Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ፍጹም መውደድ 

ፍጹም መውደድ 

የሰው ልጅ የመብላት፣ የመጠጣት፣ የመልበስና መጠለያ የማግኘት መሰረታዊ ፍላጎቶች አሉት። እነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቶቹ ለመኖር ብቻ ሳይሆን፥ የየቀን ኑሮውን በትክክልና በጤንነት ለማከናወን የሚያስችሉት አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። መሰረታዊ ፍላጎቶቹ ግን በእነዚህ ከላይ በዘረዘርናቸው ነገሮች ብቻ የሚያበቁ አይደሉም። ሰው በጤንነት ለመኖር መብላትና መጠጣት እንደሚያስፈልገው ሁሉ፥ ስሜቱ ጤናማ እንዲሆን ደግሞ፥ ከእድገቱ ጀምሮ የቤተሰብና አካባቢው ያሉ ሰዎች ፍቅር ያስፈልገዋል። ከወላጆቹ እንዲሁም ከቤተሰቦቹ ጋር ፍቅርን መለዋወጥ ያስፈልገዋል። ለዚህ ነው በትክክል የቤተሰብና የወላጅ ፍቅር ያላገኙ ልጆች፥ ውስጣቸው በጣም የተጎዳ በመሆኑ፥ ወደ ከባባድ ህይወት ውስጥ ሲገቡ የምናየው። እንዲያውም የሆነ ችግር ገጥሞን የስነ ልቦና አማካሪዎች ጋር ስንሄድ፥ ሊያማክረን የተቀመጠው ሰው፥ ችግሮቻችንን ከመስማቱ በፊት፥ መጀመሪያ መስማት የሚፈልገው፥ የአስተዳደጋችንን ሁኔታ፣ በአስተዳደጋችን ውስጥ ከቤተሰብ ያገኘነውን ትኩረት፣ ከቤተሰብ ያገኘነውን ፍቅር ሆኖ የምናገኘው ለዚሁ ነው። አንድ ህጻን ገና ከእናቱ ሆድ ሲወጣ፥ ከባድ በሆነ ለቅሶ ነው የዚህች ምድር ህይወቱን የሚጀምረው። ከዚያ ግን ገና ልብስ እንኳን ሳይለብስ፥ እናቱ ደረት ላይ አምጥተው ሲያስቀምጡት፥ የእናቱን ፍቅርና እንክብካቤ ማግኘት ሲጀምር፥ ለቅሶውን ቀስ እያለ ይተወዋል። ሰው ካደገም በኋላ፥ በእድሜውና ባለፈባቸው የህይወት መንገዶች ውስጥ የተለያዩ የህይወት ልምዶችና እውቀቶችን ቢያገኝም፥ ውስጡ ያለው የመውደድና የመወደድ ፍላጎት ግን እድሜ ልኩን የሚቀጥል ነው። ታዲያ ግን ልብ ማለት ያለብን፥ እንደ መልካችን ልዩነት፥ ሁላችንም መወደድ የምንፈልግበት መንገድ ልዩ ልዩ መሆኑን ነው። እያንዳንዳችን ፍቅርን በበለጠ መንገድ የምንረዳበት፥ ከተፈጥሮአችን ጋር የተያያዘ መንገድ አለ። እንዲያውም Grey Chapman የተባለ አንድ የመጽሀፍ ጸሀፊ፥ አምስቱ የፍቅር ቋንቋዎች በሚል ርእስ በጻፈው መጽሀፉ ላይ እንዳስቀመጠው ከሆነ፥ ለብዙ አመታቶች ባደረገው ጥናት መሰረት፥ አምስት የፍቅር ቋንቋዎች እንዳሉ፥ የሁላችንም አንድ አይነት ባይሆንም፥ ከእነዚህ አምስት ቋንቋዎች ውስጥ፥ አንድ ወይንም ሁለት ፍቅርን የበለጠ የምንረዳበትና የሰዎች ፍቅር በትክክል ልባችን ጋር ሊደርስ የሚችልባቸው መንገዶች እንዳሉ ይናገራል። አካባቢያችን ያሉ ሰዎችን የፍቅር ቋንቋ ማወቅ፥ እነሱ መወደድ በሚፈልጉበት መንገድ እንድንወዳቸው በመርዳት፥ ከሰዎች ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነት እንዲኖረን እንደሚረዳ፥ በጻፈው መጽሀፍ ላይ አስቀምጦልናል። መጽሀፉ ለህይወቴ እጅግ በጣም የጠቀመኝና፥ ከቤተሰቦቼ እንዲሁም አካባቢዬ ካሉ ሰዎች ጋር ያለኝን