Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ስኬት

ስኬት

ስኬት ስለሚለው ቃል ስናስብ መቼም ሁላችንም ልብ ውስጥ የሚመጡ ይሄን ይሄን ባሳካ ብለን በልባችን ውስጥ የምናስባቸው፣ የአጭርና የረጅም ጊዜ ስኬቶች ይኖሩናል። ከዚያም በተጨማሪ ደግሞ በአካባቢያችን ላይ የምናውቃቸው ወይንም በsocial media ገጾቻችን እነሱ እንኳን ሳያውቁን እኛ የምናውቃቸውና የምንከተላቸው፣ በየቀኑ የሚያወጡትን ፎቶዎች እያየን የስኬት ምሳሌዎች ያረግናቸው ሰዎችም ይኖራሉ። ስኬት ለሁሉም ሰው የተለያየ ትርጉም ያለውና በህይወት ዋጋ ከምንሰጣቸው ነገሮች ጋር የተያያዘ ነገር ነው። ለአንዳንዱ በልፋቱ የሚያገኘው ደሞዝና ዋጋው ነው። ለሌላው ደግሞ ትምህርቱን ጨርሶ ያሰበውን ስራ መያዝ ማግባትና መውለድ ሊሆን ይችላል። ለሌላው ደግሞ አካባቢው ባሉ ሰዎች ወይንም በብዙሀኑ ዘንድ በሰራው ስራ እውቅናና ዝናን ማግኘት ሊሆን ይችላል። “ለእኔ በጤናና በሰላም ስራዬን ሰርቼ የቀን ለቀን ውሎዬን በሰላም ካለፍኩ ስኬት ነው” የሚሉ ሰዎችም አሉ። እነዚህ ሁሉ ከላይ የዘረዘርናቸው ነገሮች ምንም ክፋት የሌለባቸው፣ እንዲያውም በዚህች ምድር ላይ ስንኖር ሊያስፈልጉን የሚችሉና የምንጠቀምባቸው ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ደግሞ ልክ እንደ አንድ ክርስቶስን በህይወቱ ለመከተል እንደወሰነ ሰው ሆነን ህይወትን ስናየው ከሌሎች ክርስቶስን ከማይከተሉ ሰዎች ለየት ያለ የስኬት ትርጉም ሊኖረን እንደሚገባ እናስተውላለን። ለመማር፣ ለማግባትና ለመውለድ የክርስቶስ ተከታዮች መሆን አይጠበቅብንም። እንዲያውም፣ ስኬትን በእነዚህ ነገሮች ከተረጎምነው፣ ከእኛ በላይ በብዙ እጥፍ የተሳካላቸው ብዙ በክርስቶስ ያልሆኑ ሰዎች በምድራችን ላይ አሉ። ታዲያ ከተጠራንበትና ነገሮችን በሙሉ ልንመዝንበት ከተሰጠን ህይወት አንጻር ስኬትን እንዴት እናየዋለን? 

