Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ኢዮብ

ኢዮብ

ብዙ ነገሮችን እንዳስብና እንዳሰላስል ከሚያደርጉኝ መፅሀፎች ውስጥ አንዱ የኢዮብ መፅሀፍ ነው። ብዙ ጊዜ የኢዮብን መፅሀፍ ስናስብ ቶሎ ብሎ ትዝ የሚለን፥ ኢዮብ ያለፈባቸው በጣም ከባባድ ፈተናዎች ናቸው። መቼም የእግዚአብሄር ፀጋ የማያሳልፈው ነገር የለም እንጂ ማናችንም ብንሆን፥ ኢዮብ ያለፈባቸውን ፈተናዎች እንኳን ልናልፍባቸው፥ ለማሰብ እንኳን የሚከብዱን ናቸው። በአንድም ሆነ በሌላ ግን፥ ዛሬ ላይ በህይወታችን የሚያልፉት ችግሮች ልዩ ልዩ ይሁኑ እንጂ፥ ኢዮብን የተሰሙት ስሜቶች ሲሰሙን፥ የተናገራቸውን ቃሎች ስንናገር፥ ኢዮብ እግዚአብሄርን የጠየቀውን አይነት ጥያቄዎች ስንጠይቅ ራሳችንን እናገኘዋለን። መፅሀፉ እንደሚነግረን ከሆነ፥ ኢዮብ ፍፁምና ቅን፣ እግዚአብሄርን የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው ነበረ። እግዚአብሄርን ከመፍራቱ ብዛት ምናልባት ልጆቼ እግዚአብሄርን በድለውት ይሆን? በማለት በልጆቹ ቁጥር ልክ ለእግዚአብሄር መስዋእትን የሚያቀርብና ልጆቹን የሚቀድስ፥ ለእግዚአብሄር ከፍተኛ የሆነ ፍርሀትና አክብሮት ያለው ሰው ነበር። ኢዮብ በእግዚአብሄር ፍጹም የተወደደና እግዚአብሄር ቅጥር ሰርቶ ይጠብቀው የነበረ ሰው ነው ። በነገራችን ላይ፥ እግዚአብሄር ቅጥር ሰርቶ እንደሚጠብቀን የተማርኩት ከኢዮብ መፅሀፍ ነው። የትኛውም ክፉ ነገር ይሄንን ቅጥር ማለፍ አይችልም። ሰይጣንም ቢሆን ይሄንን ቅጥር አልፎ ኢዮብን የነካው፥ በተፈቀደለት መጠን ብቻ ነው። ያልተፈቀደለትን አልነካም። ለዚያ ነው በአንደኛ ቆሮንቶስ መጽሀፍ ላይ ሲናገር፥ “ከምትችሉት በላይ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሄር” ተብሎ የተፃፈው። ፈቃጅ አለ። በሰማይ ተቀምጦ፥ በህይወታችን ላይ የሚሆነውን ነገር ሁሉ የሚፈቅድ ፈቃጅ አለ። 

