ትላንትና
ብቻዬን ሆኜ ጊዜ ለማሳለፍ እድል በማገኝባቸው ጊዜያቶች፥ ደስ ከሚለኝ ነገሮች አንዱ፥ ወደ ኋላ ሄጄ ያለፈውን ታሪኬን ማሰብ ነው። ማሰብ ደስ ይለኛል። ዝም ብሎ ማሰብ። ገና ከመወለዴ ጀምሮ እናቴ ስለእኔ ከነገረችኝ ታሪኮች አንስቼ ልጅነቴን፥ እንዲሁም ህይወቴ ያለፈባቸውን መንገዶች በሙሉ አስባቸዋለሁ። ያደኩባቸውን ቦታዎች፥ ልጅነቴ ያለፈባቸውን መንገዶች በሙሉ ወደ ኋላ ሄጄ ሳስብ፥ በእግዚአብሄር ፍቅር እንዲሁም በእያንዳንዱ ወቅቶቼ ውስጥ በበዛው የእግዚአብሄር ጥበቃ እገረማለሁ። ባለማወቅ ወራቶቼ ውስጥ ደግሞ እየተገለጠ የመራኝን የእግዚአብሄርን እውቀት እያሰብኩ አደንቃለሁ። ህይወቴ ላይ ባለፉት ከባባድ ወቅቶች ውስጥ፣ እንዴት አርጎ እንደረዳኝ፣ እንዴት አጠገቤ እንደነበር፣ በራሴ ማለፍ የማልችላቸውን ወቅቶች ሁሉ እንዴት አርጎ እንዳሳለፈኝ፥ ዝርዝር ሁኔታውን እያሰብኩ አመሰግናለሁ። የህይወቴ መንገድ ቀያሽ እራሱ እግዚአብሄር፣ ህይወቴን በምን ውስጥ ቢያሳልፈው የበለጠ ወደ እሱ እንደምጠጋ የሚያውቅ እሱ። በምን ውስጥ ቢያሳልፈኝ እንድማር የሚፈልጋቸውን ነገሮች እንደምማር የሚያውቅ እሱ፥ ለጊዜው ከባድ የመሰሉትን መንገዶች በሙሉ ሰብስቦ፥ ዛሬ ላይ ለሆንኩት ማንነቶቼ መሰሪያ የተጠቀመባቸውን የጥበብ አምላክ እግዚአብሄርን እባርካለሁ። ትላንትናዬን ማሰብ ደስ ይለኛል። ልቤን በምስጋና እየሞላ ከፊት ለፊቴ ያሉትን ዘመናቶች የማልፍበትን አቅም የማገኝበት እምነት ጋር ያደርሰኛል። ነፍሴ ሆይ እኔ የምልሽ፥ እግዚአብሄር ከፈጠረሽ ጊዜ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ፥ እነዚህን ሁሉ አመታቶች ከረዳሽ “ከዚህ በኋላ እኔ ልረዳሽ ስለማልችል ራስሽን ቻይ” ብሎ አምላክ ሀሳቡን የለወጠ ይመስል ስጋት የሚገባሽ ግን ለምንድነው? እሱማ እስከ ሽበት እስከ ሽምግልና ድረስ ላይተውሽ፣ ላይረሳሽና ላይጥልሽ ከራሱ ጋር ተማምሎ ከጨረሰ በኋላ እሱም አልበቃ ቢለው፥ በእጆቹ መዳፍ ላይ እንደቀረጸሽ፥ እጆቹን ባየ ቁጥር ስላንቺ እንደሚያስብ፣ ከእርሱ ጋር የጀመርሽው የፍቅር ኪዳን፥ ለዘለአለም አንቺን የመሸከም አቅም እንዳለው አታውቂም? "
“ነፍሴ ሆይ እግዚአብሄርን አመስግኚ፣ በህይወቴ እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ፥ በምኖርበት ዘመን ሁሉ ለአምላኬ እዘምራለሁ።” (መዝሙረ ዳዊት 146:1)
