Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ማንነት

ማንነት

እቤት ውስጥ ያደግነው፥ እኔ እና እህቴ ሆነን ነው። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው ብለው እነደሚናገሩት፥ ይሄ ተረትና ምሳሌ ትክክለኛ ተፈጻሚነትን ያገኘው እኛ ቤት ይመስላል። እኔና እህቴ ልጆች እያለን፥ ትንሽ እንኳን ሊቀራረብና ሊመሳሰል የማይችል የባህሪ ልዩነት ነበር የነበረን። አንዳንድ ቀን እንተያይና እንዴት እህትማማቾች ልንሆን እንደቻልን ሁለታችንም እንገረማለን። እሷ በተፈጥሮ ባህሪዋ ጸጥ ያለች፣ ከአዲስና ከማታውቀው ሰው ጋር ምንም አይነት ንግግር የማትፈልግ፥ አዲስ ሰዎችን ላለመተዋወቅ የተቻላትን ሁሉ ጥረት የምታደርግ፣ እቤታችን እንግዳ ሲመጣ፥ መኝታ ቤትዋ ገብታ በሯን በመቆለፍ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር እየሰራ ያለ ሰው መስላ ከስልኳ ጋር የምትጫወት፥ ግርግርና ስብሰባ የማትወድ፥ ሰዎችን ለመልመድና ነጻ ሆና ለማውራት ብዙ ጊዜያቶች የሚፈጁባት ልጅ ናት። እኛን ቤተሰቦቿን እራሱ የለመደችን፥ ከተወለደች ከብዙ አመታቶች በኃላ ነው። አንዳንድ ቀን አባታችን ለስራ ፊልድ ቆይቶ ሲመጣ፥ “አላውቅህም” በሚል አስተያየት ራቅ ብላ ቆማ እያየችው የፈለገ ቢለምናት የማትቀርብ ልጅ ነበረች። ትንሽ ልቧ የሚከፈተው ተመልሶ ሌላ ፊልድ ሊሄድ ሁለት ቀናቶች ሲቀሩት ነበር። እኔ እህታችሁ ደግሞ መጫወትና መሳቅ የግል ማንነቶቼ ናቸው። ጓደኞቼን የማስቅ፥ ቤት ውስጥ እንኳን የሆነ ጥፋት አጥፍቼ አባቴ ሊቆጣኝ ሲመጣ፥ ሊስቅ የሚችልባቸውን ነገሮች እያረኩ ቁጣና ንዴቱን በሳቅ አስለውጬ የማስመልስ ልጅ ነበርኩ። አዳዲስ ሰዎችን እንደመተዋወቅ የሚያስደስተኝ ነገር አልነበረም። እቤታችን እንግዳ ሲመጣ እንግዳውን ለማጫወት ካለሁበት ተፈልጌ የምጠራው እኔ ነበርኩ። ሳሎን ቤታችን ከእንግዳው ጋር በመቀመጥ፥ የማዋራቸው፣ ስለ ቤታችን የማያውቁትን ነገር በዝርዝርና በማብራሪያ በተደገፈ ሁኔታ የማስረዳ፥ አልፎም  እንግዶቹን የማጫውትና የማስቃቸው እኔ ነበርኩ። ቤት ውስጥ ካኮረፍኩና ዝም ካልኩ፥ ቤቱ ዝም ስለሚል፥ መብራት እንደ ጠፋ ነበር የሚቆጠረው። ገና የዘጠኝና የአስር አመት ልጅ ሆኜ፥ እኩዮቼ የማይሄዱበት የእሮብ እሮብ የትልልቅ ሰዎች ጉባኤና መጽሀፍ ቅዱስ ጥናት ውስጥ የምሳተፍ፣ ልቤ ውስጥ የተፈጠረውን ጥያቄ እንዲያስረዱኝ ለመጠየቅ፥ የእድሜዬ ቁጥር አነስተኛነት አሳስቦኝ የማያውቅ፣ የገባኝን ደግሞ በተቻለኝ አቅም የማስረዳ ልጅ ነበርኩ። እኔ ለእህቴ፥ ከሌላ ፕላኔት