እኛ ስኬትን ለየት ባለ መንገድ እንድናየው የሚረዳን የውስጥ አይኖቻችን ተከፍተው ከዚህች አጭር 70 እና 80 አመት ቀጥሎ የሚጀምር ዘላለም የሚባል ቁጥር የማይወስነው ዘላለማዊ የሆነ ህይወት እንዳለ መረዳታችን ነው። አያችሁ ጌታን የማያውቁ ሰዎች ስኬትን የሚተረጉሙት አይናቸው ሊያይ እስከሚችለው 70 እና 80 አመት ርቀት ብቻ ነው። ህይወታቸውን የሚያቅዱት በዚህች ምድር ቆይታ ላይ ብቻ ተመስርተው ነው። ስለዚህ ስኬት ለእነሱ አብዛኛውን ጊዜ የተያያዘው፣ ከዚህች ምድር ምቾት ጋር ብቻ ነው። እኛ ግን ስኬትን የምናየው፣ ከዚህች በጣም አጭር የምድር ቆይታ አልፈን እንድናይ እግዚአብሄር በሰጠን ሰፊ እይታ ውስጥ ሆነን ነው። ስለዚህ በጣም የምንጨነቀው ለዚህች ምድር አጭር ቆይታችን አይደለም። ለዘላለም ነው። የእግዚአብሄርን ቃል በስፋት እያነበብን ስንመጣ፣ በቃሉ ውስጥ የእግዚአብሄርን ልብ እየተረዳነው እንመጣለን። ሀሳቡን እያወቅነው፣ ከሚናገራቸው ንግግሮች፣ ከሚሰጣቸው ምሳሌዎች፣ ደጋግሞ ትኩረት ከሚሰጥባቸው ሀሳቦች፥ ዋጋ የሚሰጠው ምን ላይ እንደሆነ፣ የሚያተኩረው ምን ላይ እንደሆነ፣ ፍላጎቱ ምን እንደሆነ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እየተረዳን ወይንም እያወቅነው እንመጣለን። ታዲያ እስከዛሬ ድረስ ካነበብነው ወይንም በስብከትና በትምህርት ከሰማነው አስተውለን ካየነው፥ እግዚአብሄር ከምንም ነገር በላይ፥ ትኩረት ወይንም ቅድሚያ የሚሰጠው ዘላለም ለሚባለውና ይህቺን አጭር የምድር ቆይታ ስንጨርስ ስለምንጀምረው ህይወት ነው። እግዚአብሄር ስሙ ወይንም መጠሪያው የዘላለም አምላክ፣ መንግስቱና ዙፋኑ የዘላለም፣ ምህረትና ፍቅሩ የዘላለም፣ ለእኛ የሰጠንም ህይወት የዘላለም ነው። ወንጌል በጣም አስፈላጊና የእግዚአብሄርን ልብ የያዘ ነገር የሆነው የሰዎችን የዘላለም አድራሻ ወይንም የዘላለም መኖሪያ የሚቀይር ነገር ስለሆነ ነው። ስለዚህ የእግዚአብሄር የልቡ ትርታ ዘላለም ከሚለው ቃል ጋር በጣም የተሳሰረ ነው። ይሄ አሁን እየተነጋገርንበት ያለነውን ነገር የሚያጠናክርልንንና በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 18 ላይ ኢየሱስ ከተናገራቸው ነገሮች ውስጥ እስኪ አንዱን እንመልከት። አንድ ጊዜ ስለ ማመንዘር ትምህርት ሲሰጣቸው እንዲህ አለ። ቀኝ አይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት ሙሉ ሰውነትህ በገሀነም ከሚጣል፣ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሀልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፣ ሙሉ ሰውነትህ በገሀነም ከሚጣል  ይልቅ፥ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና አላቸው። አያችሁት የኢየሱስን እይታ። ብዙ ጊዜ እኛ ስንቀልድ እንኳን፥ በአይኔና በዚህ ሰው ቀልድ አላውቅም እያልን እንናገራለን። እውነት ነው አይን በጣም አስፈላጊ ከምንላቸው የሰውነት ክፍሎቻችን አንዱ ስለሆነ ነው። እንደ ኢየሱስ ንግግር ከሆነ ግን፥ በጣም አስፈላጊ ነው ከምንለው ከአይናችን በላይ ሌላ በጣም አስፈላጊ ነገር አለ። እሱም ደግሞ ዘላለማችንን የምናሳልፍበት ቦታ ነው። ኢየሱስ፥ ዘላለማዊ በሆነ እይታ ውስጥ ሆኖ ሲያየው፣ በምድር ላይ አስፈላጊ የምንለውን ነገር አተን ዘላለማችንን ከእርሱ ጋር ብናሳልፍ ነው ያተረፍነው። በምድር ላይ አስፈላጊ የምንለው ነገር ዘላለማችንን ካሳጣን የኢየሱስ ፍርድ ይሄ ነው። አውጥታችሁ ጣሉት ወይንም ቆርጣችሁ ጣሉት። በጣም ይጠቅመኛል ብለን የያዝነው ነገር፥ ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ህብረት ካበላሸብን፣ አውጥተን ጥለነው እግዚአብሄርን ወይንም ዘላለማችንን በጥንቃቄ ብንጠብቀው ትልቅ ማስተዋል ነው። ከአይናችን በላይ ልንጠብቀውና ልንንከባከበው የሚገባን ነገር ቢኖር፥ ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ህብረትና ዘላለማችንን ነው። 

