Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

መማር

መማር

ሰሞኑን፥ የኢያሱን መጽሀፍ ነው እያነበብኩ ያለሁት። የእስራኤልን ህዝብ ከጠላቶቻቸው ጋር ተዋግቶ እግዚአብሄር የሰጣቸውን ምድር የመውረስ ታሪክ የሚነግረን መጽሀፍ ነው። መጽሀፉን በአንድ ቃል ግለጪው ተብዬ ብጠየቅ መውጣትና መውረስ ብዬ እገልጸዋለሁ። ለነገሩ ገና መጽሀፉስ ሲጀምር እግዚአብሄር ለኢያሱ መጥቶ ለአባቶቻቸው አሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ህዝብ ታወርሳለህና ጽና አይዞህ ብሎ በእሱ ህይወት ሊሰራ ያሰበውን የማውረስ አገልግሎት አይደል እንዴ የተናገረው። ኢያሱ አለው፥ “በህይወትህ እድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም ከሙሴ ጋር እንደሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ:: አልጥልህም አልተውህም” ብሎ ይህን የሚገርም ተስፋ ከሰጠው በኋላ፥ ቀጠል አረገና ነገር ግን ሙሴ ያዘዘህን ህግ ሁሉ ጠብቅ አድርገውም። በምትሄድበት ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ህግ መጽሀፍ ደግሞ ከአፍህ እንዳይለይ ሁልጊዜ አውራው፣ ተናገረው፣ ተጫወተው ከአፍህ አትለየው። የተጻፈበትን ሁሉ እንድትጠብቅና እንድታደርገው ደግሞ በቀንም በሌሊትም አስበው። አሰላስለው። የዚያን ጊዜ መንገድህ ይቃናልሀል፣ ይከናወንልሀልም ፧ በማለት ተስፋውን ብቻ ሳይሆን፣ ተስፋው በህይወቱ ይፈጸም ዘንድ ከእሱ የሚጠበቅበትንም ነገር ነው አንድ ላይ የነገረው። ብዙ ጊዜ እግዚአብሄር በህይወታችን ተስፋን ሲሰጠን ተስፋው ላይ ብቻ ነው የምናተኩረው:: በደምብ ጆሮ ሰተን መስማት ያለብን ግን ተስፋውን ብቻ ሳይሆን፣ ተስፋው ተፈጻሚነት እንዲያገኝ፣ እግዚአብሄር ከተስፋው ጋር የሚሰጠንን መመሪያዎችም ነው። ይሄ ከተስፋው ጋር የሚሰጠን ትእዛዝ፥ ተስፋው ጋር የመድረሻ መንገዳችን ነው። የተሰጡንን ትእዛዞች ስንፈጽም፣ ተስፋው መፈጸሙ አይቀርም። እግዚአብሄር እንደሆነ ታማኝ አምላክ ነው። ወደ ከነአን ትገባላችሁ የተባሉት የእስራኤል ህዝብ፣ የተሰጣቸውን ይህን ተስፋ ሳያዩ በምድረበዳ እየሞቱ ያለቁት፣ በሚጠበቅባቸው መንገድ ስላልሄዱ ነው። እግዚአብሄርማ ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን ወደ ተስፋይቱ ምድር በማስገባት የተናገረውን ነገር ፈጽሞ ታማኝነቱን አሳይቷል። እነሱ ከተስፋው ጎደሉ እንጂ፣ ተስፋው መፈጸሙ አልቀረም። የተገባላቸውን የተስፋ ቃል ሳያዩ በምድረበዳ ከቀሩት የእስራኤል ህዝብ የምንማረው ከእግዚአብሄር የሚመጣ ተስፋ በሙሉ የዘላለም ህይወት ተስፋችንን ጨምሮ፣ የሚጠብቅብን ተስፋውን የሚመጥን የህይወት አይነት እንዳለ ነው። ተስፋው፥ ትእዛዙን የመጠበቂያ አቅማችን ነው። ሂዱበት የተባልነውን መንገድ የመሄጃ ጉልበታችን ነው። የድላችን፣ የማሸነፋችን፣ ስለ እኛ ከእግዚአብሄር አንደበት የወጣው ተስፋ ጋር የመድረሻ መንገዶቻችን ደግሞ፣ ከተስፋው ጋር የተሰጡን ትእዛዞችና መመሪያዎች ናቸው። 

በአንደኛ ቆሮንቶስ ምእራፍ አስር ላይ ሀዋሪያው ጳውሎስ የእስራኤልን ህዝብ የምድረበዳ ጉዞ በማንሳት ሁሉም ከደመና በታች እንደነበሩ፣ ሁሉም መንፈሳዊውን መብል እንደበሉ፣ ሁሉም ከአለት የፈለቀውን መንፈሳዊ መጠጥ እንደጠጡ ያ አለት ደግሞ የክርስቶስ ምሳሌ አንደሆነ ይነግረንና፣ ምንም የእግዚአብሄርን መልካምነት ያዩ ከእግዚአብሄር እጅ የበሉና የጠጡ ህዝቦች ቢሆኑም፣ እግዚአብሄር ግን ከእነሱ በሚበዙት ደስ እንዳልተሰኘ፣ ተስፋ የተገባላቸው ምድር ውስጥ ሳይገቡ በምድረበዳ ወድቀው እንደቀሩ ይነግረናል። ይህ ታሪክ የተጻፈልን ለትምህርታችን እንደመሆኑ መጠን፣ ጳውሎስም ከእስራኤል ህዝብ ውድቀት ትምህርት ይሆናሉ ብሎ ያሰባቸውን ጥቂት ነገሮች በዚሁ ምእራፍ ላይ ጽፎልናል። ሁላችንም ጉዞ ላይ ነን። ከፊታችን ተስፋዎች አሉ። ግማሾቹ ተስፋዎች በዚሁ በምድር ላይ ባለን ቆይታ ተፈጻሚነትን የሚያገኙና እግዚአብሄር ለግል ህይወታችን የገባቸው ተስፋዎች ሲሆኑ፣ ሁላችንን በክርስቶስ አምነን የዳነውን ሰዎች አንድ የሚያረገን ደግሞ የምንጠብቀው ትልቅ የዘላለም ህይወት ተስፋ አለ። ተስፋውን መጠበቃችን መልካምና በዚህች ምድር ለምናልፍባቸው ከባባድ ፈተናዎች አቅም የሚሰጠን ነገር ቢሆንም፣ ተስፋው የሚጠብቅብንን ህይወት በእግዚአብሄር ጸጋ ተደግፈን ካልኖርነው ግን፥ ልክ እንደ እስራኤል ህዝብ ተስፋውን የማጣት አደጋ ህይወታችን ላይ እንዳለ መጽሀፍ ቅዱስ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጽፎልናል።