የመጣሁ አስገራሚ ፍጥረት ነኝ። ታዲያ ቤተሰቦቼ በሙሉ ተመሳሳይ ባህሪ ስላላቸውና ከእነሱ ለየት ያለ ባህሪ የነበረኝ እኔ ስለነበርኩ፥ እነርሱ ትክክል የሆኑ፥ እኔ ደግሞ የተሳሳተ ጸባይ እንዳለኝ እያመንኩ የኖርኩባቸው ጊዜያቶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ከዚህም የተነሳ፥ እግዚአብሄር እንደ ቤተሰቦቼ ጸጥ ያልኩ እንዲያረገኝ እየለመንኩት የጸለይኩባቸው ጊዜያቶች ነበሩ። አሁን ላይ፥ በእድሜ መጨመርና እግዚአብሄር እየሰጠኝ ባለው ማስተዋል የተለወጡ አንዳንድ ባህሪያቶች ቢኖሩም፥ ምንም ብጸልይ እግዚአብሄር እስካሁን ከውስጤ ሊያወጣቸው ያልቻላቸውና ከተፈጥሮ ማንነቴ ጋር አብረው የተሰሩ ባህሪዎች አሉኝ። ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው አንድ የህይወቴ ወቅት ላይ የሁላችንም ተፈጥሮ፣ የሁላችንም ባህሪና ጸባዮቻችን በአጋጣሚ የተሰጡን እንዳልሆኑ እየተማርኩ የመጣሁት። በምታመልኩባቸው ቤተክርስቲያኖች ወይንም ባላችሁባቸው ህብረቶች ውስጥ፥ የሰዎችን ሁሉ ባህሪ አስተውላችሁ ካያችሁ፥ የሁሉም ሰው ባህሪ ልዩ ልዩ ነው። ፈጠን ያሉ፥ ሳቅና ጨዋታ የሚወዱ፥ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ማገልገል ስጦታቸው የሆነ፥ በህብረቶች ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ቀስ ያሉ፥ ዝም ያሉ፥ ፕሮግራሞች ላይ መጥተው ሰምተው ብቻ መሄድ የሚፈልጉ፥ ብዙ Activity-ዎች ውስጥ የማናያቸው ሰዎች ደግሞ አሉ። ከDNA-ያችን ጀምሮ፥ እስከ ጣት አሻራዎቻችን ድረስ እግዚአብሄር ተጠንቅቆ በልዩነት እኛን የሰራበት፥ የራሱ የሆኑ ትልልቅ አላማዎች አሉት። አንድ ጊዜ ጳውሎስ በገላትያ መጽሀፍ ምእራፍ አንድ ላይ፥ በህይወቱ ስላለፈባቸው ነገሮች፣ ጌታን ሳያገኝ በፊት ስለነበረው ማንነቶቹና ባህሪያቶቹ፥ እንዴት ቀናተኛ እንደነበረ፣ እንዴት አጥፊና አሳዳጅ እንደነበረ ከተናገረ በኋላ፥ “ነገር ግን እግዚአብሄር ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ ወዲያው ከስጋና ከደም ጋር አልተማከርኩም” በማለት ይናገራል።  እግዚአብሄር ልጁን ኢየሱስን በጳውሎስ ህይወት ለመግለጥ፣ የጳውሎስን እምነት እንጂ የጳውሎስን ባህሪና ማንነት በፍጹም አልቀየረም። “በእናቴ ማህጸን ሳለሁ የለየኝ” እንዳለው፥ እግዚአብሄር ገና ከእናቱ ማህጸን ጀምሮ ጳውሎስን ሲለየው፥ ይሄንን ማንነት፥ ይሄንን personality የሰጠው፥ በህይወቱ መስራት የሚፈልገውን ነገር ስለሚያውቅ ነው። በራሱ በጳውሎስ ማንነት፣ በቆራጥነቱ፣ በመሰጠቱ፣ ያመነበትን ነገር ከማድረግ ወደሁዋላ በማይለው ማንነቱ ውስጥ እግዚአብሄር ልጁን ኢየሱስን ገልጦታል። ጳውሎስ፥ ደፋር የሆነ፣ ለውሳኔዎቹና ላመነባቸው ነገሮች ነፍሱን እስከመስጠት የጨከነ፥ በአጠቃላይ አካባቢው ላይ ከነበሩ ሰዎች ለየት ያለ ባህሪ ያለው ሰው ነበር። የተለየ ማነነትና ተፈጥሮ የተሰጠው፣ የተለየ የእግዚአብሄር አላማ ህይወቱ ላይ ስለነበረ ነው። በጳውሎስ ማንነት ውስጥ፥ በጳውሎስ ባህሪና ተፈጥሮ ውስጥ የተገለጠው አስደናቂ የእግዚአብሄር የጸጋ አሰራር ታዲያ፥ እስከዛሬ ድረስ አለምን እየባረከ ይኖራል። 

ኢየሱስ ለአገልግሎቱ የሾማቸውን ሀዋሪያቶችን ስታይዋቸው፥ ሁሉም የተለያየ አይነት ባህሪ ያላቸው ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ዮሀንስን ብታዩት ፍቅርን የሚወድ የፍቅር ሰው ነበር። እርሱ የጻፋቸውን መጽሀፎች፥ አንደኛ ሁለተኛና ሶስተኛ ዮሀንስን ስታነቡ፥ አብዛኛው የጽሁፉ መልክቶች ስለ ፍቅር ወደ ማውራት የሚያደሉ ናቸው። ኢየሱስ ደረት ስር ጠጋ ማለት ይወዳል። ኢየሱስም ከሌሎቹ ለይቶ ዮሀንስን የሚያናግርበት፥ የፍቅር ቋንቋ አለው። እግዚአብሄር ከእኛ ጋር የሚነጋገረው፥ እኛን የሚያናግረው፥ እራሱ በሰጠን personality ውስጥ ነው። አይታችሁ ከሆነ፣ እግዚአብሄር ከአብርሀም ጋር የነበረው አይነት ግንኙነት አይደለም ከሙሴ ጋር የነበረው። እግዚአብሄር አብርሀምን ከወዳጆቹ ሁሉ ከለየው በኋላ፥ ወዳጅ ሆኖ ሲቆምለት እናያለን። ከወዳጄ ከአብርሀም የምሰውረው የለም እያለ፥ ሊያደርግ ያሰበውንና እርሱ እንኳን የማይመለከተውን ነገሮች ነበር ያወያየው የነበረው። እግዚአብሄር ከአብርሀም ጋር የነበረው አይነት ግንኙነት አይደለም ከሙሴ ጋር የነበረው። ሙሴን ያናግረው የነበረው ደግሞ፥ በክብሩ ደመና ውስጥ ነበር። ወደ ተራራ ላይ እየጠራ ነበር የክብሩን መገለጥ ያሳየው የነበረው። በእሳትና በደመና ነበር ይገለጥ የነበረው። መጀመሪያ እራሱ በኮሬብ ተራራ ላይ በእሳት ቁጥቋጦ ተአምራት ነው ወደ ራሱ አቅርቦ ልቡን የሳበውና በህይወቱ ሊያደርግ ያሰበውን አላማ በሙሉ የነገረው። እግዚአብሄር ከሙሴ ጋር የነበረው አይነት ግንኙነት አይደለም ከዳዊት ጋር የነበረው። ገና በእድሜው ማለዳ ላይ ነበር በብዙ ዝማሬና ቅኔ ከዳዊት ጋር ይነጋገር የነበረው። የእግዚአብሄርንና የዳዊትን ወዳጅነት ስናነብ፥ እግዚአብሄር ከሁሉ ነገሩ ይልቅ ከዳዊት ልብ ጋር ጥብቅ የሆነ ወዳጅነት እንደነበረው እናያለን። መጀመሪያ እራሱ ከወንድሞቹ መካከል ሊመርጠው ሲነሳ፥ ሰው ፊትን ቢያይም እግዚአብሄር ግን ልብን