Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ይሉኝታ

ይሉኝታ

ቃሉ ከህይወታችንና ከአካባቢያችን የራቀ አይደለም። ሁላችንም በአንድም ሆነ በሌላ የይሉኝታ ስሜት ተሰምቶን ያውቃል። ሰው ስለእኛ የሚለው ነገር፥ ሰው ስለ እኛ የሚያስበው ነገር ያሳስበናል። ብዙ ጊዜ ማድረግ የምንፈልጋቸውን ነገሮች፥ ሰዎች ምን ይሉኛል ብለን ፈርተን ሳናረጋቸው ቀርተን እናውቃለን። ማድረግ የማንፈልጋቸውን ነገሮች ደግሞ ሰው ምን ይለኛል ብለን ፈርተን አርገናቸው እናውቃለን። የእኛ ሀገር ባህል ደግሞ ጥሎበት ከይሉኝታ ጋር እጅግ በጣም የተሳሰረ ነው። “ይሄንን ነገር ብታረጊው ሰው ምን ይልሻል?” ወይንም “ሰው ምን ይልሀል?” መባባልን  እናዘወትራለን። አነጋገራችን፣ አለባበሳችን፣ ድርጊቶቻችንና ውሳኔዎቻችን በሙሉ ሰው የሚለውን ነገር በመፍራት ተጽእኖ ስር የወደቁ ናቸው። ሰው ቤት ሄደን ሆዳችን በረሀብ እየጮኸ “የምሬን እኮ ነው የምልሽ አሁን አሁን እኮ ነው በልቼ ጠጥቼ የመጣሁት” ብሎ መዋሸት የባህላችን አንዱ ክፍል ነው። ሰዎቹም ብሉ ብለው አብዛኛውን ጊዜ ሲጋብዙን፥ ብሉ ባይሉን የምንላቸውን ነገር ፈርተው፥ እኛም አንበላም ብለን የምንከራከረው ወዲያውኑ እሺ ብለን ብንበላ ሰዎቹ የሚሉንን ነገር ፈርተን ነው። ሌላ ምክኒያት ይኖረው ይሆን? ከሁሉ ደግሞ በጣም የሚያስቀኝና ፈገግ የሚያረገኝ፥ ከሰዎች ጋር ሱቅ ሄደን የምንፈልጋቸውን እቃዎች ሁሉ ወስደን የመክፈያው ቦታ ስንደርስ፣ ወይንም ደግሞ ሬስቶራንት ሄደን በልተን የምንከፍልበት ሰአት ሲደርስ የምንጀምረው ክርክር ነው። ግዴታ ባህላችን ስለሆነ መከራከር ያለብን ይመስላል። “እኔ ነኝ የምከፍለው። እኔ ነኝ የምከፍለው ስልሽ ተይ በናትሽ አንቺ እኔ አይደለሁ እንዴ እንብላ ብዬ ሀሳቡን ያመጣሁት። ኸረ ስርአት ያዢ” ብለን በቃላት ክርክሩን እንጀምረውና ልክ ገንዘቡን የሚወስደው አስተናጋጅ ሲመጣ፥ መታገል እንጀምርና ልንደባደብ እንደርሳለን። ምንድነው ቆይ? ለመክፈል ያለን ፍቅር ነው እንዳንል፥ አይደለም። ቤቱ ከገባ በኋላ እሰይ ዛሬ የሁሉንም ሰው እኔ ነኝ የከፈልኩት ብሎ ከልቡ የሚደሰት ሰው የለም። እንዲያውም በሰዎቹ ፊት ልክፈል ብሎ ሲከራከር የቆየው ሰው፥ ቤቱ መቶ ስላወጣው ተጨማሪ ወጪ “ዛሬ መቼም ብሬን ጨፈጨፍኩት” ብሎ ያስባል እንጂ። ጊዜው ትንሽ ቆየት ቢልም አንድ ያጋጠመኝን ገጠመኝ ልንገራችሁ። ከጓደኞቼ ጋር አንድ ሬስቶራንት ገብተን በልተን ከጨረስን በኋላ የመክፈያው ሰአት ሲደርስ፥ እኔ ነኝ የሁሉንም ሰው የምከፍለው ብዬ ያዙኝ ልቀቁኝ አልኩ። ብዙ ከተከራከርኩና ከተደባደብኩ በኋላ ቦርሳዬን ለመፈተሽ ጎንበስ ስል፥ የምከፍልበትን ካርድ ረስቼ እንደመጣሁ ካወኩ በኋላ የገባሁበትን ሼም ልነግራችሁ አልችልም። ነገሩን ሳስበው አንዴ ሳቄ ይመጣል። አንዴ ሼም ይይዘኛል። አሁን አሁን ግን ያንን አጋጣሚ ባስታወስኩት ቁጥር እንኳንም ካርዴን ረሳሁት እላለሁ። አሁን ላይ በይሉኝታ የማረጋቸው ነገሮች በሙሉ ቤቴ ከመጣሁ በኋላ ያናድዱኛል። ሀበሻ ስለሆንኩ የይሉኝታ ስሜት ቢዋጋኝም፥ ስሜቱን አሸንፌ ማድረግ ያለብኝን ነገሮች ለማድረግ፥ ማድረግ የሌለብኝን ነገሮች ደግሞ ላለማድረግ የተቻለኝን ሁሉ ጥረት አደርጋለሁ። ለሰዎቹ አዝኜ፣ ገንዘብ ስለሌላቸው ልረዳቸው ፈልጌ በርህራሄ ተነሳስቼ ስለማረጋቸው ነገሮች በሙሉ ሰዎች አወቁልኝም አላወቁልኝም ከእግዚአብሄር ዘንድ ብድራትን አገኝባቸዋለሁ። እግዚአብሄርን ደስ አሰኝባቸዋለሁ። ሰው የሚለኝን ፈርቼ ወይንም በሰዎች ዘንድ ጥሩ፣ መልካምና ደግ ሰው ለመባል የማረጋቸውን  ነገሮች ግን በእግዚአብሄር ዘንድ ግብዝ ያረጉኛል። ወይ እግዚአብሄርን አላስደሰትኩበት ወይ ገንዘቤን በአግባቡ አልተጠቀምኩበት። ካከበረኝማ በስውር ልቤን ፈትኖ ኩላሊቶቼን መርምሮ የሆንኩትን ካልሆንኩት ለይቶ ትክክለኛና በሰው የማይታየውን ማንነቴን በራሱ ሚዛን ላይ መዝኖ ከጨረሰ በኋላ ባዘጋጀልኝ የክብር ወንበር ላይ የሚያስቀምጠኝ እግዚአብሄር እራሱ እንጂ እኔ በሰው ፊት ስሜን ለመጠበቅ ወይንም ራሴን ለማክበር የማረጋቸው ነገሮች የዘላለም ብድራታቸው ምንድነው? የእውነት ሰውን የመርዳት ፍቅር ከሆነ ያለኝ፣ ሰዎቹን ልክፈልላቹ ብዬ ከእነርሱ ጋር ከምከራከር፥ ስንት የሚበላው ምሳ አጥቶ መንገድ ላይ የወደቀ ሰው በሞላበት ሀገር አይደል እንዴ የተወለድኩት? ለምን እነሱን አልረዳም? እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኝ አምልኮ ነው ተብሎ ስለተጻፈ ለምን በስውር ወላጅ የሌላቸውን ህጻናት በመርዳት ንጹህ የሆነ፥ ነውርም የሌለበት የተባለውን አምልኮ ለምን አላመልክም? ትልቅ ዋጋና ብድራት ያለው እኮ ያ ነው። ገንዘብ ያላቸውን ሰዎችማ ማንም ሰው ይጋብዛቸዋል። መንገድ ላይ የተጣሉትን ግን ማን ያስታውሳቸዋል? 

