Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

 ዝግጅት

 ዝግጅት

ዛሬ ረፈድፈድ አርጌ ነው ከመኝታዬ የተነሳሁት። እንደተነሳሁ ልቤ ወደ ቀኑ ጉዳዮቼ ቢቸኩልም፥ ኸረ በሰላም ያሳደረኝን ተመስገን እንኳን ልበለው። እግዚአብሄር ከረዳኝ ደግሞ ከቅዱስ ቃሉ ለቀኔ የሚሆነኝን ጥቂት ነገር ላንብብ ብዬ የጀመርኩትን የማቴዎስ ወንጌል ማንበቤን ቀጠልኩ። ዛሬ ያነበብኩት የማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 25ትን ነበር። ምእራፉ ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን ስለሚሆነውን ልዩ ልዩ ፍርድ በተለያዩና በሚገርሙ ሶስት ምሳሌዎች የተናገረበትና ህይወታችንን በመመልከት ራሳችንን እንድናስተካክል ያስተማረበት አስደናቂ ምእራፍ ነው። 

እነዚህ ሶስት አስገራሚ ምሳሌዎች የተለያዩ የህይወት ክፍሎቻችንን የሚያመለክቱ ናቸው። የመጀመሪያው ኢየሱስን ለመቀበል ወጥተው ዘይት ስለያዙትና ስላልያዙት አስር ቆነጃጅቶች በመናገር ሊኖረን ስለሚገባ የዝግጅት ህይወት የሚናገር ምሳሌ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በተሰጣቸው መክሊት ነግደው ስላተረፉትና ስላላተረፈው ሰው በመናገር በተሰጠን የጸጋ ስጦታዎች የማትረፋችንን አስፈላጊነት የሚናገር ሲሆን የመጨረሻው ደግሞ ኢየሱስ ተርቤ አብልታችሁኛል ተጠምቼም አጠጥታችሁኛል እንዲሁም ተርቤ አላበላችሁኝም ተጠምቼም አላጠጣችሁኝም ስለሚላቸውና ሊኖረን ስለሚገባው የማካፈል ህይወት የሚናገር ምሳሌ ነው። 

የማቴዎስን ወንጌልን ስታጠኑት፥ አብዛኛውን ጊዜ ኢየሱስ እየደጋገመና ትኩረት እያረገ በልዩ ልዩ ምሳሌዎች ለደቀ መዛሙርቱ ይናገር የነበረው፥ ስለ እግዚአብሄር መንግስት ጉዳይ ነበር። በዚህ በማቴዎስ ምእራፍ 25 ላይ ታዲያ ኢየሱስ ሶስት ልዩ ልዩ ምሳሌዎችን በማንሳት ከመጨረሻው ፍርድ ጋር ተያይዞ አንድ ክርስቲያን ህይወቱን እንዴት ማዘጋጀት እንዳለበት እና ምን ላይ ማተኮር እንዳለብት አስተምርዋል።