እግዚአብሄር ዘላለም ለሚባለው ህይወታችን የሚሰጠውን ቦታ በድርጊት ወይንም በስራ ካየንባቸው ነገሮች ዋነኛው፣ የእኛን የዘላለም አድራሻ ይቀይር ዘንድ፣ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር መላኩ ነው። መዳናችን፣ ኢየሱስ ለእኛ በመስቀል ላይ የሰራውን ስራ በማመን ብቻ ያገኘነው ስጦታ እንደሆነ እናውቃለን። ሁልጊዜ መርሳት የሌለብን ግን፣ ስጦታ የሆነው ለእኛ ብቻ እንጂ፣ ኢየሱስን ግን ያላስከፈለው ዋጋ አልነበረም። ነጻ ስጦታ የሆነው ለእኛ ብቻ ነው። ኢየሱስ ግን እያንዳንዱን የውርደት ጥግ ያየባቸው አሰቃቂ 33 አመታቶች ናቸው። እኛ ሰዎች ስለሆንን ለእኛ ሰው መሆን ቀላል ነው። መጽሀፉ ስለ ኢየሱስ ሲነግረን ግን በሰው ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፣ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ ይለናል። ኢየሱስ ራሱን ማዋረድ የጀመረው፥ የሚሰቀልበት ሰአት ሲደርስ አይደለም። መስቀል ላይ ሲውል አይደለም። ራሱ ከምድር አፈር የሰራውን ሰው ለመሆን ሲወስን ነው። ራሱን ሰው ለማድረግ ከመወሰኑ አንስቶ፣ በምድር ላይ አለ በተባለው ውርደት ስቃይና መከራ ውስጥ የማለፉ ሚስጥር፥ እግዚአብሄር ዘላለም ለሚባለው ህይወት ያለውን ቦታ በትክክል ሊያስረዳን ይችላል። ክርስቶስ በምድር ላይ እያለ የተለያዩ ሰዎችን በመፈወስ፣ ከሰይጣን እስራት ነጻ በማውጣትና በተለያዩ መንገዶች የሰው ልጆችን የረዳ ቢሆንም ዋናው የመጣበት አላማ ግን የእኛን ዘላለም ለማስተካከል ነው። እንዲያውም በምድር ላይ የሰራቸው እያንዳንዱ ተአምራቶች ወደ ምድር የመጣበትን የዘላለም ህይወት ጉዳይ ሰዎች እንዲሰሙና እንዲረዱ ልባቸውን ለማግኘት የተጠቀመባቸው መንገዶቹ ነበሩ። ከኢየሱስ በሁዋላ የሀዋሪያቶችንም አገልግሎት ስታዩ፣ በሀዋሪያቶቹ እጅ እጅግ ብዙ ድንቅና ተአምራቶች ይደረጉ ነበር። የሚገርማችሁ ግን፥ የትኛውንም ተአምራት ስታነቡ፣ ከእያንዳንዱ ተአምራት በኋላ፥ ሰዎች ባዩት ነገር እየተደነቁ ልባቸውን ለእግዚአብሄር ይከፍቱ ነበር። ጆሮአቸውን ለወንጌል ይከፍቱ ነበር። ብዙዎች ጌታን ይቀበሉ ነበር። ብዙዎች ወደ እግዚአብሄር መንግስት ይጨመሩ ነበር። ሀዋሪያቶቹም በተአምራቱ የተከፈተውን የሰዎችን ልብ ተጠቅመው፣ ወዲያው ወንጌልን ይናገሩ ነበር። እግዚአብሄር በብዙ ድንቅና ተአምራት ቃሉን በመካከላቸው ያጸና ነበር። ዛሬም ምናልባት እግዚአብሄር በእጃችን ድንቅና ተአምራቶችን ያደርግ ይሆናል። እነዚህ ተአምራቶች ግን ለራሳችን የሰዎችን ትኩረት መሰብሰቢያዎች እንዳናረግ በጣም ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ይልቁንም፥ ትንሽም ሆነ ትልቅ እግዚአብሄር በእኛ ተጠቅሞ የሰራው ነገር ካለና የሰዎችን ትኩረት እግዚአብሄር ከሰጠን፣ ቶሎ ብለን ስለ ተአምራት አድራጊው መናገር፥ እኛን ስለወደደበት ፍቅር የሰው ልጆችን ሁሉ ከሀጢያት በሽታ ለማዳን ልጁን መላኩን፣ የመዳኛ መንገዱ ደግሞ ኢየሱስ ብቻ መሆኑን ለሰዎች መመስከር ይኖርብናል። የእግዚአብሄር የልቡ ትርታ ሰዎች ከጨጉዋራ በሽታ መፈወሳቸው አይደለም። ስለ ምድራዊ ፈውሶቻችን ግድ የሚለው አምላክ ቢሆንም፣ ዋናና ትልቁ አላማው ግን ሰዎችን ከሀጢያት በሽታና ዘላለማቸውን ከሚያሳልፉበት ከዘላለም ጨለማ አውጥቶ ወደ ዘላለም መንግስቱ ማስገባት ነው። 