እንደሚያይ በመናገር፥ ሊመርጠው እራሱ የቻለበት ምክኒያት ልቡ እንደሆነ ይናገራል። ዳዊትም በመዝሙሮቹ ውስጥ ልቡን በንጽህና በመጠበቅና በእግዚአብሄር ፊት ለማቅረብ የተቻለውን ሲያደርግ እናያለን። በህግና በተአምራቱ፣ በፍቅርና በምህረቱ ውስጥ እግዚአብሄር ከዳዊት ጋር ያደረገው ንግግር አስደናቂና የእኛንም ልብ እስከዛሬ ድረስ የሚነካ ታላቅ ነገር ነው። እግዚአብሄር ከእያንዳንዳችን ጋር ያለው ግንኙነት አይነቱ የተለያየ ነው። በሰጠን ማንነት ውስጥ ነው የሚያናግረን። በሰጠን ተፈጥሮ ውስጥ ነው communicate የሚያረገን። እግዚአብሄር  እያንዳንዳችንን የሚያናግርበት የፍቅር ቋንቋ አለው። እነዚህ ቋንቋዎች ደግሞ የተለያዩ ናቸው:: ምክኒያቱ ደግሞ የሁላችንም የፍቅር ቋንቋ የተለያየ ስለሆነ ነው። ኢየሱስ ከሌሎቹ ሀዋሪያቶች በተለየ መልኩ ዮሀንስን ወደ ደረቱ ጋር የሚያስጠጋው፥ ዮሀንስ የፍቅር ሰው እንደሆነ፥ የዮሀንስ የፍቅር ቋንቋ መጠጋጋት እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው። በዮሀንስ የፍቅር ማንነት ውስጥ ታዲያ እግዚአብሄር ፍቅርን ለአለም ሰብኮበታል። የዮሀንስ ወንጌል፣ አንደኛ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዮሀንስ እያለ ፍቅርን ለአለም ጽፎበታል። ዮሀንስ ከዚህች ምድር ካለፈና ወደ ጌታ ከሄደ ስንትና ስንት ሺ አመታቶች ቢያልፉም፥ በዮሀንስ ማንነት ውስጥ በተገለጠው የእግዚአብሄር ፀጋ፥ እስከዛሬ ድረስ ፍቅርን እናነባለን፥ ፍቅርን እንማራለን፥ ፍቅርን እንሰበካለን። የጳውሎስን ጠንካራ ልብ ለማግኘት ደግሞ፥ እግዚአብሄር በደማስቆ መንገድ ላይ ከተፈጥሮ ውጪ በሆነ ታላቅ ብርሀንና ድምጽ መገለጥ ነበረበት። ኢየሱስ የጳውሎስን ልብ ሊያገኝ የሚችለው፥ በደማስቆ መንገድ ላይ በልዩና ከተፈጥሮ ውጪ በሆነ ተአምራት ሲገለጥ እንደሆነ ያውቃል። እግዚአብሄር በየት በኩል ቢመጣ ልባችንን እንደሚያገኘው  ያውቃል። በዚህ እውቀቱ ነው ልባችንን አግኝቶ ያዳነን። እግዚአብሄር ተስፋ እንኳን ስንቆርጥ፥ በምን አይነት ተስፋ ልባችንን ካለበት ዝቅታ ውስጥ ሊያወጣው እንደሚችል ያውቃል። በምን በኩል ካለንበት ተስፋ መቁረጥ  እንደሚያወጣን ያውቃል። አንዳችንን በሚያወጣን ተስፋ አይደለም ሌላችንን የሚያወጣን። የእያንዳንዳችንን ልብ ሊደግፍና ሊያነሳ የሚችለውን ተስፋ ጠንቅቆ ያውቀዋል። ምን እንደሚያስደስተን ያውቃል። ምን ልባችንን እንደሚጎዳውም ያውቃል። አባብላታለሁ ተብሎ እንደተጻፈው፣ እኛን የሚያባብልበትን መንገድ በደንብ ነው የሚያውቀው። “በጎቹ ድምጹን