በመጀመሪያው ምሳሌ፥ የተዘጋጀ ህይወት ይኑራችሁ በማለት ኢየሱስ የ10ሩን ቆነጃጅቶች ምሳሌ ይናገራል። የ10ሩ ቆነጃጅቶች ምሳሌ፥ ልክ እኛ ዛሬ ያለንበትን ዘመን ይመስላል። ሙሽራው ይመጣል ብለው ለረጅም ሰአት ቁጭ ብለው ቢጠብቁም፥ መጠበቃቸው እጅግ ሲረዝም 10ሩም እንቅልፍ እንቅልፍ ብሏቸው ተኝተው ነበር። ታዲያ በተኙበት እኩለ ሌሊት ላይ “ሙሽራው መጥቷልና ትቀበሉት ዘንድ ውጡ” የሚል ድንገተኛ ድምጽና ውካታ ሲሆን፥ ምንም እንቅልፍ እንቅልፍ ብሏቸው የተኙት 10ሩም ሴቶች ቢሆኑም፥ የኢየሱስ ድንገት መምጣት በ10ሩም ቆነጃጅቶች ላይ የፈጠረው ስሜት ግን አንድ አይነት አልነበረም። አምስቱ ልባሞች ሌሎቹ 5ቱ ደግሞ ሰነፎች ነበሩ በማለት ኢየሱስ በምሳሌው ይናገራል። ልባሞቹ ለካ ምንም ለሌሎቹ ጋር አብረው ይተኙ እንጂ ተጨማሪ ዘይት በመያዝ በዝግጅትና በጥንቃቄ ነበር የተኙት። የተዘጋጀ ማነነት ስለነበራቸው የኢየሱስ መምጣት ብዙም ግራ አላጋባቸውም። ሌሎቹ 5ቱ ቆነጃጅቶች ግን የኢየሱስ መምጣት ከፍተኛ የሆነ ድንጋጤና ግራ መጋባት ሲፈጥርባቸው ይታያል። “ወይኔ መብራታችን ሊጠፋብን ነው። እስኪ ዘይት የያዙትን ትንሽ እንዲሰጡን እንጠይቃቸው። ሙሽራው ደግሞ ደርሷል። ታዲያ ምን ይሻለናል። በናታችሁ ትንሽ ዘይት ስጡን መብራታችን ሊጠፋብን ነው” ቢሉም ልባሞቹ ዘይታቸውን ማካፈል የማይችሉበት ወሳኝ ሰአት እንደሆነ ተናግረዋል። እነዚህ 5ቱ ሰነፍ ቆነጃጅቶች ታዲያ ኢየሱስን በሚቀበሉበት ወሳኝ ሰአት፥ ዘይት ለመግዛት ወደሌላ ቦታ እንደሄዱና ሲመለሱ በሩ እንደተዘጋባቸው ኢየሱስም አላውቃችሁም እንዳላቸው እንመለከታለን።

ይሄ ምሳሌ የሚያስተምረን፥ በየትኛውም ሰአት የተዘጋጀ ህይወት ሊኖረን እንደሚገባ ነው። በየምንችልበት አጋጣሚዎች ሁሉ ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ክርስቶስን የማመን ህይወቴ ምን ይመስላል? የቅድስና ህይወቴ ምን ይመስላል? እግዚአብሄርን የመፈለግ ህይወቴ ምን ይመስላል? ህይወቴና አካባቢዬ ላይ ካሉት ሰዎች ጋር ያለኝ የፍቅርና የይቅርታ ህይወቴ ምን ይመስላል? የጸሎትና የቃል ህይወቴ የእግዚአብሄርን ቃል የመከተልና የመታዘዝ ህይወቴ ምን ይመስላል? ብለን እነዚህንና ተጨማሪ ጥያቄዎችን ራሳችንን በመጠየቅ “ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር” እንደሚናገረው ህይወታችንን ምንጊዜም ለክርስቶስ መምጣት የተዘጋጀ መሆኑን መመርመርና እርግጠኞች መሆን ይኖርብናል። ይሄንን በማድረግ ስንኖር፥ የክርስቶስ መምጣት ድንጋጤና ፍርሀት ሳይሆን ደስታና ሀሴት ይሆንልናል። 

