Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ዘላለም

ዘላለም

ዛሬ ስራ ቦታዬ በስራ ብዛት የተጨናነቀ ነበር። የስራዬ ባህሪ ከተለያዩ ሰዎች ጋር የሚያገናኘኝ በመሆኑ፣ ከሰዎች ጋር ለማውራትና ለመጫወት እድል ይሰጠኛል። በስራዬ መካከል በምወስዳቸው የእረፍት ሰአቶች ግን የምፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው። ጸጥታ። ታዲያ ዛሬም ልክ እንደ ወትሮዬ፥ አንድ ጸጥ ያለ የማረፊያ ክፍል ፈልጌ፣ ለጥቂት ደቂቃዎች ለማረፍ ቁጭ አልኩ። እፎይ ተመስገን እግዚአብሄር አምላኬ ብዬ አይኖቼን ጭፍን እንዳደረኩ፣ ልቤ ወዳላሰብኩት ሀሳብ ውስጥ ከተተኝ። ድንገት፥ በዚህች ምድር ላይ የምኖርባትን የመጨረሻዋን ቀን ማሰብ ጀመርኩ። የመጨረሻ ቀኔ ግን ምን ይመስል ይሆን? ምን አይነት ሁኔታ ላይ እሆን? የመጨረሻ ቀኔ እንደሆነ ሳውቅና በዚህች ምድር ላይ የኖርኩትን ህይወት ሳስበው ምን አይነት ስሜት ይሰማኝ ይሆን? ይሄን ይሄን ባደረኩ ኖሮ የሚል ቁጭት? ጸጸት? ወይንስ ደግሞ እፎይ መኖር ያለብኝን ህይወት በትክክል ኖሬዋለሁ። ማድረግ ያለብኝን ነገሮች ሁሉ በትክክል አድርጌያቸዋለሁ። አሁን ሄጄ አምላኬን ለማየት ናፍቄያለሁ የሚል የድልና የእርካታ ስሜት? ሀዋሪያው ጳውሎስ እንዳለው፥ በዚህች ህይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ የምናደርገው ከሆነ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። ከዚህች አጭር የምድር ህይወት ያለፈ፥ ዘላለም የምንኖርበት ህይወት አለን። ይሄ ዘላለም ደግሞ 100 አመታቶች ብቻ አይደለም። 900 እና አንድ ሺህ አመታቶችም አይደለም። ዘላለም፥ ሚሊየን እና ቢሊየን አመታቶች ብቻም አይደለም። ለአንዳንዶች፥ ኡፍፍፍፍ እግዚአብሄር ይመስገን የሚያስብል፥ ለአንዳንዶች ደግሞ፥ ይሄም ያልፋል የሚለው ቃል ከጥቅም ውጪ የሚሆንበት አለም ነው። 

አሁን ላይ ዝም ብለን ስንኖር፣ ይሄ በምድር ላይ ያለው ህይወታችን ማብቂያ ወይንም ማለቂያ ያለው አይመስለንም። ብዙ ጊዜ ማሰብ የምንፈልገው፣ ወጣትነታችንን፣ መስራት የምንችልባቸውን ጊዜያቶች፥ የህይወት ምኞቶቻችንን እና አስደሳች የሆኑትን የህይወት ጊዜያቶቻችንን ብቻ ነው። ብታምኑም ባታምኑም ግን እንደምንሞት ጊዜ ወስደን አለማሰባችን ህይወታችንን እንዴት እንደጎዳው! ሳናስበው እዚህ ምድር ላይ ዘላለም እንደምንኖር አይነት ስሜት እየሰጠ አዘናግቶናል። የተሰጠውን የምድር ቆይታ ስኬታማ በሆነ መንገድ የጨረሰው ዳዊት፥ እግዚአብሄርን ከጠየቀው ጥያቄ ውስጥ አንዱን ላንብብላችሁ። “ፍጻሜዬን አስታውቀኝ። የዘመኔ ቁጥር ምን ያህል እንደሆኑ፣ እኔ ምን ያህል ወደ ሁዋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ” (መዝ 39:4) አሁን ላይ ስንበላ፣ ስንጠጣ፣ ስንሰራ፣ ስንወጣና ስንገባ፥ ዘላለም ሀሳቡን ቀይሮ ላይመጣ የሄደ ይመስል ትዝም አይለንም። ልባችን በቀን ለቀን የህይወት ጉዳዮቻችን ተይዞና ተወጥሮ፣ ሀሳቦቻችን በሙሉ ምድር ላይ ተጀምረው ምድር ላይ ብቻ የሚያልቁ ሆነዋል። የምንማረው፣ የምንሰራው፣ የምናገባው፣ ቤት የምንገዛው፣ ገንዘብ የምናጠራቅመው፣ በዚህች ምድር ላይ ያለችዋን ቀሪዋን ጊዜያችንን ደስተኛ ሆነን ለመኖር ነው። እነዚህን ነገሮች ማድረግም ሆነ መመኘት ምንም ክፋት የለባቸውም። ክፋቱ ምንድነው? የአይምሮአችንን ቦታ በሙሉ ወሰዱና አይምሮአችንን አጠበቡት። ምድራዊ ብቻ አርገው አስቀሩን። ከዚህ ያለፈ ህይወት እንዳለ አስረሱን። አዘናጉን። ከዋናው ሀገራችን ሀሳብና ልባችንን ወሰዱት። ትልቁ የዘላለም ቤት ምኞታችንን በጊዜያዊ ነገሮች ተክተው ለወጡብን። አረሳሱን። ብዙዎቻችን ዛሬ ላይ ቀጣይነት ስላለው የዘላለም ህይወታችን የሚናገሩ ትምህርቶችን ወይንም ስብከቶችን ከመስማት ይልቅ፣ ከዚህ ምድር ጋር የተገናኘ የበረከት ወይንም የብልፅግና ወሬ ብናወራ ነው ደስ የሚለን። ዛሬ ግን እግዚአብሄር የሚፈልገው፣ ልባችንን በመንገዳችን ላይ እንድናደርግ፣ ዘላለማዊውን ህይወት በማሰብ፣ የተሰጠንን ድጋሚ እድልና ማስተካከያ የሌለው ህይወት በማስተዋልና በጥንቃቄ እንድንኖር ነው። 