ታዲያ እግዚአብሄር ለዘላለም የሚሰጠው ቦታ እጅግ በጣም ትልቅ እንደሆነ ከተረዳን፣ ስኬት ከእግዚአብሄር እይታ አንጻር ምንድነው? ስኬት ከዘላለም አንጻር ሲታይ ወይንም፣ 70 እና 80  አመታቶችን አልፎ ማየት በሚችለው መነጽራችን ስናየው ምንድነው? እግዚአብሄር አንድን ሰው የተሳካ ህይወት ነበረው የሚለው ያ ሰው በምድር ላይ በተሰጠው ጥቂት ዘመናቶች ምን አይነት ህይወት ሲኖር ነው? ይሄንን ጥያቄ ለመመለስ እንግዲህ፣ ከእኔ ተማሩ ያለው ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖረባቸው ስኬታማ አመታቶች በላይ ሌላ ሊያስተምረን የሚችል ነገር የለም። በተሰጠው በጣም አጭር አመታቶች እያንዳንዱን የተሰጡትን ጊዜያቶች በትክክል በመጠቀም ስኬታማ ሆኖ ያለፈና እኛም አሁን እየኖርን ላለነው ህይወት ትልቁ ምሳሌያችን፣ ክርስቶስ በምድር ላይ የኖራቸው አመታቶች ናቸው። በኖረባቸው ጥቂት አመታቶች ውስጥ፣ ከእግዚአብሄር ጋር ትክክለኛ ህብረት የነበረውና በትክክል የሄደ፣ ምን ማድረግ እንዳለበት የሚያውቅ፣ ማድረግ ላለበት ነገሮች በሙሉ ትክክለኛውን ጊዜ እያወቀ በትክክለኛው ጊዜ ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግ። ሁልጊዜ ተልኮ መምጣቱን የማይረሳ፣ የቀንና የለሊት ሀሳብና ምኞቱ የእግዚአብሄር የአባቱን ፈቃድ መፈጸምና ማገልገል የሆነ ፍጹም አምላክ ብቻ ሳይሆን፣ ልክ እንደ እኔና እንደ እናንተ ፈታኝ የሆነውን ስጋ ለብሶ በምድር ላይ የተመላለሰ የእግዚአብሄር ልጅ ነው። ታዲያ ይሄ ክርስቶስ፥ በምድር ላይ በኖረበት ዘመን መጨረሻ ላይ፣ የሰጠኸኝን ስራ ፈጽሜ አከበርኩህ በማለት በነበረበት ዘመን መስራት ያለበትን ሁሉ ሰርቶ ጨርሶ ስኬታማ የሆነ ሰው ንግግርን ሲናገር እንሰማዋለን። ከዚህ ንግግሩ፣ ሊሰራ የተሰጠው ስራ እንደነበረ ወይንም ተልኮ እንደመጣ መረዳት እንችላለን። ታዲያ ቃሉን ስታነቡ፣ ኢየሱስ ሊሰራ ተወስኖ በተሰጠው የምድር ቆይታው ውስጥ አንድ እየደጋገመ የሚናገረውና ሁልጊዜ ትኩረት የሚሰጥበት አንድ ነገር ነበር።  