ይሄ ወደ ኋላ ሄዶ ህይወቴን የማሰብ ልምዴን እንድቀጥልበት ከሚያበረታታኝ ነገሮች አንዱ፥ በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ ከተጻፈው የእስራኤል ህዝቦች ታሪክ የተማርኩት አንድ ትልቅ ትምህርት ነው። የእስራኤል ህዝቦች፥ በእግዚአብሄር የተወደዱ፣ በእግዚአብሄር የተመረጡ፣ ኪዳን ያላቸው ህዝቦች ናቸው። ከእግዚአብሄር ጋር በጣም ብዙ ታሪክ ያላቸው ህዝቦች ናቸው። መቼም የእስራኤልን ህዝቦች ታሪክ በደምብ አምብበነው ከሆነ፥ እግዚአብሄር በዘመናት ውስጥ ለእነርሱ ያሳየውን ፍቅር ሰማይና ምድር እንኳን ሊክዱት አይችሉም። እግዚአብሄር ለእስራኤል ህዝብ ማነው? ብለን ከጠየቅን፣ እግዚአብሄር ለእስራኤል ህዝብ፣ በእነሱና በጠላቶቻቸው መካከል በጽድቅ የፈረደላቸው የጽድቅ ፈራጃቸው ነው። ከፈርኦን ጋር ጦርነት የከፈተበት፣ እስራኤል የበኩር ልጄ ነው፥ ልጄን ልቀቅ ብሎ አባትነቱን ያሳየበት አባታቸው ነው። ምድሪቱን አንበጣ በአንበጣ፣ ተምች በተምች፣ ባህሩን ውሀውን ሁሉ ደም በደም ያደረገበት፥ በበቀልና በቁጣ የወጣበት እግዚአብሄር ለእስራኤል ህዝቦች የጽድቅ ፈራጃቸው ነው። በጠላቶቻቸው ሰፈር ጽኑ ጨለማን አርጎ፣ በእነሱ ሰፈር የደመቀ ብርሀን የሆነላቸው ብርሀናቸው ነው። እግዚአብሄር ለእስራኤል ህዝብ በአንድ ሌሊት የግብጽን በኩር በሙሉ በሞት የቀጣበት፣ የጠላቶቻቸውን መንደር በለቅሶ የሞላበት፣ ለእነሱ ደግሞ ሞገስን የሰጠበት ሞገስና ውበታቸው ነው። የኤርትራንስ ተአምራት ብናነሳ፣ ስሙ የተጠራበትን ህዝብ በደረቅ ምድር ተጠንቅቆ ካሳለፈ በኋላ አይደል እንዴ፥ በግብጽ ምድር የጨፈጨፋቸው ሳያንስ፥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ብሎ ጠላቶቻቸውን በሙሉ በኤርትራ ባህር ውስጥ የጣላቸው! ከነ ሰረገሎቻቸው እኮ ነው በውሀ በመዋጥ ለእስራኤል የማዳን ብርታትና ሀይሉን ያሳየው። “እግዚአብሄር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሄር ነው” የሚለውን ከዚያ በፊት የሰው ልጅ ዘምሮት የማያውቀውን አዲስ ዝማሬ ከእነርሱ ውስጥ ያወጣ፥ እግዚአብሄር እኮ የእስራኤል ዝማሬ ነው። ከፊታቸው ደግሞ እየወጣ ቀን ቀን በደመና፥ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በእሳት አምድ ሆኖ ብቻውን የመራቸው አምላካቸው እግዚአብሄር ነው። በንስር ክንፍ መሸከሙ ሳያስን፣ ሊሽርና ሊለውጠው የማይችለውን ኪዳን የገባላቸው ጽኑ ተስፋቸው ነው። እግዚአብሄር ለእስራኤል፣ ዮርዳኖስን የከፈለ፣ ኢያሪኮን የሚያክል የከተማ ግብም በድምጻቸው ውስጥ አልፎ ያፈረሰ ሀይላቸው ነው። ህግና ስርአትን የተማሩበት፥ እግዚአብሄር አምላክ መሆኑን ያወቁበት ስርአታቸው ነው።
