Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ሩት

ሩት

ስራ በሌለኝና በእረፍት ቀናቶቼ ማድረግ ከምወዳቸው ነገሮች አንዱ፥ በጠዋት ተነስቶ ውሀ ዳር ያለ ፓርክ በመሄድ ቀለል ያለ የእግር ጉዞ ማድረግ ነው። እንዴት አንደሚያዝናናኝ እንዴት ብዬ ልንገራችሁ! በተለይ፥ በበጋና አየሩ ሞቃታማ በሆነባቸው ጊዜያቶች፥ የማለዳው ጸሀይ ነፋሻማ ከሆነው ተስማሚ አየርና በዙሪያዬ ከማያቸው የተለያዩ የተፈጥሮ ውጤቶች ጋር ተደምሮ፥ በደስታ ብዛት ሩጪ ሩጪ ስለሚለኝ ያሰብኩትን ቀላል የእግር ጉዞ ወደ ሩጫ የቀየርኩባቸው ጊዜያቶች ጥቂቶች የሚባሉ አይደሉም። የተፈጥሮ ውጤቶች መንፈሴን እያደሱ አዲስነትን ይሰጡኛል። የእግር ጉዞ ማድረግ፥ እየሄዱ ማሰብ፥ ለራሴ ጊዜ መስጠት፣ ውስጤን ማዳመጥ፣ በተቻለኝ አቅም መመለስ የምችላቸውን የልቤን ጥያቄዎች መመለስ፣ ያልቻልኳቸውን ደግሞ የእግዚአብሄር መንፈስ መልስ እንዲሰጥልኝ መጠየቅ። እነዚህ ከራሴ ጋር የማሳልፋቸው ጊዜያቶች፥ በተለያየ መንገድ ህይወቴን ሲጠቅሙት አይቻለሁ። ብዙ ትክክለኛ ውሳኔዎችን ወስኜባቸዋለሁ። ዝምታዬን አዳምጬባቸዋለሁ። ልቤን አስተካክዬባቸዋለሁ። የእግዚአብሄር መንፈስ ሲገስጸኝ ሲመክረኝና ሲያጽናናኝ ደግሞ ሰምቼባቸዋለሁ። እናንተስ በእረፍት ቀናቶቻችሁ ማድረግ የምትወዱት ምንድነው? በዛሬው ጽሁፋችን፣ መጽሀፍ ቅዱስ ላይ ስላለች፥ በዚህ ወቅት አብዝቼ ስለማስባትና ስለምደነቅባት፥ እንዲሁም ብዙ ነገሮችን ለግል ህይወቴ ስለተማርኩባት አንዲት ሴት እንድናወራ አስቤያለሁ። ሩት። ሞአባዊት ሴት ናት።  በጣም ከሚገርሙኝና በብዙ ምሳሌነት ከምናነሳቸው ሴቶች መካከል አንዷ ናት። የህይወትዋን አካሄድ ሳየ፡ በተለያዩ ነገሮችዋ እደነቃለሁ። ምንም ከመሆን ተነስታ፣ ትውልድን የሚያልፍና ዘላለም የሚወራ ታሪክ ውስጥ መግባትዋ፥ ኪዳን ከሌለው ዘር ውስጥ መጥታ፥ የኪዳን ዘር ውስጥ መግባትዋ፣ ባልዋን ከማጣት ተነስታ ቦኤዝ ጋር መድረሷ፣ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ኢየሱስ እንኳን ሲነገር የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል ተብሎ የተነገረለትንና እንደ እግዚአብሄር ልብ የሆነውን የዳዊትን ቅድመ አያት በመውለድ የነገስታት ዘር ውስጥ መግባትዋ፣ ከዳዊት ዘር ከይሁዳ ነገድ የመጣው ደግሞ የክርስቶስ የዘር ሀረግ ውስጥ የመግባትን ማእረግ ማግኘትዋ ይገርመኛል። መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥም በስማቸው መጽሀፍ ከተጻፈላቸው ሁለት ሴቶች መካከል አንዷ ሩት ናት። የኪዳን ህዝብ የሆነችው ኑሀሚን ብትሆንም፣ መጽሀፉ የተሰየመው ግን በሩት ስም መሆኑና መጽሀፉ የእሷ ታሪክ ላይ ማተኮሩም እንዲሁ ይገርመኛል። ታዲያ ያገኘችውን ይሄንን ሁሉ ክብርና ማእረግ ስናይ፥ ሩት ማናት? ምን አይነት ሰው ናት? እምነቶችዋ ምንድናቸው? ባህሪዋ ምን አይነት ነው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳታችን አይቀርም። ብዙ ጊዜ የሩትንና የአስቴርን መጽሀፍ ሴቶች ብቻ በብዛት ሲያተኩሩበት ይታያል። ነገር ግን የሩትና የአስቴር ታሪክ ለሴቶች ብቻ፥ የነ ዳዊት የነ ሙሴና የነ ጳውሎስ ታሪክ ደግሞ ለወንዶች ብቻ ትምህርት ለመሆን የተጻፈ ሳይሆን፣ በእርግጥ ከጾታ ልዩነታችን በተወሰነ መልኩ የምንወሰዳቸው ለየት ያሉ ትምህርቶች ቢኖሩም፥ በእግዚአብሄር ቃል ላይ ከተጻፉት ሰዎች በሙሉ ካስተዋል፣ ለሁላችን የሚሆኑ ብዙ ትምህርቶች አሉ። 

ታሪኩን ስናነበው፥ አቤሜሌክ የተባለው ሰው፥ በሀገሩ ከነበረው ረሀብ የተነሳ፥ ሚስቱን ኑሀሚንንና ሁለቱን ወንዶች ልጆቹን ይዞ ወደ ሞአብ ሀገር እንደሄደ በመናገር ይጀምራል። ወደ ሞአብ ምድር ሄዶ ብዙም ሳይቆይ ነው ይሄ ሰው እንደሞተ መጽሀፉ የሚነግረን። ይሄ ሰው በሞአብ ምድር መሞቱን እንዲሁም ደግሞ የኑሀሚን ሁለት ወንዶች ልጆችዋ ሚስቶችን አግብተው አስር አመታቶችን ከኖሩ በኋላ እነሱም እንዲሁ መሞታቸውንና ኑሀሚን የሁለቱ ወንዶች ልጆችዋ ሚስቶች ከነበሩት ከሩትና ከኦርፋ ጋር መቅረትዋን በመናገር ታሪኩ ይቀጥላል። ኑሀሚን ታዲያ ባልዋንና ሁለቱን ልጆችዋን ካጣች በኋላ ወደ ህዝቧ ልትመለስ ስትወስን፥ እነዚህ የልጆችዋ ሚስቶች የነበሩት ሁለት ወጣት ሴቶች፥ ከእርስዋ ጋር ለመሄድ ጥያቄ አቅርበውላት ነበር። “አይሆንም ልጆቼ ከዚህ በኋላ ምን ቀረ ብላችሁ ነው የምትከተሉኝ? እኔ ዛሬ እንኳን አግብቼ ወንዶች ልጆችን ብወልድ ለእናንተ ባል ለመሆን ይደርሳሉ? ይልቅ እዚሁ ህዝባችሁ ውስጥ ነው ትንሽም ቢሆን የማግባት ተስፋ ያላችሁ:: እኔን ትታችሁ የራሳችሁን ህይወት ብትቀጥሉ ነው የሚያዋጣችሁ” ብትላቸው ኦርፋ እውነት እኮ ነው። እኔ በወጣትነቴ ባሌን ያጣሁ ሰው ነኝ:: ከዚህ በኋላ ደግሞ እድሜዬ ሳያልፍ ቶሎ ብዬ ማግባትና መውለድ ይኖርብኛል ብላ በማሰብና ከኑሀሚን ሀሳብ ጋር በመስማማት የደህና ሁኚ ሰላምታ ሰጠቻት። ይህቺ ሴት ምንም ያጠፋችው ጥፋት የለም። ትክክል ናት። ለእሷ፥ የማታውቀው እንግዳ ሀገርና ህዝብ ውስጥ በመሄድ ጊዜዋን ከምታባክን፥ ጊዜዋ ሳያልፍባት ቶሎ ብላ አብሯት ሊሆን የሚችል ጥሩ ሰውን ከምታውቀውና ዘመንዋን ሙሉ ከኖረችበት ህዝብ መካከል መፈለግን ነው ይሻላል ብላ ያሰበችው። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፥ አብዛኖቻችን በእነዚህ ወጣቶች ቦታ ብንሆን፣ ከኦርፋ የተለየ ነገር የምናረግ አይመስለኝም። ሩትን እኮ ልዩ ያረጋት ሰው የማይመርጠውን መንገድ መምረጧ ነው። የማታውቀው ምድር ለመሄድ፣ በዘመንዋ የማታውቀውን አምላክ ለመከተል፣ ተወልዳ ካደገችበትና ቋንቋውን፣ ህብረተሰቡን፣ ባህሉን ከለመደችው ምድር ወጥታ፥ አንዲት ተስፋዋ የጨለመባት የመሰለችን ሴት ተከትላ በመሄድ ከአዲስ ህብረተሰብና ከአዲስ ባህል ጋር ለመላመድ መወሰንዋ እኮ ነው ልዩ ያረጋት። አንዳንድ ሰዎች ግን አይገርሟችሁም? ሪስክ ለመውሰድ ደፋሮች ናቸው። ለየት ያሉ ምርጫዎች አሏቸው። የብዙሀኑ ምርጫ ተጽእኖ አያሳድርባቸውም። ያመኑበትንም ነገር ለማድረግ ብቻቸውን መቆም አይፈሩም። በሚገርም ሁኔታ ደግሞ ትልልቅ ደረጃ ሲደርሱ የምናያቸው እንደነዚህ አይነት ሰዎችን ነው። አልበርት አንስታይን ያለው አንድ አባባል ትዝ አለኝ። “ተመሳሳይ ነገር እያደረክ የተለየ ውጤት አትጠብቅ ይል ነበር”።

ኦርፋ ኑሀሚንን የመሰናበቻ ሰላምታ ስትሰጣት፥ ሩት ግን ተጠጋቻት ይለናል መጽሀፉ። አንድ ተስፋ የሌላትን ሴት ለመከተል ወሰነች። ህዝቧንና አምላኳን ተቀብላ ለመከተል ወሰነች። የሚገርመው እኮ ደግሞ ሩት የኑሀሚንን አምላክ እግዚአብሄርን ለመከተል የወሰነችው እግዚአብሄር ኑሀሚንን ሲያትረፈርፋት፣ ሲሰጣት፣ ሲባርካት አይታ እንኳን ቢሆን ብዙም ላይገርመን ይችላል። ሩት ያየችው ኑሀሚን ባልዋ ሲሞት ልጆችዋ ሲሞቱና ብቻዋን ስትቀር ነው። ሩት ከኑሀሚን የምትሰማው፣ “ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛል” ስትል ነው። ታዲያ እንዴት የኑሀሚንን አምላክ እግዚአብሄርን ለመከተል አቅም አገኘች? እግዚአብሄርን የሚያስከትል ምን ተስፋ አየች? ምን ብርሀን አየች? እኛ እኮ ታሪኩን በሙሉ አንብበን ስላወቅነው ነው ብዙም የማይገርመን። ሩት ህይወትዋ ወዴት እየሄደ እንደሆነ ምንም የማታውቅ አንድ ምስኪን ሴት ነበረች። ኑሀሚንን ለመከተል የወሰነችው፥ ዛሬ ላይ እኛ የታሪኳን መጨረሻ አውቀን እንደተቀመጥነው፥ ህይወትዋ የሚሄድበትን አካሄድ አውቃ፥ ቦኤዝን እንደምታገባ፣ የዳዊትን ቅድመ አያት ኢዮቤድን እንደምትወልድ፣ የክርስቶስ ዘር ውስጥ እንደምትቀላቀል አውቃ ህይወትዋን ቀድማ አይታ እኮ አይደለም። አንድ ነገር ውስጥ እኮ የሆነ ተስፋ ይዞ መግባትም አንድ ነገር