ከቀን ለቀን ኑሮአችን ጀምሮ እስከ ትልልቅ ነገሮች ድረስ ውሎአችንና አዳራችን በይሉኝታ የተሞላ ነው። ሰውን በጣም እንፈራለን። ሰው የሚለን ነገር በጣም ያሳስበናል። ሰው ስለእኛ የሚያስበው ነገር ያስጨንቀናል። ከዚህም የተነሳ በሰዎች ፊት ፍጹም መስለን፣ ደግ መስለን ለመመላለስ መክፈል ያለብንን ዋጋ ብቻ ሳይሆን መክፈል የሌለብንንም ብዙ ዋጋዎች እንከፍላለን። ይሉኝታ የሚለውን ቃሉን እራሱ ስታስቡት “ሰዎች የሆነ ነገር ይሉኝ ይሆን?” የሚልን የፍርሀት ስሜትን ውስጡ የያዘ ነው። ይሉኝታ ሰውን ከመፍራት ጋር፥ ሰው ስለ እኛ የሚለውን ነገር ከመፍራት ጋር በቀጥታ  የተያያዘ ነገር ነው። የይሉኝታ አስከፊ ነገሩ ደግሞ ሰዎችን ከእግዚአብሄር በላይ እንድንፈራቸው ማድረጉ ነው። እግዚአብሄርን የመፍራት ተቃራኒው እግዚአብሄርን አለመፍራት ብቻ አይደለም። እግዚአብሄርን የመፍራት ተቃራኒው ሰውን መፍራትም ነው። ሰውን በጣም እየፈራን ስንመጣ፥ ወደድንም ጠላንም እግዚአብሄርን ከመፍራታችን ሰውን መፍራታችን እየበለጠ ይመጣል። ህይወታችን እግዚአብሄርን በመፍራት መመራቱን ያቆምና ሰውን በመፍራት መመራት ይጀምራል። ሰው የሚኖረው ደግሞ በዚያ በጣም በሚፈራው ነገር ተጽእኖ ስር ነው። የምንፈራው ነገር፥ እኛን ባሪያ አድርጎ የመግዛት አቅም አለው። ያ የምንፈራው ነገር እኛን በወደደው መንገድ የመምራት አቅም አለው። ይሄ ልባችን ውስጥ ያለው ፍርሀት መሆን ያለብንን ነገሮች እንዳንሆን፣ ወይንም ከተወሰነ ክልል ውጪ ወተን ማድረግ ያለብንን ነገሮች እንዳናደርግ የሚያሰምርልን መስመር አለ። ህይወታችንን የመግዛት አቅም አለው። እግዚአብሄርን በጣም የሚፈራ ሰው ልቡ ውስጥ ትልቅ የሆነበት እግዚአብሄር ብቻ ነው። ስለዚህ ህይወቱ እግዚአብሄርን በመፍራት ስር ነው። የሚያረጋቸውን ነገሮች ሁሉ የሚያደርገው የሚወስናቸውን ነገሮች በሙሉ የሚወስነው ከሚፈራው ከእግዚአብሄር ተነስቶ ነው። ሰውን የሚፈራ ሰውም ምንም ነገር ሲያረግም ሆነ ለማረግ ሲያስብ ነገሩን የሚወስነው፥ ሰዎች ከሚሉት ነገር ተነስቶ ነው። ህይወቱ ላይ የሚወስናቸው ነገሮች ሰዎችን በመፍራት ተጽእኖ ስር ናቸው። ቀድሞ የሚያስበው ነገሩን ቢያደርገው ሰዎች ስለሚሉት ነገር ነው። አስተውላችሁ ከሆነ፥ ብዙ ጊዜ ሀጢያትና እግዚአብሄር የማይከብርባቸውን ነገሮች ስናረግ ሰዎች እንዳያዩ ወይንም እንዳያውቁ ተደብቀን ወይንም ከሰዎች ራቅ ብለን ነው የምናረገው። ነገራችንንም