ይሰሙታል። የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል” ብሎ ዮሀንስ በመጽሀፉ እንደጻፈልን፥ እያንዳንዱ በጎቹን የሚጠራበት ስምና የሚያናግርበት ቋንቋ አለው። እያንዳንዱን በጎች በስማቸው ይጠራቸዋል ሲል፥ ከእያንዳንዱ በግ ጋር personal የሆነ Relationship አለው እያለን ነው። ፈጣሪያቸው እንደመሆኑ መጠን የእያንዳንዱብ በግ ባህሪ ማንነትና ተፈጥሮ ከማወቁ የተነሳ፣ ሊገባቸው በሚችለው፣ መልኩ ነው የሚያናግራቸው። አዎ። በጎቹ ድምጹን ይሰሙታል። ሁላችንም የእረኛችንን ድምጽ ብንሰማም፥ የምንሰማበት መንገድ ግን የተለያየ ነው። አንዳንዱ በቀጥታ ድምጽ ነው የሚሰማው፣ አንዳንዱ በዝማሬ ወይንም በስብከት ውስጥ ነው የሚሰማው፣ አንዳንዱ በሌሊት ህልምና ራእይ ነው የሚሰማው፣ አንዳንዱ በቃሉ ውስጥ ነው የሚሰማው፣ አንዳንዱ በሁኔታዎች ውስጥ ነው የሚያዳምጠው። ሁሉም በጎች አንድ አይነት ስም እንደሌላቸው ሁሉ፥ እንደየስማቸው ልዩነት ከእያንዳንዱ በግ ጋር ልዩ የሆነ ግንኙነት ነው ያለው። ለእያንዳንዱ በግ ያለው ፍቅር ደግሞ ይሄ ነው። መቶ በጎች ቢኖሩትና እንዷ በግ ብትጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን ቁጭ ያረግና ያቺ የራሱ የሆነችውን አንድ በግ እስከሚያገኛት ድረስ በሄደችበት ሄዶ ይፈልጋታል። ፈልጎ ካገኛት በኋላ ታዲያ፥ “ለምንድነው ወደ ጥፋት የሄድሽው?” ብሎ ሳይቆጣትም ሆነ ሳይፈርድባት፥ ወደ ላይ አንስቶ ይሸከማትና አቅፎ ወደ ቦታዋ ይመልሳታል። 

ከሀዋሪያቶች ውስጥ ደግሞ የጴጥሮስን ማንነት ተመልከቱ። ፈጠን ያለ ነው። ጥያቄ ሲጠየቅ ለመመለስ አንደኛ እጁን የሚያወጣ፣ አስተያየት ሰጪ፣ ከሌሎቹ ፈጠን ያለ ተፈጥሮ ያለው ነው ጴጥሮስ። ሀሳቡን መግለጽ ይወዳል። ልቡ ውስጥ ያለውን ሁሉ ያወራል። ጥያቄ መጠየቅ ይወዳል። ጠቃሚ ሀሳብ ነው ብሎ ይመንበት እንጂ፥ መቼ ነው ጴጥሮስ ሀሳብ ከመስጠት ወደ ኋላ ብሎ የሚያውቀው? በዚህ ዘመን ጴጥሮስ በእኛ ህብረት ውስጥ ቢሆን፥ “አይ ችኩል ነው ለሁሉ ነገር ይቸኩላል” የምንልና “ጴጥሮስ ተረጋጋ” ብለን ከብዙሀኑ ጋር ልናመሳስለው ተሰብስበን የምንመክረው ሰው ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ጴጥሮስን ለሀዋሪያነት የመረጠው ተሳስቶ አይደለም። ኢየሱስም ሶስት አመት ተኩል ከጴጥሮስ ጋር አብሮ ሲኖርና ሲጓዝ፥ አልፎ አልፎ የሚላቸውን የተሳሳቱ ነገሮች ከመገሰጽና ከማስተካከል ውጪ፥ አንድም ቀን “ጴጥሮስ ተረጋጋ፣ እንደሌሎቹ ቀስ በል፣ አትቸኩል ብሎ ከሌሎቹ ሀዋሪያቶች ባህሪ ጋር ሊያመሳስለው ሞክሮ አያውቅም። ሌላው ቢቀር፥ ሶስት ጊዜ ሲክደው እንኳን፥ አልክድህም ብሎ የገባለትን ቃል እያነሳ “ጴጥሮስ ከዚህ ጥፋትህ ተማር ዝም ብለህ ቃል ለመግባት አትቸኩል” ብሎ በዚህ ድካሙ ውስጥ ሊወቅሰው እንኳን በፍጹም አልሞከረም። ኢየሱስ ጴጥሮስን ለዚህ ታላቅ አገልግሎት የመረጠው ተሳስቶ አይደለም። እንዲያውም ኢየሱስ ለሀዋሪያነት አስራ ሁለቱን ከመምረጡ በፊት፥ ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ ካደረ በኋላ፥ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ነው እያንዳንዳቸውን የመረጣቸው። ጴጥሮስ ኢየሱስ ወንጌልን ለአለም ለማድረስ ከመረጣቸው ዋና ዋና ሰዎች ውስጥ አንዱ ነበር። የጴጥሮስ ባህሪ ለወንጌል፣ ለእግዚአብሄር ታላቅ ስራ እና አላማ በጣም አስፈላጊ ነበር። በጴጥሮስ ህይወትና አገልግሎት ውስጥ ስለተገለጠው አስደናቂ የመንፈስ ቅዱስ አሰራር፥ መጽሀፍ ቅዱስ ብዙ ነገር ይለናል። ጴጥሮስ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ካገኘ በኋላ፣ በብዙ ሺህ ህዝቦች መካከል ተነስቶ፥ በተሞላው የመንፈስ ቅዱስ ድፍረት፥ የክርስቶስን ተቃዋሚዎች ፊት ለፊት በማናገርና በመገሰጽ፥ ብዙዎች ኢየሱስን ተቀብለው ከዘላለም ሞት እንዲያመልጡ እግዚአብሄር የተጠቀመበት ሰው ነበር። የሁላችንም ተፈጥሮ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ እጅግ በጣም አስፈላጊና ትልልቅ ስራዎችን የሚሰራ ነው። እግዚአብሄር በዝምተኛ ሰው ውስጥ መንግስቱን ያሰፋል። እግዚአብሄር በተናጋሪ ሰዎች ውስጥም መንግስቱን ያሰፋል። ይሄ መረዳታችን፥ ሰዎች ልዩ ልዩ አይነት ተፈጥሮ እንዳላቸው ተረድተን፥ በማንነታቸው እንድንቀበላቸው እኛን ከመርዳቱም በላይ፥ እኛ እራሳችን የተሰጠን ተፈጥሮ በእግዚአብሄር ዘላለማዊ ሀሳብ ውስጥ ያለ ምንም ስህተት የተሰራ እንደሆነ ተረድተን፥ ራሳችንን እንድንቀበል ይረዳናል። በሰዎች ፊት ራሳችንን የመሆንን ነጻነትም ይሰጠናል። ራሳችንን መሆናችንና ራሳችንን መቀበላችን ደግሞ፣ በእኛ ማንነት ውስጥ ሊገለጥ ላለው ለእግዚአብሄር የጸጋ አገልግሎት፥ በር ይከፍታል፥ በማንነታችን ውስጥ ሊሰራ ላለው የእግዚአብሄር አላማ በር ይከፍታል። የእግዚአብሄር የጸጋ ስጦታ የሚሰራው በሰጠን ማንነት ውስጥ ነው። በህይወታችን ላይ ያለው የእግዚአብሄር አላማ የሚሰራው በተሰጠን ተፈጥሮ ውስጥ ነው።  