ነው። ህይወቷ በምን ሁኔታ እንደሚጠናቀቅ ፍንጭ እንኳን ሳይኖራት ዝም ብላ ተስፋ የሌላት የመሰለችን ሴት ለመከተል የወሰነች ሰው ናት። ምናልባትም አካባቢዋ ላይ ያሉ ሰዎች “ሩት ምን ነካሽ አንቺ ቆይ? እኔ በእውነት ዝም ብለሽ የማይሆን መንገድ ስትሄጂ እያየሁሽ ዝም ማለት አላስችል ስላለኝ ነው የምመክርሽ:: ለምን ስለራስሽ ህይወት ግን አታስቢም? የሴት ልጅ እድሜ እኮ ቆሞ አይጠብቅም። እስካሁን ልጅ እንኳን አልወለድሽም። እዚሁ ከምታቂው ባህሉን እምነቱን ከለመድሽው ህዝብ መካከል የሚሆንሽን ሰው ብትፈልጊ ነው የሚሻልሽ” የሚሏትም የሚጠፉ አይመስለኝም። ለነገሩ ቢሏትም እኮ ትክክል ናቸው። እውነታቸውን ነው:: ደግሞም ምንም ቢናገሩ ለእሷ ካላቸው ቀና አስተሳሰብ ተነስተው ነው። ግን እኮ አንዳንድ ምክሮች ጥሩ ቢሆኑም፥ ከትልቁ ከእግዚአብሄር ፕሮግራም ጋር ግን አብረው የሚሄዱ አይደሉም። የእኛን ስኬትና ምቾት ብቻ ያካተቱ በህይወታችን ላይ ያለውን ትልልቅ የእግዚአብሄር ሀሳቦች ግን ያላካተቱ፥ ከሰው እይታ አንጻር ሲታዩ ትክክል የሆኑ፣ ከእግዚአብሄር እይታ ደግሞ ሲታዩ ሚዛን የማይደፉ ብዙ ምክሮች አሉ። 

ሩት ሁሉንም ነገር ትታ ከኑሀሚን ጋር ለመሄድ ቆራጥ ሀሳቧን ተናገረች። አንድ ውሳኔ ከወሰነች ንቅንቅ የሚያረጋት የለም። “ኑሀሚን ወደ ህዝቤ እንድመለስ አታስገድጂኝ:: ህዝብሽ ህዝቤ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል። በምትሞቺበት በዚያ እሞታለሁ። በምትቀበሪበትም በዚያ እቀበራለሁ። ከሞት በቀር እኔና አንቺን የሚለየን የለም በማለት አንድ ወንድና ሴት ለመጋባት ሲወስኑ የሚገቡትን አንድ ከባድ ኪዳን ነው የገባችላት። አዎ ብዙ ተስፋ አላቸው ካልናቸው ሰዎች ጋር ቃል መገባባት ምናልባት ቀላል ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ከአንድ ተስፋዋ ከጨለመባት፥ ብቻዋን ከቀረችና ምንም ጥቅም ከማናገኝባት ደካማ ሴት ጋር ግን ካንቺ ጋር እሞታለሁ ብሎ ኪዳን መግባት ማንነትን ይጠይቃል። በቃሎችዋ ውስጥ ማንነትዋ ይታያል። ማን እንደሆነች ያስታውቅባታል። ለነገሩ እኛም ሞኞች ሆነን እንጂ፥ ይሄ ማንነትዋ እኮ ወደ ሆነ የክብር መንገድ እንደሚወስዳት መገመት ነበረብን። ምክኒያቱ ደግሞ እግዚአብሄር ከእንደዚህ አይነት ሰዎች ጋር ወገንተኛ ስለሆነ ነው። ታሪኩን እንዳነበባችሁት፥ ሩት ኑሀሚንን ተከትላ በመሄዷ ከኑሀሚን ያገኘችው ምንም ጥቅም አልነበረም። እንዲያውም በማታውቀው ምድር ወደ ውጪ እየወጣች የሚበሉትን ነገር ይዛ በመምጣት ኑሀሚንን የምትረዳው እሷ ነበረች።  