እግዚአብሄር ለእስራኤል ህዝብ ያላሳየው መልካምነት ባይኖርም፥ አብዛኛው ህዝብ ግን የተገባለትን የተስፋ ምድር ሳያይ በምድረበዳ ላይ መቅረቱ ሁላችንንም የሚያሳዝነን ነገር ነው። መቼም ይሄ ህዝብ ከነአንን አለመውረሱ ቢያሳዝነንም፥ ሁልጊዜ ማወቅ ያለብን፥ እግዚአብሄር ከእርሱ የሚጠበቀውን ሁሉ ሳያጓድል ማድረጉን ነው። እንዲያውም የእስራኤልን ህዝብ ስናስብ ቶሎ ብለን ማሰብ ያለብን፥ የእግዚአብሄርን ታማኝነት፥ የእግዚአብሄርን ቃሉን ጠባቂነት ነው። እግዚአብሄር ለእስራኤል ቤት ከተናገረው መልካም ነገር ሁሉ ተፈጸመ እንጂ አንድም አልቀረም ብሎ፥ ቃሉ እራሱ የእግዚአብሄርን ታማኝነት አረጋግጧል። ህዝቡን ልክ እንደተናገረው ወደ ተስፋይቱ ምድር አስገብቷል። የገቡት ግን፣ በእግዚአብሄር ታማኝነት ውስጥ የታሰቡት ግን፥ እንደ እግዚአብሄር ሀሳብ የሄዱት ሰዎች ብቻ ናቸው። በጣም ብዙዎች የተስፋው ምድር ጋር ሳይደርሱ በምድረበዳ ቀርተዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእግዚአብሄር ቁጣ መንገድ ላይ አልቀዋል። ዛሬ የምናየው እግዚአብሄር የተስፋይቱን ምድር አያዩም ብሎ እስኪምል ድረስ ከልቡ ያዘነበትንና የተቆጣበትን አንድ አሳዛኝ ታሪክ ነው። የእስራኤል ህዝብ አጠቃላይ የምድረበዳ ጉዞ አርባ አመት ቢሆንም፥ ከግብጽ ተነስቶ ከነአን ለመድረስ አይደለም አርባ አመት የፈጀባቸው። ከኮሬብ ተነስቶ የተስፋይቱ ምድር ጫፍ ለመድረስ መንገዱ የሚፈጀው አስራ አንድ ቀናቶችን ብቻ ነው። ህዝቡ ታዲያ ይሄንን መንገድ ተጉዞ የከነአን ምድር ጫፍ የሆነችው ቃዴስ በርኔ ጋር ደርሶ እንደነበር መጽሀፍ ቅዱስ በዘዳግም ምእራፍ 1 ላይ ሙሴ ጽፎልናል። ታዲያ ግን የከነአን ምድር ወይንም የተስፋይቱ ምድር ድንበር ላይ ሲደርሱ፥ የተፈጠረ በዘሁልቁ ምእራፍ 14 ላይ የምናገኘው ብዙዎቻችን የምናውቀው አንድ በጣም አሳዛኝ ታሪክ አለ። በዚህ ታሪክ ምክኒያት፥ እግዚአብሄር በጣም በማዘኑና በመቆጣቱ፥ ሊገቡ ከነበሩበት ምድር ተመልሰው ወደ ኋላ በመዞር፥ ለአርባ አመታቶች ምድረበዳ ላይ እንደተንከራተቱ፥ እንዲሁም ለብዙ ዘመናት ሴይር የተባለን አንድ ተራራ ሲዞሩ እንደኖሩ እናነባለን። ዘሁልቁ ምእራፍ 14 ላይ፥ አርባ አመታቶች ሙሉ ምድረበዳ ላይ ለመንከራተታቸው ምክኒያት ስለሆነው ታሪክ እንዲህ ሲል ይነግረናል። ሊገቡባት የነበረውን ምድር እንዲሰልሉ፥ ከአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ የተመረጡ አስራ ሁለት ሰዎች ወደ ተስፋይቱ ምድር ተልከው ነበረ። እነዚህ አስራ ሁለት ሰዎች፥ የተላኩበትን ምድር ለአርባ ቀናቶች ሰልለው ወደ ህዝቡ ከተመለሱ በኋላ፥ ሁለት የተለያየ መረጃዎችን አቅርበው ነበር። ከአስራ ሁለቱ መካከል አስሮቹ፥ “ምድሪቱ የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ናት። ከነአን ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ደግሞ ሃያላንና ጽኑዎች ናቸው። በሀይል ከእኛ ስለሚበረቱ ወደዚህ ህዝብ መውጣት አንችልም። ሰዎቹ ረጃጅም ናቸው። እኛ ደግሞ በአይናችን ግምት በፊታቸው እንደ አንበጣዎች ነበርን” በማለት ሲናገሩ፥ ከተላኩት ሰዎች መካከል ሁለቱ ኢያሱና ካሌብ ደግሞ “የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም ምድር ናት። እግዚአብሄር ወተትና ማር ወደምታፈሰው ወደዚህች ምድር ያስገባናል፥ ምድሪቱንም ይሰጠናል። የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፥ እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ነው። እንደ እንጀራ ይሆኑልናል” ብለው ከአስሩ ለየት ያለ መረጃ አቅርበዋል። እነዚህ ሁለት ሰዎች በከነአን ምድር ውስጥ ያሉትን ሰዎች አስፈሪነት አይተዋል:: ነገር ግን የትኛውም አስፈሪ ነገር፥ እግዚአብሄር የተናገረውን ቃል ከመፈጸም እንደማያስቆመው አምነው ስለነበር፥ ካዩት ነገር በላይ፣ ከተሰማቸው የፍርሀት ስሜት በላይ የተገባላቸውን ተስፋ በሙሉ ልባቸው አምነው ነበር። መቼም ሰዎች እንደ መሆናችን መጠን የፍርሀት ስሜት ሊሰማን አይችልም ብንል ራሳችንን ውሸታሞች እናደርጋለን። የፍርሀት ስሜት ሁላችንንም ይዋጋናል። እግዚአብሄርም ይሄ ውጊያ እንዳለብን፥ ይሄ ስሜት እንደሚሰማን በደምብ ያውቃል። ለዚህም ነው “አትፍሩ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ” እያለ በተደጋጋሚ ቃል የሚገባልን። እምነት ማለት ግን ፍርሀት አለመሰማት ማለት ሳይሆን፥ በውስጣችን ለሚሰማን የፍርሀት ስሜት የምንሰጠው ተቃራኒ ምላሽ ማለት ነው። ፍርሀት አይሰማኝ ልንል አንችልም። እግዚአብሄርም የሚያዝነው የፍርሀት ስሜት ስለተሰማን አይደለም። እግዚአብሄር የሚያዝነው፥ የተሰማንን የፍርሀት ስሜት ስናምነው፥ እርሱ ከሰጠን ጽኑ ተስፋ ይልቅ ስናሰላስለውና ትልቅ ስናረገው ነው። ኢያሱና ካሌብ ልክ እንደ አስሮቹ ከእነርሱ ጋር እንደሄዱት ሰላዮች፥ የተስፋይቱ ምድር ውስጥ ያሉትን ቁመታቸው ረጃጅምና አስፈሪ ሰዎች አይተዋቸዋል። ምድሪቱ ውስጥ ያዩት የሚያስፈሩ ሰዎች ግን እግዚአብሄር የሰጣቸውን ጽኑ ተስፋ አላስጣላቸውም። ተስፋ አላስቆረጣቸውም። ፍርሀታቸው ከእግዚአብሄር ትልቅነት እንዲበልጥ አልፈቀዱም። ስለዚህ ለህዝቡ የተናገሩት “እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ነው፥ እግዚአብሄር ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር ያስገባናል፥ ምድሪቱንም ይሰጠናል። የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ። ጥላቸው ከላያቸው ተገፏል” በማለት የእምነትና የተስፋ፥ እንዲሁም እግዚአብሄር ከሁኔታዎች ይልቅ ትልቅ መሆኑን