ግንኙነቶች በብዙ የረዳልኝ መጽሀፍ ሆኖ ስላገኘሁት፥ ያላነበባችሁት ሁሉ እንድታነቡት እመክራለሁ። ከማንኛውም ሰው ጋር ጥቂት ጊዜ ካሳለፋችሁና ያንን ሰው ጆሮ ሰጥታችሁ ከሰማችሁት፥ መወደድ የሚፈልግበትን መንገድ ይናገራል። ባይናገር እንኳን ጥቂት ጊዜ ይፍጅብን እንጂ፥ እግዚአብሄር ማስተዋል ከሰጠን፥ የዚያን ሰው ስሜቶች አይተን መረዳት የምንችለው ነገር ነው። ዋናው ትልቁ አላማ ግን፥ በህይወታችን ላሉ ሰዎች ያለንን ፍቅር፥ እኛ ልብ ውስጥ ባለው የፍቅር መጠን ልክ መረዳት ይችሉ ዘንድ፥ የእነርሱን የፍቅር ቋንቋ ማወቅና ያንን ቋንቋ መናገር ነው። ይሄ ብዙ ድካማችንን ያቀለዋል። ለምሳሌ አንድ ሰው መውደዳችንን ሊረዳ የሚችለው ጊዜ ስንሰጠው ከሆነ፥ በጣም ብዙ ስጦታዎች በመግዛት መድከም ላይጠበቅብን ይችላል። ስጦታውን ቀነስ አርገን፥ ከዚያ ሰው ጋር ልናሳልፍና quality time ልንሰጠው የምንችልባቸውን ነገሮች እያመቻቸን፥ ለዚያ ሰው ያለን ቦታ እንዲገባው ማድረግና ከዚያ ሰው ጋር ያለንን ግንኙነት ጥሩ በሆነ መንገድ መቀጠል እንችላለን። ወደ ትልቁ ወደ እግዚአብሄርም ስንመጣ፥ እግዚአብሄር የእኛን ፍቅር በትክክል መረዳት የሚችልበትን መንገድ ሳይደብቅ በግልጽ ተናግሯል። በዮሀንስ ወንጌል ምእራፍ 14:15 ላይ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ” በማለት መወደድ የሚፈልግበትንና የእኛን ፍቅር በደምብ የሚረዳበትን ቀጥተኛ መንገድ ተናገረ። ኢየሱስዬ ብለን በቁልምጫ ቃል ብንጠራው፥ እምባችንን እያፈሰስን እንዴት እንደምንወደው ብንነግረው፥ እጆቻችንን ዘርግተን አመልክሀለሁ እያልን ብንጮህ፥ አርጉ የሚለንንና  የሚያዘንን ትእዛዞች ካላደረግን፥ የምናደርገው ነገር በሙሉ ስሜት ሊሰጠው አይችልም። እርሱ መወደድ የሚፈልግበትን መንገድ፥ ፍቅራችንን በትክክል የሚረዳበትን መንገድ ተናግሯል። እንዲያውም ያእቆብ በመልእክቱ ላይ እንደጻፈልን ከሆነ፥ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ፥ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር፥ የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል። ራሱን አይቶ ይሄዳልና ወዲያውም እንደ ምን እንደሆነ ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ህግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ስራንም የሚሰራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በስራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ፥ እግዚአብሄርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር፥ የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው::” በማለት የእግዚአብሄርን ትእዛዝ ባለመጠበቅ ውስጥ የሆነ አምልኮ ሁሉ ከንቱ መሆኑን ይነግረናል። 