ፈገግ ማለት በሚወዱ ሰዎች ፈገግታ ተፈውሼ አውቃለሁ። ኮስተር ካሉ ሰዎች ጋር ጠጋ ብዬ ደግሞ ልባቸው ውስጥ ካለው ብዙ ቁም ነገር ተጠቅሜ አውቃለሁ። ተጫዋች የሆነው መሳቅ የምንወደው፥ አብዛኛውን ጊዜ ደስተኞችና ነገሮችን ቀለል አርገን የምናይ ሰዎች የሆነው፥ መናገርና ማውራት፥ ማስረዳትና ማብራራት የወደድነው፥ በአጋጣሚ አይደለም። ዝምተኛና ኮስተር ብለን ቁም ነገሮች ላይ ማተኮር የምንወድ፥ ነገሮችን በጥልቀት የምናስብ፣ የተረጋጋንና ጠንቃቆች የሆነውም በአጋጣሚ አይደለም። መናገርና መጫወት የሚወዱ ሰዎች፥ ከየተኛውም ሰው በላይ ሀሳባቸውን በንግግር መግለጽ የሚችሉ፣ ከራሳቸው አልፈው፣ ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች ድምጽ መሆን የሚችሉ ሰዎች ናቸው። እግዚአብሄርም ለመናገር፣ ህዝቡን ለማስተማር፣ ወንጌልን ለማስፋት እንደ ጴጥሮስ አይነት ፈጣንና ተናጋሪ ሰዎችን ይጠቀማል። ዝምተኛ ሰዎች፥ ብዙ የማዳመጥ አቅም ያላቸው፥ ነገሮችን ከተለያየ አንግል ማየት የሚችሉና በጥልቀት የማሰብ ችሎታ ያላቸው ናቸው። ተረጋግተው ስለሚያስቡ፥ ጥሩ ውሳኔዎችን የመወሰን ዝንባሌ አላቸው:: አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ትእግስተኞችና አስተዋዮች ናቸው። እነዚህ በየመድረኩ የማናያቸው ግን በተለያዩ ቦታዎች ከጀርባ ሆነው ብዙ ነገሮችን የሚያስኬዱና የሚያራምዱ፥ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥም ይሄ ነው የማይባል ከፍተኛ የሆነ ሚና የሚጫወቱ፣ የጀርባ አጥንቶች ናቸው። ሁሉም ማንነቶችና ባህሪዎች ለእግዚአብሄር ክብር ተፈጥረዋል። ሁሉም ማንነቶች ለእግዚአብሄር መንግስት እጅግ በጣም አስፈላጊዎች ናቸው። አንድ ሸክላ ሰሪ፥ ጀበናን ለመስራት ሲያስብ ቡና ለማፍላትና ቡና ለመቅዳት የሚመች ቅርጽ ሰቶ አንደሚሰራው ሁሉ፣ የሁላችንም ተፈጥሮ እግዚአብሄር ልጁን ኢየሱስን በምን አይነት ሁኔታ ሊገልጠው እንደወደደ አመላካቾች ናቸው። የሁላችንም ተፈጥሮ፥ እግዚአብሄር በህይወታችን ሊገልጠው ላለው ትልልቅ ዘላለማዊ ሀሳቦቹ፥ ተስማሚ እንዲሆኑ የተሰጡን ናቸው። 

እግዚአብሄር አንድ አይነትና ተመሳሳይ ነገሮችን ፈጥሮ አያውቅም። በቀን መጀመሪያ ከፈጠራቸው ፍጥረታቶች እንኳን ብታስተውሉ፣ አመሳስሎ የሰራው ነገር የለም። እንስሳቶችን በሙሉ አንድ አይነት አላደረጋቸውም። ፈጣን የሆነችውን ጥንቸልን የሰራ አምላክ ነው፥ ቀስ ብላ የምትሄደውን ኤሊን የፈጠራት፣ እያንዳንዱ እንስሳ የራሱ መልክና ባህሪ አለው። አንዱን ፈጣን፣ አንዱን ደግሞ ቀስ ያለ አርጎ ከፈጠራቸው በሁዋላ፥ የዛኑ ቀን እግዚአብሄር የሰራውን ሁሉ አይቶ መልካም ነው አለ። እግዚአብሄር እኛንም ልዩ ልዩ አርጎ ከፈጠረን በሁዋላ፣ ሁላችንንም አይቶ በሰራው የእጁ ስራ መልካም ነው ይላል። በሺዎች የሚቆጠሩ የእጽዋት ዝርያዎችንም እንዲሁ ብታዩ ልዩነታቸው፣ የሚሰጡት የፍራፍሬና ምግብ አይነት ልዩነቱ ለእግዚአብሄር ክብርን ያመጣል። ብዙ ጊዜ አካባቢያችን ላይ ያሉ ሰዎች ልክ እንደ እኛ አይነት ተፈጥሮ ከሌላቸው፥ ሰዎቹን መቀበል ይከብደናል። ወይንም ደግሞ ከጀርባቸው ሄደን እግዚአብሄር ለራሱ ክብር የሰጣቸውን ተፈጥሮ ጥሩ ባልሆነ መንገድ እናነሳለን። “እሱ እኮ ቀዥቃዣ ነው፣ ችኩል ነው። እሷ ደግሞ ቅርፍፍ ያለች ናት” እያልን ልክ እንደ እኛ አለመሆናቸውን፥ ጥሩ ባልሆነ መንገድ ስናነሳ ይስተዋላል። የሰዎችን የተፈጥሮ መልክም ሆነ እግዚአብሄር የሰጣቸውን ማንነት መናቅ፣ በተዘዋዋሪ እግዚአብሄርን ማሳዘን ነው። ለሌላ በኩል ደግሞ፥ እኛ እራሳችን በዙሪያችን ካሉ ሰዎች ለየት ያለ ተፈጥሮ ወይንም ማንነት ካለን፥ ከሰዎች ጋር እራሳችንን ለማመሳሰል ወይንም አካባቢያችን ያሉትን ሰዎች ኮፒ ለማድረግና ውስጣችን የሌለውን ነገር ለመሆን ብዙ እንጨነቃለን። እግዚአብሄር ዋና አላማው ሰዎችን ሁሉ በክርስቶስ ፍቅር እንድንወድ፣ ሰዎችን ሁሉ እንድናከብርና ከሰዎች ጋር ያሉንን ጤናማ ህብረቶች በማክበር በመካከላችን ያለውን የመንፈስ ቅዱስ አንድነት እንድንጠብቅ እንጂ፣ የሰጠንን ማንነት ጥለን፣ እነርሱን እንድንመስል አይፈልግም። እኛ እነርሱን ከሆንን እኛን ማን ይሆናል? እግዚአብሄር ውበትን የሚያየው በልዩነታችን ባለው አንድነታችን ውስጥ ነው። እግዚአብሄር አካልን የሚያየው ሁሉም አይን ወይንም ሁሉም ጆሮ ሲሆን ሳይሆን፥ የተለያዩ የአካል ብልቶች በአንድ አካል ተገጣጥመው ሲያይ ነው።  እኔ ጆሮ ከሆንኩ ሌላ ሰው ደግሞ እጅ ነው። ሁለቱን ብልቶች ያላቸው ቅርጽ፣ መጠንና ተፈጥሮ ፈጽሞ የተለያየ፣ ስራቸውም እንዲሁ የተለያየ እንደሆነ፣ እግዚአብሄር በልዩነታችን ውስጥ ጸጋውን በማሳለፍ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ይገልጣል እንጂ እኛን ከሌሎች ሰዎች ጋር እያመሳሰለ ከማህበረሰቡ ጋር fit እንድናደርግ የማድረግ አላማ የለውም። ስለዚህ ባህሪዎች ሁሉ እግዚአብሄር በሰዎቹ ህይወት ውስጥ ሊሰራ ካሰበው ስራ አንጻር የተሰጣቸው አንደሆነ ተገንዝበን፣ እግዚአብሄር እኛን እንደተቀበለን፣ ሰዎችን ሁሉ ከነ ሙሉ ማንነታቸው መቀበልና መውደድ፥ እኛም ደግሞ እግዚአብሄር የሰጠንን ማነነት ተቀብለን፥ በዚያ ማንነት ውስጥ መሆን ፍጹም የሆነ የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው።

ፍጹም መውደድ 

ፍጹም መውደድ 

ምስጋና 

ምስጋና