ሁለተኛው ኢየሱስ በዚሁ በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 25 ላይ የሚናገረው፥ ልዩ ልዩ መክሊት ወይንም የአገልግሎት ስጦታ ስለተሰጣቸውና ስላተረፉበት ሰዎች ነው። አንድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ አቅማቸውን ካየ በኋላ፥ ልክ እንደ አቅማቸው መክሊቶችን ሰጥቷቸው ሄዶ ነበር። ከሄደበት ሲመለስ ታዲያ አምስት እና ሁለት መክሊት የተሰጣቸው ሰዎች፥ የተሰጣቸውን መክሊት አትርፈው መክሊቱን ከነትርፉ ለጌታቸው አስረክበዋል። ይሐውልህ ጌታዬ አምስት መክሊት ሰጥተሀኝ ነበር። ሌላ አምስት አትርፌ አስር አድርጌዋለሁ። ሌላኛውም ደግሞ መጣ፥ ለእኔም ሁለት መክሊት ሰጥተህኝ ነበር። እኔ ደግሞ፥ አራት አድርጌዋለሁ እያሉ መክሊታቸውን ሲያስረክቡ፥ አንድ መክሊት የተሰጠው ሰው መክሊቱን እንደቀበረና እንዳላተረፈበት ይናገራል። ጌታው ታዲያ በመቆጣት “መክሊቱን ውሰዱበትና 10 መክሊት ላለው ስጡ” በማለት ሲቆጣና ይሄንን ሰው በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት በማለት አስፈሪ ንግግር ሲናገር እንመለከታለን።

የመጀመሪያው የ10ቱ ቆነጃጅቶች ምሳሌ ኢየሱስ ሲያስጠነቅቀን የፈለገው ሊኖረን ስለሚገባው የዝግጅት ህይወት ሲሆን፥ በዚህ በመክሊት ምሳሌ አርጎ ሊናገር የፈለገው ደግሞ ውስጣችን በተቀመጡት ስጦታዎችና የአገልግሎት ጥሪዎች በትጋት መስራትና ፍሬ ማፍራት እንዳለብን ነው። ሁላችንም ውስጥ እግዚአብሄር ወዶ ስላስቀመጣቸው የጸጋ ስጦታዎች አንድ ቀን እግዚአብሄር እንደሚጠይቀን ፈጽሞ መርሳት የለብንም። በውስጣችን የተቀመጡት ስጦታዎች፥ እግዚአብሄር በምክኒያት ያስቀመጣቸውና በእነዚህ ስጦታዎች ሊያገለግል ያሰባቸው ሰዎች እንዳሉ ማስተዋል አለብን። ይሄ መክሊቱን የቀበረው ባሪያ ፈርቼ ቀበርካት እንዳለው መክሊቶቻችንን ያስቀበሩንን ፍርሀቶች በጸሎትና በእግዚአብሄር ቃል እውነት እያሸነፍን ፍሬ ማፍራታችንን መቀጠል ይኖርብናል።

ኢይሱስ በዚሁ በማቴዎስ 25 ላይ ከተናገራቸው ሶስት ምሳሌዎች የመጨረሻው ምሳሌ ደግሞ፥ ስለ መስጠት የተናገረበት አስደናቂ ምሳሌ ነው። ስለ ህይወት ዝግጅት፣ በጸጋ ስጦታ ስለማገልገል ከተናገረ በኋላ፥ በማካፈል ውስጥ ስላለው አስደናቂ ብድራት ደግሞ ሳይናገር ምሳሌውን አላጠናቀቀም። በመጨረሻው ዘመን አለ ኢየሱስ ሲናገር፥ በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ፥ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል። አብዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ እረኛም በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ይለያቸውና በጎቹን በቀኝ በኩል፣ ፍየሎቹን ደግሞ በግራ በኩል ያቆማቸዋል። ንጉሱም በቀኙ ያሉትን ተርቤ አብልታችሁኛል፣ ተጠምቼም አጠጥታችሁኛል እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፣ ታርዤ አልብሳችሁኛል፣ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና ታስሬም ወደ እኔ መጥታችሁዋልና ሲላቸው፥ መቼ አግኝተንህ ነው ያበላንህና ያጠጣንህ? መቼ አግኝተንህ ነው የጠየቅንህና ያለብስንህ ደግሞስ የተቀበልንህ ቢሉት፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ እንኳን ስላደረጋችሁት ለእኔ አድርጋችሁታል በማለት እናንተ የአባቴ ብሩካን ኑ አለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግስት ውረሱ በማለት ወደ ታላቅ መንግስቱ ይጋብዛቸዋል። በግራው ያሉትን ሰዎች ደግሞ ተርቤ አላበላችሁኝም፣ ተጠምቼም አላጠጣችሁኝም፣ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝም፣ ታርዤ አላለበሳችሁኝም፣ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝም ቢላቸው መቼ ተርበህ፣ ተጠምተህ፣ እንግዳ ሆነህ፣ ታርዘህ ወይስ ታመህና ታስረህ አገኘንህ ቢሉት፥ እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ወደ ዘላለም ፍርድ ሲጥላቸው እንመለከታለን። 