የኢዮብን ታሪክ ብዙዎቻችን እንደምናውቀው ታዲያ፥ እግዚአብሄር በእሱ ላይ በመወራረድ፥ ልጆቹን ሀብቱን እና ጤናውን እንዲያጣ አደረገው። በምድር ላይ ያለን ሰዎች የተባልን ፍጥረቶች በሙሉ፥ የምናጣው ነገር ልዩ ልዩ ይሁን እንጂ፥  ዋናው ችግራችን ማጣት ብቻ ነው። አንዳንዱ ሰው ገንዘብ ያጣል፥ ሌላው ጤና ያጣል፥ ሌላው ሰው ያጣል፥ ሌላው ፍቅር ያጣል፥ ሌላው ስራ ያጣል፥ ሌላው ደግሞ ሰላም እና ደስታ ያጣል። ኢዮብ ባለፈባቸው በእነዚህ ልጆቹን፥ ጤናውንና ሀብቱን የማጣት ችግሮች ዋና ጥያቄና ሙግቱ፥ ይሄ እንዲደርስብኝ ምን የሰራሁት በደል አለ? የሚል ነበር። ሙሉ መፅሀፉን ስታነቡ፥ የኢዮብ ጩሐት፥ ከእግዚአብሄር ጋር የነበረው ሙግት፣ ይሄ ነገር በእኔ ላይ እንዲደርስ የበደልኩት በደል የለም የሚል ነበር። ሊያፅናኑት የመጡት 3ቱ ወዳጆቹ ደግሞ፥ አይ ተው ግድ የለህም! እግዚአብሄር በፃድቅ ሰው ላይ እንዲህ ያለ ክፉ ነገር ሲያመጣ አይተን አናውቅም። አፍህን ሞልተህ ፃድቅ ነኝ አትበል። እግዚአብሄርን የበደልክበት የሆነ ነገርማ ይኖራል በማለት የሚሞግቱት ናቸው። መፅሀፉ እስከ 31ኛ ምእራፍ ድረስ፥ ኢዮብና ወዳጆቹ ባልተመለሰ ጥያቄ ውስጥ ያደረጉትን ንግግር የሚናገሩ ምእራፎች ናቸው። እስኪ ያልተመለሱ ጥያቄዎቻችሁን አስቡዋቸው። እኔማ አንዳንዴ የራሴን ህይወት ሳስበው፥ ምነው ልክ እንደ ፊልም ታሪኬን ፈጠን ፈጠን አርጌ መጨረሻዬን ባየሁት የምላቸውና፥ ልክ እንደ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ መጨረሻቸውን ለማየት፥ በጉጉት የምጠብቃቸው የህይወት ጉዳዮች አሉኝ። እናንተስ? 


ኢዮብና ሶስቱ ጓደኞቹ 31 ምእራፍ ሙሉ እርስ በእርስ የሚያደርጉትን ንግግር፣ እግዚአብሄር ቁጭ ብሎ ያዳምጣቸው ነበር። አቤት የኢዮብ ጓደኞችማ የሚገርሙ እኮ ናቸው። በጣም የሚገርም የሚገርም ነገር እኮ ነው ስለ እግዚአብሄር ይናገሩ የነበሩት። ዛሬ ላይ እኮ እነሱ የተናገሩትን እየወሰድን ነው ጥቅስና ትምህርት የምናወጣባቸው። ቆይ እንዲያውም ከ3ቱ የኢዮብ ጓደኞች፣ ሶፋር የተባለው ጓደኛው ለኢዮብ ስለ እግዚአብሄር ከተናገረው ውስጥ ትንሹን ላንብብላችሁ። ምእራፍ 11 ቁጥር 7። “ኢዮብ፣ የእግዚአብሄርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለህን? ወይስ ሁሉን የሚችል አምላክን ፈጽመህ ልትመረምር ትችላለህን? ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል ምን ልታደርግ ትችላለህ፧ ከሲኦልም ይልቅ ይጠልቃል ምን ልታውቅ ትችላለህ? ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል። ከባህርም ይልቅ ይሰፋል።”  