አንድ ቀን ታዲያ እንደለመደችው ምግባቸውን ልትቃርም ወደ ሰዎች እርሻ ውስጥ ስትገባ እግሩዋ መጽሀፍ ቅዱስ “ሀያል ሰው” ከሚለው ከቦኤዝ እርሻ ጋር ይጥላታል። ቦኤዝም ይቺ የማን ቆንጆ ናት ብሎ ሰዎችን ቢጠይቅ “ይቺ እኮ ኑሀሚንን ተከትላ የመጣችው ሩት ናት”:: ሩት ማንነትዋ በሙሉ በእስራኤል ከተማ ሲወራ ኖራል ቦኤዝ ስለ ማንነትዋም ሆነ ለኑሀሚን ስላደረገችላት መልካምነት ከእስዋ አንደበት መስማት አላስፈለገውም። “ሩት ለኑሀሚን ያሳየሽውን መልካምነት በሙሉ ሰምቻለሁ። እግዚአብሄር እንደ ስራሽ ይስጥሽ። ከክንፉም በታች መጠጊያ እንድታገኚ በመጣሽበት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሄር ዘንድ ደሞዝሽ ፍጹም ይሁን። ለመቃረም  ወደ ሌላ ቦታ እንዳትሄጂ፣ የእኔን ሰራተኞች ተጠጊ፣ ተከተያቸው። ከዚህ ከእኔ እርሻ ውሰጂ። ውሀ ባስፈለገሽ  ጊዜ ወደ ማድጋው ሄደሽ እነሱ ከቀዱት ውሀ ጠጪ። በምሳ ጊዜ ደግሞ ወደዚህ ቅረቢና ብዬ” ቢላት በግምባርዋ ወድቃ በልቧ ውስጥ ያለውን አክብሮት ገለጸችለት። ሩት ሰው አክባሪ ናት ። የሩት ሰው አክባሪነት የጀመረው ግን ቦኤዝ ጋር ሲደርስ አይደለም። የጀመረው ኑሀሚን ጋር ነው። ቦኤዝ ጋርም ያደረሳት መጀመሪያ ለኑሀሚን ባሳየችው አክብሮት ውስጥ የሄደችበት መንገድ ነው። ቦኤዝ በራስዋ ጥበብና ብልጣ ብልጥነት ያገኘችው ሰው ሳይሆን፣ መልካምነትን ለማሳየት በሄደችበት መንገድ ላይ የተጠበቀላት ሰው ነው። የራሳችንን ጥቅም ትተን ለሰዎች መልካምነትን ለማሳየት በምንከፍላቸው ዋጋዎች ሁሉ ውስጥ ለእኛ ብቻ የሚጠበቅልን በረከት አለ። የይስሀቅ ሚስት የሆነችው የርብቃ ታሪክም እኮ ልክ እንደዚሁ ነበር። ርብቃ ልክ እንደወትሮዋ ውሀዋን ለመቅዳት በወጣችበት ቀን ነው ለይስሀቅ ሚስት ለመፈለግ የመጣው የአብርሀም ሎሌ ያገኛት። ውሀ አጠጪኝ ሲላት ከጥያቄው በስተጀርባ ያለውን ድብቅ በረከት እኮ እሷ አታውቅም። እስዋ ይሄንን ሰው ለመርዳት ከቀን ለቀን ስራዋ ወጣ ብላ እሱን ብቻ ሳይሆን ግመሎቹንም ለማጠጣት ያሳየችውን መልካምነት ብቻ ነው የምታውቀው። 

የሩትን ህይወት አካሄድ እንደተመለከትነው፥ በአንድ ወቅት ከባልንጀራዋ ከኦርፋ ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የነበረች፥ ልክ እንደ ባልንጀራዋ እንደ ኦርፋ እሷም እንዲሁ ባልዋን በወጣትነትዋ ያጣች፣ በሀዘን ውስጥ ያለፈች፣ ኦርፋ ተወልዳ ያደገችበት ምድር ውስጥ ተወልዳ ያደገች ተመሳሳይ የህይወት አካሄድ የነበራት ሰው ነበረች።  