እግዚአብሄር የሚወደድ አምላክ በመሆኑ፥ እግዚአብሄርን የማይወድ ሰው መቼም የለም። ቢያንስ ከእኛ ውስጥ የለም። እግዚአብሄርም እንድንወደው ይፈልጋል። እንዲያውም እግዚአብሄር እራሱ ለእስራኤል ህዝብ ከሰጣቸው ዋና ዋና ትእዛዞች ውስጥ አንዱ፥ እርሱን እግዚአብሄር አምላካቸውን በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸው፣ በፍጹም ሀሳባቸውና ሀይላቸው እንዲወዱት ነው። ኢየሱስም ይሄ ከትእዛዝ ሁሉ የበለጠው ትልቁ ትእዛዝ እንደሆነ አረጋግጧል። ታዲያ እግዚአብሄርን በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ሀሳባችንና ሀይላችን መውደድ ማለት ምን ማለት ነው? እግዚአብሄርን መውደድ ማለት፥ ሙሉ ነፍሳችንን ተጠቅመን፣ ልባችንና ሀሳቦቻችን ውስጥ ያሉትን ቦታዎች በሙሉ ተጠቅመን፣ የሀይላችንን የመጨረሻ ጥጉን ተጠቅመን እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማድረግ ማለት ነው። ደስ የሚያሰኘውን ነገሮች ለማድረግ፥ መክፈል እስከምንችለው ዋጋ ድረስ መሄድ ማለት ነው። መክፈል እስከምንችለው የሀይላችን ጥግ ድረስ መሄድ ማለት ነው። በነገራችን ላይ እግዚአብሄር ውስጣችን ያለውን የመውደድ አቅም ያውቀዋል። ውስጣችን ያለውን የማፍቀር አቅም ያውቀዋል። ስንወድ ምን ያህል ርቀት እንደምንጓዝ፣ አንድን ነገር በጣም ስናፈቅር፥ ምን ያህል ዋጋ እንደምንከፍል፥ አንድን ነገር በጣም ስንወድ፥ የት ድረስ እንደምንሄድ ያውቃል። ኢየሱስ እኛን ሲወደን የሄደው ርቀት ይሄ ነው። ርቀቱ ከሰማይ እስከምድር ነው። ከሰማይ ተነስቶ ያንን ሁሉ ርቀት ተጉዞ ወደ ምድር መጣ። ይሄ ነው ተብሎ በቃላት የማይነገረውን ሰማያዊ ክብር ወደ ጎን ቁጭ አርጎ፥ አምላክ መሆኑን ወደ ጎን አስቀምጦ መጣና ሰው ሆነ። እኛን ሆነ። እኔና እናንተን ሆነ። እራሱ ከምድር አፈር የሰራውን ሰው ሆነ። በሰው ምስል ተገኝቶ ራሱን አዋረደ። ራሱን ከመጠን በላይ ዝቅ ዝቅ አደረገ። ሰው መሆኑ ብቻ በቂ አልሆን ብሎት፥ በዚህች ክፉ አለም መከራ ሁሉ ውስጥ አለፈ። ፍቅርን ሊገልጸው የመጣበት ይሄ ሁሉ ርቀት አልበቃ ቢለው፥ መርገማችንን ሁሉ ተሸክሞ መስቀል ላይ ተገኘ። ይሄ ሁሉ ፍቅር ይገባን ይሆን? ፍቅር ይገባን ይሆን? ይሄንን ሁሉ ፍቅር፥ አይምሮአችን መሸከም ይችል ይሆን? የፍቅሩን ከፍታ ስፋትና ጥልቀት ለመረዳት፥ ከመታወቅ የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ እንደሚለው፥ ይሄንን ፍቅር በጥቂቱ እንኳን ለማወቅ፥ ብርታት ያስፈልገናል። ይሄንን ፍቅር ለመረዳት፥ የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልገናል። እግዚአብሄር ሲወድ የሄደበት ርቀት፥ ልጁን እስከመስጠት ነው። ኢየሱስ ሲወድ የሄደበት ርቀት፥ ከሰማይ ወደ ምድር በመውረድ ራሱን እስከመስጠት ነው። ሲወድ ከልቡ ነው። ለወደደው ነገር ደግሞ፥ ራሱን መስዋእት በማድረግ ማንም የማይከፍለውን ዋጋ ከፍሏል። ከእኛም የሚጠብቀው፥ የእውነታችንን እንድንወደው ነው። መስዋእትነት