በጣም የሚገርመው ነገር ግን የኢዮብ ጓደኞች ምንም ትክክለኛና ስለ እግዚአብሄር አስገራሚ አስገራሚ ነገር ቢናገሩም፥ እግዚአብሄር ግን ፈጽሞ በንግግራቸው አልተደሰተም። ምክኒያቱ ደግሞ፥  ንግግራቸው በሙሉ እግዚአብሄር በኢዮብ ላይ ያለውን ሀሳቡን በመረዳት ስላልነበረ ነው። ከዚህ የተነሳ ንግግራቸው ኢዮብ ላይ ወደ መፍረድ ያደላ ነበር። ዋናው የምንናገረው ነገር ትክክለኛነት ብቻ አይደለም። ዋናው በምንናገረው ጉዳይ ላይ ያለውን የእግዚአብሄርን ሀሳብ መረዳት ነው። ዋናው የጊዜው ቃል ነው ወይ ነው? እግዚአብሄር በዚያ ሰአት፥ ለዚያ ነገር ወይንም ጉዳይ ወይንም ለእነዚያ ሰዎች ሊል የፈለገው ነገር ነው ወይ ነው ዋናው ቁምነገሩ። እግዚአብሄር በፍጹም ያለ እውቀት እንድንናገር አይፈልግም። አንዳንዴ ሰዎች በሚያልፉበት ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር ውስጥ፣ የእግዚአብሄርን ሀሳብ ካልተረዳን፣ ዝም እንደማለት ጥበብና ማስተዋል የለም። አንዳንዴ መልካም የሚመስሉ ነገሮችን ከመናገር ይልቅ፥ ዝም ማለት የሚሻልበት ጊዜ አለ። ዛሬ ላይ ግን ዝም ብላችሁ ዘመኑን ብታዩት፣ ሁሉ ሰው ባልገባውና ባልተረዳው የእግዚአብሄር ሀሳብ ውስጥ እየገባ አስተያየት ሰጪ የሆነበት ጊዜና ዘመን ነው። በሰዎች ጉዳይ ላይ፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ፣ በአለም አቀፍ በሽታዎች ላይ የመሰለንን ነገር የምንናገርበት አስፈሪ ጊዜ ነው። የኢዮብ ጓደኞች፥ በመፅሀፉ መጨረሻ ትክክለኛው የእግዚአብሄር ሀሳብ እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ፣ እየተናገሩ ያሉት ነገር በሙሉ ትክክል ነበር የሚመስላቸው።  “ስለዚህ ክፉ ዘመን ነውና፥ በዚያ ዘመን አስተዋይ የሚሆን ዝም ይላል”  (ትንቢተ አሞፅ ምእራፍ 5፡13) 

ኢዮብ፥ በዛ ሁሉ ያልተመለሱ ጥያቄዎችና ግራ የሚያጋባ የህይወት ፈተና ውስጥ ሲያልፍ እግዚአብሄር እንደተወራረደበትም ሆነ ሰይጣን ስለ እሱ ስለተናገረው ነገር ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። መጨረሻ ላይ እራሱ፥ አውቆ ይሆን የሞተው? እኔማ ታሪኩን እያነበብኩ መሀል መሀል ላይ ያሳዝነኝና ንገሪው ንገሪው ይለኛል። “ይኸውልህ ኢዮብ፥ ብዙ ብዙ ትርፍ ቃሎችን ስትናገር እየሰማሁክ ነው ያለሁት። እኔ ግን እውነቱን ልንገርህ? ይኸውልህ ይሄን ሚስጥር ለአንድ ሰው እንዳትናገር። ሌላው ቢቀር ለእነዚህ ሊያፅናኑህ ለመጡት ለ3ቱ ጉዋደኞችህ እራሱ እንዳትነግራቸው። እኔ አሁን በጣም ስላሳዘንከኝ ነው የምነግርህ። ይኸውልህ፥ እግዚአብሄር በጣም ባንተ ስለተማመነ እየተወራረደብህ ነው ያለው እንጂ፥ አንተ ሀጢያት ስለሰራህ ምናምን አይደለም። አንተ ግን ዋናውን እውነቱን ሳታውቅ ብዙ ብዙ ነገር ስትናገር እየሰማሁህ ነው” ልለው ብዬ እተወዋለሁ። ኢዮብም ልክ እንደ ጓደኞቹ፥ ይናገር የነበሩት ንግግሮች ከእውቀት ውጪ እንደሆኑ በመፅሀፉ በ3 የተለያዩ ቦታዎች ላይ ይነግረናል። በምእራፍ 35 ቁጥር 16 ላይ እንዲያውም፥ ኤሊሁ የተባለ አንድ በእድሜ ታናሽ፥ ነገር ግን የእግዚአብሄር መንፈስ የሞላበት ልጅ ስለ ኢዮብ ንግግር እንዲህ ይላል። “ኢዮብ አፉን በከንቱ ከፍታል። ያለ እውቀትም ቃሉን ያበዛል” በማለት ኢዮብ ይናገራቸው የነበሩት ንግግሮች ከእውቀት ውጪ እንደሆኑ ይናገራል። እንደ ኢዮብ በከባድ ነገሮች ውስጥ ስናልፍ፥ እግዚአብሄር እንዲረዳን አጥብቀን መፀለይ ካለብን ነገሮች አንዱ፥ ባልገባን ነገሮች ላይ ዝም የምንልበትን አቅም እንድናገኝ ነው። ለመናገር ጊዜ እንዳለው ሁሉ፥  ዝም ለማለትም ጊዜ አለው። አንዳንዴ ህይወቶቻችን ላይ ዝም ብሎ መፀለይን፥ ዝም ብሎ እግዚአብሄርን መጠበቅን፥ ዝም ብሎ መቆየትን የሚጠይቁ ጉዳዮች ይኖሩናል። 