ጳውሎስ የእስራኤልን ህዝብ ውድቀት እንደ ምሳሌነት በማንሳት፣ የእስራኤል ህዝብ ጣኦትን በማምለክ እግዚአብሄርን እንዳስቆጡት፣ ጣኦትን አታምልኩ ብሎ ምክሩን ይጀምራል። ጣኦት ብለን ስናስብ ወዲያው ወደ ሀሳባችን የሚመጣው፥ ከወርቅ ወይም ከብር የተሰራ ምስል ሊሆን ይችላል። አዎ በድሮ ዘመን ጣኦት ምስል ባለው ነገር ይገለጥ ነበር። ጣኦት ማለት ግን፥ ልባችን ውስጥ ያለ ከእግዚአብሄር በላይ ቦታ የምንሰጠው፣ ከእግዚአብሄር በላይ ጊዜ የምንሰጠው፣ ከእግዚአብሄር በላይ ትኩረት የምንሰጠው፣ ከእግዚአብሄር በላይ የምንወደውና አጥተነው በህይወት መኖር እንደማንችል የሚሰማን ነገር በሙሉ ነው። ምንድነው ልባችንን የያዘው ነገር? ልባችን የት ነው ያለው? ከእግዚአብሄር በላይ ልናጣው የማንፈልገው ነገር ምንድነው? ብናጣቸው የመኖር ተስፋችንን በሙሉ የሚያጨልሙትና ከዚያ በሁዋላ ህይወት እንዳይታየን የሚያደርጉን ነገሮች ምንድናቸው? እግዚአብሄርን እንወዳለን እያልን ብንዘምርና ብንናገርም ግን፥ በጥልቀት ልባችንን ስንፈትሸው ከእግዚአብሄር በላይ የምንወዳቸው ነገሮች ምንድናቸው? ሁልጊዜ የምንወዳቸውን ነገሮች እያሰብን ከእግዚአብሄር እንደማይበልጡብን ጊዜ ወስደን ልባችንን መፈተሽና መመርመር አለብን። አንዳንድ ጊዜ እኮ፣ ልብን ለመፈተሽ ጊዜ መውሰድ በጣም ጥሩ ነገር ነው። በዚህ ፍተሻ ውስጥ፣ እናገኛቸዋለን ብለን ያላሰብናቸውን ነገሮች ልባችን ውስጥ ልናገኝ እንችላለን። ህይወት የሌለውንና ነገ ላይ የምንተወውን ጊዜያዊ መኪናዎቻችንን እንኳን ገንዘባችንን ከፍለን እናስመረምር የለም እንዴ? የምናስመረምረው ደግሞ፥ መኪናው ድንገት ያላየነው ችግር ቢኖርበት፣ አደጋ ላይ ሊጥለን ይችላል የሚል ስጋት ስላለን ነው። እግዚአብሄር ጋር ወስደን ያላስመረመርነው ልብም ልክ እንደዚሁ ነው። ድንገት አደጋ ላይ ሊጥለን ይችላል። አደጋው ደግሞ፣ ከመኪና አደጋ ይብሳል። ከዘላለም ጋር የተገናኘ አደጋ ነው። መዝሙረኛው ዳዊት በዚህ በምናወራው ጉዳይ ላይ ጥሩ ምሳሌ ሊሆነን ይችላል። ልቡን እግዚአብሄር ጋር እየወሰደ፣ መርምረኝ ፈትነኝ በማለት ያስመረምር ነበር። የልቡን ደህንነት በጥብቀት ይከታተል ነበር። ልባችንን ለማስመርመር እግዚአብሄር ጋር ስንሄድ ታዲያ፣ መጀመሪያ የቃሉን ብርሀን ልባችን ውስጥ በማብራት፥ መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች በሙሉ ያሳየናል። ከልባችን ውስጥ መውጣት ያለባቸው አላስፈላጊ ነገሮች በሙሉ ይወጣሉ። ነገሮች ሁሉ ቦታ ቦታቸውን መያዝ ይጀምራሉ። እግዚአብሄርም የሚገባውን ቦታ በልባችን ውስጥ ይይዛል። ብቸኛው ተስፋችን ይሆናል። ከዚህ የተነሳ በምድር ላይ የምናጣቸው ነገሮች ለጊዜው ቢያሳዝኑንም፣ ተስፋችን ግን እግዚአብሄር ላይ ብቻ ስለሆነ አይጨልምብንም። ምንም አይነት ጣኦትም ልባችን ውስጥ እንዳይኖር ይረዳናል። 

ሁለተኛው የእስራኤልን ህዝቦች ውድቀት እንደ ትምህርት በመውሰድ ጳውሎስ አትሴስኑ በማለት ይመክረናል። መቼም አሁን ባለንበት በዚህ ዘመን አለመሴሰን ወይንም መቀደስ የሚለውን ወሬ ማንሳት እንደ ፋራ የሚያስቆጥረን ጊዜ ላይ ደርሰናል። ሁሉም ሰው ደስ ያለውን ነገር የሚያረግበት ዘመን ላይ ነን። ሁሉም ሰው የተከተለው መንገድ ነው ማለት ግን፥ ትክክለኛ መንገድ ነው ማለት አይደለም። እግዚአብሄር ከህዝብ ቁጥር ጋር ችግር የለበትም። ኖህን ብቻውን አድኖት፥ የምድርን ህዝብ በሙሉ አጥፍቶ ያውቃል። ስለዚህ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች፣ ለእኛ የስህተት መንገድ ምርጫ ተጠያቂነቱን ሊወስዱ አይችሉም። መኖር ያለብን የራሳችንን ኑሮ ብቻ ነው። አይኖቻችንን ማድረግ ያለብን ዙሪያችን ያሉት ሰዎች ላይ ሳይሆን፣ የሩጫችን ጀማሪና ፈጻሚ የሆነውን ክርስቶስን ላይ ብቻ ነው። ለእያንዳንዱ እንደ ስራው ሊከፍል ዋጋውን በእጁ ይዞ የሚመጣው እግዚአብሄር ሀሳቡን አለወጠም። አይታችሁ ከሆነ፣ ዋጋ እኮ ደሞዝ እኮ የሚከፈለው መጨረሻ ላይ ነው። እናንተ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመኖር ወስኑ እንጂ፣ በግላችሁ ማንም ሰው ሳያውቅ ለምትኖሩት እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኝ ህይወት፣ በአደባባይ በብዙ ክብር የሚከፍላችሁ አምላክ ሊመጣ የቀረው በጣም በጣም ጥቂት ጊዜ ነው።  መጽሀፍ ቅዱስ በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘነው ደህንነት ከቅድስና ጋር ቀጥተኛ የሆነ ተዛምዶ እንዳለው ይነግረናል። ብዙ ጊዜ በክርስቶስ አምነን መዳናችንን እንጂ፣ መቀደሳችንን ቦታ ስንሰጠው አይታይም። መዳንና ቅድስና ግን፣ ሁለት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። በቅድስና ጠርቶናል ተብሎ እንደተጻፈው፣ መጠራታችን እራሱ፣ ጥሪው እራሱ ቅዱስ ነው። ቅዱስ የሆነውን ጥሪ ተቀብለን፥ በረከሰ የህይወት አካሄድ ውስጥ እንድንመላለስ አልተፈቀደልንም። ስማችን እራሱ የንጉስ ካህናት፣ ለእርሱ የተለዩ ወገኖች፣ ቅዱስ ህዝቦች ነው የተባልነው። ጳውሎስ፣ የእስራኤልን ህዝብ ከተስፋቸው መጉደል በማንሳት ሊመክረን ሲነሳ፣ ሴሰኝነት ወይንም አለመቀደስ የእስራኤልን ህዝብ ትገባላችሁ ከተባሉት፥ ከተሰጣቸው ተስፋ ያጎደላቸው ምክኒያት እንደሆነ ይነግረናል። በኤፌሶን መጽሀፍ ምእራፍ 5 ቁጥር 5 ላይም እንዲሁ ጳውሎስ ሲናገር፣ “ይህን እወቁ፣ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኩስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣኦትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሄር መንግስት ርስት የለውም።” በማለት ያስጠነቅቀናል። ቅድስናን ስናስብ ብዙ ጊዜ የምናያይዘው ከዝሙት ሀጢያት ጋር ብቻ ይሁን እንጂ፣ መቀደስ ሁለንተናዊ እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል። በንግግራችን፣ በአስተሳሰባችን፣ በድርጊቶቻችን ሁሉ ልንቀደስ ይገባል። በየትኛውም ሀጢያት ብንስት ታዲያ፣ እግዚአብሄር መሀሪና ይቅር ባይ እንደመሆኑ መጠን፣ ቶሎ ብለን በንሰሀ መመለስና አቅጣጫችንን ቀይረን የጀመርነውን የቅድስና ህይወት መቀጠል እንደምንችል ማወቅ መልካም ነው። ስለ ቅድስና ስናወራ በፍጹም መርሳት የሌለብን ነገር፣ በክርስቶስ ደም ካጠበን በሁዋላ በመንፈስ ቅዱስ የቀደሰን እራሱ እግዚአብሄር ነው። የቀደሰን ስራችን አይደለም። እኛማ የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን በርኩሰት ውስጥ እንመላለስ የነበርን ሰዎች ነበርን። በዚህ በርኩትሰት ህይወት ውስጥ እንዳለን ታዲያ፣ ቅዱስ በሆነ አጠራሩ ከጠራን በኋላ፣ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም አጥቦን፣ በመንፈሱ የቀደሰን እራሱ እግዚአብሄር ነው። የቀደሰን የእኛ ስራ አይደለም። ቅድስና የሚጀምረው እግዚአብሄር እራሱ እንደቀደሰን ከማወቅ ነው። ታዲያ ምንም ብንለፋ ልናገኝ የማንችለውን ቅድስና ከሰጠን በኋላ፣ ከእኛ የሚጠብቅብን፣ የሰጠንን ይሄንን ከእግዚአብሄር ጋር የምንገናኝበትን ቅድስና እንድንጠብቀው ብቻ ነው። የእኛ ሀላፊነት በክርስቶስ ውስጥ የተሰጡንን ስጦታዎች መጠበቅና መንከባከብ ብቻ ነው። የምንጠብቀው ደግሞ፣ ቅድስናችንን ወይንም ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ህብረት ከሚያበላሹና አደጋ ላይ ከሚጥሉ ነገሮች በሙሉ በመራቅ ነው።

