። ባህሪ ነው። መፅሀፍ ቅዱስ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምእራፍ 13 ላይ የፃፈልን፥ እውነተኛ የሆነው ፍቅር፥ ስሜት አይደለም። ፍቅር በስሜት ውስጥ ይገለጣል እንጂ ስሜት አይደለም። ባህሪ ነው። ፍቅር ታጋሽ ነው፥ ቸርነትን ያደርጋል፥ አይመካም፥ አይታበይም፥ የማይገባውን አያደርግም፥ በደልን አይቆጥርም፥ ከእውነት ጋር ደግሞ ደስ ይለዋል፣ ፍቅር ሁሉን ያምናል፥ ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ደግሞ ይፀናል። ይሄ ነው እውነተኛ ፍቅር። እግዚአብሄር ፍቅር ነው ብሎ መፅሀፍ ቅዱስ ሲፅፍልን፥ እነዚህን ባህሪያቶች የተሞላ አምላክ ነው ማለት ነው በሌላ አማርኛ። የእውነተኛውን ፍቅር ትክክለኛ ትርጉም፥ ማንነቱ በሙሉ ፍቅር ከሆነው ከእግዚአብሄር እንጂ፣ ከሮሚዮ ወይንም ከጁሊየት አንማረውም። የወደፊት ትዳራችንንም እንዲቀጥል ሊያደርገው የሚችለው፥ ይሄ አይነቱ ባህሪን የተሞላ ፍቅር እንጂ፥ ስሜት አይደለም። ለዚህ ነው ትዳራችንን በስሜት ላይ ተመስርተን መወሰን የሌለብን። ምክኒያቱም ስሜት ተቀያያሪ ነው። አይታችሁ ከሆነ፥ አንድ ሰሞን ይሰማን የነበረው ስሜት፣ ሌላ ሰሞን ላይ ላይሰማን ይችላል። ትዳርን የሚያክል ትልቅ ነገር ደግሞ ስሜት ላይ፥ መልክ ላይ፥ ገንዘብና የመሳሰሉት ተቀያያሪ ነገሮች ላይ  ተመስርተን መወሰን የሌለብንም በዚሁ ምክኒያት ነው። ስለዚህ የዛሬው ፅሁፋችን ከትዳር በፊት ማሰብ ስላለብን ሁለት ትልልቅ ነገሮች ያስታውሰናል ማለት ነው። 1ኛ፥ አላማችንን በደምብ መረዳትና ማወቃችን ትክክለኛውን ሰው እንድንመርጥ ይረዳናል። 2ኛ ደግሞ ስለ እውነተኛ ፍቅር ባህሪያቶች በመረዳትና እነዚህን ባህሪያቶች በመሞላት፥ ራሳችንን ለትዳር ማዘጋጀት እንደምንችል ለማስታወስ ነው።

ኢዮብ

ኢዮብ

ትምህርት ቤት

ትምህርት ቤት