“ይሄ ሁሉ ነገር ይደርስብኝ ዘንድ የሰራሁት ምንም ጥፋት የለም” በሚለው የኢዮብ ጥያቄና ሙግት ውስጥ ትክክለኛ የሚመስል ነገር ቢኖረውም፣ እግዚአብሄር ለዚህ ሙገቱ የመለሰለትን አንድ አስገራሚ ነገር እስኪ በምእራፍ 40 ቁጥር 8 ላይ እናንብብ:: ኢዮብ “አንተ ፃድቅ ትሆን ዘንድ፥ በእኔ ትፈርዳለህን?” በማለት እግዚአብሄር ኢዮብን ይጠይቀዋል። አንተ ራስህን አፅድቀህ፥ እኔን ትኮንናህን? አንተ ራስህን ትክክለኛ አድርገህ፣ እኔን ተሳስተሀል እያልከኝ ነው? እግዚአብሄር ማጉረምረምን አጥብቆ የሚጠላው፣ ማጉረምረም በውስጡ፥ “እግዚአብሄር በህይወቴ ውስጥ እያረገ ያለው ነገር ትክክል አይደለም” የሚል ድምጽ ስላለው ነው። አንዳንድ ጊዜ በህይወቶቻችን ውጣ ውረዶች ውስጥ፣ ጥያቄዎች ይኖሩን ይሆናል። እግዚአብሄርን ለመጠየቅ ስንነሳ ግን ጥያቄዎቻችን፣ የእግዚአብሄርን ትክክለኛነት ከማወቅ መጀመር አለባቸው። ጥያቄዎቻችን፥ የእግዚአብሄርን ፃድቅነት ከማወቅ መጀመር አለባቸው። ጥያቄዎቻችን በእግዚአብሄር ፊት ሞገስ የሚያገኙት፣ ስለ ማንነቱ ባለን እውቀት ውስጥ ስናቀርባቸው ነው። ሁኔታዎች ይሄንን ባይሉንም እንኳን፣ መልካም አምላክ መሆኑን ከማወቅ ተነስተን ስንጠይቀው፣ እንደሚወደንና ለህይወታችን መልካም ሀሳብ እንዳለው ከመረዳት ተነስተን ስንጠይቀው፣ ጥያቄውን ያመጣንበት ልብ ከቃሉ ጋር የተስተካከለ ስለሆነ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ፈጽሞ አይዘገይም። የምናልፍባቸው ነገሮች፥ የእግዚአብሄርን ማንነት እንዲተረጉሙልን እድል መስጠት የለብንም። በተቻለን መጠን፥ የእግዚአብሄርን ማንነትና የእኛን የህይወት ውጣ ውረዶች ለያይተን ማየት አለብን። ለዛ ነው ሰይጣንም፥ የህይወቶቻችንን ፈታኝ ጊዜያቶች እንደ እድል በመጠቀም፣ “እግዚአብሄር መልካም ቢሆን ኖሮ፥ ይሄ ይሄ ይሄ ነገር ለምን በህይወትህ ወይንም በህይወትሸ ሆነ” በማለት በእግዚአብሄር ማንነት ላይ ለመዋሸት የሚሞክረው። እግዚአብሄር እኛ ወደ ተራራ ስንወጣ ትክክል፥ ወደ ሸለቆ ስንወርድም ትክክል ነው። እኛ ወደ ተራራ ስንወጣ መልካም፥ ወደ ሸለቆ ስንወርድም መልካም ነው። እኛ ወደ ተራራ ስንወጣ ፃድቅ፥ ወደ ሸለቆ ስንወርድም ፃድቅ ነው። የእግዚአብሄር ማንነት በእኛ የህይወት ከፍታና ዝቅታዎች አይለዋወጥም። ባህሪያቶቹና ማንነቶቹ በዘላለም ውስጥ የጸኑ ናቸው። ነህምያ ስለ አይሁድ ህዝብ መማረክና ስለ ኢየሩሳሌም ቅጥር መፍረስ በጣም ልቡ አዝኖ ሲፀልይ ያለው አንድ ነገር ልቤን ይነካኛል። እግዚአብሄር ሆይ አለ። “በደረሰብን ነገር ሁሉ አንተ ፃድቅ ነህ”። በከባድ ነገሮች ውስጥ ስናልፍ፥ እንዲህ ብሎ መናገር ቀላል ነገር አይደለም። እግዚአብሄር ግን ዋናው አላማው፥ ተቀያያሪ በሆኑ የህይወት ወቅቶቻችን ውስጥ፥ የማይለዋወጠውን ማንነቱን እንድንረዳ ማድረግ ነው። ባልገቡንና ትክክል በማይመስሉን ነገሮች ሁሉ ውስጥ ስናልፍ፥ እግዚአብሄር በረዳን መጠን፥ ደጋግመን ለነፍሳችን ማስረዳት ያለብን፥ እግዚአብሄር በደረሰብን ነገር ሁሉ ፃድቅና ትክክለኛ አምላክ መሆኑን ነው። የእግዚአብሄር ዋና ሀሳቡ በህይወት መንገዶቻችን ውስጥ ማንነቱን እንድናውቅ ነው። 