ሌላው ጳውሎስ ከእስራኤል ህዝብ ውድቀት እንደምሳሌ አርጎ የሚመክረን ነገር፥ እግዚአብሄርን እንዳንፈታተን እንዲሁም እንዳናጉረመርም ነው። ማጉረምረም የሚለውን ቃል በጥልቀት ካሰባችሁት፣ የሚሆንብኝ ነገር ትክክል አይደለም የሚል ስሜትን በውስጡ ይዟል። ይሄ ደግሞ በቀጥታ ባይሆንም በተዘዋዋሪ በእግዚአብሄር ሁሉን ነገር በትክክል የመስራት ማንነቱ ላይ የሚዋሽ ነው። በባለፈው ጽሁፋችን ውስጥ ኢዮብ ካለፈባቸው ነገሮች ለመማር ስንሞክር፥ ኢዮብ ምንም ያጠፋሁት ነገር የለም በሚለው ሙግቱ ላይ እግዚአብሄር ሲመልስለት “አንተ ራስህን ለማጽደቅ ስትል እኔን ትኮንናለህን?” በማለት እንደመለሰለት አይተናል። በአጭር ቃል ማጉረምረም ማለት እግዚአብሄር  በህይወቴ እያረገ ያለው ነገር ትክክል አይደለም ማለት ነው። ማጉረምረም የእግዚአብሄርን ትክክል መሆን ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሄርን መልካምነት እንድንጠራጠር የማድረግ ሀይል አለው። በሁሉ አመስግኑ ተብለን የታዘዝነውን ቃል መንፈስ ያጠፋብናል። ለዚህ ነው እግዚአብሄር ማጉረምረምን አጥብቆ የሚጠላው። የእስራኤል ህዝብ፣ ያለፉባቸው ከባባድ የምድረበዳ መንገዶች ቢኖሩም፣ ባለፉባቸው ከባድ መንገዶች ውስጥ በተለያየ ሁኔታ ሲያጉረመርሙ፣ የእግዚአብሄርን ችሎታ ሲጠራጠሩ እግዚአብሄር ደስ እንዳልተሰኘ የተገባላቸውን የተስፋ ምድር ሳያዩ በምድረበዳ ያስቀራቸው አንዱ ነገር ማጉረምረምና እግዚአብሄርን መፈታተናቸው እንደሆነ ጳውሎስ ትምህርት እንወስድ ዘንድ ጽፎልናል። ህይወት ሁልጊዜ ደስታ ብቻ አይደለችም። በችግር ውስጥ፣ በሀዘን ውስጥ፣ በመከራ ውስጥ የምናልፍባቸው ጊዜያቶች ህይወታችን ላይ አሉ። በእነዚህ ጊዜያቶች መጸለይና የእግዚአብሄርን እርዳታ መለመን መልካም ነው። እግዚአብሄር ሁልጊዜ እኛን ለመርዳት የተዘጋጀ፣ ጆሮዎቹን ወደ ጩሀትና ወደ ልመናችን ያደረገ አምላክ ነው። ከዚያ በዘለለ ግን ማጉረምረማችን እግዚአብሄርን ከማሳዘን አልፎ የእስራኤል ህዝብ በምድረበዳ መቅረት ውስጥ የጎላ ሚና እንደተጫወተ ከጳውሎስ ምክሮች እንረዳለን። 

ስኬት

ስኬት

ዘላለም

ዘላለም