ኢየሱስ በዚህ ምሳሌው ላይ የሚናገረው፥ የማካፈል ህይወታችን የመጨረሻው ፍርድ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽእኖ ነው። ይሄንን ምሳሌ ሳሳብ ወደ ኢየሱስ በመምጣት አንድ ጥያቄ የጠየቀው ሰው ወደ ሀሳቤ ይመታል። “መምህር ሆይ የዘላለምን ህይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” ብሎ ኢየሱስን ቢጠይቀው፥ ወደ ህይወት መግባት ከወደድክ ትእዛዛትን ጠብቅ” ቢለው ይሄንንማ ከልጅነቴ ጀምሬ ጠብቄያለሁ በማለት ይመልሳል። በቃ እንደዛ ከሆነ ደግሞ ሂድ ያለህን ሽጥና ለድሆች ስጥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ መጥተህም ተከተለኝ ቢለው፥ ከነበረው ንብረት ብዛት የተነሳ እያዘነ ወደ ቤቱ ሄደ በማለት ኢየሱስ ይናገራል። ወዲያው ታዲያ ኢየሱስ ቀጠል አድርጎ ለባለጠጋ ወደ እግዚአብሄር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው በማለት ይናገራል። በነገራችን ላይ ኢየሱስ ሰርተን ገንዘብ ማግኘታችንን እና ሀብታሞች መሆናችንን አይቃወምም ኢየሱስ የሚቃወመው አለማካፈላችንን ነው። ስንት ዳቦ አጥቶ መንገድ ላይ እያለቀሰ ያለ ህጻን ወይንም አካሉ ተጎድቶ መስራት ያቃተው ሰው እያለ ሺዎች ወይንም ሚሊየን ብሮች ባንካችን ውስጥ አስቀምጠን እሱ ላይ ጨምረን ለማስቀመጥ እንሰራለን። ለሌላቸው ሰዎች መስጠት በጣም ፓወርፉል ነው በኢየሱስ ግራ ወይንም በኢየሱስ ቀኝ የማስቀመጥ ሀይል ያለው ነገር ነው። እንደ ኢየሱስ ምሳሌ ከሆነ በዘላለም መንግስት ወይንም ወደ በዘላለም ቅጣት ውስጥ የመጣል አቅም ያለው ነገር ነው። ለሌላቸው ስናካፍል፥ ለኢየሱስ እያካፈልን ነው። ሰዎችን ስናበላ፣ ስናጠጣ፣ የታመሙትን ስንጠይቅ፣ እንግዶችን ስንቀበል፣ የታሰሩትን ስንጎበኝ፣ የበረዳቸውን ስናለብስ ለኢየሱስ እያረግንለት ነው። 

ስለዚህ በማቴዎስ ምእራፍ 25 ላይ ክርስቶስ ከተናገራቸው 3 ምሳሌዎች የምንማረው፥ የክርስቶስ መምጣት ድንገት ስለሆነ የተዘጋጀ ህይወት ሊኖረን እንደሚገባ፣ በተሰጠን የጸጋ ስጦታ ደግሞ መስራትና ማትረፍ እንደሚገባ እንዲሁም ደግሞ ለሌላቸው ሰዎች በማካፈል መኖር እንዳለብን ነው። 

ፍለጋ

ፍለጋ

እውቀት

እውቀት