በየቀኑ ሀሳባችን ውስጥ ሊኖርና ሁሌ ልናስበው ከሚገቡ ነገሮች አንዱና ዋነኛው የዘላለማችን ጉዳይ ነው። ሰው ህይወቱ ዘላለማዊ ነው። ታዲያ መጨረሻ ከሌለው ዘላለም ላይ ለክቶና ወስኖ ለእኛ ለሰው ልጆች እግዚአብሄር የሰጠን ይህቺ የምድር ቆይታችን፥ መጀመሪያዋን እንጂ የቱ ጋር እንደምታልቅ ማናችንም አናውቃትም። በጣም ማወቅ ያለብን ደግሞ፣ በዚህች በአጭሯ የምድር ቆይታችን ላይ የምንኖረው የህይወት አይነት፥ ማለቂያና ማብቂያ የሌለውን ዘላለም እንዴት እንደምናሳልፈው ይወስናል። በደምብ ካሰባችሁት፣ ከዚህ በላይ ምን የሚያስፈራ ነገር አለ? ሰው ገንዘብ ቢያጣ ሰርቶ ይተካዋል፣ ሰው ጤና እንኳን ቢያጣ ወይ ታክሞ ይድናል፣ ወይ ህመሙን ታግሶ ይኖራል፣ ወይ ደግሞ ወደ አምላኩ ይሄዳል። ህይወቱ ከአምላኩ ጋር ትክክል ይሁን እንጂ ሞት ወደ ዘላለም ደስታው የመሻገሪያ መንገዱ ነው። ሰው ግን ህይወቱ ላይ እግዚአብሄር ከሌለ ወይንም ደግሞ እግዚአብሄር ከእርሱ የሚጠብቅበትን ህይወት ካልኖረ እዛ ሄዶ አያስተካክለው። ወይንም ጥሩ ጥሩ ምክኒያቶች ብሎ የሚሰበስባቸው ምክኒያቶቹ በእግዚአብሄር ፊት አቅም አግኝተው ምክኒያት አይሆኑለት። መጽሀፍ ቅዱስ እንደሚል፣ የጠራንን በማወቅ፣ ለህይወትና እግዚአብሄርን ለመምሰል የሚያስፈልገውን ሁሉ ስለሰጠን፣ ለኖርነው የህይወት አይነት የምናቀርበው ምንም አይነት ምክኒያት ሊኖረን አይችልም። ዘላለም ውስጥ እኮ ስንገባ፣ በምድር ላይ ያካበትነው የትኛውም ሀብት ትርጉም አይኖረውም። አሁን የምንለብሳቸው ጥሩ ጥሩ ብራንድ ያላቸው ልብሶች ምንም ትርጉም የላቸውም። ዘላለም ውስጥ ስንገባ፥ ዛሬ የምናወጣቸው ዜሮ ማይል የሆኑ ዘመናዊ መኪናዎቻችን ምንም ትርጉም የላቸውም። ዛሬ የምንኖርባቸው የተንጣለሉ ግራውንድ ፕላሶች ትርጉም የላቸውም። ዘላለም ውስጥ ስንገባ በሰዎች ዘንድ ያገኘናቸው ክብርና ዝናዎች ወይንም ሰለብሪቱዎች ምንም ትርጉም የላቸውም። የምድር ሀያላንና ክቡራን፣ ሚሊየነሮችና ቢሊየነሮች እኮ ምንም ትርጉም የላቸውም። ትርጉም ያለው አንድ ነገር ብቻ ነው። እንደ እግዚአብሄር ሀሳብና ፈቃድ የኖርነው ህይወት ብቻ። በዚህ ምድር ላይ ቁጭ ብለን የምናካብተው ዘላለማዊነት ያለው ሀብት፥ እንደ እግዚአብሄር ሀሳብና ፈቃድ የምንኖረው ህይወት ብቻ ነው። ሌላው ቀርቶ፥ መጽሀፍ ቅዱስ ላይ ከተጻፈውና ከራሱ ከክርስቶስ አንደበት እንደሰማነው ከሆነ፣ ትንቢት መናገራችን፣ አጋንንት ማውጣታችን፣ ድንቅና ተአምራቶችን ስናደርግ እድሜያችንን ሙሉ መኖራችን እራሱ ትርጉም ላይኖረው ይችላል። በዚያን ቀን አለ ክርስቶስ በማቴዎች ምእራፍ 7 ከቁጥር 21 ጀምሮ ሲናገር፥ በዚያን ቀን፥ ብዙዎች እንዲህ ይሉኛል አለ። ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተእምራት አላደረግንምን ይሉኛል። የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅሁዋችሁም እናንተ አመጸኞች ከኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባችሁዋለሁ አለ። ከላይ ግን አንድ ነገር አለ። በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግስተ ሰማያት የሚገባ አይደለም አለ። በነገራችን ላይ ክርስቶስ ያላቸው እነዚህ ትንቢትን የሚናገሩ፣ አጋንንትን የሚያወጡ፣ ብዙ ድንቅና ተአምራትን የሚያረጉት ሰዎች አህዛቦች አይደሉም። በክርስቶስ መጀመሪያ አምነው የዳኑ ሰዎች ናቸው። ክርስቶስ ግን ከቶ አላውቃችሁም አይደለም እላቸዋለሁ ያለው። ከቶ  አላወኩዋችሁም እላቸዋለሁ አለ። ለካ ክርስቶስ የሚያውቀን በአገልግሎታችን ብዛትና አስደናቂነት አይደለም። የሚያውቀን ፈቃዱን በማድረግ በምንኖረው ህይወት ውስጥ ነው። በእርሱ ዘንድ ያለን እውቅና ይሄ ብቻ ነው። ምናልባት የአገልግሎቶቻችን ብዛት እውቅናን የሚሰጠን በሰዎች ዘንድ ብቻ ሊሆን ይችላል። ምድር ተሰብስቦ ቢያውቀን ግን በስሙ ያገለገልነው ክርስቶስ ካላወቀን ምን ትርጉም አለው? እግዚአብሄር ተአምራቶችን የሚያደርግ ሰው አይደለም የሚፈልገው፣ እግዚአብሄር የሚፈልገው ፈቃዱንና የልቡን ሀሳብ የሚኖርለትን ሰው ነው። ተእምራቶችን ማድረጋችን መጥፎ ነው እያልን ግን አይደለም። ተእምራቶቹ የእግዚአብሄርን ፈቃድ በመኖርና በማድረግ ውስጥ መሆን አለባቸው እያልን ነው። 