በተቻለን መጠን ደብቀን በሚስጥር ነው የምይዘው። ነገሩን በስውር ስናረገው እግዚአብሄርን አንፈራውም። ያረግነውን ግን በሆነ አጋጣሚ እንኳን ለመናገር ሰዎች የሚሉንን ነገር እንፈራለን። ነገሩን ስናረገው፥ በእኛ ላይ ስልጣን ያለውን ማዳንም መግደልም የሚችለውን፣ ከገደለ በኋላ ደግሞ ወደ ገሀነም ለመጣል ስልጣን ያለውን እግዚአብሄርን አንፈራውም። ያረግነውን ነገር ለመናገር ግን በህይወታችን ላይ ምንም የማድረግ ስልጣን የሌለውን ሰውን እንፈራለን። የድሮ ክርስቲያኖች በሆነ ነገር እግዚአብሄርን ሲያሳዝኑ፥ ከሰው ፍርሀት የእግዚአብሄር ፍርሀት ቢብስባቸው፥ ሰው ሁሉ በተሰበሰበበት ጉባኤ መድረክ ላይ ወጥተው በዚህ በዚህ ጉዳይ እግዚአብሄርን አሳዝኜዋለሁ ብለው ያረጉትን በእግዚአብሄር መንፈስና በእግዚአብሄር ህዝብ ፊት በመናዘዝ፣ ንሰሀ በመግባትና ህዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ ድፍን ጉባኤው ከጸለየላቸው በኋላ፥ ተፈተውና ተፈውሰው  ወደ ቤታቸው ይሄዱ እንደነበር ሰምቻለሁ። በዚያ ጊዜ በጣም የሚፈራው የእግዚአብሄር ህልውና ነበር። በጣም የሚፈራው ሰው አልነበረም። በጣም የሚፈራው ሰው የሚለው ነገር አልነበረም። ከዚህም የተነሳ የእግዚአብሄር ክብር በመካከላቸው በሙላት እንደነበርና የእግዚአብሄር መንፈስ በብዙ ሀይል በሚታይ በሚጨበጥና በሚዳሰስ ሁኔታ በመካከላቸው ይሰራ እንደነበር አሁን እንኳን በህይወት ካሉ ብዙ አባቶቻችንና እናቶቻችን አንደበት ሰምተናል። ዛሬ ላይ እኮ እኛ ሰውን እየፈራንና ውጪያችንን ብቻ በማሳመር ፍጹም እየመሰልን፥ ውስጥ ውስጡን ብዙ ነገራችን እየሞተ ነው። ጭንቀታችን ሁሉ ሰው ስለሚያየው ነገር ብቻ ሆነ። በአደባባይ ላይ ራሳችንን እያሳመርን፥ ልክ ክርስቶስ ፈሪሳውያንን ይነቅፍባቸው እንደነበረው ውስጣችን እየሞተ ተቸገርን። ፈሪሳውያንን እኮ ካስታወሳችኋቸው፥ ለኢየሱስ አገልግሎት በጣም ፈተና የነበሩ መንፈሳዊ የሚመስሉ፥ በማእዘን ላይ ሰው ሊያያቸው በሚችልበት ቦታ ላይ ቆመው ቃል የሚያነቡ፥ በልባቸው ላይ ግን እግዚአብሄር ያልከበረባቸው። ጭንቀታቸው ሁሉ ሰው ስለሚያየው ነገር የሆነ፥ የስውር ህይወት የሌላቸው፥ ሰው የሚያየው እንጂ እግዚአብሄር የሚያየው ህይወት የሌላቸው፥ በሰው ዘንድ ሊያገኙ ስለሚችሉት ክብር ብቻ የሚጨነቁ፣ የሀይማኖት መልክ ያላቸው፣ የሀይማኖቱን ስርአት ጠንቅቀው የሚያውቁና የሚከተሉ፣ በሰው