የተሞላበትን ፍቅር ነው ህይወታችን ውስጥ ማየት የሚፈልገው። ዋጋ እየከፈልን እንድንወደው። ራሳችንን ለእርሱ እንድናኖር። በሰጠን እስትንፋስ ሁሉ እርሱን እንድናከብረው። ያኔ እኛን ሲፈጥረን በውስጣችን ባስቀመጠው አቅም ሁሉ እንድንወደው፥ በአቅማችን ውስጥ ያለውን ነገር ብቻ ነው የጠየቀን። ትዝ ይላችሁ ከሆነ ነግደው አንዲያተርፉበት መክሊትን የሰጣቸው ባለቤት ሲመጣ፣ አምስት መክሊት ለሰጠው፥ ሌላ አምስት እንዲያተርፍበት ብቻ ነው የጠየቀው። ሁለት መክሊት ለሰጠውም እንዲሁ፥ ሌላ ሁለት እንዲያተርፍበት ብቻ ነው የጠበቀበት። ሁለት ሰጥቶት አምስት እንዲያተርፍ አልጠበቀበትም። አምስት ሰጥቶት ሌላ አምስት ያተረፈውንም፥ ሁለት ሰጥቶት ሌላ ሁለት ያተረፈውንም ሁለቱንም፥ አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ ብሏቸዋል። ከሰጣቸው ቁጥር በላይ እንዲያተርፉ በፍጹም አልጠበቀባቸውም።  ምክኒያቱ ደግሞ፥ የሰጣቸው መክሊት እንደየአቅማቸው ስለሆነ ነው። እዛው ቃሉ ላይ ስታነቡ፥ መክሊቱን ሳይሰጣቸው በፊት “ለእያንዳንዱ እንደ አቅሙ” የሚል ቃል ታገኛላችሁ። ለእያንዳንዱ እንደ አቅሙ፥ ለአንዱ አምስት ለአንዱ ሁለት ለአንዱ ደግሞ አንድ ሰጣቸው ይላል። ሁላችንም ውስጥ እግዚአብሄር ያስቀመጠው አቅም፣ ጸጋ እና ስጦታ የተለያየ መሆኑን ማወቃችን፥ እራሳችንን ከማንም ሰው ጋር compair ሳናደርግ፥ በተሰጠን ነገር ውስጥ ብቻ እንድንሰራ ይረዳናል። እግዚአብሄር ከእኔ የሚጠብቀው ውስጤ ያለውን ሀይል ሁሉ ተጠቅሜ፥ እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ሁሉ እንዳደርግ፣ ውስጤ ባስቀመጣቸው ስጦታዎች ሁሉ እንዳገለግለው፥ ውስጤ ያለውን የመውደድ አቅም በሙሉ ተጠቅሜ እንድወደው ነው የሚፈልገው። ከእኛ የሚጠብቃቸው ነገሮች፥ በውስጣችን እንዳስቀመጠው፣ አቅም፣ ጉልበት፣ ችሎታና ብቃት እንዲሁም የጸጋ ስጦታ መጠን ይወሰናሉ። እግዚአብሄር እንድንወደው የሚፈልገው፥ ውስጣችን ባስቀመጠው የመውደድ አቅም ልክ ነው። ግድ የለሾች ስንሆን በደምብ ያውቃል። ውስጣችን ያለውን አቅም በሙሉ ተጠቅመን ስንወደውም በደምብ ያውቃል። ኢየሱስ አንድ ጊዜ በቤተ መቅደስ ቁጭ ብሎ፥ ሰዎች የሚሰጡትን መባ ይመለከት ነበር። ብዙ ባለጸጎች ትልልቅ ብር ይሰጡ ነበር። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ግን አንዲት መበለት ሴት፥ ሁለት ሳንቲም ስትጥል አየና እንዲህ አለ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ይህቺ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች። እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ሰጡ። ይህቺ ሴት ግን፥ ከጉድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች” በማለት ኢየሱስን በዚህች መበለት ሴት በመገረም ሲናገር እናየዋለን። እነዚህ ባለጸጎች የጣሉት የገንዘብ ብዛት የኢየሱስን ልብ ሲይዘው፥ ልቡን ሲነካው አይታይም። ገንዘብ፣ ብርና ወርቅ ሁሉ የእርሱ ነው። በዚያች መበለት ሴት ግን የተደነቀው፥ ልቡ የተነካው፥ የሰጠችው የገንዘብ መጠን ከሌሎች ሰዎች የገንዘብ መጠን ስለበለጠ አይደለም። እንዲያውም ከሁሉ ያነሰ መጠን ያለው ሳንቲም የሰጠችው እሷ ነች። የተደነቀው፥ ሁሉንም ስለሰጠች ነው። ከጎደላት ነገር ስለሰጠች ነው። ሙሉ ነገርዋን ይዛ፥ ያላትን ሁሉ ይዛ ወደ እግዚአብሄር ቤት ስለመጣች፥ ሙሉ ነገርዋን ለእግዚአብሄር ስላመጣችና ስለሰጠች ነው ኢየሱስ የተደነቀው። እኛ ጋር ያለው ነገር ከሌሎች ሰዎች ማነስ ወይንም መብለጥ፥ የእግዚአብሄርን ልብ አይገዛውም ምክኒያቱም እኛ ውስጥ ያለው ከሰዎች ይበልጣል ወይንም ያንሳል ብለን የምናስባቸውን ነገሮች ሁሉ ሰጪ፥ እግዚአብሄር እራሱ ነው። ልቡን የሚገዛው፥ ሙሉ ነገራችንን በፊቱ ማቅረባችን ነው። በሙሉ አቅማችን ለእርሱ የምንሆናቸው ነገሮች ናቸው። በሙሉ ልባችን፣ በሙሉ ነፍሳችን፣ በሙሉ ሀሳባችንና ሀይላችን እርሱን መውደዳችን ነው። በሙሉ መሰጠት የምናደርጋቸው ነገሮች ናቸው። ታዲያ እርሱ በቃሉ እንደተናገረው፥ መወደድ የሚፈልገው፥ ህጎቹንና ትእዛዞቹን በመጠበቅ ውስጥ ነው። ከዚህ ውጪ የሆነው ፍቅራችን፥ እግዚአብሄር ልብ ጋር አይደርስም። 

ነገሮችን ከልባችን ሳናረግ ስንቀር፥ ነገሮችን እንደ ነገሩ ስናደርግ እግዚአብሄር ያውቃል።  በሙሉ አቅማችንና ሀይላችን ትእዛዞቹን ለመጠበቅ ዋጋ ስንከፍልም እግዚአብሄር ያውቃል። በልባችን የምናወጣና የምናወርዳቸው ሀሳቦች እንኳን ከፊቱ የተሰወሩ አይደሉም። ዳዊትም በመዝሙሩ ይናገራል “ስለ ከንፈሮችን ቃል ጭንቅ የሆኑ መንገዶችን ጠበቅሁ” በማለት የእግዚአብሄርን ትእዛዝና ህጎች ለመጠበቅ፥ ጭንቅ በሆኑ መንገዶች ውስጥ ማለፍን እንደመረጠና የሚያስከፍለውን ዋጋ ሁሉ እንደከፈለ ይነግረናል። ዛሬ ታዲያ እኛ የራሳችንን ህይወት ስንመለከት፥ እግዚአብሄርን እንወደዋለን ወይ? እኛ ብንጠየቅ፥ አዎ እግዚአብሄርን እወደዋለሁ ብለን እንመልስ ይሆናል። እግዚአብሄር ግን ህይወታችንን አይቶ ይወዱኛል ይላል ወይ? የእግዚአብሄርን ትእዛዞች ለመኖር የሚያስከፍለውን ዋጋ እንከፍላለን ወይ? መክፈል ቢያቅተን እንኳን፥ እርሱን በመታዘዝ ውስጥ የሚያስከፍለውን ዋጋ ለመክፈል ፈልገን እንዲረዳን እንጠይቃለን ወይ? በነገራችን ላይ እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኝ ህይወት ለመኖር በጣም እየፈለግን አቅም ስናጣና ግድ የለሾች ሆነን ባለመታዘዝ ጎዳናዎች ስንሄድ እነዚህ ሁለቱ፥ በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። እግዚአብሄር ከእርሱ እርዳታን ከልባችን እንለምነው እንጂ፥ ከለመነውና ካሰብነው እጅግ አብልጦ ማድረግ የሚቻለው አምላክ ነው። ድካማችንን ሁሉ ይረዳል። ለደካማ ሀይልን ይሰጣል። ጉልበት ለሌለው ደግሞ ብርታትን ይጨምራል። በጸሎቶቻችንና በልመናዎቻችን ውስጥ የጸጋውን ብርታት እያሳለፈ፥ ከወደቅንበት እያነሳ ያቆመናል። የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይብናል። የሀይሉን