ኢዮብ ምንም ቅንና እግዚአብሄርን የሚፈራ ሰው ቢሆንም፥ እግዚአብሄር ማን መሆኑን በትክክል ያወቀው፥ በፈተናው መጨረሻ ላይ ነው። መጨረሻ ላይ፥ እግዚአብሄር ለኢዮብ ለመመለስ ሲመጣ፥ 31 ምእራፎች ሙሉ ያለፈበትን ከባድ ፈተና ምክኒያት አይደለም የመለሰለት። የነገረው ታላቅነቱን ብቻ ነው። የነገረው ሁሉን ቻይነቱን፥ ፈጣሪነቱን፥ አልፋና ኦሜጋ መሆኑን፥ ፍጥረታትን ሁሉ ፈጣሪ መሆኑን፥ በአጠቃላይ እግዚአብሄር ለኢዮብ በ4 ሙሉ ምእራፎች የነገረው ማንነቱን ብቻ ነው። ኢዮብ አለው። ምድርን ስመሰርት አንተ የት ነው የነበርከው? የምድርን መስፈሪያዎች ስወስን፥ መሰረቶችዋን ስተክል፥ የማእዘንዋን ድንጋይ ሳቆም አንተ የዛኔ የት ነበርክ? ብርሀን የት እንደሚኖር አውቃለሁ አለ እግዚአብሄር። ጨለማን ከብርሀን እየለየ የምስራቅን ነፋሶች በምድር ላይ የሚበታትን አምላክ እንደሆነ። ለወገግታ ስፍራውን የሚያስታውቅ፥ በቀላዮች መሰረት ውስጥ የሚመላለስ፥ ወደ ባህር ምንጮች ውስጥ ዘልቆ የሚገባ፥ ለሚያንጎዳጉድ መብረቅ መንገድን የሚያበጅ፥ ደመናትን በራሱ ጥበብ የሚቆጥር፥ መብረቆችን ወደ ወደደው ቦታ የሚልካቸው፥ ሰው በሌለበት ምድረበዳ ዝናብን የሚያዘንብ፥ የቁራን ልጆች የረሀብ ድምፅ የሚሰማ፥ ንስርን በአፉ ትእዛዝ በከፍታ ላይ የሚያበር፥ ለሰው ልጆች ልብ ማስተዋልን የሚሰጥ አምላክ መሆኑን ነው የነገረው።  31 ምእራፍ ሙሉ ኢዮብ ስላለፈበት ፈተና እግዚአብሄር ያነሳው ምንም ነገር አልነበረም። 