ስርአት ውስጥ ብቻ የሚኖሩ ግንኙነታቸው ከሰው ጋር ብቻ የሆነ እግዚአብሄር ግን የማያውቃቸው ሰዎች ነበሩ። ለትምህርታችን በቃሉ ላይ እንደተጻፉልን፥ ከህይወታቸው ልንማር የምንችለው በጣም መጨነቅ ያለብን ሰው ስለሚያየው ነገራችን እንዳልሆነ ነው። በጣም መጨነቅ ያለብን ሰዎች ስለ እኛ ስለሚሉት ነገር አይደለም። እግዚአብሄር ስለሚለው ነገራችን ነው። በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ከህይወታቸው እንማር ዘንድ የተጻፉልንን እግዚአብሄር በህይወታቸው የሰራባቸውና የተጠቀመባቸው፥ሰዎች እነ አብርሀም፣ እነ ሙሴ፣ እነ ዳዊት፣ እነ ኤልያስ፣ እነ ኢያሱ እና እነ ጳውሎስ እነዚህ ሁሉ፥ ከውጪ ማንነታቸው ይልቅ ለውስጥ ማንነታቸውና እግዚአብሄር ብቻ ለሚያየው ነገራቸው ዋጋ የከፈሉ፣ ሰውን ለማስደሰት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሄርን ለማስደሰት የኖሩ ሰዎች ናቸው። 

እግዚአብሄርን መፍራት ማለት፥ ሀያ አራት ሰአት በእርሱ እይታ ውስጥ መሆናችንን ማሰብ ማለት ነው። አንድ በእድሜ ከእኛ ተለቅ ያለ ሰው እንኳን እኮ አጠገባችን ካለ፥ ንግግራችን፣ አቀማመጣችን ሁሉ ነገራችን በሙሉ ለዚያ ሰው ካለን አክብሮት ጋር የተያያዘ ነው የሚሆነው። በዚያ ሰው እይታ ውስጥ እያለን ልክ ብቻችንን እንደሆንን እንደፈለግን ካወራን፣ እንደፈለግን ከተቀመጥን እንደፈለግን ከሆንን የዛ ትልቅ ሰው አጠገባችን መኖር ምንም ስሜት ካልሰጠን ያንን ሰው አንፈራውም አናከብረውም ምናልባትም ንቀነዋል ማለት ነው። የዮሴፍን ህይወት ካስታወሳችሁት ያቺ ግብጻዊት ሴት ሰውን በጣም ስለምትፈራ፥ ሰው የሌለበትን ሰአት ጠብቃ ስለ ሀጢያት ማውራት ስትጀምር፥ ዮሴፍ ግን የሰዎች መኖርና አለመኖር ልቡን ሲይዘው አይታይም። ነገር ግን “በእግዚአብሄር ፊት እንዴት ሀጢያትን እሰራለሁ ሰው ኖረም አልኖረም ሁልጊዜ በእግዚአብሄር እይታ ውስጥ ነኝ” አለ። ይሄ በስውር ያከበረው እግዚአብሄር ታዲያ፥ ጊዜውን ጠብቆ በግልጽ በአደባባይ በመላው ሀገር እና ህዝብ ላይ ዮሴፍን ሲያከብረው እናያለን። እግዚአብሄርም አለ “ያከበሩኝን አከብራለሁና የናቁኝም ይናቃሉና ይህ አይሆንልኝም።” ለዮሴፍ፥ የሰው መኖርና አለመኖር በእግዚአብሄር ፊት ማድረግ ያለበትን ትክክለኛ ነገር ላለማድረግ ተጽእኖ አልፈጠረበትም። እግዚአብሄር ደግሞ ልቡ ያለው እዛ ሰአት ጋር ነው። ሰው