ነገር ግን የኦርፋ ታሪክ ከማንኛውም ኪዳን ከሌለው ሞአባዊ ሰው ያልተለየ ታሪክ ሆኖ ሲያልፍ፣ የሩት ህይወት ግን መጀመሪያ ላይ ተስፋ ያጣ ይምሰል እንጂ፥ አጨራረሱ ግን ዘላለም የሚወራ ታሪክ ሆኖ ማለቁ፣ መንገድዋ ላይ ይመጣሉ ብላ ካልጠበቀቻቸው በረከቶች ጋር መገናኘቷ፣ ዘሯ ኪዳን ከሌለው ዘር ተነስቶ “በትረ መንግስት ከይሁዳ ነገድ አይጠፋም” የተባለለት ነገድ ውስጥ መግባቱ በጣም አስደናቂ ነገር ነው። እነዚህ በአንድ ወቅት ላይ ተመሳሳይ ቦታ ላይ የነበሩ ወጣት ሴቶች ህይወታቸውን ልዩ ልዩ ያደረገው የመረጡት የህይወት ምርጫ ብቻ ነው። አንዳንዴ ህይወት ላይ የምንመርጣቸው ምርጫዎች የሚወስዱን መንገዶች የሚገርሙ ናቸው። ኦርፋ ኑሀሚንን የመሰናበቻ ሰላምታ ከሰጠቻት በኋላ፣ ታሪኳም እንዲሁ ከመጽሀፉ ውስጥ ተሰናብቶ ከዚያ በኋላ ስለገጠማት የህይወት ታሪኳ የተጻፈ አንድ ነገር እንኳን የለም። ሩት የሚለው መጽሀፍ ግን የተጻፈው ሩት በመረጠቻቸው የህይወት ምርጫዎች ምክኒያት ነው። መጽሀፉ የሚተርከው ሩትና ህይወትዋ ላይ የመረጠቻቸው ምርጫዎች ስለወሰዷት የክብር መንገዶች ነው። አንዳንድ ምርጫዎች ዝም ብለው ይገርሙኛል። አንዳንድ ህይወት ላይ ያሉ ምርጫዎች የሚወስዱን መንገዶች ይገርሙኛል። ወደድንም ጠላንም ህይወታችን በየቀኑ በምንመርጣቸው ምርጫዎች ተጽእኖ ስር የወደቀ ነው። መቆጣጠር የምንችለው የምንመርጣቸውን ምርጫዎች እንጂ እነዚህ ምርጫዎቻችን ህይወታችን ላይ የሚያመጡትን በጎም ሆነ መጥፎ ተጽእኖዎች መምረጥ አንችልም። የሩትን ህይወትና የመረጠችው ምርጫ የወሰዳትን መንገዶችና ህይወቷ ላይ ያመጣውን በረከቶች አንብቤ ዝም ብዬ እየተገረምኩ፥ ሀሳቦችን አውጥቼ አውርጄ ብዙ ካሰብኩ በኋላ፥ እግዚአብሄርን አንድ ጥያቄ ጠየኩት። “እግዚአብሄር ሆይ ታዲያ ህይወታችን ላይ በየጊዜው ለምርጫ የሚቀርቡልን ብዙ መንገዶች አሉ። በረከት ያለባቸው መንገዶች የትኞቹ እንደሆኑ በምን እናውቃለን? ብለው እግዚአብሄር መለሰልኝ እንዲህም አለኝ። “የምትመርጫቸውን ምርጫዎች በሙሉ ከፍቅርና ከመልካምነት ተነስተሽ ምረጪ። በእነዚህ መንገዶች ውስጥ ላንቺ ብቻ የተጠበቀ በረከት አለ አለኝ። ሩት የራስዋን ጥቅም ፍጹም ባለማሰብ ለኑሀሚን ያሳየችው ፍቅር የወሰዳት መንገድ ነው ከበረከቶችዋ ጋር ያገናኛት” ብሎ መለሰልኝ። ሩት ከቦኤዝ የዳዊትን ቅድመ አያት ኢዮቤድን ወለደች። ሴቶችም ኑሀሚንን መጥተው “ዋርሳ ያላሳጣሽ እግዚአብሄር ይባረክ ስሙም በእስራኤል ይጠራ። ከሰባት ወንዶች ልጆች ይልቅ ለአንቺ ከምትሻልና ከምትወድሽ ምራት ተወልዶአልና” አሏት።  

መዳኔ

መዳኔ

ስኬት

ስኬት