ኢዮብም ልክ ይሄንን እውቀት ሲያገኝ፣ ሲሟገት የነበረበትን ጥያቄዎቹን ረስቶ ስለ እግዚአብሄር ባገኘው አዲስ እውቀት መደነቅ ሲጀምር እናየዋለን። ወዲያው የራሱን ጥያቄዎች በሙሉ ረስቶ አዲስ በበራለት በእግዚአብሄር ማንነት በመደነቅ እግዚአብሄርን እንዲህ ይለዋል:: “እነሆ እኔ ወራዳ ሰው ነኝ:: የምመልስልህ ነገር ምንድነው? እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ፥ አንድ ጊዜ ተናገርሁ አልመልስምም። ሁለተኛ ጊዜም ከእንግዲህ ወዲህ አልናገርም አለ። ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደሆንክ ሀሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ በማለት ስለ እግዚአብሄር ልዩ የሆነ እውቀት ሲገባበት እናያለን። እስከዛሬ እግዚአብሄር ሆይ አለ፣ ስላንተ መስማትን በጆሮዬ ሰምቼ ነበረ። አሁን ግን አይኔ አየችህ አለ። ልክ ስለ እግዚአብሄር ማንነት የሆነው ይሄንን ትክክለኛ እውቀት ሲያገኘው፣ ወዲያው ከእግዚአብሄር ጋር ሲስማማ፣ እግዚአብሄርም ከነበረው እጥፍ አድርጎ ምርኮውን ሁሉ ሲመልስለት፥ እንዲሁም በፊት ከነበረው ይልቅ አሁን የሰጠውን ሲባርክለት እናያለን። ለካ የአንዳንድ ችግሮቻችን መልስ የችግሮቹ መልስ አይደሉም። መልሱ እግዚአብሄርን ማወቅ ነው። ለካ አንዳንድ ጊዜ ህይወታችን በብዙ ጥያቄዎች የሚሞላው ስለ እግዚአብሄር ያለን እውቀት ያነሰ ስለሆነ ነው። እግዚአብሄር ማንነቱን ብቻ ለኛ በመናገር የሚመልስልን ጥያቄዎች አሉ። እግዚአብሄርን ብቻ በማወቃችን የሚመለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። የአንዳንድ ጥያቄዎቻችንና ሙግቶቻችን ምክኒያቶች እግዚአብሄርን በትክክል አለማወቅ ነው። 

ዘላለም

ዘላለም

ከትዳር በፊት ማወቅ ያሉብኝ ነገሮች

ከትዳር በፊት ማወቅ ያሉብኝ ነገሮች