በማያየን ሰአት እኛ ማነን? ማንም ሰው አካባቢያችን ላይ በሌለ ሰአት፣ ጭር ባለበት ሰአት፣ ሰዎች በዙሪያችን በሌሉ ሰአት እኛ ማነን? ዳዊትም በመጽሀፉ ላይ ሲናገር አለ:: “በሌሊት ጎበኘኸኝ ልቤንም ፈተንከው እንዳለው፥ በለሊት እግዚአብሄር ልባችንን ይፈትናል። ሌሊት ሲሆን፣ ጨለማ ሲሆን፣ ጨለማ ስለሆነ የወደድነውን ለማረግ ከሰዎች መሰወር በምችልበት ሰአት፣ ሰው ሁሉ ተኝቶ አየሩ ጸጥ ባለበት ሰአት፣ ምንም አይነት የኮሽታ ድምጽ በሌለበት ሰአት እግዚአብሄር ልባችንን ለመፈተን ወደ እኛ ይመጣል። ልባችንን በራሱ ሚዛን ላይ ያስቀምጠዋል። መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፉልን ምሳሌዎች ውስጥ እግዚአብሄር አርግ ብሎ ያዘዘውን ነገር እንዳይታዘዝ ሰውን መፍራት አሰናክሎት ከእግዚአብሄር ፊት ስለተጣለና በህይወቱ ያስጀመረውን የክብር መንገድ ሳይጨርስ በሚያሳዝን ሁኔታ ከእግዚአብሄር ሀሳብ ስለወጣ አንድ ሰው ጥቂት ነገር እንበል። ንጉስ ሳኦል። አንድ ጊዜ ነው አማሌቃውያን የተባሉትን የእግዚአብሄር ህዝብ ጠላቶች ፈጽሞ እንዲያጠፋ እግዚአብሄር ያዘዘው። አማሌቃውያን የእስራኤል ህዝብ ከግብጽ ሲወጡ በመንገድ ላይ ትልቅ ተግዳሮት የነበሩ ህዝቦች ነበሩ። ነገሩ ካለፈ ከብዙ አመታቶች በኋላ፥ በህዝቡ ቀልድ የማያውቀው እግዚአብሄር ለካ ሊበቀላቸው ጊዜ እየጠበቀላቸው የነበሩ፥ የበቀል ፍርድ ከእግዚአብሄር ዘንድ የወጣባቸው ህዝቦች ነበሩ። አይገርማችሁም! እግዚአብሄር እኮ ተበቃይ ነው። የህዝቡን ጠላቶች እንደ ራሱ ጠላቶች ቆጥሮ ሊበቀል ይነሳል። ጠላቶቹን ሊበቀል ደግሞ ጊዜን ይጠብቃል። አማሌቅን ለመበቀል እግዚአብሄር ሲነሳ፥ እንኳን ህዝቡን ቀርቶ ግመሎቻቸውን፣ በጎቻቸውንና አህያዎቻቸውን እንኳን ሊምር አልወደደም። ታዲያ እግዚአብሄር ለዘመናት በልቡ የያዘውን የህዝቡን ጠላቶች የመበቀል አላማ ለመፈጸም ያሰበው በንጉስ ሳኦል ነበር። ንጉስ ሳኦልም ይሄንን የእግዚአብሄር ሀሳብ ቢረዳም “ፈጽመህ አማሌቅን አጥፋልኝ” በተባለው መሰረት ፈጽሞ ያለማጥፋቱና ያለመታዘዙ ምክኒያት ሰዎችን መፍራት እንደሆነ በአንደኛ ሳሙኤል ምእራፍ 15:24 ላይ ራሱ በግልጽ ይናገራል። ሳኦል ከእግዚአብሄር ይልቅ ሰውን ይፈራ ነበር። እግዚአብሄር ከሚሰጠው ክብር ይልቅ ሰዎች ስለሚሰጡት ክብር ይጨነቅ ነበር። ከዚህም የተነሳ ሳሙኤል እግዚአብሄርን ስለመበደሉ ሲነግረው፣ “አዎ እውነት ነው