የሚያስታውስ ቃል ነበር የተናገሩት። የፍርሀት ስሜት ሲሰማን፥ ሁለት ምርጫዎች አሉን። አንዱ የተሰማንን ስሜት ተቀብለንና አምነን፥ ሊሆንብን ስለሚችለው ክፉ ነገር እያሰብን እግዚአብሄር የሰጠንን ተስፋዎች መጣል ሲሆን፥ ሌላኛው ደግሞ ውስጣችን እየተሰማን ላለው የፍርሀት ስሜት ጽኑ እምነት የሞላበት ምላሽ መስጠትና፥ እየደጋገምን ተስፋችንን በማሰብ ማመን ነው። የእግዚአብሄርንም ታማኝነት ማሰላሰል ነው። የጦር እቃችሁን ልበሱ፣ ታጠቁ፣ ቁሙ እያለ በሰፊው መጽሀፍ ቅዱስ ስለ መንፈሳዊ ጦርነት የሚነግረን፥ ስለ ስጋዊ ውጊያ አይደለም። የውጊያው ቦታ አይምሮአችን ውስጥ ሲሆን፥ ዋናው የጠላቶቻችን አላማ ደግሞ፥ ውስጣችን ያለውን የከበረ እምነት ማስጣል ነው። ምክኒያቱም እምነታችን፥ የእግዚአብሄርን ክብር የምናይበት፥ ወደ ተስፋችን የምንገባበት፥ የእግዚአብሄር ልጆች ከመሆን አንስተን፣ እስከ ትንንሽ ጉዳዮች ድረስ ብዙ ተአምራቶችን የምናይበት ትልቅ የእግዚአብሄር ስጦታ ስለሆነ ነው።
በሚያሳዝን ሁኔታ ግን የእስራኤል ህዝብ ከኢያሱና ከካሌብ ቃል ይልቅ የአስሩን ቃል አምነው፥ “ምነው በግብጽ ምድር ሳለን በሞትን ኖሮ፣ ወይንም በምድረበዳ ላይ በሞትን ኖሮ፥ እግዚአብሄር በሰይፍ እንሞት ዘንድ ወደዚህች ምድር ለምን ያገባናል? ወደ ግብጽ መመለስ አይሻለንምን? እንዲያውም ኑ አለቃ እንሹምና ወደ ግብጽ እንመለስ ብለው ሲናገሩ። እግዚአብሄር እጅግ በጣም ተቆጥቶ፥ አንድ የሚገርም ነገር ሙሴን ሲለው እዛው ዘሁልቁ ምእራፍ 14 ላይ እናነባለን። እግዚአብሄርም አለ “ይህ ህዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? በፊቱስ ባደረግሁት ተአምራት እስከ መቼ አያምንብኝም?” አለ። እግዚአብሄር ፍርሀታቸውን ያየው እንደ ንቀት ነበር። እግዚአብሄር ፍርሀታቸውን ያየው፥ እርሱን እንደናቁት ነበር። ከላይ እንደዘረዘርነው ያንን ሁሉ ተአምራት ሲያደርግ የነበረው፣ በምድረበዳ ላይ አንዴ መናን እያወረደ፣ ውሀውን ደግሞ ከአለት ውስጥ እያፈለቀ፣ አንዴ ደመና እየሆነ፥ ደግሞም የእሳት አምድ እየሆነ ሲመራቸው የነበረው፥ ለካ ዛሬ ላይ ለሚገጥማቸው ለዚህ ፈተና እምነት እንዲሆንላቸው ነበር። ለካ ዛሬ ላይ እንዲያምኑት ነበር ትላንትና ጠላቶቻቸውን ሁሉ በኤርትራ ባህር መካከል የጣለላቸው፣ በመንገዳቸው የተዋጓቸውን ጠላቶቻቸውን ሁሉ እየተዋጋና እያሸነፈ ድል ነሺነቱን ያሳያቸው፥ ለካ ዛሬ በተመሳሳይ ችሎታው እንደሚሰራ፣ የተአምራት አምላክ እንደሆነ እንዲያምኑት ነበር። ልክ ከግብጽ እንደወጡ እኮ፥ የኤርትራ ባህር ገጥሟቸው ሲፈሩ ምንም አላላቸውም። ሀይሉን እስከሚያሳያቸው ድረስ ከእነርሱ ምንም አይነት እምነት አልጠበቀም። ተአምራቱን እያለማመዳቸው ሲመጣ ግን፥ ትላንትና ሲሰራ ባዩበት