ብርታት ይገልጥብናል። ሌላው ቀርቶ፥ የእግዚአብሄርን ቃል የመጠበቅ ፍላጎቱ እንኳን ባይኖረን፥ እውነተኞ ሆነን እግዚአብሄርን ከጠየቅነው፥ ፍላጎትን እንኳን ሳይቀር ይሰጠናል። አንተን እንድወድህ እርዳኝ ካልነው፣ ላንተ ዋጋ እንድከፍል እርዳኝ ካልነው፥ አንዳች እንደፈቃዱ ብንለምን የሚሰማን አምላክ ይሰማናል፥ ደግሞም ያደርግልናል። አቅቶን እርዳኝ ባልነው ነገር ላይ፥ የእርዳታ እጆቹን በፍጥነት የሚዘረጋ አምላክ ሲሆን፥ በግድ የለሽነት ዝም ብለን ስለምንሄድባቸው መንገዶች ከምንከፍለው ዋጋ ግን ሊያድነን አይችልም። አለመታዘዝ ዛሬ ላይ ምንም የሚያመጣብን ነገር ያለ አይምሰል እንጂ፣ በህይወታችን የሚያስከፍለን ዋጋ በጣም ብዙ ነው። አሁን እንኳን በዚህች ምድር ላይ የምንከፍለው ዋጋ በሙሉ፥ እኛ ሰዎች አታድርጉ ብሎ በኤደን ገነት ያዘዘንን ትእዛዝ ያለመታዘዛችን ውጤት ነው። ቀድሞ ግን እግዚአብሄር ተናገረ፥ ያንን የዛፍ ፍሬ መብላት ሞትን እንደሚያመጣ አስቀድሞ ከማስታወቅ ወደ ኋላ አላለም። የአዳምና ሄዋን አለመታዘዝ፣ እነርሱ ላይ ብቻ ሳይሆን ሞትን ያመጣው፥ የአለም ህዝብ ሁሉ ላይ ነው። አለመታዘዛችን ተጽእኖ የሚያመጣው እኛ ላይ ብቻ አይደለም። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ብለን ከህይወቱ ልንማር የምንችልበት አንድ ሰው፥ በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ አለ። ንጉስ ሰለሞን። እግዚአብሄር እንደ ልቤ ያለው የመዝሙረኛውና የእስራኤል ንጉስ የሆነው የዳዊት ልጅ ነው። ንጉስ ሰለሞን፥ ገና ከመወለዱ ጀምሮ እግዚአብሄር የወደደውና እራሱ እግዚአብሄር በነቢዩ በናታን ልኮ፥ ስሙን ይዲዲያ ብሎ የጠራው ሰው ነው። አባቱ ዳዊት ወደ ንግስና ለመምጣት በጣም ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፏል። ለነፍሱ እንኳን በሚያሰጋው በሞት ጥላዎች ውስጥ አልፏል። ሰለሞን ግን ንግስናን ያገኘው፥ ምንም ዋጋ ሳይከፍል በሚያስብል ሁኔታ ነው። ንጉስ ሰለሞን በእግዚአብሄር ዘንድ፥ በጣም የተወደደ ሰው ነው። እግዚአብሄርን ገና ምንም ነገር ሳይለምን፣ እግዚአብሄር እራሱ ልመናውን ለመስማት ወስኖ፥ ምን ላርግልህ ብሎ ወደ ህልም ራእዩ የመጣለት ሰው ነው። ከለመነስ በኋላ፥ ልመናው ጭራሽ እግዚአብሄርን አስደስቶት ቢገኝ፥ የለመነውን ነገር ከመስጠት በተጨማሪ፥ ያለመነውን ሀብትና ብዙ ባለጠግነት ያትረፈረፈው ሰው ነው። ሰለሞን በእግዚአብሄር ዘንድ የተወደደ ሰው ነው። እግዚአብሄር ፊት ለፊት ተገልጦ አንዴ ብቻ አይደለም፥ ሁለት ጊዜ አናግሮታል። ኸረ ይሄ ብቻ አይደለም። አባቱ ዳዊት በተሰጠው ዘመን ሊሰራ እጅግ በጣም ተመኝቶ የነበረውን የእግዚአብሄርን ቤት ለመስራት እድል ባያገኝም፥  አባቱ ዳዊት ያላገኘውን ይሄንን ትልቅ እድል በማግኘት፥ በእስራኤል ውስጥ የመጀመሪያውን ቤተመቅደስ ለመስራት እድል የተሰጠው ትልቅ የእግዚአብሄር ሰው ነው። ታዲያ ይሄ በእግዚአብሄር የተወደደው ንጉስ ሰለሞን፥ በአንደኛ ነገስት