ብዙ ጊዜ የክርስቶስን ንግግሮች በደምብ አስተውላችሁ አይታችሁት ከሆነ እየደጋገመ የሚለው አንድ ነገር አለ። የአባቴን ፈቃድ አደርጋለሁ ይላል። እንዲያውም አንድ ጊዜ በዮሀንስ ምእራፍ 6 ቁጥር 38 ላይ ከሰማይ የመጣሁት የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ እንጂ የራሴን ፈቃድ ለማድረግ አይደለም በማለት ይናገራል። ክርስቶስ በምድር ላይ ሲኖር፣ የሰውን ስጋ እንደመልበሱ፣ ልክ እንደ ሁላችንም፣ የራሱ ፈቃድ የነበረው ቢሆንም፣ ፈቃዱን ግን አልተጠቀመበትም። ሙሉ ፈቃዱን ለአብ በማስገዛት የተላከበትን የአባቱን ፈቃድ በሙሉ መስዋእትነት ኖሮና ፈጽሞ ነው ያለፈው። እኛም እንዲሁ እዚህች ምድር ላይ ለመኖር እንደመጣን ማሰብ የለብንም። ተልከን እንደመጣን ነው ማሰብ ያለብን። የላከንን ፈቃድ አድርገን ለማለፍ ነው የመጣነው። የምንኖረው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማድረግ ብቻ ነው። አላማ አለን። ግብ አለን። በዚህ ምድር ላይ የተሰጠን ቆይታ፣ መጀመሪያ እንዳለው ሁሉ መጨረሻም አለው። የህይወት ስኬት ብለን የምንለው ልክ እንደ ዳዊት በተሰጠን ዘመን፥ የእግዚአብሄርን ሀሳብ ኖሮና አገልግሎ ማለፍ መሆን ይኖርበታል። በዚህች ምድር ላይ ስንኖር፥ አጥብቀን መፈለግ ያለብን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ነው። ማወቅ ያለብን ግን መንፈሳዊነት አይደለም በእግዚአብሄር ፊት የከበረ ዋጋ ያለው። የእግዚአብሄርን ሀሳብና ፈቃድ በመኖር ውስጥ ያለ መንፈሳዊነት ነው የከበረ ዋጋ ያለው። አገልግሎት አይደለም በእግዚአብሄር ፊት ዋጋ ያለው። የእግዚአብሄርን ሀሳብና ፈቃድ በመኖር ውስጥ ያለ አገልግሎት ነው የከበረ ዋጋ ያለው። ዋጋ ያለው አግልግሎት ብቻውን ቢሆን ኖሮ ክርስቶስ ከቶ አላወቅኋችሁም ያላቸው አጋንንት ሲያስወጡ፣ ትንቢት ሲናገሩ፣ ልዩ ልዩ ተእምራቶችን በማድረግ ያገለገሉ ሰዎች ዋጋ ይኖራቸው ነበር። በእግዚአብሄር ፈቃድ፣ ሀሳብና ምሪት ውስጥ ያለ ህይወታችንና አገልግሎታችን ነው ዋጋ ያለው። በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ መኖርን፥ ለሁለት ከፋፍለን ማየት እንችላለን። አንደኛው፥ በቃሉ ውስጥ የተጻፈልን እግዚአብሄር በሁላችንም ህይወት ውስጥ ሊያያቸው የሚፈልጋቸው ፈቃዶቹ ናቸው። ለምሳሌ ወንድሞቻችንን እህቶቻችንን መውደድ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተሰጠ የእግዚአብሄር ፈቃድ አይደለም። ሁላችንም እግዚአብሄርን እንከተላለን ብለን የወሰንን ሰዎች በሙሉ እንድንኖረው የተጠየቅነው የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው። በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ የተጻፉልን ህጎችና ትእዛዛት በሙሉ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ከሆነው ከሁላችን እግዚአብሄር የሚጠብቅብን የህይወት ስርዓቶች ናቸው። ሁለተኛው ደግሞ እግዚአብሄር ለግል ህይወታችን የሚሰጠን ፈቃዶቹ ናቸው። ለምሳሌ አገልግሎትን ብንወስድ፣ እኔና እህቴ ሁለታችንም የክርስቶስ ተከታዮች ስንሆን፣ በሁለታችንም ውስጥ እግዚአብሄር ያስቀመጠው ልዩ ልዩ የሆነ የጸጋ ስጦታዎችን ነው። ስለዚህ እግዚአብሄር በእህቴ ውስጥ ያስቀመጠውን የጸጋ ስጦታ እንዳገለግል አይጠብቅብኝም። የሚጠብቅብኝ፣ በእኔ ውስጥ ያስቀመጠውን የጸጋ ስጦታዎች እንዳገለግል ነው። ሕይወቴን ፕላን ያደረገው፣ እኔ እንዳገለግለው በፈለገው አገልግሎቶች  ውስጥ ነው። ከዚህ አገልግሎት አንጻር ትእዛዞችን ሊሰጠኝ ይችላል። ስለዚህ በጋራ በቃሉ ውስጥ በተሰጡት የእግዚአብሄርን ህጎችና ትእዛዞች ለመኖር እየሞከርኩ፣ እግዚአብሄር በግል ህይወቴ ደግሞ ያለውን ሀሳቡንና ፈቃዱን እርሱ በረዳኝ መጠን ለመኖር እሞክራለሁ ማለት ነው።  ይሄ በእግዚአብሄር ፈቃድና ሀሳብ ውስጥ በየእለቱ የምንኖረው ህይወታችን ታዲያ፣ በእግዚአብሄር ዘንድ የምንታወቅበት፣ ዝገት የማያጠፋው፣ ሌቦች ቆፍረው የማይሰርቁት ምድር ላይ ቁጭ ብለን በሰማይ የምናከማቸው መዝገባችን ነው። ሀብታችን ነው። ከዚህች ምድር ካለፍን በሁዋላም ልክ እንደ እነ ዳዊት በእግዚአብሄር ዘንድ መታሰቢያ ያለው ህይወታችን ነው። ዳዊት የዚህች ምድር ህይወቱን ጨርሶ ካለፈ ስንትና ስንት ሺ አመቱ ቢሆንም ዛሬም ግን ስለ ዳዊት የምናወራው፥ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ስለኖረው ህይወቱና እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ባገለገለው አገልግሎቱ ምክኒያት ነው።  እንዲያውም ህይወቱን በሙሉ መጽሀፍ ቅዱስ አጠቃሎ ሲያወራው ዳዊት በገዛ ዘመኑ የእግዚአብሄርን ሀሳብ ካገለገለ በሁዋላ አንቀላፋ ይለናል።