በድያለሁ፥ ነገር ግን በህዝቡ ሽማግሌዎች ፊት አክብረኝ” ብሎ ሳሙኤልን ሲለምነው እናያለን። እግዚአብሄርን ከመበደሉ በላይ፣ ያስጨነቀው በሰዎች ፊት ሊያጣ የሚችለው ክብር ነበር። እውነተኛ ንሰሀ ግን፣ ከእግዚአብሄር ዘንድ ስለምናጣው ነገር ፈርተን የምንገባው አይደለም። ልክ ዳዊት አንተን ብቻ በደልኩ ብሎ ልቡ እንደተሰበረ፥ እግዚአብሄርን ስለመበደላችን ብቻ ልባችን ተሰብሮ እግዚአብሄር ሌሎች ነገሮችን እንዳይወስድብን ሳይሆን፣ ብዙ የንግስና ክብር እያለው፣ ብዙ ሊወሰድብኝ ይችላል ብሎ ሊፈራ የሚችልበት ነገር እያለው፣ ቅዱሱ መንፈስህን እራስህን፣ ህልውናህን ግን እንዳትወስድብኝ ብሎ እንደለመነው፥ እግዚአብሄርን ብቻ እሱን እንዳናጣው በመፍራት ነገሩን ደግመን ላለማረግ ወስነን የምንገባው ነገር ነው። ሰዎችን የመፍራት ትልቁ አደጋ  እግዚአብሄር ያዘዘንን ነገሮች፣ እግዚአብሄር በህይወታችን ሊሰራ ያሰባቸውን ነገሮች እንዳናደርግ ትልቅ መሰናክል የመሆን አቅም አለው። ሳኦል በዚህ ምክኒያት ከጀመረው ትልቅ የክብር መንገድ እንደወጣ፣ ካላስተዋልንና እግዚአብሄር ካልረዳን፣ ሰውን በመፍራት፥ ከትልቁ ከእግዚአብሄር ሀሳብ ልንወጣ እንችላለን። ብዙዎቻችን ትልልቅ አላማ እግዚአብሄር በህይወታችን ላይ አለው ነገር ግን ሰዎችን መፍራት ማድረግ ካለብን ነገሮች አስቁሞን ሊሆን ይችላል። ሁልጊዜ ሰዎችን መፍራት ወደ ልባችን ሲመጣ አንድ ነገር ራሳችንን ማስታወስ መልካም ነው። ሁሉም ነገር ያልፋል። ፍጥረት ሁሉ ያልፋል። እኛ ሰዎችም ብንሆን እናልፋለን። ከዛሬ ሀያ ሰላሳና አርባ አመታቶች በኋላ፥ ብዙዎቻችን ምድር ላይ በህይወት አንኖርም። ዛሬ ላይ ግን የምናገለግለው የእግዚአብሄር ሀሳብና ፈቃድ ለዘላለም ይኖራል። በቅርቡ በእግዚአብሄር ፊት ስንቆም፣ ላልታዘዝነው የእግዚአብሄር ሀሳብ ሰዎችን መፍራታችን በእግዚአብሄር ፊት ምክኒያት ሆኖ የመቆም አቅም የለውም። ሁሉም በተሰጣቸው መክሊቶች ሲያተርፉ፣ አንድ መክሊት የተሰጠው ሰው ፈርቼ መክሊቴን ቀበርኳት እንዳለው ብንልም ምክኒያት መሆን አይችልም። መታዘዛችን ውስጥ ብዙ የእግዚአብሄር ሀሳብ አለ። መታዘዛችን ውስጥ፥ ብዙ የሚጠቀሙ የሚገለገሉ ሰዎች አሉ። ከመታዘዛችን ጀርባ ብዙ የሚድኑ፣ የሚፈወሱና የሚጽናኑ ሰዎች አሉ። ይሄ እንዳይሆን ግን ሰዎች የሚሉንን መፍራት እንዳያስቆመን ሁልጊዜ መጸለይም መጠንቀቅም ይኖርብናል። 

ምስጋና 

ምስጋና 

ትላንትና

ትላንትና