ተአምራቶች መጠን እምነታቸው እንዲያድግ ፈልጎ ነበር። የእስራኤል ልጆች ደግሞ ትልቁ ችግር፥ ትላንትና እግዚአብሄር በህይወታቸው ላይ ያደረጋቸውን ተአምራቶች መርሳት ነበር። የእግዚአብሄርን ተአምራቶች ቶሎ ይረሱ ነበር። ይሄንን በመዝሙረ ዳዊት ምእራፍ 106 ላይ ስለ እስራኤል ህዝብ ሲጽፍ እንዲህ ይላል፥ “የኤርትራንም ባህር ገሠጸ እርሱም ደረቀ፥ እንደ ምድረበዳ በጥልቅ መራቸው። ከሚጠሉአቸውም እጅ አዳናቸው፥ ከጠላትም እጅ ተቤዣቸው። ያሳደዱአቸውንም ውሀ ደፈናቸው። ከእነርሱም አንድ አልቀረም። በዚያን ጊዜ በቃሉ አመኑ፥ ምስጋናውንም ዘመሩ። ፈጥነውም ስራውን ረሱ፥ በምክሩም አልታገሱም።“ በማለት እግዚአብሄር ትላንትና በህይወታቸው ያደረጋቸውን አስደናቂ ተአምራቶች፥ ቶሎ መርሳታቸውን ጽፎልናል። ትላንትና ላይ ያዩትን የእግዚአብሄር ተአምራቶች መርሳታቸው ታዲያ፥ ዛሬ ላይ ህዝቡ በገጠማቸው ችግሮች ላይ እግዚአብሄርን ላለማመናቸው ምክኒያት ሲሆን እናያለን። እግዚአብሄርም እምነት ስላጡበት ስለዚህ ጉዳይ ሲቆጣ፥ ሀይልና ብርታቱን ደግሞም ሁሉን ቻይነቱን ለህዝቡ ለማሳየት፥ ትላንትና በግብጽ ምድር ላይ እንዲሁም ባለፉባቸው የምድረበዳ መንገዶች ውስጥ ባደረጋቸው ተአምራቶች መጠን አለማመናቸው፥ እጅግ አስቆጥቶት ነበር። ለካ እግዚአብሄር ትላንትና ህይወታችን ላይ በሰራቸው ተአምራቶች ልክ ነው እንድናምነው የሚፈልገው። ከእያንዳንዳችን የሚጠብቀው የእምነት መጠን አንድ አይነት አይደለም። መጠኑ ባየናቸው ተአምራቶች ልክ ይወሰናል። ብዙ ተአምራቶች ካየ ሰው ብዙ እምነት ይጠበቃል። እኛ ደግሞ እግዚአብሄር ይመስገን ህይወታችን ሁሉ ተአምራት አይደል እንዴ! የተአምራት ችግር እንኳን የለብንም። ህይወታችንን ዞር ብለን ብናየው፥ ብዙ የተከፈሉ የኤርትራ ባህሮች አሉ። ብዙ የወረዱልን መናዎች አሉ። ብዙ የፈለቁልን ምንጮች አሉ። ብዙ የእግዚአብሄርን ተዋጊነት አይተን እግዚአብሄር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሄር ነው ብለን የዘመርንባቸው ድሎች ህይወቶቻችን ውስጥ አሉ። እነዚህ ድሎች ታሪክ ሆነው በታሪክ መዝገቦቻች ላይ የሚቀመጡ ብቻ ሳይሆኑ፥ ህይወት ያለባቸው፣ የዛሬውን ህይወት የማስቀጠል ሀይል ያለባቸው እምነቶቻችን ናቸው። እኛ የእድሜ ዘመን የተአምራት ልምድ ያለን ሰዎች ነን። የእግዚአብሄርን ተአምራት ያላየንበት ጊዜ ህይወታችን ውስጥ የለም። ጠላት እንደሚገሳ አንበሳ ዙሪያችንን በሚዞርበት 24 ሰአት ውስጥ፥ በሰላም ወጥቶ መግባት እራሱ፥ እራሱን የቻለ ተአምራት ነው። መኖራችን እራሱ ተአምራት ነው። እግዚአብሄር ትላንትና የጠበቀን፣ ትላንትና ያሻገረን፣ ትላንትና የመገበን፣ ትላንትና የተዋጋልን ዛሬ ላይ ለሚገጥሙን ችግሮች እምነት እንዲሆነን ነው።