ምእራፍ 11 ላይ እንደምናነበው፥ በሰላም ኖሮ ኖሮ በትክክል ሄዶ ሄዶ፥ ልክ ወደ እድሜው መጨረሻ አካባቢ ላይ ሲደርስ፥ እግዚአብሄር “አምላኮቻቸውን ትከተሉ ዘንድ ልባችሁን በእውነት ያዘነብላሉና ወደ እነርሱ አትግቡ” ካላቸው አህዛብ ሴቶች ጋር መጫወት ጀመረ። እዛው ምእራፍ ላይ ስታነቡ፥ አንድ አስደንጋጭ ቃል ታገኛላችሁ ንጉሱም ሰለሞን በሞአባውያን፣ በአሞናውያን፣ በኤዶማውያን፣ በሲዶናውያን፣ በኬጢያውያን ሴቶች ይልና በብዙ እንግዶች ሴቶች ፍቅር ተነደፈ ይላል። እግዚአብሄር ካሰመረለት መስመር መውጣቱ፥ በጠላት እንዲነደፍ ነው ያደረገው። ታዲያ የዚህ አስከፊ ነገር ውጤት እራሱ ሰለሞን ጋር ብቻ ቢያበቃ ምን አለበት? የሰለሞን አለመታዘዝ፥ መንግስቱን ከእጁ ቀደደው። በዳዊት ዘመን የጸናው መንግስት፥ ሰለሞን ጋር ሲደርስ ሊጸና አልቻለም። እግዚአብሄርም ሰለሞንን አለው “ይህን ሰርተሃልና ያዘዝሁህንም ቃል ኪዳኔንና ስርአቴን አልጠበቅህምና፥ መንግስትህን ከአንተ ቀዳድጄ ለባሪያህ እሰጠዋለሁ። ነገር ግን ከልጅህ እጅ እቀድደዋለሁ እንጂ፥ ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ይህን በዘመንህ አላደርግም። ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም፥ ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጣለሁ እንጂ፥ መንግስቱን ሁሉ አልቀድድም” አለ። የሰለሞን አለመታዘዝ መዘዙ፥ የእስራኤልን ህዝብ ለሁለት ከፍሏል። የእስራኤል ቤት እና የይሁዳ ቤት ተብሎ መከፋፈል የጀመረው፥ ከሰለሞን መንግስት አለመታዘዝ በኋላ ነው። ምንም ሰለሞን እግዚአብሄርን ቢበድልም፥ ስለ አባቱ ስለ ዳዊት ሲል ግን እግዚአብሄር favor አረገለት። የሰለሞን ልጅ የሆነው ሮብአም ደግሞ፥ ስለ አባቱ ስለ ሰለሞን አለመታዘዝ ምክኒያት መንግስት ከእጁ ተቀደደ። ዳዊት ለልጁ ለሰለሞን መልካም ነገርን አሳልፎ፥ ከዚህች ምድር አለፈ። ዳዊት ለልጁ ለሰለሞን፥ የጸናች መንግስትን አሳልፎ ሰጠ። በአባቱ በዳዊት ምክኒያት፥ የሰለሞን መንግስት ጸና። ሰለሞን ግን ለልጁ ለሮብአም፥ የጸናች መንግስትን አሳልፎ ሊሰጥ አልቻለም። የሮብአም መንግስት ግን፥ ከአባቱ ከሰለሞን የተነሳ ሊጸና አልቻለም። መታዘዛችንም ሆነ አለመታዘዛችን ልጆቻችንንና ዘሮቻችን ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ በጣም ከፍተኛ ነው። መንግስትን ከመንግስት የለየው የሰለሞን አለመታዘዝ ነው። ህዝብን ከህዝብ የለየው፥ የሰለሞን አለመታዘዝ ነው። በአንድ መንግስት ትተዳደር የነበረችውን እስራኤልን ከፋፍሎ ሁለት መንግስት ያደረገው የሰለሞን አለመታዘዝ ነው። ከዚያ በፊት በነበሩት ሁለት የእስራኤል ነገስታት፥ እስራኤል በአንድ መንግስት ትተዳደር የነበረ ቢሆንም፥ የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት በመባል የእስራኤልን መንግስት ለሁለት መከፋፈል የጀመረው በሰለሞን አለመታዘዝ ምክኒያት ነው።

ያእቆብ

ያእቆብ

ማንነት

ማንነት