በዚህች ምድር ላይ ስንኖር የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማድረግ ከሚረዱን ነገሮች አንዱ በዘላለም ውስጥ እግዚአብሄር የሰጠንን ተስፋዎች ማሰብ ነው። ነገሮቻችንን ሁሉ ከዘላለም አንጻር መመልከት። ደስታውንም ሀዘኑንም፣ ስኬቱንም ችግሩንም ሁሉን ነገር ከዘላለም አንጻር በማየት፥ ሁሉ ጊዜያዊ እንደሆነ ማሰብ። መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰጡንን የዘላለም ተስፋዎች ሁሌ ማሰብና እነሱን አጥብቀን መያዝ። በላይ ያለውን እሹ እንደተባልነው፣ በምድር ያለውን ሳይሆን በላይ ያለውን መሻት። በላይ ያለውን ማሰብ። ይሄንን ስናደርግ፣ ላለንበት ምድራዊ ነገሮች ያለን አመለካከት ቀስ በቀስ መቀየር ይጀምራል። በመከራ ውስጥ ስናልፍ፣ ጊዜያዊ እንደሆነ ስለምናስብ የምንታገስበትን አቅም ይሰጠናል። መኖር ያለብንን የእግዚብሄርን ሀሳብና ፈቃድ ለመኖር አቅም የሚሰጠን ከፊታችን ያለው የዘላለም ተስፋ ነው። ክርስቶስ እንኳን በእብራውያን መጽሀፍ ምእራፍ 12 ላይ ሲናገር በፊቱ ስላለው ደስታ የመስቀሉን መከራ ለመታገስ አቅም እንዳገኘ ይነግረናል። እንዲሁ የእምነት አባቶቻችን እነ ሙሴ ከእግዚአብሄር ህዝብ ጋር መከራን መቀበልን ለመምረጥ አቅም የሰጣቸው ከፊታቸው ያለውን ብድራትና የዘላለም ተስፋ መመልከታቸው፣ እንዲሁ ደግሞ እነ ጳውሎስና ሀዋሪያቱም የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመኖርና ለማገልገል እንዲሁም የገጠማቸውን ከባባድ መከራዎች ለማለፍ የረዳቸው፥ እየመጣ ያለው የክብር ተስፋ ውስጥ ያለው አቅም ነው።

መማር

መማር

ኢዮብ

ኢዮብ