የእግዚአብሄር ፈቃድ። ፈቃዴን ለማድረግ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነው የመጣሁት ይላል። የራሱን ፈቃድ አያደርግም። አካባቢው ላይ ያሉ ሰዎችን ፈቃድም አያደርግም። ጊዜያዊ ጥቅም ሊያስገኙለት የሚችሉትን ጥሩ ጥሩ እድሎችና አጋጣሚዎችም አይጠቀምባቸውም። ሰዎች ተሰብስበው እናንግስህ ሲሉትም አልፈልግም እያለ ጥሎዋቸው ይሄዳል። የእሱ ልብ ያለው ከፍታም ዝቅታም ጋር አይደለም። ልቡ ያለው የተላከበትን ወይንም ወደ ምድር የመጣበትን የእግዚአብሄርን ፈቃድ መኖርና ማገልገል ላይ ብቻ ነው። ከተላከበት አጀንዳ ትንሽ ፈቀቅ የሚያረገው አጋጣሚም፣ እድልም፣ ከፍታም ዝቅታም አልነበረም። ኢየሱስ በእግዚአብሄር እንደተላከ የልቡ ምኞት ደግሞ የላከውን የእግዚአብሄርን ፈቃድ መፈጸም እንደነበረ፣ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለው ብሎ ልኮናል። የላከን ደግሞ የእሱን ሀሳብና ፈቃድ እንድንኖርና እንድናገለግል ነው። እሱ የኖረውን ህይወት እንድንኖር ነው። በዚህ በተላክንበት ህይወት ውስጥ፣ የመጀመሪያው ሀላፊነታችን እንደ ተላከ ሰው ማሰብ መጀመር ነው። የሆነ ነገር ለመስራትና ለማገልገል የተላኩ ሰዎች ነን። በየቀኑ የምንሰራውና የምናደርገው ደግሞ የላከንን ሀሳብና ፈቃድ ነው። ከላከን ጋር በጸሎትና ቃሉን በማንበብ ያነበብነውን ደግሞ ለመኖር በመሞከር ውስጥ የጠበቀ ህብረት አለን። በዚህ ህብረታችን ውስጥ የሚሰጡንን ምሪቶች በመቀበል በየቀኑ እንኖራቸዋለን። የየቀኑ ኑሮአችን በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ የተጠበቀ ነው። የምናገለግለውም፥ አገልግሉ ተብለን የተላክንበትን መልእክት ብቻ ነው። በዚህ ውስጥ እግዚአብሄር እኛን ያውቀናል። ዋናውና ትልቁ የህይወት ስኬታችን ይሄ ብቻ ነው። የልቡን ሀሳብ መኖርና ማገልገል። ሳይፈጥረን በፊት ስለ እኛ የጻፈውን በየቀኑ መኖር። ልክ እንደ እምነት አባቶቻችን ዋጋ የምንከፍልበትን ህይወትና አገልግሎት ለእግዚአብሄር እንደ መስዋእት ማቅረብ። ፈቃዳችንን በሙሉ ለፍቃዱ ማስገዛት። ለዘላለም የእርሱ ባሪያዎች በመሆን ውስጥ ያለውን ዘላለማዊ ክብር ማግኘት። እንደ ኢየሱስ በምድር ላይ ዝቅ ብሎ፣ በዘላለም ውስጥ ከፍ ማለት። ከምናልፍበት የምድር ውጣ ውረድ፣ ስቃይና መከራ ጋር የማይወዳደረው ዘላለማዊ ክብር ውስጥ መግባት። በክርስቶስ ውስጥ ያገኘነውን ልጅነት ጠብቆ እግዚአብሄርን መውረስ፣ የመንግስቱ ተካፋዮች መሆን፣ በዘላለም እረፍት ውስጥ ለዘላለም መኖር። ይሄ ነው የእኛ ግብ። ይሄ ነው የእኛ ስኬት። 

ሩት

ሩት

መማር

መማር